
ዋለልኝ አየለ
አዲስ አበባ፡- በየዓመቱ ህዳር 29 ይከበር የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሰላምና አንድነትን በሚሰብኩ የሰላም አምባሳደሮች ዓመቱን ሙሉ እንደሚከበር ተገለጸ። በጭፈራ ብቻ ሲከበር የቆየው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ሰላምና አንድነትን ሊያመጣ በሚችል መንገድ መከበር እንደሚኖርበት ተጠቆመ ።
ኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዓሉን አስመልክተው ከትናንትበስቲያ በሰጡት መግለጫ ፣ የኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንት የሁነቶች አደራጅ አቶ ቢኒያም ፈቃዱ እንደገለጹት፤ በዚህ ዓመት በሚከበረው 15ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ‹‹ቆንጂት አንድነት›› የተሰኘ የቁንጅና ውድድር ይካሄዳል። ከሁሉም ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ሦስት ሦስት ቆነጃጅት ተወዳድረው አሸናፊዎች በየክልላቸው የሰላም አምባሳደር ይሆናሉ ብለዋል። የሚመረጡት የሰላም አምባሳደሮች ሰላምና አንድነትን በመስበክ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን ይሠራሉ።
የማጠቃለያ ዝግጅቱም የፊታችን ዕሁድ ህዳር 27 ቀን በሸገር ፓርክ እንደሚካሄድ ጠቁመው፣ የሚመረጡት ቆነጃጅት የመጡባቸውን አካባቢዎችና የወከሏቸውን ብሄሮች ባህልና ትውፊት እንደሚያስተዋውቁ አስታውቀዋል።
በአምባሳደርነታቸውም እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ በየአካባቢያቸው ከሚገኙ ወጣቶች ጋር በሰላም ዙሪያ ይሠራሉ። ይህም በአገሪቱ ሲሸረሸር የቆየውን ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲስተካከል ይረዳል ብለዋል።
ለ15ኛው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የየክልል ተወካዮች ወደ አዲስ አበባ እየመጡ መሆኑን የገለጹት አቶ ቢኒያም፤ ብሄሮቻቸውን ወክለው የሚመጡት ቆነጃጅት የአገር አንድነት ላይ የሚያተኩር ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
የኢስት አፍሪካ ኢንተርቴይመንት ባለቤት አቶ ሞቲ ሞሮዳ በበኩላቸው፤ ‹‹ቆንጂት አንድነት›› በሚል የሰላም አምባሳደር መሰየም ያስፈለገው በሰላም ጉዳይ በአብዛኛው ወጣቶች ላይ መሥራት ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል። የአገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ ቡድኖች ለጥፋት የሚጠቀሙት ወጣቶችን ነው። ወጣቶች ላይ ስለሰላምና አንድነት በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር የተሻለ እንደሚሆን አጋጣሚ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኘው አርቲስት ቀመር የሱፍ በሰጠው አስተያየት፤ እስከዛሬ የነበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የሚታወቀው በዘፈንና ጭፈራ ነው፤ የዘንድሮውን ልዩ የሚያደርገው የኢትዮጵያን ውጫዊና ውስጣዊ ውበት በሚያሳይ መልኩ ለማክበር መታሰቡ ነው ብሏል።
የኢትዮጵያን ውስጣዊ ውበት ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። አንድ ሰው ዓመቱን ሙሉ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ቢዞር አንድም ቀን ተመሳሳይ ምግብ ሳይደግም የተለያየ ምግብ ሊመገብ የሚችልበትን ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ገልጿል። ይህን ደግሞ የኢትዮጵያ ድንቅ መገለጫ እንደሆነ አመልክቷል።
‹‹እኔ ኦሮሞ ነኝ፣ ኦሮምኛ ነው የምዘፍነው፤ ይሄንን ባህሌን የኢትዮጵያ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንዲወዱልኝና እንዲያከብሩልኝ ከፈለኩኝ ወደ እነርሱ መቅረብ አለብኝ›› ያለው አርቲስት ቀመር፤ የየትኛውም ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ባህልና ወግ የሚከበረውና የሚጠበቀው የሌላውን ሲያከብርና ወደሌላው ሲቀርብ መሆኑን ገልጿል።
በቆንጂት አንድነት የቁንጅና ውድድር ላይ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ እንደሚደረግ። ቆነጃጅቱ የሰላም አምባሳደር በሚሆኑበት ዓመት ሌሎች የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንደሚሠሩ በመግለጫው ተጠቅሷል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም