“በክልሉ በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም ጉድለቶቹ ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርብናል” – አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

አዳማ ፡- የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እንደ ክልል በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም በአንዳንድ ዘርፎች የተስተዋሉ ጉድለቶችን በመገምገም በአዲሱ በጀት ዓመት በእቅዳችን መሠረት ማሳካት ይኖርብናል ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ እና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ትናንትና በአዳማ ከተማ ገልማ አባ ገዳ ሲካሄድ እንዳሉት፤ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸማችን እንደክልል ፈርጀ ብዙ ውጤቶች የተገኙበት ቢሆንም በአንዳንድ ዘርፎች የተስተዋሉ ጉድለቶችን በመገምገም በ2018 በጀት ዓመት በእቅዳችን መሠረት ማሳካት ይኖርብናል። ባለፈው በጀት ዓመት ለተገኘው ውጤት የአመራሩ ጥንካሬ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አስታውሰዋል።

በ2017 በጀት ዓመት የተስተዋሉ ደካማና ጠንካራ አፈጻጸሞችን በደንብ ገምግሞ በተለይም ደካማ አፈጻጸሞች ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበው፤ የ2018 በጀት ዓመት ባለፈው ዓመት የታዩ ጎድለቶችን ለይቶ ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ጉባዔው በአምስት ነጥቦች ላይ ትኩረት አድርጎ መወያየት እንደሚገባው አመልክተው እነዚህም፣ የባለፈው በጀት ዓመት አፈጻጸማችን ምን ይመስላሉ? ምንም እንኳን በርካታ ውጤቶች ቢመዘገቡም በአንዳንድ ዘርፎች ለምን በሚፈለገው ልክ መሥራት አልቻልንም?፤ ከኢኮኖሚ አንጻር ገቢያችንን ለምን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ አልቻልንም?፤ የግብር አሰባሰብ እና የምርታማነታችን ሁኔታ ምን ይመስላል? እና ህብረተሰቡ ምን ያህል ቁጠባን ባህል አድርጓል? የሚሏቸው ጉዳዮችን በጥልቀት መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይም እንዲሁ ቀልጣፋና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ያልተቻለው ለምንድነው? ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤ በዚህ ስር የመልካም አስተዳደርና የሰላም ጉዳዮች ትኩረት የሚደረግባቸው እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም የሥራ እንቅፋት የሆኑ አካባቢያዊነትና ጎሰኝነት እንዳሉ አንስተው፣ ሰዎች ጥፋት አጥፍተው ሃይማኖትን እና አካባቢን መደበቂያ የሚያደርጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ በእቅዶች በውጤታማነት ላይ ፈተና እንደሆነ አንስተው፣ በግምገማው በጥልቀት እየተፈተሸ ማስተካከያ የሚደረግባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

በአመራሩና በሥራ አስፈጻሚው ዘንድ የፓርቲውን የፖለቲካ አስተሳሰብ ተላብሶ ከመሥራት አንጻር ያሉ ድክመቶችንም ጉባዔው የሚፈትሻቸው እንደሚሆን አቶ ሽመልስ አመልክተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ጠንካራ ፓርቲን በመመሥረት ጠንካራ መንግሥትን እውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛል። በተሠሩት ሥራዎችም በ2017 በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፍ ክልሉ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል። በክልሉ የተጀመረው የፓርቲና የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እውነተኛ ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ የወል ትርክትን በማጠናከር የዜጎችን ትስስር እና አንድነት ለማጎልበት የሚያግዝ እንደሆነ አብራርተዋል።

በጉባዔው ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናትም በርካታ ጉዳዮች የሚመከሩባቸው እንደሆነ ተመላክቷል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You