በአዲስ አበባ የታክሲውን ቁጥር ብዛት ለታዘበ መላው የከተማዋ ነዋሪ ሁሉ የታክሲ ደንበኛ ነው እንዴ ሊል ይችላል። ጠዋትና ማታ በየፌርማታው የታክሲ ወረፋ የሚጠብቀውን ተሳፋሪ ብዛት ለተመለከተ ደግሞ ያ ሁሉ ታክሲ የት ገባ ማለቱ አይቀርም። አዲስ አበባም ገና በርካታ የትራስፖርት አገልግሎት እንደሚያስፈልጋት ይታዘባል።
ይህን ማንሳቴ ስለትራንስፖር አገልግሎት ለማንሳት አይደለም። ጉዳዬ ሌላ ነው። ነገር ግን እስኪ በቅድሚያ የታክሲ ደንበኞች የሆናችሁ ስለታክሲ ስታስቡ በቅድሚያ አእምሮአችሁ ውስጥ በቅድሚያ የሚመጣው ምንድነው የሚል ቀለል ያለ ጥያቄ ላንሳ።
የብዙዎቻችሁ መልስ የተለያየ ቢሆንም በርካታ ተመሳሳይ ትዝታዎች እንደሚኖሩ ግን አልጠራጠርም። ጥያቄው ታዲያ ለእናንተ ብቻ አይደለም። ለኔም ነውና ራሴን ጠየኩ። እና በቅድሚያ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ ወደድኩ።
እኔ በታክሲ በተሳፈርኩ ቁጥር በቅድሚያ የሚታየኝ እና ትኩረቴን የሚስበው የታክሲ ውስጥ ጥቅሶቹ ናቸው። ባይገርማችሁ አንዳንዴ ቁጭ ብዬ እነሱን እያነበብኩ በሃሳብ እዋጣለሁ፤ አንዳንዴም ከአጠገቤ ያሉ ተሳፋሪዎች እስሚታዘቡኝ ድረስ እስቃለሁ። አልያም በስሜት አወራለሁ።
የታክሲ ውስጥ ጥቅሶችን ስናነሳ ታዲያ እንደቀልድ ከጥቅሱ ስር የምትጻፈው የደራሲው ስም ከከእምሮ የሚጠፋ አይደለም። ብሩክ”” በሚል እንደፊርማ የምትቀመጥ ጽሁፍ አለች። የብዙዎቹ ጥቅሶች ደራሲም ይኸው ሰው እንደሆነ መገመት ይቻላል (ምንም እንኳን ብዙዎቹ የህዝብ ግጥሞችን መነሻ በማድረግ የሚጻፉ ቢሆንም)።
ብዙዎችን የታክሲው ውስጥ ጥቅሶች ለየት የሚያደርጋቸው ወቅታዊነታቸው ነው። በተለይ በአገራዊና ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም በዓም አቀፍ ሁነቶች ዙሪያ ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት የሚስተካከላቸው ያለ አይመስለኝም።
የታክሲ ውስጥ ጥቅሶችን ይዘቶች ስንመለከት የማይዳስሱት ጉዳይ እንደሌላ መታዘብ ይቻላል። ከጾታዊ የፍቅር ግኙነት እስከ ሀገር ፍቅር፤ ከሀገራዊ ጉዳይ እስከ ግለሰብ፣ ከማህበራዊ እስከ ኢኮኖሚ ጉዳይ፣ ወዘተ በነዚህ ጥቅሶች ይዳሰሳሉ። አቀራባቸውንም ስንመለከት አብዛኞቹ አስተማሪና በጨዋ አቀራረብ የሚቀርቡ ሲሆን ጥቂቶቹ ግን ስነምግባርን የጣሱና ብልግና የተቀላቀለባቸው ናቸው። ጥቂት የሚባሉት ደግሞ በተላይ የሴቶችን ክብር የሚያሳንሱ ሆነው እናገኛቸዋለን።
እነዚህን ጥቅሶች እያነሱ አንድ በአንድ መተንተን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አይደለም። ይልቁንም ትውስታን ለማጫር በመሆኑ ካሰባሰብናቸው ጥቅሶች ውስጥ ጥቂቶቹን እንደየባህርያቸው ለትውስታ ብቻ እንጠቁማችኋለን። ከዚህ በተረፈ ግን በዚህ ላይ ጥናት ማድረግ የሚፈልግ አካል በስፋት ሊሄድበት ይችላል ብዬ እገምታለሁ(እስካሁን ካልተሰራበት ማለቴ ነው)።
የፍቅር ነክ ጥቅሶች
እነዚህ ጥቅሶች ፍቅርን የሚገልጹት በተለያየ አውድ ነው። አንዳንዶቹ ጾታዊ ፍቅርን የሚያጎሉ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ የሀገር ፍቅርንም የሚያካትቱ ናቸው። በነዚህ ውስጥ ግን በተለይ ከፆታ አንጻር አስነዋሪ ጥቅሶች መኖራቸውንም ልብ እንበል። እኛ ግን እነዚህን አላካተትንም።
ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች አታግቡ ጋቢና ሹፈሩ ላደጋ
ይጋለጣልና፣
ፍቅር ካለ ፍሪጅ ይሞቃል፣
የእናት ሞትና የድንጋይ መቀመጫ እያደር ይቆሮቁራል፣
በፍቅር ለወደቀ የመሬት ስበት ተጠያቂ አይደለም፣
ሹፌሩን በፍቅር እንጂ በነገር መጥበስ ክልክል ነው፣
ፍቅር ካለ ታክሲ ባስ ይሆናል፣
ሹፌሩን በፍቅር ማሣቅ እንጅ በነገር ማሣቀቅ ክልክል ነው
ፍቅረኛዬን አጣው ብለህ አትጨነቅ ታክሲም ማጣት አለና
ጠጋ ጠጋ በሉ! ! በኛ ታክሲ ተዋውቀው ብዙ ሰው ተጋብቷል
አንድ ማፍቀር ግድ ነው፤ ሁለት ማፍቀር ግን ንግድ ነው፤ ሶስት ማፍቀር ግን ኮንትሮባንድ ነው ወዘተ
ሌላውና ትልቁ የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች መልዕክት ደግሞ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። በተለይ አንዳንዶቹ ጥቅሶች እንደቀላል የሚታዩ ቢመስሉም የህረተሰቡን የኑሮ ሀኔታ የሚተቹ፤ በታክሲ አገልግሎት እና በታክሲ አገልግሎት ላይ የህብረተሰቡን አመለካከት ጭምር የተሳሳተ መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው።
እንኑር ብለን ነው እንጂ መሞት አያቅተንም!
የያዝናት እድሜ አይደለም ለጠብ ለፍቅር እንኳን አትበቃም!
ብቸኝነት ደስ የሚለው ሽንት ቤት ብቻ ነው፣
ሟች ከመሞቱ በፊት ፍቅረኛውን ዜብራ ላይ ይስም ነበር
ታክሲ ውስጥ መጨቃጨቅ አሸባሪነት ነው
ሰዉ ብቻ ነው የምንጭነው ፣በስህትት የተሰቀለ ካለ ይውረድ
የሰራ የእጁን የተቀመጠ የቂጡን ያገኛል
መብትዎ ታክሲ ላይ ትዝ አይበልዎ
ጤፍና በርበሬ ሲወደድ ችላቹ ታክሲ ላይ ታማርራላችሁ
በታክሲ ውስጥ ጥቅሶች መንግስም ቢሆን አንዱ የትችት ማዕከል ነው
መንግስትና ተሳፋሪ ሊወርዱ ሲሉ ነገር ነገር ይላቸዋል
ስልጣን የህዝብ ማስተዳደሪያ እንጂ ማስፈራሪያ አይደለም
ጠጋ ጠጋ በሉ! ! በኛ ታክሲ ተዋውቀው ብዙ ሰው ተጋብቷል
የግለሰቦችንም ባህርይ የሚዳስሱ ጥቅሶች የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች የትኩረት ማዕከሎች ናቸው።
ነገረኛ ተሳፋሪ አደባባይ ላይ ‹‹ወራጅ አለ›› ይላል
መዶሻ ጭንቅላት ያለው ሰው ሁሉም ሰው የሚስማ ይመስለዋል
ከሰራህ ትበላለህ ካልሰራህ ሲበሉ ታያለህ
የበታችነት ከተሰማ ዛፍ ላይ ውጣ
ጠጋጠጋ በሉ የአባይ አደራ አለብን
ለወሬኛ እና ለአምስት ሳንቲም መልስ የለንም
ምን ጊዜው ቢረዝምም ቋንጣ እና ባለ ስልጣን መውረዱ አይቀርም
ጠጋ ጠጋ በሉ ሁሉም ቅርብ ወራጅ ነው ከፈጣሪ በቀር
የዓለም ሙቀት መጨመር መንስኤ ጭቅጭቅ ነው
ሂሳብ ሳይከፍሉ ሃሳብ አይጀምሩ
ኑሮና ታክሲ ካልታገሱት አይሞላም፤ ታክሲና መግስተሰማያት ሞልቶ አያውቅም
ሱሪህን ሳይሆን ራስህን ዝቅ አድርገህ ኑር
ሞላ የሰው ስም ነው ተጠጉ
ጠጋ ጠጋ በሉ የቻይና እዳ አለብን
ትችትና ሻወር ከራስ ይጀምራል
ከሙስና የፀዳ የስራ ዘርፍ የታክሲ ሹፌር ብቻ ነው
ከስልጣን እና ከጫት ላይ መነሳት ይከብዳል
እንግዲህ እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ናቸው። የታክሲ ውስጥ ጥቅሶች ከላይ እንደጠቀስኩት ዘርፈ ብዙ ናቸው። እነዚህ ጥቅሶች አጠቃላይ የማበረሰቡን ሥነልቦና ለመረዳት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው መገመት ይቻላል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2012
ወርቁ ማሩ