ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ሃይማኖቶች ሀገር ነች። ጥንታዊ ከሚባሉ የሺዎች ዓመታት ታሪክ ባለቤት ከሆኑ ጥቂት ሀገራት መካከልም አንዷ ናት። በዘመናት መካከልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍታ ላይ ከነበሩ ሀገራት ተርታ የተሰለፈች ጭምርም ነች። ሕዝቦቿም የአንድ ቤተሰብ ያህል ለረጀም ዘመናት አብረው የኖሩ፤ ክፉና ደግ ቀናትን አብረው ያሳለፉ በብዙዎች ዘንድ የአብሮነት ምሳሌ ተደርገው የሚጠቀሱ ናቸው።
በረጅም የአብሮነት ታሪካቸው ብዙ የሚጎረባብጡ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ከሁኔታዎቹ በላይ ሆነው በአብሮነታቸው ጸንተው የኖሩ ህዝቦች ናቸው። በየዘመናቱ የነበሩ ትውልዶች ለአብሮ መኖር መሰረት የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን በመገንባት ረጅም ዘመናትን የተሻገረ ሀገራዊ አሴቶች ባለቤት አድርገዋታል።
የሀገሬው ህዝቦች ለሞራል እሴት መሰረት የሆኑ ሃይማኖቶች መገኛ ብቻ ሳይሆን ከዚሁ ሃይማኖታዊ አሴቶች ከሚመነጭ ማንነት በሃይማኖት ምክንያት የተሰደዱ የሃይማኖት ደቀ መዝሙሮች የአደጋ ጊዜ መሸሸጊያ መሆን የቻለች ሀገርም ነች። ህዝቦቿ ለእውነት ካላቸው ቀናኢነት አንጻርም ፈርሀ እግዚአብሄር መለያው የሆነ ጨዋ ህዝብ ሀገር ነች። ከዚህ የተነሳም ከሀገሪቱ የረጅም ዘመን ታሪክ ውስጥ በህዝብ ደረጃ የሚጠቀስ ግጭትና የግጭት ታሪክ የለም።
በአንድ በኩል በሃይማኖትና ሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ በአብዛኛው የሚመሰረተው የህዝቦቿ የሞራል አሴቶች በፈጠሩት ስብእና፣ በሌላ በኩል ይህ ስብእና የገራው ማንነት በሀገሪቱ ሕዝቦች መካከል የወንድማማችነት፣ የአንድነት መንፈስ ከፍ ብሎ እንዲወጣና የሀገራዊ ማንነት መገለጫ እንዲሆን አስችሏል።
ከዚህ ይልቅ በየዘመኑ የሚነሱ የገዥ መደቦች /ቡድኖች / በፈጠሯቸው የአገዛዝ ሥርዓቶች ይህንኑ ዘመናት የተሻገረ የህዝቦችን አብሮነት መንፈስና ከዚህ የሚመነጨውን አብሮ ተጋብቶና ተዋልዶ ቤተሰብ ሆኖ የመኖር እሴት ሲፈታተነው ቆይቷል። ለዚህ ደግሞ የሩቁን ትተን በቅርቡ በጁንታው ቡድን የሆነውን መጥቀስ ይቻላል።
ጁንታው ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችን የፖለቲካው የፍጆታ ሸቀጥ አድርጎ አትራፊ ለመሆኑ ላለፉት 27 ዓመታት የሄደበት የሴራ መንገድና መንገዱ በመላው ሕዝባችን ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ሀገራዊ እሴት ላይ ፈጥሮት የነበረው አደጋና አደጋው የፈጠረውን ግራ መጋባት ለማውራት ጊዜ ያለፈበት አይደለም። በአንድ በኩል የሀገሪቱ ተፈጥሯዊ ውበት የሆኑት ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቆርቋሪ በመምሰል ፣ ሕዝብን ከሀገራዊ ማንነቱ በማፋታት የመንደር ማንነት እንዲላበስ በማድረግ የማንነት ግራ መጋባት ውስጥ ከቶታል። ከዚህ በሚመነጭ የፖለቲካ ትርፍ ጊዜ ለመግዛትና በጊዜ ውስጥ ራስን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ለመሳል፤ በዚህ የተሳሳተ ምስል አዲስ የገዥ መደብ ፈጥሮ የገዘፈ ቁመና ለማላበስ ረጅም ርቀት ተጉዟል።
በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን የሀገሪቱን መለያ የሆኑ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አዲስ እና ልዩ የተስፋ ዘመን የመጣላቸው ያህል ከወረቀት ባላለፈ የፖለቲካ ዲስኩር ማዳመቂያ እንዲሆኑ ቀን ቆጥሮ የሚከበር ብሄራዊ ቀን በማወጅ ፤ በአንድ ቀን የበዓል አከባበር የፖለቲካ ዲስኩሩን ስጋ አልብሶ ህይወት ለመስጠት ሞክሯል።
ከዚህ የአደባባይ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጀርባ ያሉ ብዙ ሴራዎችን ነቅሶ ማውጣት ይቻላል። በአንድ በኩል ስለ ሀገሪቱ ብሄር ፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ከጣራ ባላይ ሲጮህ የነበረው የፖለቲካ ስርዓቱ ለእነዚህ የሀገር ውበቶች በሀገረ መንግሥቱ የሰጠውን ስፍራ ማየት በራሱ የስርዓቱን የአደባባይ ጩኸት ከንቱነት ማሳያ ነው።
በሀገረ መንግሥት ምስረታ ውስጥም ሆነ በሀገር ጉዳይ ላይ እነዚህ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የነበራቸው ውክልና ምን ይመስል እንደነበር ማየት በቂ ነው። በሀገር ጉዳይ ፖለቲካዊ ባለመብት የነበሩ የትኞች ብሄረሰቦች ነበሩ? ከነዚህም ውስጥ የትኞቹ ለማዳመቂያና የትኞቹ በዋና ባለቤትነት የተሰለፉ ነበሩ የሚለው ለማንም የተሰወረ አይደለም።
የፖለቲካ ስርዓቱ በአንድ በኩል ቀን ቆጥሮ ስለህዝቦች አብሮነት እየሰበከና ከጆሮ በላይ እየጮሀ ባለፉት 27 ዓመታት በብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬን ፤ ጥላቻንና የበቀል አስተሳሰብ የሚያረግዙ አዋላጅ የማይፈልጉ የጥፋት ሴራዎችን በግልጽም በስውርም ሲከውን ኖሯል።
በተጠናና በታቀደ መልኩ በመንግሥት መዋቅር በተደገፈና በጁንታው ቡድን ፋይናንስ በሚደረጉ ግጭቶች የቱን ያህል የሀገሪቱ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዋጋ እንደከፈሉ ይታወቃል። ጥላቻንና በቀልን በሚያነሳሱ የክፋት ትርክቶች ሕዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት የተደረጉ ጥረቶችና ትርክቶች፣ ያስከፈሉን ዋጋም ቀላል አይደለም ።
ዛሬ ይህንን የሀገሪቱን ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ስናከብር በርግጥም ሀገሪቱ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሀገር መሆኗን፣ ይህ እውነተኛ ውበቷ ከዚያም በላይ የህልውናዋ መሰረት መሆኑን ተረድተን እና ገብቶን መሆን አለበት። ዕለቱን ስናስብም የሀገሪቱ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የኢትዮጵያ አንድነትና ጥንካሬ መሰረት መሆናቸውን ተረድተን አሱኑ ለማድመቅ መሆን አለበት።
በተለይ አሁን በህዝቦች አብሮነት ላይ ስጋት የሆነው የጁንታው ስርዓተ መቃብር የሚፈጸምበት ወቅት ላይ ስለምንገኝ፤ ይህ ቡድን የህዝቦችን አንድነት ለመፈታተንና በህዝቦች መካከል የፈጠረውን አለመተማመንና መጠራጠር ከዚያም ከፍ ብሎ የዘራውን የጥላቻና የዘረኝነት የጥፋት አረም ከውስጣችን በመንቀል ራሳችንን ለመጪው ዘመን ተስፋ በሁለንተናዊ መልኩ በማዘጋጀት መሆን ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም