አዲስ አበባ፡– በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተጎዳውን ማህበረሰብ ማገዝ የሚያስችል ሰው ተኮር ሥራ እየሠራ መሆኑን የትግራይ ክልል ቀይመስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር የትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ መኮንን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ማህበሩ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ከአባላቱ መሰብሰብ የነበረበትን ገቢ ለመሰብሰብ አላስቻለውም። ያም ሆኖ ከዋናው ጽህፈት ቤት ጋር በቅንጅት በመሥራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ድጋፍ ለማግኘት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር የሚሰጣቸውን ሁሉንም አይነት ድጋፎች እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቅርንጫፉም አቅሙን በማጠናከር በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የጤና፣ የመጠለያ፣ የምግብ እና የገንዘብ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍ በክልሉ መሠረታዊ የመድሃኒቶች አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፤ የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር ዋነኛ መገለጫ የሆነውና የሕይወት አድን ሥራን የሚሠራው የአምቡላንስ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በ2017 ዓ.ም ከተካሄዱ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተቋሙን መልሶ የማደራጀት ሥራ አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ብርሃኑ፤ በድንገተኛ አደጋ ርዳታ ምላሽ ላይም በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። መደበኛ አገልግሎቶችን ለማስቀጠል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የአቅም ውስንነት ቢኖርበትም፤ በድንገተኛ አደጋ ምላሽ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት እና የተጎዱ ጤና ጣቢያዎችን ጠግኖ አስፈላጊውን ግብአት በማሟላት ላይ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የቀይመስቀል ማህበር ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያደርገው ከማህበረሰብ እና ከማህበሩ አባላት በሚሰበሰብ ገቢ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ ማህበሩም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከውጭ ድጋፍ ጥገኝነት እንዲላቀቅ የሁሉም ርብርብ ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቀይ መስቀል ድጋፍ የሚሰጥ እንጂ፤ ድጋፍ የሚያስፈልገው ተቋም እንዳልሆነ የሚታሰበው እሳቤ መስተካከል እንዳለበት ጠቁመው፤ ከውጭ የሚመጣው ድጋፍም እየቀነሰ በመሆኑ ዜጎች የማህበሩ አባል በመሆን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ወጣቱም ሠብዓዊነትን የተላበሰ ትውልድ በመሆን በሠብዓዊ አገልግሎት የበጎ ፈቃድ ተግባራትን እንዲፈጽም የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም