የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና ያለውን የግብርና ዘርፍ በማዘመን ሀገሪቱ በዘርፉ ራሷን ከመቻል አልፋ የውጭ ምንዛሪን እንድታገኝ የሚያደርጉ በርካታ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር ታዬ ታደሰ እንደሚናገሩት ኢንስቲትዩቱ በምግብ ሰብል ራሳችንን ለመቻል አስፈላጊ በሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ምንዛሪ ይሆናሉ በሚባሉ እንዲሁም የምግብ ይዘትን ከማሻሻል አኳያ በተመረጡ ሰብሎች ላይ ምርምሮችን እያካሄደ ነው።እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በሀገሪቱ የግብርናው ዘርፍ ባለፉት አሥርት ዓመታት ለውጥ አሳይቷል።በምርት ዕድገት ደረጃም ከስምንት እስከ 10 ከመቶ ምርታማነት እድገት አስመዝግቧል፤ ይህ ቢሆንም ግን እድገቱ ሀገሪቱ ካስቀመጠችው ግብ አንጻር ሲታይ አነስተኛ ነው።በየዓመቱ ከሚመረቱ ሰብሎች በተለይም የምግብ ሰብሎች የሚባሉትን ስንዴን፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ማሽላና ሩዝን ብንመለከት በአማካይ ያደገው የምርት መጠን በየዓመቱ ከአንድ ኩንታል በታች ነው።ይህም ከሀገሪቱ እድገት ጋር ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው።ይህንን ከመቀየር አኳያ አሁን ከምናመርተው ዕጥፍ ምርት መስጠት የሚችሉ የምርምር ውጤቶች ያሉ ሲሆን፣ የግብዓት አቅርቦት ላይ ያለው ክፍተት ግን ምርታማነትን ለመጨመር ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል።ይህ ማለት ግን ያሉን የቴክኖሎጂ አማራጮች ሙሉ በሙሉ ፍላጎታችንን የሚያሟላ ነው ማለት አይደለም፡፡
በሀገሪቱ እጅግ በርካታ ዝርያዎች ተለቀዋል፤ ጥቅም ላይ የዋሉት ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።ኢንስቲትዩቱ ብቻ ከ740 ያላነሱ ዝርያዎችን የለቀቀ ቢሆንም እነዚህ ዝርያዎች አብዛኞቹ አርሶ አደሩ እጅ አልደረሱም።የዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ምርምር የማውጣትና ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ትስስሩ ጠንካራ አለመሆኑ ነው፤ ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም ትስስሩን ማጠናከር ይፈልጋል።አዲስ ቴክኖሎጂ ሲወጣ በቀዳሚነት ተጠቃሚን ማዕከል ማድረግ ሲኖርበት፣ ቴክኖሎጂው ወደ አርሶአደሩ የሚደርስበት መንገድም አብሮ መታሰብ ይኖርበታል።ቴክኖሎጂዎችን አርሶ አደሩ ዘንድ ለማድረስ የሚረዱ መንገዶችን ለመፍጠር የሚመለከታቸው አካላት በትስስር መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በምግብ ሰብሎች የሚያካሂዳቸው ምርምሮች እንዳሉ ሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግብርና ውጤቶችን በማቀናበር ሂደቶችን ማድረግ የሚችሉ ኢንዱስትሪዎች በስፋት እየመጡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለእነርሱ ግብዓት የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማውጣትና በበቂ እንዲመረት ማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራው ያለ ሥራ ነው።የብቅል ገብስ፣ የዳቦ ስንዴና የመኮረኒና ፓስታ ስንዴ በይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማውጣት ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት።ከዚህ ጎን ለጎንም የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው? በሚለው ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጥራት ያለው ቴክኖሎጂን ለማውጣት የሚያስችል አቅም የመገንባት ሥራዎችም በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
በተጨማሪ እንደ ኑግና ሰሊጥ የመሳሰሉት የቅባት ሰብሎች ላይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወጥተዋል።ለውጭ ምንዛሪ ከሚውሉ ደግሞ እንደ ቡና፣ ቦሎቄና ቅመማ ቅመም ካሉ ሰብሎች ቦሎቄ የቫይታሚን ኤ ይዘት እንዲኖረው፣ በቆሎ የቫይታሚን ኤና አይረን ይዘት እንዲኖረው ሆኖ አዳዲስ ዝርያዎችን ማውጣት ተችሏል።በቦሎቄ የወጣውን ዝርያ አርሶ አደሩ ዘንድ የማድረስ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ የበቆሎው ዝርያ የምርምር ውጤቱን ጨርሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ እየተጠበቀ ይገኛል።
የምግብ ይዘትን ከማሻሻል አኳያ በአትክልትና ፍራፍሬ የሚደረጉ ምርምሮችም በከተማም ሆነ በገጠር ያለው ማኅበረሰብ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኝ ከማድረግ በተጨማሪ፣ አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ሰርቷል።ኢንስቲትዩቱ በ2011 ሰብል ዘመን የተለያዩ 36 ዝርያዎችን ሲያስመዘግብ፣ በዚህ በጀት ዓመት ደግሞ 18 ዝርያዎችን እንደ ጤፍ፣ ማሽላ በቆሎና በሌሎች የተለያዩ ሰብሎች ላይ ለማስመዝገብ ቀርበዋል።
እንደ ምርምር ተቋም ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመበት የግብርና ቴክኖሎጂን ማመንጨት፣ የመነጩትን ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደር ጋር ማድረስና ተጠቃሚ የማድረግ ሶስት መሠረታዊ ዓላማዎች እንዳሉት ያወሱት ዳይሬክተሩ የምርምር ሥራ ውጤት አርሶ አደሩ እጅ መድረስ ከቻለ ትርፋማ ነው ማለት እንደማይቻል ይናገራሉ።ከዚህ አኳያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ እጅ ገብቶ ለምርት እንዲበቃ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ በግብርናው ዘርፍ አሁን ያሉብንን ችግሮች ባሉን ቴክኖሎጂዎች ልንፈታ እንችላለን፤ ቢሆንም ግን አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች አሉ።የግብርናው ዘርፍና የእርሻ ሥርዓቱ በተለያየ የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይቀየራል፤ አሁን በሰው ኃይል የሚሰሩ የእርሻ ሥራዎች በማሽን ይተካሉ፣ የኅብረተሰቡ ፍላጎትም ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና እየተለወጠ ሲሄድ ይሄን ማስተናገድ የሚችል የምርምር ሥራ ያስፈልጋል፤ በዚህ ረገድ ምርምሩን የማዘመን አቅምን መገንባት ይጠይቃል።
በቅርብ ጊዜ እንደ ተቋም በተመረጡ አምስት ሰብሎች ማሽላ፣ በበቆሎ፣ በቆላ ጥራጥሬና በሽንብራ ዝርያዎች ላይ የማዘመን ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በአዲስ መልክ ጤፍንም የማስገባት ዕቅድ አለ።እነዚህ ሥራዎች ውጤት እንዲያሳዩና ለምርት እንዲበቁ ምርምሮቹን በሁሉም ክልሎች ለማስፋት ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን እየተወጣ ሲሆን ሌሎች ተቋማትም አብረው እየተናበቡ ውጤታማ የሆነ የምርምር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል።
ዶክተር ደሳለኝ እንደሚሉት ሌላኛው የምርምር ፕሮግራም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ምርምር ሲሆን፣ በዚህ ምርምር በዋናነት የሚሰራው በየጊዜው እየታጠበ ወደ ወንዝ የሚገባውን አፈር የመጠበቅ ተግባር ነው።በቂ የሆነ ለም አፈር እያለን ነገር ግን እኛ እየተራብን በየጊዜው ማዳበሪያ የምንጨምርበት አፈር ሄዶ ግብጽን እያጠገበነው ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት መጠበቅ እንዲቻል አፈሩ በተፋሰስ ውስጥ እንዳይሄድና ባለበት ተጠብቆ እንዲቆይ ወይም ወደ መሬት እንዲሰርግ የሚያደርግ የምርምር ሥራ እየተሰራ ነው።በዚህ በከፍተኛ ደረጃ የግብርና ልማቱን በሚያግዝ የምርምር ሥራ የተለያዩ አካላዊና ኬሚካላዊ ዘዴዎችን በመጠቀም እንዴት አፈር እና ውሃን ማዳንና ማከም እንደሚቻል በርካታ ተሞክሮዎች እየተሰሩበት ይገኛል ይላሉ።
ሌላኛው በመስኖ ላይ የሚሰራው የምርምር ፕሮግራም ነው።በዚህ ፕሮግራም በዝናብ መልማት የማይችሉ ወይም በቂ ዝናብ ማግኘት በማንችልባቸው፣ በተለይም ቆላማ ቦታዎች ላይ በመስኖ ማልማት የሚያስችል ምርምር ይካሄዳል፤ በምርምሩ የትኛው ቦታ ምን ያህል ውሃ ይፈልጋል፤ የትኛው ሰብልስ ምን ያህል ጊዜ ውሃ ማግኘት ይፈልጋል የሚሉት ይጠናሉ። በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ቦሎቄና ሽንኩርት ላይ በዋናነት ሲሰራ በሌሎችም ሰብሎችና አትክልቶች ላይ ምርምሩ ተካሂዶ ተግባራዊ ይደረጋል፤ ከዚህ በተጨማሪ በቂ ዝናብ በሚያገኙ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የሚባሉትን በዋናነት ነው እንጂ ይሔ ብቻ አይደለም ውሃ በማይገኝባቸው በቆላማ ከመሬት ወጥቶ የሚሄደውን ውሃ በመያዝ ለሚቀጥለው የሰብል ዘመን የምንጠቀምበት የውሃ ማቆር ሥራም ይሠራል።
የጨዋማ አፈር ምርምር ፕሮግራም ሰባተኛው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ 11 ሚሊዮን ያህል ሄክታር መስኖ በሚጠቀሙ በተለይ ወደ አፋር፣ ሱማሌ፣ ትግራይና መሆኒ በሚባሉ አካባቢዎች ላይ ከውሃ አያያዝና አጠቃቀም እውቀት ማነስ ሳቢያ ጨዋማ አፈር ይፈጠራል።ስለሆነም ይህ ጨዋማ አፈር እንዳይፈጠርና ከተፈጠረም ወደ ነበረበት ለመመለስና አፈሩን ማዳን እንዲቻል የጨዋማ አፈር
ምርምር ይካሄዳል።ስምንተኛው የአዳዲስ ማዳበሪያዎች ፍተሻ ፕሮግራም ነው።በዚህ ፕሮግራም ከውጭ የሚገቡ ማዳበሪያዎችን አስመጪዎቹ ወይም ላኪዎች ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ይፈተሽልን የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ።ማዳበሪያው ለሀገራችን ሥነ ምህዳር ይስማማል ወይ ጥራትና ምርታማነትን ይጨምራል ወይ የሚለው ከተፈተሸ በኋላ ለሀገራችን ጠቃሚና ምርታማነትን የሚጨምር እንዲሁም አሉታዊ ተጽዕኖን የማያስከትል ከሆነ “ይሆናል” ተብሎ ሐሳብ የሚሰጥበት ፕሮግራም ነው።
