
ዲጂታል ኢኮኖሚ በዋናነት በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እገዛ የሚገነባ ነው። ይህ የዲጅታል ኢኮኖሚ ግንባታ በኢንፎርሜሽን እና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) የታገዙ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎችን፣ የፋይናንስ ሥርዓቶችን፣ ግብይቶችን እና ግንኙነቶችን ያጠቃልላል።ይህም ሰዎች የንግድ ሥራ ዕድሎችን በማስፋት በኩል ጉልህ አበርክቶ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የምርትና አገልግሎቶች ግዢና ስርጭት በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ እንዲስፋፋ በማድረግ በኩልም የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት ሚናው የጎላ ነው። ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልና የአገልግሎቶችን ጥራት ለማሻሻል እና ለኢኮኖሚያዊ እድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚገልጹት።
የወረቀት ገንዘብን በሂደት ለማስቀረት የሚያስችልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያግዝ በመሆኑ ሌብነትን በመቀነስ በኩልም ፋይዳው ጉልህ እንደሆነም ይገለጻል። ሰሞኑን ኢትዮ ቴሌኮም፣ ዳሽን ባንክ እና ኤታ ሶሉሽንስ የኢ.አር.ፒ፣ ፖስ እና ካሽ ሬጅስትር አገልግሎቶችን በአንድ ላይ ለመስጠት የሚያስችል “ዙሪያ” የተሰኘ የቢዝነስ ዲጂታል ሥርዓትን በጋራ ይፋ አድርገዋል።
ይህ “ዙሪያ” የተሰኘ የቢዝነስ ዲጂታል ሥርዓት በመስተንግዶ፣ በአስመጪና ላኪ፣ በማኑፋክቸሪንግ እና ችርቻሮ ንግድ ዘርፍ ለተሰማሩ ድርጅቶችና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በእጅጉ የሚያዘምን እና የደንበኞችን የግብይት ተሞክሮና የአገልግሎት ርካታ በእጅጉ የሚጨምር እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ቢዝነስ ኦፊሰር አቶ ብሩክ አድሃና እንዳሉት፣ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን የላቀ የዲጂታል መፍትሔ አስተማማኝ በሆነው እና ለተለያዩ ተቋማት የላቀ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው በቴሌክላውድ መሠረተ ልማት ከማስተናገድ ባሻገር ከ54 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉትን የቴሌብር የክፍያ ሥርዓትን መጠቀም ያስችላል።
በወረቀትና በማሽን ይሠራ የነበረውን የክፍያ ሥርዓት ወደ አንድ ወጥ አተገባበር የሚያመጣ ሥርዓት መሆኑን የገለፁት አቶ ብሩክ፤ ይህም የውጭ እና የሀገር ውስጥ የክፍያ ካርዶችን እንደሚቀበልና የሂሳብ ሥራን ቀላል እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
“ዙሪያ” ለአጠቃቀም ቀላል እና ፈጣን፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ መሆኑን አንስተው፤ ለነጋዴዎች የፋይናንስ እንቅስቃሴን በቀላሉ ለማወቅ እንደሚረዳና የተሻለ የክፍያ መፈጸሚያ አማራጭ እንደሚሆን ጠቁመዋል። “ዙሪያ” የንግድ ሥርዓቱን በማዘመን የተገልጋዮችን ጊዜና ገንዘብ የሚቆጥብ ነው። እንዲሁም የንግድ ሥርዓትን እና አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ነው ያብራሩት።
የኢታ ሶሉውሽን መሥራች እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ተመስገን ገብረህይወት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ “ዙሪያ” የዲጂታል ሥርዓት የኢ.አር.ፒ (ERP)፣ የፒ.ኦ.ኤስ (POS) እና ካሽ ሬጂስተር አገልግሎቶችን በአንድ ላይ መስጠት ያስችላል። “ዙሪያ” የዲጂታል ሥርዓት የኢ.አር.ፒ ሲስተምን ከአንድ ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ መጫን የሚያስችል ሲሆን በክላውድ የታገዘ አሠራርን አንድ ላይ አሟልቶ የያዘ ከመሆኑ ባሻገር ከንግድ እድገት ጋር አብሮ ሊሰፋ እንደሚችል ገልፀዋል።
በተጨማሪም “ዙሪያ” ሁሉንም የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ካርዶች መቀበል የሚችል፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ኮሚሽን ዕውቅና የተሰጠው የሂሳብ ምዝገባ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።እንዲሁም ነጋዴዎች የሚያንቀሳቅሱትን ሀብት በቀላሉ ለማስተዳደር እና ማንኛውንም የክፍያ መረጃዎች በአንድ ያካተተ ደረሰኝ ማግኘት ያስችላል ነው ያሉት።
ይህም ፈጣን የቢዝነስ ግብይትን፣ ግልጽ አሠራርን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ከወረቀት ገንዘብ ንክኪ የጸዳ የቢዝነስ ግብይትን በመተግበር ከገንዘብ ንክኪ የጸዳ ማህበረሰብ ለመፍጠር እና የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
“ዙሪያ” በሀገር በቀል አቅም በልፅጎ ከሀገሪቱ የንግድ ድባብ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የቀረበ እንደሆነ አመልክተው፤ ለሀገራችን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
ነጋዴዎችና አገልግሎት አቅራቢዎች ከአንድ ቅርንጫፍ ምዝገባ ጀምሮ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን እንደየፍላጎታቸው መጠን በፈለጉት ጊዜ ሌሎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በቀላሉ ወደ ሶሉሽኑ ማካተት ይችላሉ። ደንበኞች ከሀምሌ አምስት ቀን 2017ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱን በwww.zoorya.et ማግኘት የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዳሸን ባንክ ደግሞ ለዚህ አገልግሎት የሚውለውን ማሽን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከማመቻቸት ባለፈ ለአገልግሎት አቅራቢ ደንበኞች “አሁን ይግዙ ቀስ ብለው ይክፈሉ” የሚል የፋይናስ አቅርቦት እንደሚያመቻች ገልጿል። ከዳሸን ባንክ የክፍያ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰርም ለደንበኞች ቀላል የክፍያ አማራጭ የሚያመቻች መሆኑንም አስታውቋል።
ሶስቱ ተቋማት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ነጋዴዎች ዘመናዊ የዲጂታል ሶሉሽኖችን በማቅረብ የሥራ ቅልጥፍናና የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም አገልግሎታቸውን ይበልጥ እንዲጎለብት የማድረግ ተግባር በጋራ እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም