የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሰሞኑን በአዲስ አበባ 2ኛውን የኮሜሳ ተቋማት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል፤ ይህንኑ መድረክ ተከትሎም 6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ነጋዴ ሴቶች ፌደሬሽን የንግድ ትርኢት እና የንግድ ሳምንት ተስተናግዷል።
በንግድ ትርኢቱ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የውበት መጠበቂያ ምርቶች፣ አልባሳትና ጌጣጌጦች፣ ምግብ ነክና የአግሮ ኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ሌሎች ም ርቶች ቀርበውበታል።
ወይዘሮ የዚች ዓለም ካሳ ሰሞኑን በስካይላይት ሆቴል የተካሄደው የዚህ የንግድ ትርኢት ታዳሚ ነበሩ። ቀደም ሲል በአትክልት ተራ የፓፓያ፣ የሙዝና ማንጎ ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ የፍራፍሬ ተረፈ ምርቶች በብዛት በመመልከት እነዚህን ተረፈ ምርቶች በመጠቀም የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማበረከት ገበያውን ለመቀላቀል የወጠኑት ወይዘሮ የዚች ዓለም፤ ጥረታቸው ተሳክቶም ዘደይ አግሮ ኢንዱስትሪን እውን አድርገዋል፡፡
በፍራፍሬ ማቀነባበር ዘርፍ ላይ የተሠማራው የዘደይ አግሮ ኢንዱስትሪ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የዚች ዓለም ካሳ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያን በጎ ነገር ማስተዋወቅና በተለያዩ ሀገራት ምርቱን መሸጥ ወሳኝ ነው። ይህንን ማሳካት ያስፈልጋል በሚል ይህን ሥራ ለመጀመር ችለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅታቸው በተመሠረተበት ወቅት በንግድ ማዕከላት ከመርቲ በስተቀር የሀገር ውስጥ ምርት ባለመኖሩ ይህንን መቀየር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በማመን እሳቸውም ተመሳሳይ ምርት ወደ ማምረት መግባታቸውን አስታውሰዋል።
ሥራውን የጀመሩት ጤናማ እና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለህብረተሰቡ ማቅረብ እችላለሁ፣ በሂደቱም በአትክልት ተራ አካባቢ ይታይ የነበረውን የፍራፍሬ ምርት ብክነት መቀነስ እችላለሁ በሚል እሳቤ እንደነበር ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለሙከራ በቤት ውስጥ በውስን ሀብት የተጀመረው ሥራ ቀስ በቀስ አድጎ በማሽን በመታገዝ ማምረት እስኪችል አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ ተደርጎበታል።
ድርጅቱ አሁን ካፒታሉ 50 ሚሊዮን ብር ደርሷል፤ ከ50 በላይ ለሚሆኑ ሰዎችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤ ከሠራተኞቹ መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
በወቅቱ በርካታ ምርቶች ከውጭ ይገቡ ስለነበር ተቀባይ የንግድ ማዕከላትንም ሆነ ሕብረተሰቡን የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ጠቃሚ ስለመሆኑ ማሳመን ከባድ ሆኖባቸው እንደነበርም ይጠቁማሉ።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ከጤና እና ከአየር ንብረት ለውጥ አንጻር ምርቱ የሚታሸገው በጠርሙስ ነው። ጠርሙስ አገር ውስጥ ስለማይመረት ከውጭ ማስመጣት ከባድ ሆኗባቸውም ቆይቷል። ሥራቸው ይበልጥ እንዳይቀላጠፍ ተግዳሮት እየሆነ ነው።
አሁን ምርታችንን ሰው ለምዶታል፣ የገበያ ችግር የለብንም። የምርት ጥራትን ለመጠበቅ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነትን ማዕከል ያደረጉ ሰርተፍኬቶች አሉን ሲሉ ያብራራሉ።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ንግድ ለመጀመር ነገሮች ቀለል ያሉበት ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ የሚሉት ወ/ሮ የዚችዓለም፤ ከአንዱ ሌላው ለመማር የሚችልበት ሁኔታም ሰፊ ነው፤ ይህም እንደመልካም አጋጣሚ ሊጠቀስ ይችላል ባይ ናቸው።
አሁን ባለው ሁኔታ የመነሻ ካፒታል ለማግኘት ለሴቶች ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ ብድር ለማግኘት የግድ ማስያዣ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፤ ለብድሩ የሚጠየቀውን ለማሟላት አስቸጋሪ መሆኑን ነው ወ/ሮ የዚችዓለም የገለጹት። ወ/ሮ የዚችዓለም ድርጅታቸው ከማርማላት ባሻገር ፍራፍሬ በማድረቅ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የሀገር ባህል ፋሽን ልብስ አምራቿ ማላዊቷ ኤሚ ሳካ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ መሳተፏን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የተፈጠረ መልካም አጋጣሚ ስትል ገልጻዋለች። የሥራ ግንኙነት እና መልካም ጓደኝነትን ለመመሥረት መድረኩ እንደሚጠቅምም ተናግራለች።
‹‹ኮሜሳ ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ መሳተፌ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወከሉ ሴት ነጋዴዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለመመልከት አስችሎኛል›› ስትልም ትናገራለች።
የንግድ ትርኢትና ባዛሩ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ያደረጉትን ሁሉ አመስግና፣ መድረኩ የሃሳብ ልውውጥ ለማድረግ አግዞኛል ስትል ትናገራለች።
እሷ እንዳለችው፤ መድረኩ የሀገሯን ባህል ለማስተዋወቅ አስችሏታል፣ የሌሎች ሀገሮችን ባህልም ለመመልከት እድል ሰጥቷታል። በዋናነት ደግሞ የገበያ ትስስር መፍጠር ያስቻላትም ነው።
በ2013 ዓ.ም በተገኘ ብድር ሥራ የጀመሩት የኦቦሮ ቡና መሥራችና ባለቤት ወይዘሮ ጸሃይ ደመቀ፤ በ 10 ሺህ ብር ካፒታል ሥራ ጀምረው ምርቱን ሲያስተዋውቁ መቆየታቸውን ይጠቁማሉ።
ቡና በመቁላት ፈጭተው ለገበያ እንደሚያቀርቡ ጠቅሰው፣ ሥራው ዘንድሮ ወደሙሉ ሥራ መሸጋገሩን እና ካፒታላቸውም ወደ 600 ሺህ ብር ማደግ መቻሉን ይናገራሉ።
የቀድሞ ሥራቸው አላዋጣ ሲላቸው በቢዝነስ ሃሳብ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና የወሰዱት ወይዘሮ ጸሀይ፣ ምን ልሥራ የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን ሃሳብ ማመንጨት እንዳስቻላቸውም ነው የሚናገሩት። ሁሉም ሥራ ችግር እንዳለው ገልጸው፣ በአቅማቸው ሊሠሩ የሚችሉትን ለማግኘት ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ለመሥራት የተመቻቸውና በፍቅር ሊሠሩት እንደሚችሉም ያመኑበት ቡና መሆኑን ተረድተው ወደ ቡና ሥራ ገብተዋል። የቡና ቅምሻ ሥልጠና ወስደው ከብድር ተቋም ገንዘብ ተበድረው ወደ ሥራው ገብተዋል።
ሥራ ለመጀመር አስቸጋሪ ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የገበያ ትስስር እንደሚጠቀስ በመጠቆምም፤ እንደኮሜሳ አይነት የንግድ ትርኢትና ባዛር የገበያ ትስስር በመፍጠር ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የንግድ ሥራ ለመጀመር ቀላል አለመሆኑን የሚጠቁሙት ወይዘሮ ጸሃይ፤ ፍቃድ ለማውጣት፣ ድጋፍ ለማግኘት የሚጠየቀውን ማስያዣ በማሟላት ብድር ለማግኘትም ከባድ ነው፣ ወለዱም ብዙ ጫና ይፈጥራል ሲሉም አመልክተዋል።
ኬላዎች መብዛታቸው ዋጋው እንዲንር ምክንያት መሆኑንም ይጠቁማሉ። የቡና ገበያ ውድድር ከፍተኛ እንደመሆኑ፤ እንደጀማሪ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ያነሳሉ። የቡና ማሸጊያም በቀላሉ የማይገኝ መሆኑም ሌላው ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር አባል በመሆኔ መረጃውን በቀላሉ ለማግኘት ችያለሁ፣ በባዛሩ ላይ ለመሳተፍም እድል አግኝቻለሁ ሲሉም ይናገራሉ።
የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መድረኩ ጠቃሚ ቢሆንም፤ ያለሁበትን ደረጃ ለመለካት ተመሳሳይ ምርት ይዘው የገቡ የውጭ ነጋዴዎች አልገጠሙኝም ሲሉም ገልጸዋል።
እሳቸው እንደጠቆሙት፤ በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓቱ ቀለል እንዲል ቢደረግ መልካም ነው፣ ወደንግድ ሥርዓቱ ሳይገቡ መቆየት ጊዜና ገንዘብ እንዲባክን ያደርጋል። የመሥሪያ ቦታ ለማግኘትም ብዙ ጥረት ማድረግን ይጠይቃልና አሠራሩን ምቹና ቀላል ማድረግ ይገባል።
የነጋዴ ሴቶችን አቅም ማጠናከር እና እርስ በእርስ ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበት ዓላማው አድርጎ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 6ኛው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ሴት ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ትርዒትና ኮንፍረንስ ዓላማውን ባሳካ ሁኔታ መጠናቀቁም ተጠቁሟል፡፡
በመርሃ ግብሩ ከ21 የኮሜሳ አባል ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት መቶ በላይ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችና ነጋዴዎች ተሳትፈውበታል። የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማፋጠን የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ አስፈላጊ እንደመሆኑ የተዘጋጀው ባዛርና ኮንፍረንስ ይህንኑ ዓላማ የደገፈ ነበር።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር ደኤታ ያስሚን ውሀብረቢ፤ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማበረታታት የቀጣናውን እና የሀገርን ልማት ለማፋጠን እንደሚያስችል ይናገራሉ። የንግድ ትርኢትና ኮንፍረንሱ ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች ምርቶች እና አገልግሎቶች የገበያ እድልና ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም የወጪ ንግድን በማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አስታውቀዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ ሁነቱ የቀጣናውን እምቅ ሀብት እና የፈጠራ ውጤቶችን የሚያስተዋውቅ መድረክ በመሆኑ በቀጣናው የሚገኙ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ሥራ ፈጣሪዎች በንግዱ ዓለም በሚያጋጥሟቸው ችግሮች እና መልካም እድሎች ዙረያ እንዲመክሩና ልምድ እንዲለዋወጡ ያስችላል፡፡
የኮሜሳ ጄነራል ሴክሬታሪ ቼልሲ ሙፑዱ ክዋምፕዌ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ስልት፣ ማዕድን እና ቱሪዝም ልማትን በማጎልበት ክልላዊ ውህደትን ማፋጠን ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።
በአፍሪካ ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ፣ ፈጠራ የታከለበት የኢኮኖሚ ልማት በመተግበር ጠንካራ፣ ተወዳዳሪ እና አካታችነትን መሠረት ያደረገ ልማትን ማረጋገጥ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
መድረኩ የአባል ሀገራቱን ሕዝብ እርስ በእርስ ለማቀራረብ እድል የፈጠረ መሆኑን የሚጠቁሙት ክዋምፕዌ፤ በቀጣናው የሚከናወነውን የአገልግሎት ዘርፍ እና ንግዶችን የማስተዋወቅ አጋጣሚንም መፍጠሩን ይጠቅሳሉ። በጋራ የመፍትሄ ሃሳቦች በማመንጨት የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመጠቀም ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ ግንባታ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
የገበያ እድልን ያመቻቻል፣ ኢንቨስትመንትንም በማስተዋወቅ የማይተካ ሚና ተጫውቷል ሲሉም ክዋምፕዌ አስታውቀዋል። በመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችና ዲጂታል ፋይናንሺያል አካታችነት በኩልም የማይተካ አስተዋጽኦ እንደተጫወተም አስታውቀዋል። ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ላይ እሴት በመጨመር የሴቶችንና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባካተተ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ያሉ ስትራቴጂካዊ መርሃ ግብሮች በመቅረጽ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በማነቃቃት በዘርፉ እያስመዘገበ ያለው አመርቂ እመርታ ሊበረታታ ይገባዋል ሲሉም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ይህ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ውጥን ተቋማዊ ቅንጅት፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብርን እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች ተወዳዳሪነት ማሳደግ ላይ ያተኮረ እንደመሆኑ ኮሜሳ ለኢትዮጵያ ታምራት ስኬት የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ ነው፡፡፡
በኮሜሳ አባል ሀገራት ግብርናን ለማዘመን፣ ድንበር ዘለል የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለማሳደግ፣ አካታችና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የማኑፋክቸሪንግ ሥነ- ምህዳርን ለማጎልበት የተጀመሩ ጥረቶች እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እንደገለጹትም፤ ኢትዮጵያ የኮሜሳ መስራች ሀገር እንደመሆኗ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
አፍሪካ በ2063 ለማሳካት ከያዘቻቸው አጀንዳዎች የሴቶችን እኩልነትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተጠቃሽ እንደመሆኑ፤ ለትግበራው ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። ኢትዮጵያም በዚህ በጀት ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ እና ተወዳዳሪነትን ያሳደገ መሆኑንም አፈ- ጉባዔ ታገሰ ጠቅሰዋል።
የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ትስስርና እድገት ለማፋጠን የሴቶችን ተሳትፎ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበው፣ ኮሜሳ ለሴት ሥራ ፈጣሪዎች እያደረገ ያለው ተግባር ሊበረታታ እንደሚገባው ይናገራሉ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የኮሜሳ አባል ሀገራት ሴቶች በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ እድገት እና የንግድ ትስስሮች መጎልበት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑንም ጠቅሰው፣ የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግም የኮሜሳ አባል ሀገራት የበለጠ ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሴቶች ገበያን በማስፋፋት እና ማህበረሰብን በመንከባከብ ለሀገር ያላቸውን ሚና በማሳደግ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በወጪ ንግድ እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም