ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ለማዋል የአባይ ግድብ እንዲገደብ የነበረው ፍላጎት ዘመን ያስቆጠረና የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ የሚቸረው ፍላጎት ነበር። ይህ ፍላጎት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የታየ ለመሆኑ የታሪክ ማስረጃዎች ምስክር ናቸው። የዓባይን ወንዝ ውሃ ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠርና የመጠቀም ፍላጎት በግብፅና በሱዳን በኩል ዘመንን የተሻገረ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሃሳብ በመቃወምና በተቻላቸው መድረኮች ሁሉ ተፅዕኖ የመፍጠር ፍላጎታቸው አንዳንዴም በኃይል እስከ ማስፈራራት የሚደርስ ነበር።
ወቅቱ የዓባይ ወንዝን መገደብና ለጥቅም ለማብቃት ገንዘብና ዕውቀትን የሚጠይቅ በመሆኑ ግድቡን ለመሥራት የሚያበቃ ኢኮኖሚያዊ አቅም ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የማስጠበቅ ፍላጎቱ ቢኖራትም እንኳ በተግባር ለመተርጎም የሚያስችላት የኢኮኖሚና የዕውቀት አቅሙ አልነበራትም። ሥራውን በውጭ ብድርና የቴክኒክ ድጋፍ ለማከናወን ቢሞከርም ብድር የሚያበድሩ ድርጅቶችም ሆኑ ሀገራት አሻፈረኝ በማለታቸው ዓባይ የሀገሩን ልጆች ርሃብና ድህነት ሳይፈታ የግብፆች ሲሳይ ሆኖ ኖሯል።
የንጉሡ ሥርዓት በደርግ ሥርዓት ከተተካም በኋላም የአባይ ወንዝ በገንዘብ እጥረትና በእርስ በርስ ጦርነት ተግባራዊ ሊሆን እንዳልቻለ መረጃዎች ያስታውሳሉ። የደርግ ሥርዓት አብቅቶ ሥልጣኑን የተረከበው የኢህአዴግ መንግሥት በራስ በጀት የአባይ ግድብን ለማስጀመር የማንም ፍቃድም ሆነ ድጋፍ እንደማያስፈልግ በመወሰን በሕዝቡ ተሳትፎ እገነባዋለሁ በሚል ወደ ግድብ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
ይህ ውሳኔ የግድቡ ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን በማለት የእኔነት አስተሳሰብ እንዲያዝ አድርጓል። በዚህ የእኔነት አስተሳሰብም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለግድቡ ማስፈፅሚያ የሚሆን የቦንድ ግዥና የገንዘብ ዕርዳታ ላይ ተሳትፏል።
ይሁን እንጂ በከፍተኛ አገራዊ ስሜት የተጀመረው ግድብ በተቀመጠለት የጊዜና የወጪ መጠን ማጠናቀቅ ያልተቻለበት ሁኔታ የተፈጠረው ከፍተኛ ብክነትና ምዝበራ በመፈፀሙ ሲሆን፤ ይህ አሳዛኝ ድርጊት በወቅቱ የሕዝቡን የተነሳሽነት ሞራል ዝቅ ያደረገ ቢሆንም ከኢህአዴግ የወጣው የለውጥ ኃይል በምዝበራ ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ በማድረግ በግድቡ ግንባታ ላይ የተከሰተውን ግድፈት በማረምና ግንባታው እንዲጠናቀቅ የሚፈልገውን ኢትዮጵያዊ ፍላጎት ለማሟላት ባሳየው ቁርጠኛነት የወደቀውን የሕዝቡን ሞራል ከፍ የሚያደርግና የሚያኮራ ተግባር አከናውኗል።
በቀደመው የታችኞች የተፋሰሱ አገራት በተለይም በግብጽና በሱዳን በኩል በተደጋጋሚ ለድርድር አመቺ ያልሆኑ የራስ ፍላጎትና ጥቅምን ብቻ መሠረት ያደረጉ ተቀባይነት የሌላቸው ሃሳቦች ደንቃራ እየሆኑ ድርድሩ በስምምነት እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።
የግብጽ ሦስተኛ አደራዳሪ እንዲገባ የመፈለግ ሀሳብና ሙከራዎች አልሳካ ሲሉ ብልጣብልጥ አካሄድ በመጠቀም ይዘውት የነበረውን አቋም ማስፈፀም እንዲያስችላቸው ከአሜሪካን እና ከዓለም ባንክ ጋር በሰሩት ደባ ታዛቢ በሚል ሰበብ ገብተው ክፍተቱን ተጠቅመው ወደ አደራዳሪነት ሚና ከፍ በማለት ጫና የመፍጠርና የማስገደድ እርምጃ መሞከራቸው በጉልህ ታይቷል።
በኢትዮጵያ በኩል የታየው ጠንካራ አቋም ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት መድረክ እንዲመለስ አስችሎ ባለበት ሁኔታ የግድቡ ውሃ ሙሌት እውን መሆኑ ታላቅ ስኬታማነትን አጎናጽፎ በእኔነት ስሜት የግድቡን ውጤታማነት ሲከታተሉ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ደስታን ሲያጎናጽፍ፤ የግድቡ ግንባታ እንዳይሳካ ለሚፈልጉትና ተሸጠ ብለው ውዥንብር ለመፍጠር የሞከሩትን ደግሞ ተስፋ ያስቆረጠ ሆኗል። በዚህም መላ ኢትዮጵያውያን በአዲስ መንፈስ ለግድቡ ፍጻሜ ባላቸው አቅም ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ መነሳሳት ያሳዩበት ሆኗል።
ይህ ወቅት ቀጣዩ የግድቡ ሥራዎች ላይ መሠረታዊ ስምምነት ለመድረስ ድርድር የሚደረግበት ጊዜ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም በላይ በአንድነት ድጋፋቸውን ማሳየት የሚጠበቅባቸው ወቅት ነው። እስካሁን የተደረጉ ድርድሮች የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመልማት መብትና ፍትሃዊነት የተመረኮዙና ያረጋገጡ ለመሆኑ የተገኙት ድሎች ዋቤ ናቸው። በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለው ድርድርም የዚሁ አካል በመሆኑ በውጤታማነት የሚጠናቀቅ እንደሚሆን ኢትዮጵያውያን ይዘውት የተነሱት እውነታ ማረጋገጫ ነው!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012