የቄስ ትምህርት ቤት ቆይታዬን አጠናቅቄ አንደኛ ክፍል ስገባ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማኋትን የእንግሊዝኛ ቃል አልረሳትም፤ ሲት ዳውን ! ይህቺ አንደኛ ክፍል በአንደኝነት የተማርኳት የእንግሊዝኛ ቃል ከፊሏ ተወስዳ እንደ ዳዊት ስትደገም እየሰማሁ መገረም ይዣለሁ። እዚህም ዳውን ዳውን ! እዚያም “ዳውን ዳውን” … ጭፈራው ሁሉ “ዳውን ዳውን” ሆኗል።
እነ ዳውኔ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ስም እየተጠቀሱ “ዳውን ዳውን” እያሉ መዋል ሲሰለቻቸው የዳውናቸውን መድፍ አዙረው ወደ ኢትዮጵያ መተኮስ ጀመሩ። “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” ማለት ሥልጣኔ ሆነ። በመሰልጠንና በመሰይጠን መካከል ያለው ድንበር ቀጭን ሳይሆን አይቀርም። ስትሠየጥን እትብትህ የተቀበረባትን አገር ቆፍረህ መቅበር ያምርሃል።
አባቶቹ የከፍታ ማማ ላይ ያወጣትን አገር ዳውን ዳውን እያለ ወደ ተዘፈቀበት የጥላቻ ጉድጓድ ሊጎትታት ለሚሞክረው ዳውኔ ልናዝንለት ይገባል። በሽታ ይዞት ነውና ዳውን ዳውን ሲል እኛ በመልሱ “ዳን ዳን” በማለት እንዲድን መወትወት መጀመር አለብን። አሻፈረኝ ካለም “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ እኛም “ዳውን ዳውን ዳውኔ” እያልን በሚገባው ቋንቋ ልናናግረው ይገባል።
ዳውኔ … አንተ እኮ አታፍርም! ዳውን ዳውን ሲል የሚያምርበት ዲያስፖራ ብቻ ነው ትለኝ ይሆናል። በእኛ አገር አተረጓጎም እንደሁ ጉረቤት አገር ጅቡቲ ሁለት ዓመት ተቀምጠህ ከመጣህም ዲያስፖራ ነህ። ምን ነካህ ዳውኔ … መንግሥት አልባ ሆና በከረመችው ሱማሊያም ከሰነበትክ ማዕረጉን አትከለከልም። ስለዚህ አትድከም አገር ውስጥም ብዙ ዲያስፖራ አለን። በርከት ብለን “ዳውን ዳውን” ዳወኔ እንልሃለን።
“ታላቁ መሪ” በመንግሥታቸው የጸጥታ ኃይል ላይ ድንጋይ ሲወረወር “መንግሥት ሾላ አይደለም በድንጋይ የሚወርደው” ይሉ ነበር። ታዲያ ዛሬስ በዳውን ዳውን የቃላት ውርወራ መንግሥትን ዳውን ማድረግ የሚቻል ይመስልሃል? አትሞኝ ዳውኔ። ይልቅስ ከዳውን ዳውን በሽታህ ለመዳን ዓይንህን በድፍን ተልባ አጥበህ የአገርህን ታሪክ፣ ባህል፣ የሕዝቦቿን አንድነት፣ አልደፈር ባይነቷንና የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤትነቷን ተመልከት። ዳውኔ ወድጄ አይደለም እኮ ደርሶ መካሪ ሆኜ ያረፍኩት፣ እናንተ እኮ የአገራችሁን ትክክለኛ መልክ የማየት ዕድል ገጥሟችሁ አታውቁም። እውነት እልሃለሁ አንጀት ትበላላችሁ።
አንድ ባልቴት “እንጀራ የኛ አይደለም። የእነ እከሌ ባህል ነው። ከዚህ በኋላ እንጀራ የሚበላ ከእኛ ወገን አይደለም “ በማለት አደባባይ ወጥተው ዳውን ዳውን እንጀራ ሲሉ ሰማን። ወይ ጉድ! እውነት ለመናገር ይህችኛይቱ ዳውን ዳውን እንኳን ደልታኛለች። የኢትዮጵያ ሕዝብ ፋሽን የሆነውን ዳውን ዳውን መከተል ቢጀምር አደባባይ ወጥቶ ዳውን ዳውን ኑሮ ነበር የሚለው። ዳውን ዳውን ጤፍ፤ ዳውን ዳውን ሽንኩርት፤ ዳውን ዳውን የቤት ኪራይ፤ ዳውን ዳውን ስኳር፤ ዳውን ዳውን ዳይፐር፤ ዳውን ዳውን ትራንስፖርት፤ ዳውን ዳውን ዘይት … ውይ ዘይት እንኳን ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ በመደረጉ ዳውን አድርጎ አምስት ሊትሩ በ330 ብር እየተሸጠ ነው።
ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ አደባባይ እንዳትወርድ አድርገው የሰቀሏት ኃይሌ ገብረሥላሴና ደራርቱ ቱሉ በልበ ደንዳኖቹ በነ ዳውኔ ተሸማቅቀዋል። ኃይሌ ኢትዮጵያ ዳውን ዳውን ለሚሉት ልቦና ይስጣቸው ብሎ ንግግሩን ጀመረ። ለጠቅ አድርጎ “ሁሉን ነገር አግኝተህም ሀገርህን የምትፈልግበት ጊዜ ይመጣል። የመኖሪያ ፍቃድ አግኝተህ፤ ዜጋም ከሆንክ በኋላ ጭምር ላንተ አገርህ የምታስፈልግበት ጊዜ ይመጣል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ዜጎቻችን የሆነውን ተመልከት” ሲል ለነ ዳውኔ ምክሩን ለገሰ። ኃይሌ ይህን ሲናገር ከተማችንን የሞሏት ነብዮች ያልተናገሩትን ትንቢት ነበር የተናገረው። የወርቅ ሜዳሊያው ጠብ የማይልበት ኃይሌ የሚናገረውም ነገር ጠብ አይልም እንዴ የሚያሰኝ ነገር ተፈጠረ። “በዱባይ ዳውን ዳውን በማለት ሰልፍ የወጡት ኢትዮጵያውያን … በነፍስ ወከፍ 3ሺ ድርሃም እንዲቀጡና ዳውን ዳውን ብለው ወዳጣጣሏት ሀገራቸው ዲፖርት እንዲደረጉ የዱባይ ፍርድ ቤት ወሰነ” የሚል ዜና ሰማን። ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉም የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዘው፤ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እየበረሩ ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ ማለታቸው ተገቢ አይደለም፤ አገር አላቸው አያሰኛቸውም ስትል ድርጊቱን ተቃወመች። መሰልጠን እንዲህ ነው ዳውኔ !
የእነ ዳውኔን የእንግሊዝኛ ችሎታ ስመለከት የዶክተር ፍቃደ አዘዘ አንድ ግጥም ትዝ አለኝ። ዶክተሩ “እየሄድኩ አልሄድም” በሚል ርዕስ በ1989 ዓ.ም ባሳተሙት የግጥም መጽሐፍ ገጽ 47 ላይ በከበደ ሚካኤል የአጻጻፍ ስልት የተጻፈ “የእንግሊዙ ኤክስፐርት” የተሰኘ ግጥም አካተዋል። እነሆ !
ቋንቋ ሳያጡ – ተብተው
ያሏቸውን ቋንቆች አጣጥለው ፣
በሰው ቋንቋ አብጠው ፣
በአደባባይ በቋንቋቸው ለሌላ ቋንቋ ለፍልፈው ፣
ጥብቅና ለሌላ ቋንቋ ቆመው ፣
ሲሟገቱ በክራባት ታስረው ፣
አንድ ኤክስፐርት ቢጤ ነገር ፣ ቢሰማቸው ፣
“አሉኝ!” ብሎ በርሮላቸው ፣ ካለበት ከንፎ መጣላቸው።
ቀረባቸው !
አያቸው !
ግን ሲያቸው ፣
ከላይ እታች ሲቃኛቸው ፣
ለካስ ሁሉም “አንደር” ሆነው ፣
“ፋዘር-ማዘር-ጀርል” ናቸው ፣
የችርችል ዲስኩር የላቸው።
“አቤቱ ፈጣሪያቸው !
ምነው ጨከንክባቸው ?!”
ጮኾ ማለት እየቃጣው
በሆዱ “ኤሎሄ” ብሎ ፣
እሮሮውን ገታው በዛው።
እያደር ሲያስተውላቸው ፣
ለካስ ቋንቋው ነው ጠላታቸው ፣
ስሙን ያለ ተግባር አስታቅፏቸው ፣
አይጥሉት እያማራቸው ፣
አይይዙት እያቃታቸው ፣
ሳያውቁት የገደላቸው ፣
ሳያስቡት የፈጃቸው ፣
አፍ ተጆሮ ሸብቦ ፣
አንገዳግዶ አንተባትቦ ፣
ቆላልፎ ያስቀመጣቸው ፣
በትምህርት ስም ድንቁርናን እንዲዘሩ ያገዛቸው ፣
ለካስ ቋንቋው እራሱም ነው የ “ሊቆቹ” ጠላታቸው።
ሳይሰሙት – ሳይናገሩት – ሳያነቡት
ለማይሰማ – ለማይናገር – ለማያነብ
ብጤያቸው ፣
በየሜዳው ሲደሰኩሩት ፣
ሰማ አየና
ኤክስፐርት ተደመመ ፣
በትራጀዲው ተነካ።
ጥቂት ቆየና ደግሞ ፣
ሳቀ ከት-ከት ብሎ ፣
በትራጀዲው ኮሜዲም አይቶ ፤
ክራባትና ሱፍ ፣ ነጭ ሸሚዝ ለብሶ ፣
በንባዊ ትጋት ፣ የታከተው መምህር ፣
በምናቡ መጥቶ ፤
“ዜይ ኢዝ ! ዊ አም!” ብሎ ሲያስተምር ሕፃናት ፣
እርሱን ለማስደሰት ባልተለመደ ፍቅር
በተለየ ብርታት ፣
ተመልክቶ የነበር በአንድ “አስተውሎት” ወቅት ፣
ታየው እንደገና ባሳብ መስታወት።
በሁለቱ ድምር ፣ በሀዘንና ሳቅ ፣
አልድን ቢል ህሊናው ፣ ከመሸማቀቅ ፣
“ምንም በሌለበት ከምዳክርበት ፣
ምናል በጊዜዬ እንጨት ብፈልጥበት ?
እኔ ነኝ ያለ ሊቅ ፣ የቋንቋ መላዕክት ፣
መጥቶ ይፈውሳቸው ፣ ከዚህ ዓይነት ትንግርት
ጭንቅላት ኖሯቸው ፣ እንሰልጥን ካሉ ፣
በቋንቋቸው ይስሩ!”
ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ፣
ገባ ተሀገሩ ፣ ሄደ ተመልሶ ፣
አእምሮውን ሳይስት ፣ ጤንነቱን ይዞ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012
የትናየት ፈሩ