የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሰሞኑን በይፋ ስምምነት አድርገዋል፡፡ የተኩስ ማቆም ውሳኔ ተላልፏል፡፡ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ ያካሄደው የእርቅ ስነ ስርዓት በአምቦ ከተማ በኦሮሞ ባህል መሰረት ኮርማ በሬ በማረድ የተካሄደ ነበር፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ኮርማ በሬ በማረድ የተፈጸመው እርቅ በገዳ ስርዓት መሰረት የተከናወነ ነው፡፡ ኮርማ በሬ ማረድ በአብዛኛው በሁለት የተጋጩ የተለያዩ ሰዎች ወይም አካላት በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ እንዲፈቱ፣ መለያየትና ደም መፋሰስ እንዲያስቀሩ ይቅር እንዲባባሉ ለማድረግ፣ ቂም እንዳይዙና እንዲተውት የሚገባ ቃል ኪዳን ነው፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አቶ ጋሻው አይፈራም፤ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ኦነግ ያደረጉት ስምምነት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች የነበረውን የጸጥታ ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ በሁለቱ መካከል የነበረውን አለመግባባት ፈትቶ ወደ ስምምነት ለመምጣት ያስችላል ይላሉ፡፡ ይህ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ላይ የነበረውን የሰላምን እጦት ይቀርፋል፡፡ በኦሮሞ ማህበረሰብ በአገር በቀል የግጭት አፈታት ለተከናወነው እርቅ ከፍተኛውን ሚና የተወጡት አባ ገዳዎች ናቸው ይላሉ፡፡
በሁለቱ መካከል የተካሄደው ስምምነት በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ አንዱ ሌላውን ጥሎ የሚያልፈበት አግባብ ነበረ፡፡ በቀጣይ ይህ እንደሚቀር ይጠበቃል፡፡ ኦዲፒና ኦነግም እንደተፎካካሪ ፓርቲዎች እርስ በእርሳቸው እንደሚተያዩ፣ አንዱ ለሌላው ግብአት እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ አገር ቀጣይነት እና ዘላቂነት ላለው ሰላም መስፈን የተሻለ ነገር አለው ይላሉ አቶ ጋሻው፡፡
‹‹አብሮ መስራት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ግን አብሮ ሲሰራ ልዩነቶች ይኖራሉ›› የሚሉት መምህሩ፤ የፍላጎት አለመጣጣም ሊኖር እንደሚችሉ፣ ራዕይ፣ ርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲያቸው ሊለያይ እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ አንድ አገር ሉአላዊነትና የተከበረች ሆና እንድትቀጥል፣ ለህዝብ ደህንነትና ለህዝብ ጥቅም መቆም ያስፈልጋል፡፡ በእርቅ ስርዓቱም ሆነ በስምምነቱ እንደተገለጸው፤ አብረው ሊሰሩ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ በጋራ መስራት ይገባቸዋል፡፡ ይህ ከቀጠለ በኢትዮጵያ የነበረው የጥሎ ማለፍ የፖለቲካ አሰላለፍ ሙሉ በሙሉ ባይቀርም እንኳን የተወሰነ ትምህርት ይወሰድበታል፡፡
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ደህንነት፣የአገር ሉዐላዊነት ሰላም እና የህዝብን ጥቅም ማስከበር አብረው ሊሰሩ የሚችሉባቸው ጉዳዮች ይሆናሉ የሚሉት አቶ ጋሻው፤ የርዕዮተ ዓለም፣ የፖሊሲና የፖለቲካ ልዩነቶችን በመጠበቅ በጋራ ጉዳዮች አብረው ይሰራሉ ይላሉ፡፡
እስካሁን ሲተገበር የነበረው ከአገር ወጥቶ ጦርነትን እንደ አንድ የእስትራቴጂ መታገያ ዘዴ የመውሰድ አዝማሚያ የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ውስጥ የሚከት ሁኔታ እንደነበር ያስታውሱና፤ ሁኔታዎቹ ይቀረፋሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም አቶ ጋሻው ይናገራሉ፡፡
እንደ መምህሩ ማብራሪያ፤ በእርቅና የሰላም ሂደቱ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት አባገዳዎችና ሴቶችን ያቀፈው ሀደ ሲቄዎች ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ችግር እንዲፈቱ የተደረገውን የሰላምና የእርቅ ጥሪ መቀበላቸው ሊመሰገኑበት ይገባል፡፡ ከኦሮሞ ህዝብ አብራክ እንደመውጣታቸው የኦሮሞ ህዝብ መለያ የሆነውን የገዳ ስርዓት አክብረው መተግበራቸው ህዝባዊነታቸውን ያሳያል፡፡
ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ፣ እርቅ ማወረድም ተገቢ መሆኑን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም የሚፈልጉትን በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር ችግሮችን ፈትተው ሰላማዊ የመታገያ መንገዶችን መርጠው እንዲሰሩ አባገዳዎች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሁለት የግጭት ተዋናይ አካላት በአገር በቀል ግጭት አፈታት ዘዴ ተጠቅመው ሰላማዊ መስተጋብር ፈጥረዋል፡፡ የገዳ ስርዓት የሚፈጸምባቸው የእርቅ ስነ ስርዓት አይነቶች አሉ፡፡ አገር በቀል የግጭት መፍቻ ከመደበኛ የፍትህ ስርዓት ባልተናነሰ ውጤት አላቸው፡፡ ቂም በቀል እንዲቀር ያደርጋሉ፣ ምህረት እንዲደረግ ያስችላሉ፣ ወደ ሰላማዊ መስተጋብሩ እንዲመለሱ እና በቋሚነት ህብረት እንዲኖራቸው ያግዛሉ ይላሉ አቶ ጋሻው፤ ትግበራው የአባ ገዳዎች መሆኑንና ሚናውም ከፍተኛ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የአገር በቀል የግጭት መፍቻ መንገዶች ዋነኛው ዓላማቸው በራሳቸው መንገድ እውነትን ማፈላለግ፣ ትክክለኛነትን ማረጋገጥ እና ሐቅን ማውጣት ነው፡፡ ምህረትን ማውረድ እና የእርቅ ስርዓትን መፈጸምንም ያካትታል፡፡
በአገር ውስጥ የተለያዩ የዕርቅ መፈጸሚያ ስርዓቶች አሉ፡፡ የሚፈጸሙበት መንገድ እንደ ስፍራው ሊለያይ ይችላል፡፡ እንስሳት በማረድ፣ ቄጤማ በመጎዝጎዝና በመያዝ፤ የሚፈጸሙ የእርቅ ስነ-ስርአቶች አሉ፡፡ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የእርቅ መፈጸሚያ መንገድ ቄጤማ መጎዝጎዝ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ አረንጓዴ ነገር በመሆኑ ልምላሜንና ተስፋን ለማሳየት ነው ይላሉ፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል የተፈጸመው የእርቅ ስርዓት የተፈጸመው ኮርማ በሬ በማረድ ነው፡፡ ይህ በገዳ ስርዓት ያለ ነው፡፡ ኮርማ በሬ ማረድ በተለያየ ማህበረሰብ የተለየ ትርጓሜ ይኖረዋል፡፡ በአብዛኛው ግን በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ፣ መለያየትና ደም መፋሰስ እንዳይመለስ የሚገባ ቃል ኪዳን ነው ሲሉ አቶ ጋሻው ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በሰላማዊ መንገድ የሚገናኙ ወንድማማቾች ሆነዋል የሚል መልዕክትም ያዘለ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች የተስማሙባቸውን ጉዳዮች መተግበር እንደሚገባቸው፣ ሉዐላዊነት፣ የአገር ሰላምና የህዝብ ደህንነት ማስጠበቅና መሰል አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም ያመለክታሉ፡፡
በአገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ አገር በቀል የግጭት አፈታትና የአካባቢ ጥበቃ ስርዓቶች የሚጎለብቱበት መንገድ ሊኖር ይገባል፡፡ ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ማበጀትም ያስፈልጋል፡፡ መንግስት ችግር ሲፈጠር ብቻ ‹‹ኑ አስታርቁኝ›› ብሎ ከየቤታቸው ማፈላለጉ ውጤት አይኖረውም፡፡ ከፍትህ ስርዓቱ ጎን ለጎን እንዲተገበሩ በማድረግ አንድነትን የማጎልበት ሚናቸውን እንዲወጡ ማስቻል ያስፈልጋል ብለዋል መምህር ጋሻው፡፡
የኦዲፒ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ታዬ ደንደአ እንደሚሉትም፤ ቀደም ሲልም ‹‹ፍትህ ለሁሉም›› በተባለ ተቋም ከዞኖች የተወከሉ ተሳታፊዎች በተገኙበት አምቦ ከተማ የሰላም ጉባኤ ተካሂዶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱም በቀጣይነት ምሁራንን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብና አባገዳዎችን ያሳተፈ ጉባኤ እንዲካሄድ ተወስኖ እንደነበር ይጠቁማሉ፡፡ አባገዳዎችም በጉባኤው እርቅን በአጀንዳነት ይዘው መነሳታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
እርቁ ለሰላም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል የሚሉት አቶ ታዬ፤ ግጭት ለተለያዩ ጉዳቶች የሚዳርግ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ የህይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት መውደም እና በማህበረሰቡም የሞራል ጉዳት እንደሚያደርስም ያነሳሉ፡፡ አባገዳዎች ችግሩ በአገር በቀል የግጭት አፈታት ዘዴ እንዲፈታ ማድረጋቸው ለአገሪቱ ሰላም መስፈን፣ ለአንድነትና ለልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡
እርቁ እንዲፈጸም ተነሳሽነቱ የመጣው ከአባ ገዳዎች መሆኑን አቶ ታዬ ይጠቅሱና፤ ግልጽ ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑ፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወጣቶች መሳተፋቸው፣ የተኩስ አቁም ለማድረግ መወሰኑ፣ ስራዎቹ የሚጠናቀቁበት ቀናት መወሰኑና ተግባሮች መለየታቸው እስካሁን ከተካሄዱት ስምምነቶች እንደሚለየው ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ታዬ ማብራሪያ፤ የኦነግን የታጠቀ ሰራዊት ትጥቅ ለማስፈታት፣ ሰራዊቱንም ወደ ካምፕ ለማስገባትና ሌሎች ስምምነቶች ላይ የተደረሱ ጉዳዮችን ለማስፈፀም የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ በትግበራው ግልጽነት ማስፈን አለበት፡፡ ዝርዝር ስራ ውስጥ ሲገባ ከአገሪቱ ህግና ህግ መንግስቱ አኳያ መተግበር አለበት፡፡ ህግን መጻረር የለበትም፡፡ በፍጥነት ማከናወን ይገባዋል፡፡ ሁለቱንም ወገኖች ያማከለና ሚዛናዊ ስራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
ችግሮች ረጅም ጊዜ የተከማቹ በመሆናቸው ዘዴ ይፈልጋሉ፡፡ በትዕግስት መተግበር አለባቸው፣ አብሮ መስራትን ይጠይቃሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም በመተባበር ለስምምነቱ ተገዢ በመሆን ህግን አክብረው መስራት ይገባቸዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ በተደረገው ትግል የዴሞክራሲ ጸሃይ መውጣት ጀምሯል፡፡ ህዝቡ የወጣው ጸሃይ እንዳይጠልቅ መስራት አለበት፡፡ ለህግ የበላይነት በመቆም፣ በመከባበር፣ ለህግ የበላይነት መቆም ይገባል፡፡ በምክንያት መደገፍና መቃወምን ባህል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለአገር ሰላም፣ ብልጽግናና ዕድገት በጋራ መስራት ይገባል፡፡
