በቤትና በቢሮ እንጨት ሥራዎች ማምረት ሥራ ለሦስት አሥርት ዓመታት ዘልቋል።መጀመሪያ በቀለም አስመጪነት አሁን ደግሞ በቀለም አምራችነት ዘርፍ በመሳተፍ በመስኩ የሚታየውን የጥራት ክፍተት ለመሙላት ጥረት እያደረገ ይገኛል።በዚሁ የቀለም ማምረት ሥራ በስፋት በመሳተፍና ጥራትን በመጨመር ምርቶቹን ወደ ውጭ አገራት ለመላክ ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰም ነው- አዶሊስ ቀለም አምራች ኩባንያ።
አቶ ሚኬሌ ግራፊ የአዶሊስ ቀለም አምራች ኩባንያ ባለቤትና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው።ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ጨርቆስ አካባቢ ነው።የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጣልያን ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ከዚሁ ትምህርት ቤት በምህንድስና ሞያ ትምህርታቸውን ለአምስት ዓመታት ተከታትለው እ.ኤ.አ በ1992 ተመርቀዋል።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት አባታቸው ቀድመው ባቋቋሙትና አዶሊስ የቤትና የቢሮ እንጨት ሥራዎች ማምረቻ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ውስጥ አብረው የእንጨት ሥራዎችን መሥራት ጀመሩ።አባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላም ከቀሩ ቤተሰቦቻው ጋር በእንጨት ሥራው ቀጠሉ፡፡በወቅቱ የእንጨት ሥራ ገበያው ፉክክር ቢኖርበትም፣ውጣ ውረድ ግን ብዙም አልነበረውም።
የእንጨት ሥራ የፊኒሺንግ ሥራ አካል በመሆኑ የግድ ከኮንስትራክሽን ዘርፉ ጋር እንደሚገናኝ አቶ ሚኬሌ ተረዱ።በኮንስትራክሽን ዘርፍ ትምህርቱም ሞያውም የነበራቸው በመሆኑና በእንጨት ሥራውም የፊኒሺንግና የዲዛይን ሥራዎችን ጠንቅቀው በማወቃቸው ይህም ወደ ቀለም ሥራ የሚያመጣ መሆኑን ተገነዘቡ።በቀለም ሥራ ያለውን የጥራት ክፍተት በማየትም ከአስር ዓመት በኋላ በአባታቸው የተጀመረውን የቤትና የቢሮ እቃዎች እንጨት ሥራ ኩባንያ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀለም አስመጪነትና አምራችነት እንዲሸጋገር አደረጉ።
በሀገሪቱ እየተገነቡ የነበሩ ባለ አራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎች የሚፈልጉትን የቀለም ደረጃ ለማሟላት ጥራት ያላቸው ቀለሞች በሀገር ውስጥ ገበያ ብዙም የሚገኙ አለመሆናቸውን የተረዳው ኩባንያቸው የቀለም ሥራውን የጀመረው በቅድሚያ ከውጭ አገራት በማስመጣት ነበር።ቀለሞቹን ወደ ሀገር ውስጥ ካስገባም በኋላ በመጀመሪያ በገበያ ውስጥ ማለማመድና ማስተዋወቅ ይቀጥላል፡፡ከዚያም የቀለም ፍላጎት መኖሩን አረጋግጦ ወደ ማምረት ይሸጋገራል።
ኩባንያው ቀለሞቹን ሲያመርት በጥራት ሳይደራደርና ለቀለም ምርት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ አገራት በማስመጣት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ቀለም ወደ ማምረት ገብቷል።በሦስት ምዕራፎችም እየሠራ ይገኛል።በመጀመሪያ ምዕራፍ የቀለም ምርቶችን በመለየት ከመደበኛ የግርግዳ ቀለሞች አንስቶ የፀረ ባክቴሪያና ፀረ ፈንገስ እንዲሁም ለውስጥና ውጭ አገልግሎት የሚሆኑ ቀለሞችን ማምረት ጀምሯል።በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ዲኮራቲቭ ወይም የማሳመሪያ ቀለሞችን ለማመርት እየተዘጋጀ ይገኛል። እነዚህን የቀለም ምርቶች በዚሁ በጀት ዓመት መጨረሻ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ዕቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርቱ ዘግይቷል።ይሁንና ምርቱን በ2013 ዓ.ም ለማምረት አቅዷል።
ኩባንያው በውጭ አገር የሚመረቱ ጥራት ያላቸው ቀለሞችን በአገር ውስጥ በማምረት የውጭ አገር ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት አስቦ እየተንቀሳቀሰም ነው፡፡በሦስተኛው ምዕራፍም ምርቶቹን ወደ ውጭ አገራት የመላክ ዕቅድ ይዟል።በውጭ ገበያ ለመግባትና ተወዳዳሪ ለመሆንም ጥራት ላይ ይበልጥ አተኩሮ እየሠራ ይገኛል።የቀለም የቴክኖሎጂ ሽግግር ወደ አገር ውስጥ ለማምጣትም ጥረት አድርጎ በኩባንያው የሚሠሩ ባለሞያዎች ልምዳቸውን እንዲያዳብሩ ረድቷል።
ኩባንያው በአዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ በራሱ ቦታ ላይ ቀለሞቹን እያመረተ ይገኛል።የቀለም ቴክኖለጂ በጣም ቀላል ቢሆንም ትልቁ ጉዳይ ያለው ምርቱ ሳይቆራረጥና ጥራቱ ሳይቀንስ ማምረት ላይ ነው፡፡በዚህ ሂደት ደግሞ ጥሬ ዕቃ ትልቁን ሚና የሚጫወት በመሆኑ ኩባንያው አስፈላጊ ጥሬ እቃዎችን በሟሟላት የቀለም ምርቶችን እያመረተ ይገኛል።ጥሬ እቃዎችንም ሙሉ በሙሉ ከውጭ አገራት እያስመጣ ቢሆንም፣በአሁኑ ወቅት ግን በሚፈልገው ልክ እያገኘ አይደለም።ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንድ ጥሬ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረት እያደረገ ይገኛል።የሀገር ውስጥ ጥሬ ዕቃ አምራቾች ኩባንያው በሚፈልገው ልክ ጥራታቸውን ማሻሻል ከቻሉ ኩባንያው ከውጭ አገር የሚያስገባቸውን ጥሬ እቃዎች ሙሉ በሙሉ በመተው የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን ብቻ ለመጠቀም አስቧል።
‹‹ኩባንያው የሚያቀርባቸው የቀለም ምርቶች ዋጋቸው ውድ ቢሆንም፣ ምርቱን ግን በከፍተኛ ጥራት ነው የሚያመርተው››ያሉት አቶ ሚኬሌ፣ሥራ ላይ ሲውል ቆይታውም ከፍተኛ መሆኑን ያብራራሉ።ቀለምን ውድ የሚያደርገውና ጥራቱንም የሚጨምረው የሰው ጤናንም ኩጉዳት የሚከላከለው ሊድ ከሌለው ነው ያሉት አቶ ሚኬሌ፣ ኩባንያው እያመረተ ያለው ቀለምም ሊድ እንደሌለው ያመለክታሉ፡፡በሀገሪቱ የቀለም ስታንዳርድ እስካሁን ድረስ እንዳልወጣ ጠቅሰው፣ወደፊት አንድ ቀለም ሊድ እንዳይኖረው የሚከልል ስታንዳርድ መውጣቱ እንደማይቀር ይናገራሉ።
እንደ አቶ ሚኬሌ ማብራሪያ፤ቀለም ሲቀባ ውጤቱ ጥሩ እንዲሆን ለባለሞያዎች ልዩ ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ለእዚህም ኩባንያው ሥራውን የጀመረው ሁለት አቅጣጫዎችን ይዞ ነው።አንደኛው የራስን ሠራተኛ በማሰልጠን በራስ ስም ቀለሞችን በማምረት ውጤቱን መሸጥ ሲሆን፣ይህም በምርቱ ላይ ውስንነት በመፍጠሩ ኩባንያው ከኩባንያው ውጭ ባለሞያዎችን በማምጣት አብሮ መሥራት የሚለውን ሁለተኛ አማራጭ ተከትሏል፤ በቀለም ዘርፍ ከኩባንያው ውጭ 50 ለሚሆኑ ሠራተኞች ስልጠና በመስጠት ራሳቸውን እንዲችሉና እንዲለውጡ አድርጓል።እነዚሁ ሰልጣኛች ራሳቸውን ችለው በግላቸውም ከኩባንያው ጋርም አብረው እየሠሩ ይገኛሉ።
የቀለም ማምረት ሥራውን ኩባንያው ሲጀምር የነበረው ካፒታል አንድ ሚሊዮን ብር የማይሞላ ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን ካፒታሉ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል።የሚያመርታቸው የቀለም ምርቶችም ከአስር አይበልጡም ነበር።ዛሬ ላይ ግን ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ የቀለም ምርቶችን እያመረተ ይገኛል።ባጠቃላይም ኩባንያው በአምስት የቀለም ዘርፎች ላይ አተኩሮ ይሠራል።እነዚህም የግድግዳ፣ የኢፌክትና ዲኮሬሽን፣ የኢንዱስትሪ ቀለሞች ወይም ኢፖክሲ ፍሎሪን፣የፈርኒቸር እና የህትመትና በመጠጥ እቃዎች ላይ የንግድ ምልክትን ለማስፈር የሚውሉ ቀለሞች ናቸው።
የፈርኒቸር ኢንዱስትሪው በተለይ የቀለም ቅብና አጨራረስ ላይ የጥራት ችግር የጎደለው መሆኑን በማየት ፖውድር ኮት የተሰኘውን ቀለም የራሱን ቴክኖሎጂ በተከተለ መልኩ ኩባንያው በማምረት ማናቸውም በፈንኒቸርና በብረት ዘርፍ ተሰማርተው ለሚገኙ የዚህ ቀለም የጥራት ግብአት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።
በቀለም ዙሪያ ሌላው ከፍተኛ ፍላጎት እየታየበት የመጣው የህትመትና በመጠጦች ላይ የንግድ ምልክትን ለማስፈር የሚውሉ ቀለሞች ናቸው፤እነዚህን ቀለሞች ለማምረት ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ ኩባንያው በቅርቡ በዚሁ ዘርፍ ኢንኮችን ወደ ማምረት ተሸጋግሯል።ይህ የቀለም ዘርፍ የሚጠይቀው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ቢሆንም፣ኩባንያው ቀለሙን ለማምረት ኢንቨስት እያደረገ ይገኛል።
በሁሉም ቀለም በሚጠይቁ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ በመግባት እየሠራ ያለው ኩባንያው፣ጥራቱንና የቀለሙን ቴክኖሎጂ በመረዳት አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ውስን በመሆናቸው ቅርንጫፎችን በሂደት በመክፈት ራሱን እያሰፋ ይገኛል።እስካሁን ባለው ሂደትም ኩባንያው ሃያ ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በቀጣይ ቁጥሩን ወደ ሃምሳ ከፍ ለማድረግ አቅዷል።
በቀጣይም ኩባንያው ገበያውን በማስፋት ተደራሽቱን ለማረጋገጥ ይሠራል። በርካታ ዜጎችንም በማሳተፍ ከዚህ የበለጠ ለመሥራትም ፍላጎትም ይዟል። በቀለም ኢንዱስትሪ የሚታየውን ክፍተት በማየት ለመሙላትና ለደምበኞቹ ለመድረስም አቅዷል።በዚህም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ ተስፋ ሰንቋል።
በሀገሪቱ እያደገ ከመጣው የግንባታ ሴክተር እኩል የቀለም ፍላጎትም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደመጣ አቶ ሚኬል ይጠቁማሉ፤በዛው ልክ የምርቱ መጠን ከፍ እያለ እንደመጣ ጠቅሰው፣ጥራቱ ላይ ብዙ መሥራት እንደሚቀረው ይናገራሉ።አብዛኛው ወደ ኩባንያቸው የሚመጣ ደምበኛም ጥራትን የተረዳ እንጂ ዋጋውን የሚያይ እንዳልሆነ ይገልፃሉ።
በቀለም ላይ ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት እንዳለበት ጠቅሰው፣ተጠቃሚዎች ገንዘባቸውን ወጪ አድርገው የሚገዟቸው ቀለሞች የረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ጥራት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውም ይጠቁማሉ።ይህም ዛሬ የሚያወጡትን ገንዘብ በቀለሙ ጥራት ምክንያት በጊዜ ሂደት ሊመለሱት እንደሚችሉ ማወቅ እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ።
ቀለም ሦስት ነገሮችን ማሟላት እንደሚገባው የሚጠቅሱት አቶ ሚኬሌ፣ መታጠብ እንዳለበት፣ ቀለሙንና ይዘቱን መቀየርም እንደሌለበትና ኩባንያውም ይህን ዋስትና ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ይመሰክራሉ።ተጠቃሚዎችም ወጪን ለመቀነስ ሲሉ ምን ማስቀደም እንዳለባቸው ማወቅ ይገባቸዋል ይላሉ።በዋጋም ሆነ በጥራት የተሻለ የሚሉትን የቀለም ምርት መምረጥ እንዳለባቸውም ይመክራሉ።
በአሁኑ ወቅትም ጥራት ላይ የማተኮሩ ጉዳይ ከተጠቃሚው ዘንድ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ያስረዳሉ።ወደኩባንያቸው እየመጣ ያለው ደምበኛም ይህንኑ ያወቀና ጥራት ላይ ምንም አይነት ድርድር የማያደርግ መሆኑን ያረጋግጣሉ።
በየትኛውም አለም የፀረ ባክቴሪያ ቀለሞች ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉት ትምህርት ቤትና ሆስፒታሎችን በመሰሉ የህዝብ ተቋማት ውስጥ መሆን እንዳለባቸውም አቶ ሚኬሌ ተናግረው፤ ይህንንም መንግሥት በስታንዳርድ ውስጥ ቢያስገባና አስገዳጅ ቢያደርገው እንዲህ አይነቱን ቀለም የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና እነዚህ ተቋማትም በዚሁ ቀለም ብቻ እንደሚጠቀሙ ይጠቁማሉ።መንግሥትም እነዚህን ቀለሞች በስታንዳርድ ውስጥ ማስገባት እንዳለበት ያመለክታሉ።
በቀለም ዘርፍ በመሰማራትና ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ረገድ እንደተሳካላቸው የሚገልፁት አቶ ሚኬል፤ የዚህ ትልቁ ሚሰጥር ከተቀሩ የኩባንያው ሠራተኞች ጋር በጋራ መሥራታቸውና ምርቶቻቸው ምንም አይነት ለውጥ ሳያሳዩ ዘላቂነት ባለው መልኩ መመርታቸውን ይጠቅሳሉ።ጥራት ላይ ማተኮራቸውና ቀድመው ዕቅዶችን አውጥተው መንቀሳቀሳቸውም ሌላው የስኬታቸው ሚስጥር መሆኑን ይናገራሉ።
መነሻቸውን አውቀውና መድረሻቸውን አልመው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙና ወደመድረሻቸው የሚወስዳቸው ዘላቂነት ያለውና ጥራት ላይ ያተኮረው ሥራቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ውጣውረድ ሲያጋጥማቸው በበጎ የማየትና ከችግሩም ተምሮ የመነሳትና ጥቅም የማውጣት ልምድ እንዳላቸውም ይናገራሉ።
ኩባንያቸው በአስር የቀለም ምርቶች ሥራውን ጀምሮ በአሁኑ ወቅት በአምስት የተለያዩ የቀለም ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረቱ፣ ከዚህ ቀደም ከውጭ ሲያስመጣቸው የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉ፣ ከኩባንያው ጋር አብረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞችም መለወጣቸው በራሱ የኩባንያው እድገትና ስኬት ማሳያ መሆናቸውንም የጠቁማሉ።
በተመሳሳይ በዚህ የቀለም ማምረት ሥራ ገንዘባቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉ ባለሀብቶችም የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ከማሳደድ ይልቅ በጥራት ላይ በማተኮርና የተጠቃሚውን ፍላጎት በማየት ኢንቨስት ቢያደርጉ ሊሳካላቸው እንደሚችሉ አቶ ሚኬሌ ይጠቁማሉ።ባለሀብቶች ወደ ሰፊው ገበያ ከመግባታቸው በፊት በቅድሚያ ጠባቡ ላይ ማተኮር እንደሚገባቸውና ቀስበቀስ ወደሰፊው ገበያ መቀላቀል እንደሚችሉም ይመክራሉ።ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢንቨስትመንታቸው ደምበኛ ተኮር መሆን እንዳለበትና ደንበኛንም ያከበረ ሊሆን እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2012
አስናቀ ፀጋዬ