ፍሬህይወት አወቀ
በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር በፋይናንስ ዘርፍ የሚገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2013 ዓ.ም በጀት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በጊዜያዊ የሂሳብ መረጃ መሰረት ከታክስ በፊት በድምሩ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን እንዳተረፉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል። ይህ አፈጻጸም የልማት ድርጅቶቹ አቅደውት ከነበረው የብር 4 ነጥብ 36 ቢሊዮን ትርፍ አንጻር ሲታይ ክንውናቸው ከዕቅዳቸው 87 ነጥብ 35 በመቶ መሆኑ ታውቋል።
ከተገኘው ከአጠቃላዩ የሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ከፍተኛውን ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ወይም ከዕቅዱ 78 በመቶ በማትረፍ የዘርፉ ትርፍ አፈጻጸም 81 ነጥብ 23 በመቶ ያህል ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። በአምናው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንጻር አፈጻጸሙን አሻሽሎ ከኪሳራ የወጣው ደግሞ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ብር 455 ሚሊዮን ሊያተርፍ ችሏል። ይህም ለዘርፉ አጠቃላይ ትርፍ የ11 ነጥብ 93 በመቶ አስተዋጽኦ በማድረግ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል። የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ደግሞ በሩብ ዓመቱ ብር 260 ነጥብ 56 ሚሊዮን ወይም የዕቅዱን 75 በመቶ አትርፎ ለዘርፉ ትርፍ አፈጻጸም የስድስት ነጥብ 83 በመቶ ድርሻ በማበርከት ሦስተኛ ደረጃን መያዙን በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት ያስገኙት ትርፍ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ምን እንደምታ አለው ብለን ላነሳነው ጥያቄ በዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንትና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዳዊት ወይሶ የሚከተለውን ሙያዊ ሀሳብ አካፍለውናል። ዶክተር ዳዊት እንዳሉት፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ነው የተከሰተው ። ይሄ ደግሞ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ አሳርፏል። በኢትዮጵያም ላይ የዚሁ ነጸብራቅ ቢኖርም በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር የጎላ አይደለም። የተመዘገበው ውጤትም አበረታች መሆኑን ይናገራሉ ።
የኢትዮጵያ በጀት ዓመት ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሰኔ 30 እንደመሆኑ ሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ውስጥ የቆየችው ከአስራ ሁለት ወራት ውስጥ አራት ወራት ብቻ እንደነበር ገልፀው፤ 75 በመቶ የሚሆነው የቢዝነስ እንቅስቃሴ ጤናማና በኮሮና ተፅዕኖ ውስጥ አለመውደቁን አስረድተዋል። በመሆኑም በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተቋማት ከሌሎች ሀገራት አንፃር ሲታዩ ተጋላጭነታቸው የቀነሰ እንደነበር ዶክተር ዳዊት ይጠቅሳሉ ።
ነገር ግን ሌሎች የዓለም ሀገራት ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የጀመረው በበጀት ዓመታቸው መጀመሪያ በጥር ወር አካባቢ በመሆኑ ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሊመታ ችሏል። ስለዚህ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተከሰተበት ወቅት የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት መሆኑ ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ አግዞታል የሚል እምነት እንዳላቸው ዶክተር ዳዊት ይናገራሉ።
በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ተቋማት በተለይም ባንኮች የሚያገኙት ትርፍ ከሚያበድሩት ብድር መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ዳዊት፤ የንግድ ባንክ አብዛኞቹ ብድሮችም አስቀድመው የተሰጡና ለረጅም ጊዜ ካበደሯቸው ብድሮች ከሚያገኘው ወለድ ትርፋማ መሆን እንደቻለ ይታመናል ብለዋል። ነገር ግን በሌሎች ሀገራት ባንኮች በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ ምክንያት ለባለሀብቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በከፊል ወለድ የመሰረዝ ሁኔታ እንደነበር እና ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህ እንዳልነበርና ንግድ ባንክ ሲያገኝ የነበረውን ገቢ እያገኘ የቀጠለ መሆኑን አመልክተዋል።
እርግጥ ነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተስፋፋበት በሦስት ወራት ውስጥ ደፍሮ የሚበደር ባለሀብት ባለመኖሩና የመበደር አዝማሚያ በመቀነሱ ንግድ ባንክ የዕቅዱን መቶ በመቶ ማሳካት አልቻለም። በተመሳሳይ ባንክ ውስጥ የሚቀመጡ ተቀማጮች ቀጥለዋል። ስለዚህ ማበደር ያልቻላቸው የማህበረሰቡ ተቀማጮች የሚያሳድሩት ጫና አፈፃፀሙን ዝቅ የሚያደርገው መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የኮሮና ቫይረስ በሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማየት የሚቻለው በተያዘው በጀት ዓመት ነው ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ ዓመቱ የኮቪድ ተጋላጭነት የቀጠለበት መሆኑንም አስታውሰዋል። ከዚህ አንፃር አመርቂ ባይሆንም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውጤት አስመዝግቧል ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ከሚያበድራቸው ብድሮች ግዙፍነትና አይነቶች አንፃር ሲታይ ያገኘው ትርፍ በቂ አይባልም። ይሁንና ልማት ባንክ ከዚህ ቀደም ሲያበድር የነበረው ብድሩን ለማይመልሱ ባለሀብቶች መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ዳዊት፤ ባንኩ በራሱ ለመቆም እንኳን ጥያቄ ውስጥ የገባ እንደነበርና በየዓመቱ በመንግሥት ድጋፍ የቀጠለ ነው ። በዚህም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ታክሎበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ይህን ጫና በመቀነስ አሁን ላይ የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ልማት ባንክ አሁንም አጠራጣሪ ነገሮች ይኖሩታልና ሊፈተሽ ይገባል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።
የመድህን ድርጅት ትርፋማነት በዓመት ውስጥ በሚደርሱ የጉዳት መጠኖች የሚወሰን መሆኑን የገለፁት ዶክተር ዳዊት፤ ድርጅቱ ጥሩ ሰራም አልሰራ ለኢንሹራንስ የሚሸፍነው የክፍያ መጠን ይወስነዋል ብለዋል። በየጊዜው ከፍም ዝቅም ሊል የሚችል ሆኖ የውጤታማነት ባህሪ የማይታይበት ድርጅት ቢሆንም ጥሩ ነው ማለት ይቻላል ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ የውጤታማነት ባህሪ የሚለካው በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በንግድ ባንክ መሆኑን ይናገራሉ ።
በተለይም ንግድ ባንክ በቀጣይ ትርፋማ ሆኖ መቀጠል የሚያስችለው ከፍተኛ የሆነ ተቀማጭ ያስፈልገዋል። ነገር ግን በዚህ ዓመት ተቀማጭ በበቂ ሁኔታ ይጨምራል ለማለት አስቸጋሪ እንደሚሆን ያመለከቱት ዶክተር ዳዊት፤ በኮሮና ቫይረስ ተፅዕኖ የህብረተሰቡ ገቢ እየቀነሰ መምጣቱንና ያገኛትን ገቢ ወይም ትርፍ በዕለታዊ ፍጆታ ላይ ማዋሉ ተቀማጩን የሚቀንሰው እንደሚሆን ይገመታል ይላሉ።
ስለዚህ ተቋማቱ በቀጣይ ትርፋማ ሆነው መቀጠል እንዲችሉ ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ዶክተር ዳዊት ጠቁመዋል። በተለይም ንግድ ባንክ የሚያበድረውን ብድር በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን እየለየ ማበደር ከቻለ ትርፋማ መሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም