
-በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የጤና አገልግሎት ይሰጣል
አዲስ አበባ፡- በዘንድሮው ክረምት የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉ በሽታዎች መከላከልና ህክምና ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ። የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ ተቋማትን ሊያሻሽሉ የሚችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ የጤና በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ርካታ ማግኛ ነው። በመሆኑም ባለሙያዎች ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ስፍራ ይሰጣሉ። ለዚህም ማሳያው ባለፉት ዓመታት ከሀገር ውጭ የሚገኙ ዲያስፖራዎችንና በሀገር ውስጥ የሚገኙ የግልና የመንግሥት የጤና ተቋማት በማስተባበር ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የነፃ ህክምና አገልግሎት ማግኝታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ዓመት በነበረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የነጻ ሕክምና ማግኘታቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ እስከአሁን ያለውን ተሞክሮ በማየት በዘንድሮው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የነፃ ህክምና ለመስጠት የሚሠራ እንደሚሆን ተናግረዋል። ወቅቱ ክረምት በመሆኑ እንደ ወባ ያሉ በሽታዎች የሚከሰቱበት አጋጣሚ ሰፊ ነውና ይህንን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሠራ አመልክተዋል።
የወባ በሽታን ለመከላከል በ70 ሄክታር መሬት ላይ ውሃ የሚይዙ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራዎች እንደሚከናወኑ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ አገልግሎታቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችን ማስወገድ፣ መሣሪያዎችን መጠገንና ትርፍ የሆኑ ወይም የማያስፈልጉ አይነት ሆነው የተገኙ ለሌላ የጤና ተቋማት መስጠት የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ አንዱ አካል ይሆናል ብለዋል።
የጤና ተቋማትን ምቹና አገልግሎት በማሻሻል በአጠቃላይ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ብር ለማዳን እንደታቀደም አስታውቀዋል።
ክረምቱ ያለንን የምናጋራበትና አካባቢዎቻችንን ለታካሚዎች እንዲሁም ለሠራተኞች ምቹ የምናደርግበት ይሆናል የሚሉት ዶክተር መቅደስ፤ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በዚህ ዓመት አዲስ ተግባር እንደሚጀመርም አመላክተዋል። ይህም 17 የጤና ተቋማትን የማደስ እና ፅዱ የማድረግ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎት በገንዘብ የሚተመን ባይሆንም ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ከማውጣት መታደግ የተቻለበት እንደሆነ የተናገሩት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ፤ በዚህ ዓመት በአጠቃላይ ከሶስት ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሀግብር ለምግብነትና ሌሎች ዘርፎች ከሚያገለግሉት ባሻገር ለመዲሃኒትነት የሚያገለግሉ ከ10ሺህ በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ በ2017 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ250ሺህ በላይ ችግኞች በጤናው ዘርፍ እንደሚተከሉና ከዚህ ውስጥም 25ሺህ የሚሆኑት ለመዲሃኒትነትና ለምርምር የሚያገለግሉ ችግኞች መሆናቸውን አመላክተዋል።
ከእዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎች የነፃ የህክምና አገልግሎት፣ አቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ፣ የህክምና መሣሪያዎችን መጠገን፣ ደም ልገሳና በሌሎችም ዘርፎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሥራት ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት እንደሆነም ገልጸው፤ ዘንድሮም በተለይም ከፍተኛ የጤና ችግር ያለባቸውን ዜጎች ከማገዝ አኳያ ከፍተኛ ሥራ እንደሚከናወንና ለዚህም በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያና ከዚያ ውጪ ያሉ አጋር አካላት እንዲያግዙና በዚህ በጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሁለት ወር ክረምት የጤና በጎ ፈቃድ ማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ ባለፈው ዓመት ስኬታማ ተግባራት ያከናወኑ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም