ደማቅ አለፍ ብሎ ደብዛዛ ቀለም የተቀባች ነች ህይወት፡፡ ዛሬ መነሻና መገኛቸው እታች ቢሆንም ህልም አልመው ነገን ተስፋ አድርገው እላይ ለመድረስ እየተጉ የሚገኙ ወጣቶችን የህይወት ውጣ ውረድ ልናወጋችሁ ወደድን፡፡ ያገኘናቸው የሃዋሳ ሃይቅ የሚለግሰውን በረከት ተጠቅመው ህይወታቸውን ለመቀየር ሲታትሩ ነው፡፡
የመጀመሪያው ኡስማን ከድር ይባላል፡፡ ሀዋሳ ሀይቅ ላይ አሳ በማስገር ህይወቱን ይመራል፡፡ ገና ወጣት ቢሆንም በዚህች አጭር ህይወቱ የገጠሙትን ከባድ የህይወት ፈተናዎችና ዛሬ ድረስ የቀጠለውን የህይወቱን ዝንቅ ገጠመኞች አውግቶናል፡፡
የተነጠቀ ልጅነት
ኡስማን የ18 አመት ወጣት ነው፡፡ የአሳ ማስገር ስራ መተዳደሪያው ቤተሰቡን መደገፊያው ወደፊት እደርሳለው ብሎ ላለመለት ህልሙ መሸጋገሪያው ነው፡፡ የኡስማን የትውልድ መንደር ከሀዋሳ በቅርብ ርቀት የምትገኘው ቡሽሎ የተባለች የገጠር መንደር ናት፡፡ እስከ 7 ዓመቱ ድረስ ባይጠግብም ከእናቱ ማጀት ቤት ያፈራውን ተቃምሶ በአባት ፍቅር እና ግሳጼ በእህትና ወንድሞቹ መካከል የልጅነት ጊዜውን አሳልፏል፡፡ እንደ ከተሜው ጡጦ አስነጥሎ ሀሁን አጥና በሶፍት ገርፎ ምግብ ብላ የሚባልበት መንደር አይደለም ቡሽሎ፡፡
በዚያ መንደር ትምህርት ለመጀመር ፈርጠም ማለትና የትምርትን ጣዕም በደንብ መገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡ ኡስማን በትምህርት መጀመሪያ እድሜው ወደ ትምህርት ቤት አልተወሰደም፡፡ በሆሄ መለያ እድሜው ከመንደሩና ከቤተሰቡ ተነጥሎ በአጋጣሚ የትውልድ ቀየውን መልመድ ግድ አለው፡፡
ወጣት ኡስማን ፈቅዶና ወዶ አልነበረም ከቤተሰቡ የተለየው፡፡ በወቅቱ ሀዋሳ ሀይቅ ላይ የአሳ ማስገር ስራ ይሰሩ የነበሩ ሰዎች እነ ኡስማን ቀዬ ደርሰው ኡስማንን አባብለው ከቤተሰቡ ሰውረው ወደማያውቀው መንደር ይወስዱታል፡፡ ወዴት እንደሚወስዱት አይጠይቅ ነገር በልጅነት አዕምሮዎ ክፉ ይገጥመኛል ብሎ አያስብ፤ መመለስ ቢፈልግ እንኳ ጉልበቱ ያልጠነከረ ገና እንቦቀቅላ ልጅ ነውና ወደሚወስዱት ቦታ መሄድ ግድ ሆነበት፡፡
ቤተሰቦቹ የጠፋባቸውን ልጅ ለማግኘት ብዙ ጣሩ ነገር ግን ሳያስቡት ካጠገባቸው የራቀው ኡስማን ፈጽሞ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ ኡስማን ከቤተሰቡ ለይተው የወሰዱት ሰዎች በከረሜላና ብስኩት እያበሉ ወደሚፈልጉት ቦታ ሲያመሩ ከቤተሰቡ መካከል እሩቅ ያሉ ዘመዶቹ ጥሩ ምግብ እየመገቡ ወደሚጫወትበት መዝናኛ የሚወስዱት እንጂ ከወላጆቹ ዳግም ሊገናኝ ወደማይችልበት እሩቅ ሀገር የሚያቀኑ መሆኑን አያውቅም፡፡
በልጅነት አዕምሮው መልካምን ነገር እንጂ መጥፎ ይገጥመኛል ብሎ እንዴት ያስብ?
ኡስማንን ከቤተሰቡ ነጥለው የወሰዱት ሰዎች አሳድገው፣አስተምረውና አንጸው ለቁም ነገር ሊያበቁት አስበው አልነበረም፡፡ ይልቁም ባልፈረጠመ ጉልበቱ ባልጸና ሰውነቱ ጨክነው በልጅነት አስቸጋሪ የህይወት ፈተና እንዲጋፈጥ እንጂ፡፡ እጅግ አስፈሪ በሆነ መልኩ በየጊዜው ማዕበል በሚንጣት ጀልባ ላይ በድቅድቅ ጨለማ የአሳ ማስገሪያ መረብ እንዲጠብቅላቸው አደረጉት፡፡
የቤተሰብ ናፍቆት
ቤተሰብ የሁሉ ነገር መነሻና መድረሻ ነውና ፈቅደውም ይሁን ሳይሹት መናፈቁ አይቀሬ ነው፡፡ ኡስማን እየቆየ ሲሄድ የቤተሰቡ ናፍቆት ጸንቶበት ከሁለት ጊዜ በላይ መንገድና አቅጣጫውን ባያውቀውም ወደ ቤተሰቡ ለመመለስ ሙከራ አድርጓል፡፡ ከሀይቁ ዳር ሲሆን መንገዱን አቋርጦ ብዙ ተጉዞ ወደ ቤተሰቦቹ ሊመለስ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም፡፡ የትውልድ የመንደሩን ስም በትክክል አለማወቁ መጀመሪያ ሲመጣ የተጓዘበትን አቅጣጫ አለመለየቱ ከቤተሰቦቹ እንዳይገናኝ አደረገው፡፡ ጫካ፣አቀበትና ቁልቁለት አቋርጦ ተጉዞ ተስፋ ሲያጣ ወዳሰለቸው ቦታ ይመለሳል፡፡
ጊዜው እየነጎደ እሱም እያደገ ሲሄድ ምግብ ብቻ እየሰጡ ያሰሩት የነበሩት አሳ አስጋሪዎቹ ገንዘብ ይሰጡት ጀመር፡፡ ኡስማን በጊዜው በቀን የተወሰነ ገንዘብ ይሰጡት እንደነበር ይናገራል፡፡ እያደር የሚያገኘውን ገንዘብ ለፈለገው ነገር ማዋል በመጀመሩ ይታለልና ከቤተሰብ ጋር ለመገናኘት የነበረው ጉጉት እየቀነሰና ሙሉ ጊዜው በስራው ላይ እያደረገ መጣ፡፡ የሚያገኘው ገቢ እየጨመረ ሲሄድ መላመዱ ሲጠነክር እዚያው ረግቶ መኖርን ቀጠለ፡፡
አስጨናቂው የአሳ ማጥመጃ መረብ ጥበቃ
ወጣት ኡስማን በዚያ በለጋ ዕድሜው ሀይቁ መካከል ከሌላ መሰል ጓደኛው ጋር ሌሊቱን የተዘረጋ መረብ ጥበቃ ያድራሉ፡፡ በእናት እቅፍ በሚያንቀላፋበት እድሜው በአባት ጥበቃ ማደጊያ ዘመኑ ጥቅሙ በውል እንኳን ያልተገለጸለት መረብ መዘርጋት፤ ጠዋት ጸሀይ ወጥቶ አሳ አስጋሪ የሆኑት የጀልባና የማስገሪያ መረቡ ባለቤቶች እስኪመጡ መጠበቅ የሰርክ ተግባሩ ሆነ፡፡ ውርጭ በበዛበት ድቅድቅ ጭለማ አስፈሪውን ሌሊት መጋፈጥም እጣፈንታው፡፡
የባህርን ማዕበል ያህል መጠኑ አይግዘፍ እንጂ ሀዋሳ ሀይቅ ላይ ወጀብ መከሰቱ የተለመደ ነው፡፡ ኡስማን ሌሊት የተዘረጋውን የአሳ መረብ ሌባ እንዳይወስደው በድቅድቅ ጭለማ ከመጠበቅ በተጨማሪ መረቡ በሚዘረጋው በተንጣለለው ሃዋሳ ሀይቅ መካከል ላይ ንፋስ እየመጣ ከሚነሳው ማዕበል በተደጋጋሚ በእድል ከሞት እንደተረፈ ይናገራል፡፡ እጅግ የበዙ አስፈሪ ሌሊቶችን እንዳሳለፈና አሁን ድረስ በተደጋጋሚ የሚገጥመው ከባዱ ፈተና ሌሊት መረብ ዘርቶ በሚጠብቅበት ጊዜ የሚነሳው ማዕበል እንደሆነ ይናገራል፡፡
ዛሬና የወደፊት ህልም
ኡስማን ዛሬ አድጎ ወጣት ሆኗል፡፡ የሚሰራው ስራ የ11 ዓመታት ልምድ ሆኖት ከአሳ ማጥመጃ መረብ ዝርጋታና ጥበቃ በተጨማሪ አሳ ማጥመድ ቋሚ ስራው ሆኗል፡፡ አሳ አጥማጆቹ ጋር ተደራድሮ በፍቃዱ ይሰራል፡፡ ዛሬ ይሄን አድርግ የሚሉትን ሳይሆን ለመኖር ይሄን ማድረግ አለብኝ የሚለው በራሱ ነው፡፡ የትምህርትን ጥቅም ተረድቶ ጀምሮም ነበር፡፡ በዚህም እስከ ስድስተኛ ክፍል መድረስ ቢችልም ዛሬ ህይወት ከብዶት አቋርጦታል፡፡ ሌሊት የአሳ መረብ ጥበቃ ስራ ላይ ስለሚያድር ቀን ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ ለመማር እንቅልፍ አስቸግሮት ማቆሙን ይናገራል፡፡
ሁሌም ለትምህርት ባለው ፍቅር ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መሄድና እንደሌሎች አቻዎቹ በቀለም ትምህርት ከፍ ያለ ቦታ መድረስን ምኞቱ ነው፡፡ ሁኔታዎች ምቹ ቢሆኑለት መማርና ሀኪም መሆን ይፈልጋል፡፡ የቀኑ መደበኛ የትምህርት ክፍለ ጊዜ አልሳካልህ ሲለው የማታ ትምህርት ጀምሮ ነበር፡፡ ቀን የሚሰራው ስራ ለኑሮው በቂ ስላልሆነለት አዳሩም ስራው ላይ ማድረግ ግድ አለውና ሳይሳካለት ቀረ፡፡
ኡስማን አሳ ለማጥመድ በሌሎች ሰዎች ጀልባና መረብ ስለሚጠቀም ባጠመደው አሳ ብዛት የሚወሰን የቀን ገቢ ያገኛል፡፡ በቀን የሚያገኘው ገቢ እንደ ወቅቱ የሚለዋወጥ ሲሆን በለስ በቀናው ወቅት እስከ አምስት መቶ ብር የሚያገኝ ሲሆን፤ ብርዳማና ንፋስ በሚበዛባቸው የበጋ ወቅቶች አሳ በብዛት ስለማይኖር ቀኑ ሙሉ ሲደክም ውሎ አዳሩን በጥበቃ ቢያድርም የሚጠመድ አሳ ከጠፋ ምንም እጁ ላይ የማይደርስበት ጊዜ የበዛ ነው፡፡
የሚያገኛትን የቀን ገቢ ለምግብ ለቤት ኪራይና ለአንዳንድ ወጪዎቹ የሚያውል ሲሆን፤ የተረፈችው ጥቂት ገንዘብ ቁጠባ ጀምሮ ያስቀምጣል፡፡ ቢሆንም የበዛውን ጊዜ ቋሚ ገቢ ስለማያገኝ የቆጠበውን መልሶ እያወጣ ለሚፈልገው ወጪ ያውለዋል፡፡ ወደ ፊት የራሱን ጀልባና አሳ ማጥመጃ መረብ ኖሮት ገቢውን ማሳደግና መለወጥ የሚፈልገው ኡስማን ዛሬ የልፋቱን ያህል በቋሚነት ገቢ ባያገኝበትም ስራው ላይ በትጋት መስራት እንዳለበት አምኖ ሁሌም ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡
አሳሳቢ ጉዳዮች
ሃዋሳ ሀይቅ በፊት ይሰጥ የነበረው የአሳ ምርት ዛሬ ላይ እየቀነሰ አንዳንዴም ለምግብነት የሚውል አሳ እስከማጣት ደርሷል፡፡ ኡስማንና መሰሎቹ መተዳደሪያቸው መዋያና ማደሪያቸው የአሳ ማጥመጃ መረብ መዘርጋት ማስገርና ለባለ ጀልባዎች ማስረከብ ነውና የምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄድ እጅጉን ያሳስበዋል፡፡ ሌላም የሚያሳስብ ጉዳይ አለ በታዳጊ ወጣቱ ኡስማን አዕምሮ ውስጥ፡፡ በሚሰራው ስራ ደስተኛ ቢሆንም ቋሚ የሚለው ገቢ የሌለው መሆኑና አልፎ አልፎም የሚያገኘውን ገንዘብ ቆጥቦ ገቢ በማያገኝበት ጊዜ ስለሚያጠፋው መሻሻልና መለወጥ ቢናፍቅም ሁሌም ወደ ኋላ የሚመልሰው ጉዳይ ነውና ዘላቂ መፍትሄ አለማግኘቱ ያሳስበዋል፡፡
ኡስማን ዛሬ ላይ ህይወት ፋታ ስትሰጠው ድሮ በልጅነቱ ሳይፈልግ የተለያቸው ቤተሰቹን ወደ ትውልድ ቀዬው እየሄደ ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ሁሌ ‹‹የምኞቴ ማሳኪያ፣የህልሜ መዳረሻ›› የሚለው ትምህርት የመማር እድልን ዛሬ አልታደለም፡፡ የልጅነት እድሜውን ያላገናዘበ ጉልበትን የሚያዝለው ስራው ለትምህርቱ የሚሆን ጊዜ አላተረፈለትም፡፡ ህይወት ሀዋሳ ሀይቅ ላይ በኡስማን ከድር ገፅታዋ እንዲህ ይነበባል፡፡
በሃይቁ ውስጥ የሚገኘውን በረከት ተገን አድርጎ ኑሮን ለማሸነፍ ከሚታትረው ወጣት ኡስማን ህይወት ሻገር ስንል በዳርቻው ተስፈኛዋን የአሳ ሾርባ ነጋዴ ወጣት እናገኛለን፡፡
ሀዋሳ አሞራ ገደል ሀይቅ ዳር አሳ አስጋሪዎች ሁለገብ ማህበር የከለለው የሀዋሳ ሀይቅ ቅጥር ግቢ የብዙዎች መተዳደሪያ ነው፡፡ ከሎሚ አዝዋሪ እስከ አሳ አስጋሪ ከአሳ ጥብስ ሻጩ እስከ የአሳ ሾርባ ነጋዴው በእንግድነት ሃዋሳ ተገኝቶ ወደ አሞራ ገደል ላመራ ሰው በቅንነት የራሱ የተለየ ጣዕም ባለው የአማርኛ ዘዬ ልዩ መስተንግዶ ይደረግለታል፡፡ እዚያ ለተገኘ እንግዳ አምባዛ ይሁንልህ ወይስ ፊሊቶ ካሻህም ቆሮሶ እየተባለ የአሳ አይነቶች በተለያየ ጣዕምና መጠን አስመርጠው ቢያሻው ጥብሱን ቢፈልግ የአሳ ሾርባው ይቀርብለታል፡፡ አለፍ ሲልም የአሳ ቁርጥ ከሎሚና ቢላ ጋር ይቀርብለታል፡፡
ከመግቢያው በር ግራና ቀኝ በተርታ በቋሚ አጠና እንደ ነገሩ ተሰርተው በሳጠራ ተከፋፍለው በረድፍ የተደረደሩ የአሳ ጥብስና ሾርባ መሸጫ ቤቶች ከፊት ለፊታቸው በአግዳሚ ወንበር በተሰየሙ ደንበኞች ተሞልተዋል፡፡ በስፍራው ከሚሰሩት በደንበኞችዋ አያያዝና በስራ ትጋቷ የምትታወቀው በረከት ጴጥሮስ አንዷ ነች፡፡ የ19 አመት ወጣት ነች፡፡ ትውልድና እድገትዋ ሃዋሳ ከተማ ቀበሌ 05 ልዩ ስሙ ሆጋኒ ተብሎ በሚጠራ ሰፈር ነው፡፡ የህይወት ሌለኛው ገጽታ ሃዋሳ ላይ በዚህች ዛሬ ታሪኳን በምናወጋችሁ ወጣት ላይ ማሳየት ወደድን፡፡ በረከት የራስዋ የሆነ ደረጃውን የጠበቀ ትልቅ ሆቴል እንዲኖራት የገዘፈ ህልም አላት፡፡ የዛሬ ትጋትና ብርታትዋ ለአላማዋ መሳካት መንገድ ነውና ለለውጥዋ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በረከት የሃዋሳ ሀይቅን ተጠግታ ሀይቁ ያበረከተላትን አሳ ሾርባውን በልዩ ጣዕም አዘጋጅታ በመሸጥ እራስዋን ከመቻል ባለፈ ቤተሰቦቿን ትረዳለች፡፡
የኑሮ ጫና የፈጠረው መላ
ያኔ በረከት ገና አስራ ሶስት አመትዋ ነበር፡፡ እንኳን ተቀጥሮ ሰርቶ ገንዘብ ሊገኝ ይቅርና ስራ ተሰርቶ ገንዘብ ሊገኝ እንደማይችል በቅጡ ሊገነዘቡ እንኳን የሚከብድበት ዕድሜ፡፡ በረከት በችግር ምክንያት የጀመረችው ትምህርት ልታቋርጥ ደረሰች፡፡ የአባቷ በህይወት አለመኖር እና በከተማ ጽዳት ስራ ይሰሩ የነበሩት እናትዋ ያገኙት የነበረው ገቢ እጅግ አነስተኛ መሆን ቤት ውስጥ ያለውን ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ አባባሰው፡፡ ከአራት ወንድሞችና ሶስት እህቶቿ ጋር የኑሮ ጫናው ቢከብዳቸው እንደሌላው ትምህርት ቤት ሄደው ትምህር መከታተል ቢያቅታቸው ረሀቡ ቢጸናባቸው የሚቆረስ የሚጎረስ ፍለጋ ከቤት ተወጥቶ አቅም የፈቀደውን ለመስራት ተሞከረ፡፡
የማያውቁትን ስራ መሞከር ያልወጡበትን ደጅ ማማተር በህይወት ውስጥ የሚገጥምን ፈተና ለማለፍ ግድ ነውና በረከት በልጅነትዋ ኑሮን ለማሸነፍ ከቤት ወጥታ መንቀሳቀስ ስራ ይሉት ለስዋ አዲስ ነገር መላመድ ግድ ሆነባት፡፡ ሳትጠነክር ኑሮ አስገድዷት ባትፈልግም ህይወት በልጅነት አሳስቧት ለመኖር የሚያስችል ነገር ቢኖር ብላ ከቤት ወጥታ ደጅ ማማተር ለመደች፡፡
ቤተሰባዊ የኑሮ ጫና አላስችል ቢላት ገና በ13 ዓመትዋ ወደ አሞራ ገደል በማምራት ለአሳ ጥብስ ሻጮች ሎሚ አዙራ በመሸጥ የተወሰኑ ሳንቲሞችን ማግኘት ጀመረች፡፡ ለቤተሰቧ አምስተኛ ልጅ የሆነችው በረከት ያኔ ስራ ስትጀምር ስራውም አካባቢውንም እንደማታውቀው ትናገራለች፡፡ ሎሚ አዙራ የምታገኛቸውን ሳንቲሞችን አጠራቅማ ለምግብና ለሚያስፈልጋት ነገር በማዋል ሊቋረጥ ተቃርቦ የነበረውን ትምህርቷን መቀጠል ቻለች፡፡ የሎሚ ንግዱ እያደገ የምታገኘው ገቢም እየጨመረ ሲሄድ ከሚያስፈልጋት ወጪ በመቆጠብ ጥቂት ገንዘብ አጠራቀመች፡፡
ዛሬ
በረከት በሎሚ ሽያጭ ያገኘችውን ገንዘብ አጠራቅማ የሀይቅ ዳር አሳ አስጋሪዎች ማህበር አባል በመሆንና የመስሪያ ቦታ በመረከብ የራስዋን የሆነ የአሳ ሾርባ መሸጫ ቤት ከፍታ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ዛሬ ላይ አጣፍጣ የምታዘጋጀው የአሳ ሾርባ ንግድ መተዳደሪያዋ ነው፡፡ ቀን ላይ ስራዋን እየሰራች ማታ ላይ ትምህርቷን ትከታተላለች፡፡ ወደፊት ትልቅ ቦታ ለመድረስ ጠዋት ማታ በስራና በትምህርት ለምትታትረው በረከት ዛሬም ቢሆን ህይወት አልጋ ባልጋ አልሆነችላትም፡፡
ብዙ ተሰርቶ አነስተኛ ብር ከሚገኝበት ስራዋ የምታገኘውን ጥቂት ገንዘብ ለራስዋና ለቤተሰብ እንደ ነገሩ አስፈላጊ የሆነውን በሙሉ ሳይሆን ይብስ የጎደለውን እየሞላች ከጎደለው ላይ ቀንሳ ነገዋን የተሻለ ለማድረግ ቁጠባ ጀምራለች፡፡ የአሳ ሾርባ በመሸጥ በቀን እስከ ሰባ ብር እንደምታገኝ የምትገልጸው በረከት ለምትሰራበት ቤት የኪራይ ክፍያና ለቤተሰቧ ድጎማ አድርጋ የቀረውን በመቆጠብ ላይ ትገኛለች፡፡
አመለ ሸጋዋና ተግባቢዋ ወጣት በረከት የምትሰራው ስራ እጅግ በጣም የምትወደው መሆኑንና ወደፊትም ለተሻለ ደረጃ መሻገሪያዋ አድርጋ እንደምትቆጥረው ትናገራለች፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ከምግብና ፍላጎትዋ ቀንሳ በ6 አመት የስራ ቆይታዋ አስራ አምስት ሺ ብር አጠራቅማለች፡፡ ደንበኞቿን ጥሩ አድርጎ በመያዝ የተሻለ ገቢ ለማግኘት የምትጥረዋ በረከት ለስራ ያላት ፍቅርና ለመለወጥ ያላት ጉጉት ወደፊት ጥሩ ደረጃ ላይ የምትደርስ ልበ ሙሉ ተስፈኛ ወጣት መሆኑዋን አመላካች ነው፡፡
የበረከት ስጋት
በረከት የ10 ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ለኑሮ በምታርገው ሩጫ ትምህርቷ ላይ ጫና ተፈጥሮ ወደፊት ሀኪም ለመሆን የምታደርገው ጥረት እንዳያስተጓጉልባት ትሰጋለች፡፡ የአሳ ሾርባው ስራ ከባድ መሆንና በየጊዜው የሚገኘው ገቢም እያነሰ መሄዱ ትምህርትዋ ላይ የምታደርገው ትኩረት እንደሚቀንሰው ትናገራለች፡፡ ብዙ ተለፍቶ የሚገኘው ገቢ እራስን ካላስቻለ፤ በአንደም በሌላም መልኩ ያቀዱትን ለማሳካት በሚደረግ ጥረት ውስጥ እንቅፋት መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡
በረከት ለነገ ለውጧ በምታደርገው ሩጫ የመስሪያ ቦታዋን ይበልጥ በማስተካከል የተሻለ ስራ ለመስራት እንድትችል ድጋፍ አለማግኘቷና አካባቢው ላይ በመሰል ስራ የተሰማሩ ሌሎች ወጣቶችን ጨምሮ ገቢያቸው ከቀን ወደ ቀን እያነሰ መሄዱ ያሳስባታል፡፡ ለገቢው መቀነስ ዋንኛ ምክንያት አድርጋ የምትጠቅሰው ደግሞ የአሳ ምርት መቀነስና የምትሰራበት ቦታ ለተጠቃሚ ምቹ አለመሆን መሆኑ ትናገራለች፡፡ ‹‹ይህ ስራ እንዳቅማችን ውለን የምንገባበት፤ ቤተሰባችን የምንረዳበትና የምንኖርበት ነው›› የምትለው ወጣት በረከት የሚመለከተው አካል የአሳ ምርት የቀነሰበት ምክንያት ለይቶ መፍትሄ እየሰጠ ካልሄደና ችግሩ እየተባባሰ ከሄደ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥመን ይችላል የሚል ስጋት ገብቷታል፡፡
‹‹የእንጀራ ምጣዳችን ይህቺ ሀይቅ ነችና እኛ በተቻለን መጠን ቆሻሻ ወደ ሀይቁ እንደይገባ የጽዳት ስራ እንሰራለን›› ትላለች በረከት የውሎ መግቢያቸው የእለት ጉርሳቸው ምንጭ የሆነውን ሀዋሳ ሀይቅ ባለበት እንዲቀጥል የአሳ ምርቱ እንዲጨምር የሚያደርጉበት ጥረት ስትናገር፡፡
መልዕክት ለወጣቶች
ወጣት በረከት ለለውጥዋ የምትተጋ ታታሪ ሰራተኛ ነች፡፡ ‹‹ብዙ ወጣቶች ያለ ስራ ጊዜያቸውን ሲያባክኑ ሳይ ያሳዝነኛል›› የምትለው በረከት ወጣቶች ኑሮን ለማሸነፍ መትጋትና በራሳቸው መቆም እና ጠንካራ መሆን ለሀገራቸውም ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረግ አለባቸው በማለት ምክሯን ትለግሳለች፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011
ተገኝ ብሩ