ድሮ የውሀ ዲፕሎማሲ ሲባል ከቁብ እማንቆጥረው ሁሉ ዛሬ ጆሯችንን እያቆመ ይገኛል። ወደን አይደለም፤ ሀሳቡን በሰማንበት ፍጥነት አባይን ወደ አእምሯችን ይዞ ከተፍ ስለሚል፤ እግረ መንገዱንም የግብፅን ዲፕሎማሲ አይሉት የቃላት ጦርነት ስለሚያስታውሰን እንጂ።
የውሀ ዲፕሎማሲ የራሱ የሆኑ ባህሪያትና መርሆች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ውይይት፣ ፍትሀዊነት፣ የጋራ መግባባት፤ እኩል ተጠቃሚነት፣ የውሀ አያያዝ፣ አጠቃቀም፣ አመራርና የመሳሰሉትን ያካትታል። በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ መርሆቹ የማይነቃነቁ ችካሎች ናቸው። እነዚህ መርሆች ዋና አላማቸው በውሀ ጉዳይ አገራት ወደ ግጭትም ሆነ ጦርነት እንዳይገቡና ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲመጡ ማድረግ ነው።
የውሀ ዲፕሎማሲ (hydro-diplomacy / water diplomacy) ጉዳይ ሲነሳ የውሀ ጉዳይ ቀዳሚ ነው። በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ጉዳዩ እንደምናየውና እንደ ምንሰማው ቀላል ሳይሆን ሲበዛ ውስብስብ ነው። ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ “በከባድ ልፋትና ትእግስት በተካሄደ ድርድርና ውይይት የመጀመሪያው ምዕራፍ ግብ ላይ ደርሷል።” እንዳሉት የድርድር ሂደቱ እጅግ ከባድ እንደነበር ሁሉም ጉዳዩን በጉጉት ሲከታተል የነበረ ሁሉ በሚገባ የሚያውቀው ነው። በተለይ ድርድሩንም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ከባድ ያደረገው ማን እንደሆነ ይታወቃል። ግብፅ ነች። አንዴ አንዱ ጋር አንዴ እዛ ጋር፤ ቆይታ ይብራራልኝ፤ ትንሽ ቆይታ ደግሞ ዋ … በማለት ለማስፈራራት መሞከር ብዙ ብዙ ግራ አጋቢ ተግባራትን ስትፈፅም መቆየቷ ነው ለድርድሩ መወሳሰብ ዋናው ምክንያት።
ከግብፅ ቀድማ ኢትዮጵያ የምታካሂደው የውሀ ዲፕሎማሲ ትግል ከግብጽ ሳይንቲስቶች፣ መሃንዲሶች፣ የህግ አዋቂዎች እና የዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር ውይይት መክፈት ቢችል እና በዓለም አቀፍ መድረክ ደግሞ የአፍሪካ ህብረትን፣ የተባበሩት መንግሥታትን፣ የአሜሪካን፣ የአውሮፓን፣ የዓለም ባንክን፣ የአይ.ኤም.ኤፍን ድጋፍ ማግኘት ቢችል ሁሉም ቀላል ይሆን ነበር የሚሉ አሉ። ይህ እውነት አይደለም አይባልም። ምክንያቱም መንግሥትም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያ በሁሉም መንገድ (ሚዲያውን ጨምሮ) የግብፅን ያህል አለመንቀሳቀሷና ግብፅ አረቡን አለም ጭምር ጠራርጋ ለመውሰድ እየተንደረደረች መሆኗን እየተናገሩና አሁንም መንግሥት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት እየመከሩ መሆናቸው ነው።
ቢቢሲ አማርኛው በአንድ ወቅት የኦሬጎን ዩኒቨርሲቲ የመልክኣ ምድር ፕሮፌሰሩ አሮን ዎልፍን ጠቅሶ እንደዘገበው “ስለ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ውሃ ስናወራ ሦስት ነገሮችን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል”፤
“የመጀመሪያው ጉዳይ የውሃ እጥረት ነው። ሁለተኛው ደግሞ እሱን ተከትሎ የሚመጣው ፖለቲካዊ ቀውስ ነው። . . . ሦስተኛው ጉዳይ ግን ከሁለቱ የተለየ እና ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ሲሆን፤ እሱም የድንብር አቋራጭ የውሃ አካላት ጉዳይ ነው። ማለትም ሁለት እና ከዚያ በላይ ሀገራትን የሚያዋስኑ የውሃ አካላት በላይኛው እና በታችኛው ሀገራት መካከል የውሃ አጠቃቀም መብትን በተመለከተ ሊፈጠር የሚችለው አምባጓሮ አስጊነት ነው። የዚህ ፅሁፍ ትኩረት ሦስተኛው ላይ ነው።
ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ከዛሁ ጋር በተያያዘና ዘመናትን በዘለቀ ኢፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀምን በተመለከተ ባደረጉት ጥናት እንደገለፁት የአባይ ተፋሰስ የውሀ ገብነትና በረሀማነት ሁለት ተቃራኒ ጫፎችን በአንድ የሚያስተሳስር ቢሆንም፤ ሁለቱን ጫፎች በአንድ ማስተሳሰርና የጥቅም ተጋሪ ማድረግ አዳጋች ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል።
እንደ ማሞ ውድነህ ፅሁፍ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የስለላ ተግባሯን የጀመረችው ከሰባት ሺህ ዓመታት በፊት ሲሆን ይህም የጥንቱን ኑብያን መውረርንና አባይና ቀይ ባህርን መቆጣጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው። ማሞ እንደሚሉት ይህ ድሮም ነበር፣ ዛሬም አለ፤ ወደፊትም ይኖራል።
የኢትዮጵያ፣ አባይና ግብፅ ገዳይ እንዲህ እንደሚወራው ቀላል አይደለም። ዘመናትን የተሻገረ ሲሆን ከአፄ ዘርአያእቆብ (1426-1460) ጀምሮ በግብፅ ፀብ አጫሪነት ምክንያት ከፍተኛ ውዝግብ የነበረ ሲሆን ዘርአያቆብ ግብፅ ትንኮሳዋንና በክርስቲያን ወንድሞች ላይ እያደረሰች ያለችውን ጥቃት ካላቆመች አባይን ሊያቆሙት፤ ወይም አቅጣጫውን ሊያስቀይሩት እንደሚችሉ በደብዳቤ መግለፃቸውና እሷም በዚህ ደብዳቤ ምክንያት አደብ መግዛቷ ተጠቃሽ ነው።
በቅርብ የ”ዘመን” መፅሄት ላይ እንደሰፈረው የግብፅና የኢትዮጵያ ግንኙነት በግልፅ መደፍረስ የጀመረው በመሀመድ አሊ ፓሻ (ከ1805 እስከ 1848 ግብፅን የመራ) ዘመን ሲሆን “ግብጽን ለማዘመን” በሚል መነሻ አባይን ለመቆጣጠር ማቀዱና የልጅ ልጁ ከዲቭ እስማኤል የአያቱን ሌጋሲ ለማስቀጠል መፈለጉና በመሀመድ ፈለግ ሊሄድ መሞከሩ ነው። ናስር፣ ሳዳት፣ ሙባረክ … እያልን አሁኑ አልሲሲ ድረስ ብንመጣ ያላቸው አቋም ያውና ያው ሆኖ ነው የምናገኘው። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ እንደሚሉትም አታካች ነው፡፡
ፕሮፌሰር ያዕቆብም እንደሚሉት የአባይ ጉዳይ አሁን የተጀመረ ሳይሆን የቆየ የኢትዮጵያ የመገንባት ህልም ነው። እሳቸው እንደሚሉ ኢትዮጵያ በ1894 ዓ/ም የአባይ ተፋሰስንም ሆነ ገባሪ ወንዞችን ፍሰት ላለመግታት በይፋ ቃል ገብታ ነበር። ግብፅና ሱዳን በ1994 ዓ.ም ተፋሰሱን በብቸኝነት ለመጠቀም በድብቅ ሲደራደሩም ኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ ተቃውማ መግለጫ አውጥታ የነበረ ሲሆን የመግለጫው ይዘትም የሁለቱ ሚስጥራዊ ድርድርና ውሳኔ ፍፁም ስህተት መሆኑን፤ ክፍፍሉም ኢፍትሀዊ መሆኑን፤ ኢትዮጵያ ወደ ፊት ተፋሰሱን በወቅቱ ለነበረውም ሆነ ለመጪው ትውልድ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲባል ጥቅም ላይ ልታውለው እንደምትችል የሚያመለክት ነበር።
“ከዚህም ባለፈ ግብፅ በ1972 ዓ/ም ከአባይ ተፋሰስ የምታገኘውንና በታላቁ የአስዋን ግድብ የሚንጣለለውን ግዙፍ ውሀ በካናል (ቦይ) ወደ ሲናይ በረሀ በመውሰድ ለማልማት አዘጋጅታው የነበረውን እቅድ በመቃወም በወቅቱ በሌጎስ ተካሂዶ ለነበረው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ አቤቱታ በማሰማት ፍትሀዊነትን ብትጠይቅም” ሰሚ አለማግኘቷን የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ “በወቅቱ የግብፅ ምላሽ የነበረው ‘ኢትዮጵያ የግብፅን የመጠቀም መብት ካልተቀበለች ገደል ልትገባ ትችላለች’ የሚል አሳፋሪ ምላሽ” መስጠቷንም አስታውሰዋል።
ይህ የግብፆች ፉከራና ከዲፕሎማሲ ፍልስፍና ጋር አምርሮ የተጣላ ኢትዮጵያንና አባይን የተመለከተ አስተያየት የአንድ መሪ ብቻ አይደለም፤ ሁሉም በሚባል ደረጃ ተመሳሳይ አንደበት ነው ያላቸው። ከሳዳት “ኢትዮጵያን በቦንብ መደብደብ …”፣ ከናስር “ወደ ጦርነት የምንገባ ከሆነ የሚያስገባን ውሀ ብቻ ነው…” እስከ ቅርቦቹ በአንድ በተን /የኮምፒውተር ቁልፍ/ ነው የምናጠፋት” ድረስ አንድ ናቸው። የፑትሮስ ፑትሮስ ጋሊም ሴራ የእነሱው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ እንጂ ሌላ አይደለም። ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት ከጀመረች ወዲህ ግብፅ ህገመንግስቷ ውስጥ “አባይን የነካ …” የሚል አንቀፅ (“አንቀፅ 44”ን ይመለከቷል) ማካተቷም የዚሁ ከውሃ ዲፕሎማሲ መራቋን እንጂ ሌላ አያሳይምና ዛሬም እዛው ነች ማለት ነው።
በአሁኑ ሰዓት “የውሃ ጦርነት” የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መለያ ይሆናል እየተባለ ቢነገርም እርግጥ አስካሁን ፈታኝ የሆነ ነገር አላስተዋልንም። ነገር ግን በእስያ እና በአፍሪቃ እየተስተዋለ ያለው የሕዝብ ዕድገት ተፈጥሯዊ ሀብቶች ላይ አደጋ እየጣለ ይገኛል። የዓለማችን ሙቀት መጨመርም አንዳንድ የውሃ ምንጮች እንዲደርቁ ምክንያት እየሆነ ነው። ውሃ ለግጭት መነሻ ነጥብ ሊሆን እንደሚችለው ሁሉ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ለዓለማ’ቀፋዊ ዕድገት ትልቅ መሰረት መሆኑ ይታወቃል።
“Why ‘hydro-politics’ will shape the 21st Century” ጥናት የኢትዮጵያና ግብፅን በአባይ ወንዝ ላይ ክፍለ ዘመናትን ያስቆጠረ ውዝግብ ያካተተ ሲሆን አገራት ምድር ያፈራችውን የተፈጥሮ ፀጋ ‘የኔ የኔ’ ሳይባባሉ በጋራ መጠቀም ያለባቸው መሆኑንና ወደ አልተፈለገ የውሀ ጦርነት መግባት እንደሌለባቸው፤ ለውሀ ዲፕሎማሲ መርሆች ሊገዙና ሊመሩ እንደሚገባ ያስገነዝባል።
“WATER RESOURCES AS A CHALLENGE OF THE TWENTY-FIRST CENTURY” (2004, World Meteorological Organization)ም ችግሩን በበርካታ ምሳሌዎች በማስደገፍ የሚያብራራ ሲሆን መፍትሄውም የጋራ ውይይት፣ ፍትሀዊነት፣ እኩልና የጋራ ተጠቃሚነት መሆኑን ያስገነዝባል። ተጨማሪ ካስፈለገም “‘Oil Then,’ ‘Water Now’: Another Reason for War in the 21st Century?” መፈተሽና የጉዳዩን እጅግ አሳሳቢነት መረዳት ጠቃሚ ሲሆን ከሁሉም መረዳት የሚቻለው የኢትዮጵያ የውሀ ዲፕሎማሲ ግብፅ ከምትከተለው እጅጉን የተሻለና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ነው።
ከላይ ካየናቸውም ሆነ ሌሎች ጉዳዩ ቀጥታ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጥናቶች መረዳት እንደሚቻለው ለአሁኑም ሆነ ወደፊት ለሚነሱ የውሀ ጥያቄዎች መፍትሄው የግብፅ የቅኝ ግዛት ውል ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ በኩል ለዘመናት ፀንቶ የኖረው የፍትሀዊ ተጠቃሚነት አቋምና የውሀ ዲፕሎማሲ መርሆችን ማክበር ነው። በታላቁ የህዳሴ ግድብም በኢትዮጵያ በኩል እየታየ ያለው ይኸው ነው።
ይህ በ1956 ዓ/ም ለመገንባት ተወጥኖ የነበረው ጥረት፣ እንደ ፕሮፌሰር ያዕቆብ ጥናት፣ ዛሬ ላይ ተሳክቶ የኢትዮጵያን የተፋሰሱ ተጋሪነት እያረጋገጠ፤ የአንድ አገር የብቻ ሀብት መስሎ የሚታየውን የፖለቲካ አስተሳሰብና እምነት በመቀየር ላይ ጉልህ ምልክት በመሆን ትልቅ ድርሻን እየተጫወተ መሆኑን የተለያዩ አለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች እየገለፁት ይገኛሉ።
ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚሉት [ግድቡ] በአንድ አገር የበላይነት ስር ወድቆ ዘመናትን ያስቆጠረውን የፖለቲካ ቅኝት የቀየረ፤ የሰሜንና የምስራቅ አፍሪካን የውሀ ፖለቲካ ወደ ፍትሀዊነት ያሸጋገረ፤ የአፍሪካ የውሀ ማማ የምትባለዋን ኢትዮጵያንና በአባይ ተፋሰስ ሀብት ላይ ተስፋዋን የሰነቀች የበረሃ ጫፍ ላይ ያለችውን ግብፅ ከዚህ በኋላ በፍትሀዊነት መርህ የሚያስተሳስር መቀነት፤ የዘመናት የኢፍትሀዊነትን ቀንበር በመስበር የተፋሰሱ አገራትን ነፃ ከማውጣት ባሻገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ በአህጉራችንና በኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው [ብሄራዊ] ምልክት ነው።
ግድብ ያሳድጋል፣ ከድህነት ያወጣል ወዘተ ብቻ ሳይሆን፤ ከገደቡና ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት ልምድ እንደምንረዳው ያስፈነጥራል። ለዚህ ደግሞ ከቀዳሚዋ አሜሪካና ግድቧ (ሁቨር) ጀምሮ በጦርነት ስትታመስ የነበረችው አሁን ላይ በቀጠናው ካሉ ተፋሰስ አገራት ጋር በመስማማት የካቡል ወንዝን በፍትሃዊ መልኩ በመጠቀም ላይ እስከምትገኘው አፍጋኒስታን ድረስ ያለው ተጨባጭ እውነት ማስረጃ ነው። በመሆኑም የውሀ ዲፕሎማሲ የቀልድ አይደለምና ለጋራ ተጠቃሚነት እንጂ ቅኝ ግዛትን እንደገና በመናፈቅ ለብቻ ተጠቃሚነትን ዘመኑ አይፈቅድምና ኢትዮጵያ ወደ ግብፅ ሳይሆን ግብፅ ወደ ኢትዮጵያ ልትመጣ 21ኛው ክፍለ ዘመን ያስገድዳል።
በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተካሄደ ያለው የሶስትዮሽ (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ) ስምምነትም በዚሁ መልኩ ይጠናቀቃል የሚለው የብዙዎች ተስፋ ነው። ጉዳዩን ከፀጥታው ምክር ቤት ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ያደረገችው ኢትዮጵያም ከሁለቱ ተደራዳሪ አገራት የምትጠብቀውም ይሄው ስለመሆኑ መጠራጠር አይቻልም፤ ተስፋው የሁላችንም ነው። (ነጋ ጠባ እንደ እስስት መልኩን የሚቀያይረው፣ ስንትና ስንት ስምምነቶችን እያፀደቀ የሚሽረው፣ የህዳሴ ግድቡ እንዲከሽፍ የማይፈነቅለው ድንጋይና የማይበጥሰው ቅጠል የሌለው የግብፅ አቋምም በዚሁ ልክ እራሱን ሊቃኝ እንደሚገባ ሳይቋረጥ እየተመከረ ሲሆን፤ ቀረርቶም ሆነ ፉከራ፣ በሚስጥር ጦሩ እንዲዘጋጅ ማድረግም ሆነ ሌላ አይበጅምና መፍትሄው ወደ መሀል መምጣት መሆኑን የመሀመድ ሚዛኑር ራሃማን (2012) ያስረዳልና ለግብፅ በዚሁ መንገድ ማሰቡ ተገቢ ነው።)
ከዘርፉ ምሁርነት እስከ ተደራዳሪነት የዘለቁት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖም የሚሉት ይሄንኑ ነው። “ለወደፊቱም የትብብር አካሄድን በማፅናት አገሮች ተባብረውና ውሀ የሁሉም ስለሆነ ለሁሉም በሚጠቅም መልኩ እንዴት እንደሚሰራ ተረድተው ይህን ማደራጀት ይጠበቅባቸዋል።”
“በዚህ በኩል ኢትዮጵያ [ግድቡን] ለመስራት ያሳየችው ትጋትና ትእግስት እንዲሁም ብልሀትና እውቀት ከራሷ አንፃር ብቻ ሳይሆን በምስክሮችም ፊት የተረጋገጠ” መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰሩ በባላንጣነት የቆሙ አገሮችና ህዝቦቻቸውንም በተለየ አቅጣጫ የመሩትም መሪዎች ከዚህ አካሄድ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚማሩም ይገልፃሉ።
አጣብቂኝ ውስጥ ያለችውን ሱዳንና አቋሟን እንኳን ልንገነዘብላት ብንችል፤ ወደዚህ መስመር መምጣት እየተገባው መምጣት ያልቻለው የግብፅ የውሃ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ከዚህ ሊማር እንደሚገባው ግን ሳይጠቀስ ሊታለፍ የሚገባው አይሆንም። ሲሳደቡ እንደኖሩት ሁሉ ሲሳደቡና ሲዝቱ መኖርም የ21ኛው ክፍለ ዘመን የውሃ ዲፕሎማሲም ሆነ የዲፕሎማሲው ፍልስፍና (Diplomatology) አይፈቅድም፤ “ኢትዮጵያ ግድቡን ከገነባችና አቅም ካገኘች ግብፅ ላይ የድሮ ቂሟን ትወጣለች፤ ትበቀላታለች። ስለዚህ ቶሎ ብላ ወደ ጦርነት በመግባት ያችን ደሀ አገር ግድቡን ከመገንባት ማስቆም አለባት።“ የሚለው በካይሮ “Al Ahram Center for Political and Strategic Studies” ምርምር ማእከል የNile basin ተመራማሪ ቂል አስተሳሰብም ዘመኑን አይመጥንምና በግብፅ አጀንዳ ዝርዝር ውስጥ ካለ በነጭ ሊሰረዝ ይገባዋል። የ”ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ”ም ከእቅዱ ጀምሮ የታሰበው ለጋራ እንጂ አንዱን ጥሎ … ለመሄድ አለመሆኑን ማሰብ (እንደ አንድ አገር የውሀ ዲፕሎማሲ ዘርፍ) ያስፈልጋል።
እዚህ ላይ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ግብፅ ኢትዮጵያን በጦርነት ከግድቡ ለማስቆም ማወጇን ተከትሎ “ይህ ነገር ለማንም አይጠቅምም። ለግብፅም ለኢትዮጵያም፤ ባጠቃላይ ለማንም አይጠቅምም። ለአጠቃላይ አፍሪካም ከጉዳት በስተቀር ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም። ቆይ፤ ግብፅ ተርባይኑን ከመታ በኋላ ውሀው የት ይሄድብኛል ብላ ነው እንዲህ የምትጨነቀው፤ ተመልሶ እኮ ወደ እዛው ነው የሚሄደው።” ማለታቸው ለጥቅስ የሚበቃ ነውና ላልሰማ እናሰማለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ግርማ መንግሥቴ