ኢትዮጵያ የባህል መድረክ ናት። ልጆቿን ባህል መግባና አስተሳስራ ዘመናትን በፍቅር ያሸጋገረች። በዚህ ምክንያት እንደ ዜጋም ሆነ ማህበረሰብ እንኮራለን። እናት አገራችን የአብሮነት እሴት የጋራ ሀብት የታደለች ነች። ለምለሟ ምድራችን ሲደክሙ ደግፎ፣ ሲወድቁ አንስቶና ዳብሶ የሚያድን የብዝሓነት ተምሳሌት የሆነ ህዝብ ባለቤት ናት። ለልጆቿ ያላትን ከመቸር፤ የቋጠረችውን ሁሉ ፈታ እንኩ ከማለት ለአፍታ ችላ ብላ አታውቅም። ዋናው ቁምነገር ያዘለው ጥያቄ ‹‹እኛ ልጆቿስ የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ወይ?›› የሚለው ነው። ‹‹አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩ በል›› አይደል ወጉም አባባሉ።
ወገን አገርህን ፈልገህ አግኝተሀል? የትስ ነው? አገር ማለትስ በራሱ ምንድነው? እንደ እኔ እንደኔ አገር ማለት ሰው ነው። አገር ያለ ሰው ምንም ነው። እመነኝ ጋራ ሸንተረሩ፣ ውቅያኖስ፣ ባህሩ ሰው ከሌለ ምንም ናቸው። ሰው ባይኖር ስም እንኳን አይኖራቸውም ነበር። መጠቀሚያ ናቸው። በቃ! አገርህን ስታስብ የቅርብ ወገንህና አጋርህ ውስጥ ፈልግ። ለሱ የምታደርገው በጎ ነገር ሁሉ ለአገርህ እንዳደረክ ቁጠረው። የምታልመው ጥሩ እሳቤ ሁሉ የተቆርቋሪነትህን አመላካች መሆኑን አትዘንጋ።
ይህችን የባህል መድረክ፤ የአኩሪ ታሪክ ባለቤት፤ ዛሬ ላይ ደጉ ገበሬና ሁሉም ዜጎቿ ‹‹አገሬ ክብሬ መጠለያዬ›› ይሏት ይሆን? እርግጥ አገር ወዳድነት የህዝቦቿ ባህል ወግ እንጂ ጊዜያዊ ሆይ ሆይታ አይደለም። ታዲያ መውደዳችንን በምን እንለካለን? በተግባርስ እንዴት እናሳያለን? ‹‹እውነት አገር ማለት ሰው ነው›› የሚለውን ብሂል አምነን የሚገባውን ክብር እንሰጥ ይሆን?
“ለወገን ጥላ ሆኖ መቆም ሀበሻ የለመደው አኩሪ ባህሉ ነው” ይባላል። ይህ ቢሆንም አባባሉ ቅሉ ለወገኑ የእግር እሳት የሆነውን ቤት ይቁጠረው። በየቦታው ኢትዮጵያን አገር ያደረጋት ሰው መሆኑ የሚዘነጋ ስንት አለ መሰላችሁ። ቀዬውን ያቀናውን፣ ጋራ ሸንተረሩን ያለማውን ሰው ለቁራሽ መሬት በግፍ አፈናቅሎ አገሬን ልቀቅ የሚለው ለመሆኑ ‹‹አገር ማለት ሰው ነው›› የሚለውን ብሂል ይረዳው ይሆን?
ቀድሞ የነበረውና የተላበስነው አብሮነታችን መሰረቱ ጠንካራ ነው። ያጠነከሩቱ አያት ቅድመ አያቶቻችን ደግሞ አገር ማለት ሰው መሆኑ ገብቷቸው ነበር። የሚገጥሙንን ፈተናዎች ሁሉ ተጋፍጠን ለማለፍ ጥሩው መንገድ ይህን መገንዘብ ነው። አሁን አሁን ‹‹ሰው›› የማለት ልማድ የጎደለን ይመስላል። ‹‹ሰው አገር ነው›› ብለን ማሰብ ስንጀምር ማክበሩም መከባበሩም አብሮ ይመጣል። ያ ደግሞ ትስስራችንን ያጠናክር ዘንድ ፍቱን መድኃኒት ነው።
ወዳጄ ሰውንም ሆነ ወገንህን አክብር፤ ደግሞም አንግሥ። ያን ጊዜ አገርህን ታነግሣለህ። ምክንያቱም እያንዳንዳችን ያነገሥናቸው ሰዎች ተጠረቃቅመው ነው አገር የሚመሰርቱት።
ሰው በተባለ ፍጡር ተመስርታ በትውልድ ቅብብሎሽ የምትዘልቀው በልጆቿ ትጋት የምትሻገረው አገር ፈተና ሲጋረጥባት የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትናፍቃለች። ዛሬ ወገን ወቅታዊ በሆኑ የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ወድቆ ይገኛል። ኢትዮጵያን የምትወድ ከሆነ ይህን ክፉ ጊዜ ከወገንህ ጋር አብረህ ተሻገረው። አገሬን የምትል ከሆነ ኮሮና በፈጠረው ችግር በየቤቱ የተራበና የተጠማ ወገንህን ዞር ብለህ ተመልክት። አግዝ፣ እርዳ። ያኔ ኢትዮጵያ ትፀናለች።
ኢትዮጵያን በሰው ውስጥ ፈልጋት። ሰው የሚባለውን ፍጡር ተረድተህ አገር የሚሉት ቅኔ መቀኘት ጀምር። ከጠላት የሚከላከላት የአብራኳ ክፋይ በችግር ጊዜ የሚደርስላት መከታዋን ትሻለች። በዚህ ወሳኝ ጊዜ በጋራ ሆኖ የሚመክት፣ የሚመጣውን ፈተና በፅናት የሚታገል፣ ከምንም በላይ አገርና ህዝብን የሚያድን፣ ቆራጥ ጀግንነት የተላበሰና ከራሱ ይልቅ ለሌላው የሚያስብ ትውልድ ትሻለች።
ይህ ትርጓሜ ያልገባቸው አንዳንዶች የተፈጠረው ችግር መጠቀሚያ ሲያደርጉት ማየት ግን ያማል። በተለይ የኮሮና ወረርሽኙን ተከትሎ በህዝብ ላይ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ጫና መንግሥት ከህብረተሰቡ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ካልተሻገረው በቀር በህዝቡ ላይ ትልቅ ፈተና ፈጥሯል።
የነጋዴዎች በሁለት እግራቸው መቆም ሰው በመኖሩ ምክንያት መሆኑን መንገር፤ አገር ማለት ከራስ የሚያካፍሉት እንጂ ከሌላ የሚሞጨልፉት አለመሆኑን ማሳወቅ ይገባል። ህዝብን ከማዳን፣ ወገንን ከማትረፍና ኢኮኖሚን ከመታደግ ይልቅ የግል ጥቅማቸውን ያስበለጡ አንዳንድ ነጋዴዎች በማህበረሰቡ ላይ ዋጋ በመቆለል ለእንግልት መዳረጋቸው ተደጋግሞ ተሰምቷል።
የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ኃላፊነታቸውን በመዘንጋት ማህበረሰቡን ላልተገባ ወጪና ኢኮኖሚያዊ ስጋት ዳርገውታል። የኮሮና ወረርሽኝን መስፋፋት ተከትሎ ህዝቡ ወደ መደብርና የገበያ ቦታ በሚያመራበት ወቅት የገጠመው የዋጋ ንረት እጅግ ያልጠበቀው ሆኖበታል።
እነዚህን ግፈኛ ነጋዴዎች ነው ‹‹በሰው ውስጥ አገራችሁን ፈልጉ›› ማለት ያሰኘኝ። ህዝቡ ወትሮ ገበያው ላይ በቀላሉ የነበረው እቃ ‹‹የለም›› ተብሎ አልያም ከነበረው ዋጋ ሦስት አራት እጥፍ ጨምሮ ያገኘዋል። እነዚህ ነጋዴዎች ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ቀውስም ሆነ የአቅርቦት ችግር የህዝቡን ችግርና ወቅታዊ አጋጣሚውን በመጠቀም ብቻ ለመክበር እየሞከሩ ይገኛሉ።
ስለ አገር ደንታ የሌላቸው፤ ስለ ወገን ቁብ ማይሰጣቸው ነጋዴዎች በመንግሥት ተገቢ የሆነ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል። ነገር ግን ህዝቡ በተለየ መልክ አንድ አስተማሪ የሆነ ቅጣት ቢቀጣቸው ብዬ አሰብኩ። መደብርና ሱቆቹን ከማሸግ ባለፈ ሊገለሉና ሊወገዙ ይገባል። ሸፍጠኞች ስማቸው የድርጅታቸው ስም ከነጥፋታቸው በመገናኛ ብዙሃን ህዝብ እንዲያውቀው ቢደረግ ብዬ አሰብኩ። ምክንያቱም ጥፋታቸውን ህዝብ ያውቀዋል፣ ይገስጻቸዋል። ከእነሱ ደንበኝነት ይርቃል። በአጠቃላይ ከመንግሥትም በላይ በመጥፎ ተግባራቸው ህዝብ ይቀጣቸዋል። ያለ ህዝብ ደግሞ ንግድ የለም፤ ትርፍም አይታሰብም።
የአገር ትርጉሙ የጠፋቸው ስግብግቦች በራሳቸው እየፈጠሩ አልያም አንዳች ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ሰበብ እየፈለጉ፤ የማህበረሰቡን የመግዛት አቅም ያላገናዘበ ዋጋን እንዳሻቸው ይቆልላሉ። ህዝብን የሚበዘብዙት ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንገር ይገባል። እርግጥ መግሪያው መንገድ ብዙ ቢሆንም ከመንግሥት ቅጣትና ዕርምጃ ባለፈ ማህበረሰቡ የተግባራቸውን ነውርነት ሊነግራቸው ይገባል። ይህን የሚያደርግበት ማህበራዊ፣ ባህላዊና አገር በቀል እሴት ሞልቶ ተትረፍርፎታል።
አገር ማለት ከሰው የዘለለ ትርጉም የሌለው መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላቸዋል። በመጨረሻም ይህን ማስታወስ ወደድኩ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ህልውና አደጋ የሆኑትን ፈተናዎችን ሁሉ ለመቋቋም ማህበራዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ይገባናል። ያኔ የማንሻገረው ችግር አይኖርም። ቸር ያሰማን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2012
ተገኝ ብሩ