የሚኒስትሮች ም/ቤት ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ዉሳኔዎች አሳልፏል፡፡
ም/ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ስለምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን፣ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት በሕብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳት መከላከል እና መቆጣጠር፤ ደህንነቱ፣ ፈዋሽነቱና ጥራቱ ባልተረጋገጠ መድሃኒት እንዲሁም ደህንነቱ እና ውጤታማነቱ ባልተረጋገጠ የህክምና መሳሪያ ምክንያት በሰው ላይ የሚደርስን የጤና ችግር መከላከል እና መቆጣጠር በማስፈለጉ የጤና ሚኒስቴር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብ እጥረትና የሥርዓተ ምግብ መዛባት የረዥም ጊዜ ተግዳሮቶች ሆነው የቆዩ ሲሆን መንስኤዎቹም ስር የሰደደ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ፣ ዝቅተኛና ከሚጠበቀው በታች የሆነ የእናቶችና የህጻናት ክብካቤና አመጋገብ ስርአት፣ ከፍተኛ የሆነ የግልና የአካባቢ ንጽህና ጉድለት እና ልማዳዊና ባህላዊ የአመጋገብ ስርአቶች የመሳሰሉት ችግሮችን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር ብሔራዊ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ፖሊሲ አዘጋጅቶ፣ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውልም ወስኗል፡፡
ም/ቤቱ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግሥት እና በእስራኤል፣ በፈረንሳይ፣ በሞሮኮ መንግሥታት መካከል የተደረጉትን የአየር አገልግሎት ስምምነትን ለማጽደቅ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግስት እና በሞሮኮ መንግሥት መካከል የተደረገውን የኢንቨስትመንት ጥበቃ እና የግብርና ዘርፍ ትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
በመጨረሻ ም/ቤቱ ለመቀሌ ውሀ አገልግሎት አቅርቦት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. እና በቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ መካከል የተደረገውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን በብድር የተገኘው ገንዘብ በመካከለኛ ጊዜ የሚከፈል፣ የወጪ ጫናው ቀላልና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ም/ቤቱ የብድር ስምምነቱን ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