አጭሯ ቀጭኗ ባልቴት የሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ላይ ቆመው እንደ ሃዘንተኛ አፍና አፍንጫቸውን በነጠላቸው አፍነው ቁልቁል ወደ ወንዙ እያዩ ጭንቅላታቸውን እየወዘወዙ ተክዘዋል። እኛ ደግሞ በአካባቢው ካለው የመተንፈሻ አካል ጸር ከሆነው መጥፎ ጠረን ራሳችንን ለመጠበቅ እየተጣደፍን እናልፋለን። የባልቴቷ ነገር ግራ ስላጋባን ሶስታችንም ተመልሰን ምን ሆነው እንደሆነ ጠየቅናቸው።
እኔ ምን እሆናለሁ አሉ ኮስተር ብለው። አታዩትም እንዴ ይሄ ወንዝ በነጋ በጠባ እየጠቆረ ይመጣል በዛ ላይ ይይዘው ይጎተተው አንዳች ቆሻሻ አያጣም አሁንማ ብሶበት አረፋውም ይጠቁር ይዟል አሉ።
ጸሀዩዋ ትሆን እንዴ አላቸው ጓደኛችን በማሾፍ።
ባልቴቷም በዋዛ አላለፉትም ጸሀይ እሚያጠቁር ቢሆን አንተ ከወንዙ ቀድመህ ሻንቅላ ትሆን ነበር ብለው በዛው ወደ ማጉተምተማቸው ገቡ።
ድሮ ቀረ… ወንዝ ድሮ ቀረ …
ደሞ ወንዝም ድሮ ቀረ ይባላል እንዴ ? ማዘር
አዎ እውነቴን ነው ድሮ ቀረ መባል ሲያንሰው ነው፡፡ ድሮ ወንዝ ተወርዶ ጽዳት ይጠበቅ ነበር እንጂ እንዲህ እንደዛሬው ወንዝን ጎርፍ ካልመጣ የሚሸሽ አልነበረም። ለማቋረጥ እንኳ ቢፈለግ በዚያው እግራችንን ለቅለቅ ብለን ነበር የምናልፈው። ኧረ ስንት ነገር ነበረ … እዚሁ አዲስ አበባ እንኳ ሲከፋም ሲተከዝም ወንዝ ተውርዶ ነበር የሚንጎራጎረው። ዛሬ እንዲህ ሊያደርጉት።
እማማ እዚህ ሽታው ጥሩ አይደለም ያሳምምዎታል። ግን እነማን ናቸው እንዲህ ያደረጉት። ምክሩን ጥያቄ አስከትዬ አቀረ ብኩላቸው።
ከተሜው እንጂ ሌላ ማን ይሆናል? መቼም እስከዛሬ ወንዝ የሚወር ጠላት መጣ ሲባል አልሰማ ንም፤ ይሄ እኮ ወራራ ነው አሉኝ በቆሙበት።
ባልቴቷን ገፋፍተን ካሰናበትን በኋላ አገር ያወራበት ችግር እንዲህ እያደገና እየተስፋፋ የመምጣቱን ነገር የየራሳችንን መፍትሄ በማመ ላከት ከጓደኞቼ ጋር በሰፊው አወጋንበት፡፡ የሶስታችንም ምክንያትና የመፍትሄ ሃሳብ ግን ለየቅል ነበር። የተስማማንበት ነገር ቢኖር በቁጥር የሚታወቁት ዋናዎቹ የአዲስ አበባ ወንዞች ብቻ ሳይሆኑ በየደጃፋችን ከአመት እስከ አመት የሚፈሱትም ቦዮች ያው ጥቁር መሆናቸውን፤ ችግሩ ደግሞ የመጥቆራቸው ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ቦታዎች ያሉት ወንዞችና ቦዮች ከአቅማቸው በላይ ከፈሳሹ ቆሻሻ ይልቅ የያዙት ደረቅ ቆሻሻ መብለጡን እንዲሁም ዛሬ ዛሬ የአዲስ አበባ ጌጥ እየሆነ የመጣውም የውሃ መያዣ ኮዳ (ሀይላንድ) የእነዚህ ትልልቅ ወንዞችም ሆነ ቦዮች የሜዳውና የመንገዱ ሁሉ መለያ ጌጥ እንደሆነ ነበር።
በምክንያትና በመፍትሄ ባነሳነው ሀሳብ እኔ የከተማዋ የህዝብ ብዛት ቀን ከቀን እየጨመረ መምጣቱ ዋናው ምክንያት መሆኑን አስቀመጥኩ። ለማስረጃም የእኛን ቤተሰብ በማንሳት፡- እኛ ግቢ ስድስት ቤተሰብ ብቻ ነበር የምንኖረው፣ ለረጅም ዓመታት ተከራይ የሚባል ነገር አልነበረንም፣ የቆሻሻ ማጠራቀሚያው ማዳበሪያ እንኳን የሚሞላው በግድ ነበር። በዛ ለይ በሳምንት አንድ ቀን ቆሻሻ የሚሰበስበው መኪና ሳያቋርጥ ስለሚመጣ ቆሻሻ ብርቅ ነበር። አሁን የእኛ ግቢ እንኳን ድንኳን መጣያ ገመድ መዝለያም ቦታ የለውም፡፡ ከጎረቤት የሚለየን ካልሆነ ግድግዳችንን እንኳ በቅጡ ማየት አይቻልም ቤት ይሰራል ይከራይል ፤ቤት ይሰራል ይከራይል… ትንሽ ቦታ ከተረፈች አንድ ዘመድ ይመጣና ከዛኛው ክፍል ጋር ብትቀላቅላት ይላል አባታችን ተቀብሎ ተግባራዊ ያደርጋል። አሁን እኛ ግቢ በጣራ የማይገናኝ ቤት የለም። ታዲያ ይሄ ሁላ ሰው በሶስት መቶ ካሬ መሬት ላይ በአንድ የቧንቧ ውሃ መስመር፣ በአንድ መጸዳጃ ቤት፣ በአንድ ሻወር እየተጠቀመ እንዴት ቆሻሻው አይበዛም። በመሆኑም መፍትሄ የሚሆነው ወደ አዲስ አበባ የሚደረገውን ፍሰት መቀነስ ብቻ ነው ካልሆነ … ሃሳቤን ዘጋሁ።
አይደለም ዘመኑ የፈጠራቸው በካይ ቆሻሻዎች መብዛታቸው እንጂ የሰው መብዛት የቆሻሻ መብዛትን አያመጣም፤ ማንም ፈልጎ ቆሻሻ አይፈጥርም አለ የኔ የሃሳብ ተቃዋሚ የሆነው ጓደኛዬ። ማብራራቱንም ቀጠለና ድሮ ፌስታል አናውቅም ነበር፤ ሀይላንድ የለም ባጠቃለይ ለአካባቢ ብከለት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የፕላስቲክ ምርት በብዛት አልነበረም። ከፕላስቲክ ምርት የሚታወቁት ኮንጎ ጫማ፣ ጋዴ ጫማ፣ ቦቲ ጫማ፣ ሳህንና ኩባያ ብቻ ነበሩ። በዛ ዘመን የውሃ ባሊው የብረት ሳፋው የብረት ታንከሩ እንኳ ቢሰቀል የብረት ነበር። ይሄ እንግዲህ ከእኛ በፊት የነበረውን የባዶ እግር፣ የእንቅብና ቁና እንዲሁም የጋንና የማሰሮን ዘመን ትተን ነው።
በእኛ የልጅነት ዘመን እንጀራና ዳቦ ሲገዛ በዳንቴል ነበር የሚያዘው፤ አናቶቻችን ገበያ ሲወርዱ ቅርጫትና ዘንቢል ይዘው ነበር። እነዚህ ደግሞ መሬት ጥለህ አፈር ለበስ ብታረጋቸው በወር ውስጥ የሚበሰብሱ ናቸው። ቅርብ ግዜ እኮ ነው ይቺ ኬንያ የምትባል ሀገር በርካታ የፕላስቲክ ምርት ልካ ያበላሸችን። አሁን ደግሞ ቻይና ሁለት ዳቦ የማይዝ ፌስታል እያመረተች በየመንገዱ ስኳሩ ቲማቲሙ ሽንኩርቱ ሁላ ሲበተን ይውላል ይሄ አገልግሎት ተብሎ ደግሞ ወንዙ ሜዳው ሀገሩ ሁሉ በፌስታል ይበከላል፡፡ በዛ ወቅት ከየቤቱ የሚወጣው ቆሻሻ ለመቃጠል እንኳ ጊዜ አይወስድበትም ነበር፡፡ ለኩሰኸው ዞር ስትል አመድ ይሆናል፡፡ አመዱም ሲበተን በቀላሉ አፈር ይሆናል። አሁን እኮ ፕላስቲኩ፣ ጎማው ማይካው አንተ ካለጣፋኸው ሲነድ ውሎ ሲጨስ ያድራል። በዛ ላይ በዚን አርከፍክፈህ እንኳ ብታነደው ሳይበሰብስ የሚኖር የተጨማደደ ልጅ ጥሎብህ ነው የሚጠፋው። ስለዚህ በቀጥታ ወደ ባህላችን ተመልሰን ከፕላስቲክ ምርቶች ካልተፋታን መፍትሄ አናገኝም።
በሁለታችንም ሃሳብ ያልተስማማው አባሪያችን (ጓደኛችን) ቅጥ ያጣው የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታችንና ራስ ወዳድነታችን እየተስፋፉ በመምጣታቸው የተከሰተ ችግር መሆኑን በማስረጃ በማስደገፍ አቀረበ። የአዲስ አባባ ሰው እንኳን ቆሻሻውን በአግባቡ ሊያስወግድ ይቅርና በመንገድ ዳር የተቀመጡትን የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች እንኳ በአግባቡ አይዝም ብሎ ጀመረ። ሃምሳ ግዜ የሚበሰብስና የማይበሰብስ ቆሻሻ እንለይ እየተባለ ይነገራል፡፡ ህዝቡ ግን የተረፈውን ምግብ በፌስታል ቋጥሮ ይጥላል። ሃምሳ ሳንቲ ሜትር ስፋት የሌለው ቦይ ውስጥ ጆንያ ሙሉ ቆሻሻ ይጥላል። ባዶ ገንዳ ቆሞ ዳር ላይ ቆሻሻውን ዘርግፎ ይሄዳል። አብዛኛው ሰው ወንዞች ለቆሻሻ ማስወገጃነት የተፈጠሩ ይመስል ትንሹንም ትልቁንም ቆሻሻ ይዞ የሚሮጠው ወደ ወንዝ ነው። ለሀቁ ከነዋሪው በላይ አጥፊ የለም ችግሩ ግን በይበልጥ ለጉዳት የሚዳርገው ነዋሪውን ሳይሆን በከተማዋ አጎራባች ያሉ አካባቢዎችን ነው። አዲስ አበባ ሆኖ ከወንዝ ውሃ የሚጠቀም አታገኝም ከከተማዋ ወጣ ስትል ግን ከብቶቹ ሰዎቹ ለንፅህና መጠበቂያና ለሌሎች ነገሮችም ይጠቀሙበታል። በዛ ላይ የገጸ ምድር ውሃ መበከል ለከርሰ ምድሩም መበከል መንስኤ ይሆናል።
በፊት ስል በፊት መቼ እንደሆነ እንዳትጠይቁኝ እንጂ በመቅጣት ይታመን ነበር አሉ፡፡ ሰው ሲቀጣ ስለማያጠፋ ተብሎ ማለት ነው። አሁን ደግሞ ማስተማር ይቀድማል በሚል ምልከታ ቅጣቱ ተዘንግቷል እንደኔ ግን ሁለቱም የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሳያውቅ ያጠፋውን ማስተማር አንድ ነገር ነው እያወቀ የሚያጠፋውን ማስተማር ግን ችግሩን ከማበረታት የዘለለ ፋይዳ የለውም።
አባሪያችን ንግግሩን ቀጠለ የነዋሪው ችግር ስል ግን አስተዳደሩንም ያጠቃልላል መቼም በእርግጠኘነት በመንግስት በኩል ወይ በኤጀንሲ አልያም በዳይሬክቶሬት ደረጃ ለዚህ ጉዳይ የተቋቋመ ክፍል መኖሩ አይቀርም። እኛ በትምህርት ቤት ብቻ የምናውቃት «ዳይሬክ ተርነት» ዛሬ ያልገባችበት ጓዳ የለም። ስለዚህ እነሱም ምን እየሰሩ እንደሆነ መጠየቅ አለበት። ለዚህም የተመደበ ገንዘብ ካለ የት እንደገባ መታወቅ አለበት። ማን ያውቃል እነሱስ ወንዝና የወንዝ ዳርቻ እናጽዳ ብለው ቢሯቸውን እያጸዱ ቢሆንስ።
በአዳራሽ ጫጫታና በማስታወቂያ ጋጋታ ከተማን ማጽዳት አይቻልም። በዛ ሰሞን እንደ ወረት በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተሳትፎ ጭምር የተጀመረው የከተማ ጽዳት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የዘመቻውን ወሬ ሳንጠግበው ተደበስብሶ ቀረ። በእርግጥ ያኔም ቢሆን ላይ ላይዩን እንጂ የውሃ መውረጃውን ውስጥ ውስጡን አልፈተሸም ነበር። የሚገርመው ሌሎቹም የሀገሪቱ ከተሞች ይሄንኑ እንደ ምርጥ ተሞክሮ ወስደው እየተገበሩት ነው።
አባሪያችን ልንመልስለት አቅምም ስልጣንም የሌለንን ጥያቄ ጠይቆን ንግግሩ ገታ። ግን እስከ መቼ ይሆን ይቺ አዲስ አባባና ነዋሪዎቿ የቆሻሻ ፋብሪካ መሆናቸው ሳያንስ በከተማዋ ዙሪያ ያለውን ህዝብ እየበከሉ የሚኖሩት?።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011