በተጠቀሱት ስምንት ፕሮግራሞች እስከ ዘንድሮው የ2012 በጀት ዓመት 248 የምርምር ሥራዎች ሲኖሩ፣ ለ2013 ዳይሬክቶሬቱ ያቀደው ሲጨመር ደግሞ ወደ 316 የምርምር ሙከራዎች ይኖሩታል።ከቴክኖሎጂ ማውጣት በተጨማሪ ቴክኖሎጂዎችን የማስተዋወቅ ሥራም ይሠራል፤ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት 4122 ወንድ አርሶ አደሮች 1231 ሴት አርሶ አደሮችን ወጣቶችን መድረስ ችሏል።ይህ ቴክኖሎጂን የማስተዋወቅ ሥራ በትንሽ ቦታ የሚሠራ ሲሆን የማስፋፋት ሥራ ደግሞ በሰፋፊ ቦታዎች ላይ ኩታ ገጠም መሬት ላይ ለ1246 አርሶ አደሮችና 351 ሴት አርሶ አደሮች በጥቅሉ 1597 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ማስፋፊያዎች ሥራ ተሠርቷል።ከዚህ በተጨማሪ የሚወጡ ቴክሎጂዎችን አርሶ አደሩ እንዴት እንደሚጠቀምባቸው ይረዳ ዘንድ ዳይሬክቶሬቱ ስልጠና ይሠጣል፤ በዚህ ዓመት ብቻ ለ8339 አርሶ አደሮች ስልጠና ሰጥቷል።
እየተካሄዱ ያሉ ምርምሮች እንደ ሀገር ግብርናውን በምን ደረጃ ያግዙታል በሚለው ላይ ዶክተር ደሳለኝ እንዳሉት፣ በማዳበሪያ ረገድ ሀገራችን ወደ 14 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በየዓመቱ በውጭ ምንዛሪ የምታስገባ ሲሆን ይህ የምርምር ሥራ ካደረገው አስተዋጽዖ መካከል የማዳበሪያ አጠቃቀምን በመጨመር ምርትና ምርታማነትን መጨመር መቻሉ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከጥራጥሬ ሰብሎች ጋር ታሽቶ በሚጨመረው ማዳበሪያ አማካኝነት የማዳበሪያ ፍጆታን ቀንሶ የተሻለ ምርታማ መሆን የሚያስችለው ምርምርም ከፍተኛ ጠቀሜታን አስገኝቷል።አሲዳማ አፈርን በማከምና ውሃማ መሬትን በማንጣፈፍ ፕሮግራሞች ምርት ፈጽሞ መመረት የማይቻልባቸውን አካባቢዎች እንዲመረትባቸው በማድረግ ምርታማነትን ከ60 ከመቶ እስከ 300 ከመቶ መጨመር ችሏል።ውሃማ መሬትን በማንጣፈፍም ምርታማነትን እስከ ሦስት እጥፍ መጨመር ተችሏል።
እየተካሄዱ ያሉ የምርምር ሥራዎች ለግብርናው ዘርፍ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ያላቸው ፋይዳ እጅግ የላቀ ቢሆንም ሙሉ አቅምን ተጠቅሞ የተሻለ ለመስራት መሠረታዊ የሚባሉ ተግዳሮቶች እንዳሉ የጠቆሙት ዶክተር ደሳለኝ፤ እርሳቸው እንዳሉት በተለይ የበጀት እጥረትና ለምርምር ሥራ የሚውሉ ኬሚካሎችን ለማግኘት የሚከፈለው ዋጋና የሚወስደውን ጊዜ በዋናነት ይጠቅሳሉ።በተፈለገው ልክ ምርምሮችን ለማካሄድ የሚያስችል መሠረተ ልማትን ለማሳደግና የኬሚካል ግዢ ለማከናወን የሚበጀተው በጀት በጣም ያንሳል።በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ በይበልጥ ምርምር የሚደረግበት የአፈርና የእጽዋት ምርምር እንዲሁ በደፈናው የሚካሄድ ሳይሆን ለምርምር አስፈላጊ የሆኑ ኬሚካሎችን በመጠቀም በመሆኑ የኬሚካል እጥረቱ ሥራውን በከፍተኛ ደረጃ ወደኋላ እየጎተተው ይገኛል።ከዚህ አንጻር ግዢ ኤጀንሲና ገንዘብ ሚኒስቴር እገዛ ቢያደርጉ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።ሌላው ትልቁ ችግር ደግሞ የቴክኒሺያኖች እጥረት ሲሆን በዚህ ምክንያት ላብራቶሪዎች ወደ መቆም ደረጃ እየደረሱ ይገኛሉ።ስለሆነም በአጠቃላይ ለተፈጥሮ ሐብቱ ያለው የመንግሥት አናሳ ትኩረት መለወጥና እንደ ሀገር ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የሚኖረውን ሰፊ አስተዋጽዖ በመገንዘብ ማገዝ ይኖርበታል የሚለው የዶክተር ደሳለኝ የመጨረሻ መልዕክት ነው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2012
አብርሃም ተወልደ