በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ደማቅ አሻራ ማሳረፍ ከቻሉ ጥቂት ክለቦች መካከል በዋነኛነት ይጠቀሳል። «ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውበትም ድምቀትም ነው» ይሉታል። ክለቡ የሚከተለው የኳስ አጨዋወት ውበትን፤ በኳስ ፍቅር የተደራጁት አስደማሚ ደጋፊዎቹ ያላበሱት ድምቀት እንዲህ አይነቱን ማንነት እንዳላበሱት ይነገራል። በ1975 ዓ.ም በቡና ቦርድ ሥር «ቡና ገበያ» ስፖርት ክለብ በሚል የተመሰረተውና፤ በቀጣይነት የቡና ላኪዎች ማህበር ከምርት ገበያ ጋር በመሆን በጀት እየመደቡለት በቦርድ በመመራት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው፤ አንጋፋው ኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ።
ኢትዮጵያ ቡና በአራት የአፍሪካ ውድድሮች የመሳተፍ ዕድል አግኝቷል። በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ በ1985 የኢትየጵያ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ በ1990 ተሳትፏል፡፡ በተጨማሪም ሻምፒዮና ዋንጫ በተደጋጋሚ እንደማንሳቱ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ተደጋጋሚ ተሳትፎ አግኝቷል፡፡ በተለይ ከ1991-93 በተከታታይ ለሦስት ዓመታት ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈ ክለብ ነው፡፡ ውድድሩ ያኔ የአፍሪካ የዋንጫ አሸናፊዎች ዋንጫ CAF cup winners cup ተብሎ ነበር የሚጠራው። በ1991 የብሩንዲው ኢንተርስታር ራሱን በማግለሉ ቅድመ ማጣሪያውን ካለፈ በኋላ በመጀመሪያው ዙር ለቀጣይ ዓመት 1992 የማላዊውን ቴልኮም ዎንደደርሰን 3ለ0 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ካለፈ በኋላ በግብጽ ዛማሊክ ጋር ሦስት አቻ ከተለያየ በኋላ በመለያ ምት ተሸንፎ ወጥቷል፡፡ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ በቀረበበት 1983 ከሁለተኛ ዙር አላለፈም የሞዛምቢኩ ማጂጄ ራሱን ካገለለበት በኋላ በካሜሩኑ ኩምስ ስትራይከርስ ተሸንፏል፡፡
ቡና በከፍ ካራም ሁለት ጊዝ ተሳትፏል፡፡ በ1986 በሱዳን አልምሩዳ በ1996 ደግሞ በሊቢያው አልናስር ተሸንፎ ከአንደኛው ዙር አላለፈም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በአራት የአፍሪካ ውድድሮች የመሳተፍ መልካም የሚባል ታሪክ ባለቤት ከመሆን በተጓደኝ፤ በሀገር ውስጥ በጥሎ ማለፍና አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ስኬቱን በጉልህ አሳይቷል። ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በነበረው የ20 ዓመታት ጉዞ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት አለመቻሉ ለብዙዎች እንቆቅልሽ መሆኑ አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያ ቡና የታሪኩ፣ የገናናቱን በርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የመሆኑን ያህል የሊጉን ዋንጫን ደጋግሞ አለማንሳቱ ስለምን ይሆን? የሚሉ በርካቶች ናቸው። የክለቡ ዋንጫ አለማንሳት በእጅጉ የሚያንገበግብና የሚያስቆጫቸው ደጋፊዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ይሁንና ይህ ውጤት ማጣቱ የደጋፊዎችን ቁጥር አልቀነሰበትም እንዲያውም በተቃራኒው የቡና ደጋፊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች በህብረት ተሰድረው ቆመው ተቃቅፈው እያዜሙ ሲንቀሳቀሱ ሲወዛወዙ ከሩቅ ለሚመለከት ቡናማ ወንዝ ላይ ማዕበል የሚንከባለል ነው የሚመስለው፡፡
በአዲስ አበባ ስታድየም ቀኝ ጥላ ፎቅ፣ ካታንጋ እና ሚስማር ተራ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ግዛቶች ናቸው፡፡ ለስታድየም ውበትና ድምቀት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱት ደጋፊዎቹ ‹የሊግ ዋንጫ ጥማችን አንድ ቀን ይሳካል ›እያሉ ተስፋ ሳይቆርጡ ክለቡን በመደገፍ ጉዟቸውን ዛሬም እንደ ትናንቱ በጽናት እንደቀጠሉ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ደጋፊዎች ክለብ ከዋንጫ በላይ ስለመሆኑ ማሳያ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ደማቅ አሻራ ማሳረፍ ከቻሉ ጥቂት ክለቦች መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሱት ቡናማዎቹ 12/12/12 ላይ «የቡና ቤተሰብ ሩጫ» ለማካሄድ ሽር ጉድ እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል። በኢትዮጵያ ቡና ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ቡናማዎቹ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስታድየም ቀኝ ጥላ ፎቅ፣ ከታንጋ እና ሚስማር ተራ ከሚያሰሙት ማራኪ የድጋፍ ዜማ ተሻግሮ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ሁነት ሲፈልጉ ቆይተዋል። ቡናማዎቹ ‹ክለብ ከውጤት በላይ ነው፣ ቡና ደሜ ነው› የሚለውን መፈክር በተግባር ማሳየት የሚያስችለው ሁነት ለዓመታት ተጠንስሶ በ2007 ዓ.ም ነበር ሊወለድ ችሏል።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ክፍሌ አማረ፤ የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ የተጀመረው በ2007 ዓ.ም መሆኑን በመግለጽ ይሄንኑ መረጃ ያጠናክራሉ። በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አዘጋጅነት በየዓመቱ የሚካሄደው «የቡና ቤተሰባዊ ሩጫ» አላማ ያደረገው «በክለቡ ቤተሰባዊ ትስስርን መፍጠርና ማጠናከር እና የክለቡን የገቢ አቅም ለማጠናከር »መሆኑን በኢትዮጵያ ቡና ጥላ ሥር የተሰባሰቡትን ደጋፊዎች የሚያሳትፈው ሁነት ተጀመረ። ከአምስት ዓመት በፊት 8 ሺህ ቤተሰቦችን በማሳተፍ ተጀመረው ሁነቱ፤ በ2ኛው ዙር የቡና ቤተሰብ ሩጫ የተሳታፊውን ቁጥር ወደ 20 ሺህ በማሳደግ በታላቅ ድምቀት ለመካሄድ ተቻለ። የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የድምቀቱ መጠን እያደር አብቦና ደምቆ በ30 ሺህ ተሳታፊዎች ሦስተኛው የቡና ቤተሰባዊ ሩጫ ለመካሄድ በቅቷል። የክለብን ጥቅም ለማጉላት «ቡና ደሜ ነው» የሚለው ሀቀኛ ደጋፊ ለክለቡ ያለውን ፍቅርና መጠንከር ተሳትፎው ወሳኝ መሆኑን እያደር በመገንዘብ ይመስላል በ4ኛው የኢትዮጵያ ቡና ቤተሰባዊ ሩጫ ላይ የተሳታፊው ቁጥር ከ40 ሺህ በላይ ሊያሻቅብ የቻለው። በኢትዮጵያ ቡና ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ቡናማዎቹ ዘንድሮ እንዳምናው ደምቀው ለመታየት 12/12/2012 ዓ.ም ቡናን ከልብ በሚል ቀጠሮ እንደተያዘ አቶ ክፍሌ ገልጾልናል። የኢትዮጵያ ቡና ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ መርሐ ግብር ዘንድሮ 5ኛው ዙር የሚካሄድ ይሆናል። የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች በድምቀት የሚያሰባስበውን ይህን ሁነት በተለያዩ ሁነቶች ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታወቋል።
«የቤተሰብ ሩጫ ውድድሩን ለማካሄድ አሁን ያለንበት ወቅት እንደማያስችለን ይታወቃል። የዓለምን ሕዝብ ሥጋት የሆነው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሩጫ ውድድሩን ለማከናወን የሚያግድ ቢሆንም፤ ዕለቱን በተለየ መልኩ ለማሰብ ዕቅድ ተይዟል። የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ውድድርን የክለቡ ደጋፊዎች ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ቲሸርቱን ለብሰን ባለንበት ሆነን ከክለባችን ጋር በልብ በመገናኘት የምንሮጥ ይሆናል። የአረንጓዴ አሻራን ቀንን ምክንያት በማድረግ ደጋፊው በየአካባቢው ችግኝ ይተከላል። በተጨማሪም የደም ልገሳ መርሐ ግብር ሌላኛው የዕለቱ አብይ ጉዳይ ይሆናል »ሲል አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫን እንዲህ በመሰለ መልኩ ለማካሄድ የታሰበ መሆኑን የገለፀው አቶ ክፍሌ፤ በዚህ መሠረትም የቲሸርት ሽያጭና ምዝገባ በመደረግ ላይ ሲሆን፤ የአንዱ የመሮጫ ማልያ ዋጋ ከአንድ የፊት ማስክ ጋር ለአዋቂ 350 ብር ለህፃናት 300 ብር እየተሸጠ ይገኛል። 12 ቁጥር የታተመበት የመሮጫ ቲሸርት ሽያጩ በክለቡ ጽፈት ቤት (ሜክሲኮ) እና በማህበሩ ጽህፈት ቤት (ቡልጋሪያ)፣ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ በየአካባቢው ይሸጡ በሚገኙ የመሸጫ ቅርንጫፍ ቦታዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በተቋቋሙ እድሮች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክቷል። በ5ኛው የኢትዮጵያ ቡና የቤተሰብ ሩጫ ሁነት ላይ ከ40 እስከ 60 ሺህ ቤተሰቦች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከቲሸርት ሽያጩም እስከ 14 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ታሳቢ ተደርጓል። በመሆኑም ክለቡ በኮሮና ምክንያት የደረሰበትን የፋይናንስ መንገራገጭ በተወሰነ ደረጃ ለማስተካከል የሚረዳውና የሩብ ዓመት የተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያን መሸፈን የሚያስችል ገቢ ማግኘት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ክፍሌ ነግሮናል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
ዳንኤል ዘነበ