በአገር ውስጥ ያለውን መልካም ባህል ወደጎን በመተው የሌላ አገር አሰራርን እንዳለ በመቅዳት በአገር ውስጥ መተግበር እንደአገር ውጤታማ አላደረገም የሚሉት አቶ ታዬ፤ ህጉና ስርዓቱ የህዝቡን ስነ ልቦናና የአገርን ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ መሆን እንደሚገባው ይጠቅሳሉ፡፡ በአገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች እንደ በአባ ገዳዎች እንደሚፈጸሙት አይነት ያሉ ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎችን ማጠናከር የዴሞክራሲ ስርዓቱን ለማጎልበት፣ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ፣ አብሮነትን ለማጠናከርና ግጭትን ለማስወገድ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ያብራራሉ፡፡ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶችንና የእርቅ መፈጸሚያ መንገዶችን ማበረታታት ይገባል ሲሉም መክረዋል::
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መካከል የተካሄደው የተኩስ ማቆም ውሳኔ በተጨማሪ፤ የኦነግ ሰራዊት በጥቂት ቀናት ውስጥ ካለበት ጫካ ወጥቶ ወደ ካምፕ እንዲገባም ተወስኗል፡፡
በእርቅ ስነ ስርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲቄዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ወጣቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና የአምቦ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። በመድረኩ ላይም መንግስት እና ኦነግ በኦሮሞ ባህል መሰረት ኮርማ በሬ በማረድ በይፋ የእርቅ ስነ ስርአት መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡ ሁለቱም አካላት ወደ ደም መፋሰስ እንደማይገቡ እና ያለፈውን ነገር በመተው ስለወደፊቱ ብቻ በጋራ ለመስራት በእርቅ ስነ ስርዓቱ ቃል ገብተዋል። በመድረኩ ላይም ስምምነት ላይ የደረሱባቸው ዝርዝር የውሳኔ ነጥቦች ይፋ ተደርጓል።
በስምምነቱ መሰረት በመንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር መካከል ጦርነት ቆሟል፡፡ ወደ ግጭት የሚያስገቡ ትንኮሳዎች ሙሉ በሙሉ መከልከሉ ይፋ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ አንዱ በሌላው ላይ መግለጫ ማውጣት ሙሉ በሙሉ መከልከሉንም ተገልጿል፡፡ የኦነግ ሰራዊት ካለበት ቦታ በሙሉ ትጥቅ ፈትቶ ወደ ካምፕ እንዲገባና ሂደቱም ከበቂ ጥበቃ ጋር በክብር አቀባበል እንዲከናወን ይደረጋል።
ሰራዊቱን ወደ ካምፕ የማስገባት ስራ በ20 ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ አለበት፡፡ በእነዚህ ቀናት ውስጥም 10 ቀናት ዝግጅት የሚደረግበት፤ ቀሪው 10 ቀናት ደግሞ ሰራዊቱ ወደ ካምፕ የሚገባበት ይሆናል፡፡
ወደ ካምፕ የማስገባት ሂደቱም በሶስት ደረጃዎች ተከፋፍሎ ይካሄዳል፡፡ በዚህም የመጀመሪያም ወደ ወረዳ ከተሞች እንዲሰባሰቡ፣ በመቀጠል ወደ ተዘጋጀላቸው ካምፕ እንዲገቡ ማድረግ በመጨረሻም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት አቀባበል ማድረግ ይሆናል፡፡
በዚህ ወቅት ትጥቅ ይዞ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው፡፡ ክልከላውን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም አካል ላይ መንግስት ህግን የማስከበር ስራ እንዲሰራ ተፈቅዷል፡፡ የኦነግ ሰራዊት ካምፕ ከገባ በኋላም አጠቃላይ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጎ የመንግስት የፀጥታ አካላት መቀላቀል ለሚፈልጉ እንደሚያሟሉት መስፈርት እንዲቀላቀሉ ተወስኗል፡፡
የኦነግን የታጠቀ ሰራዊት ትጥቅ ለማስፈታት እና ሰራዊቱን ወደ ካምፕ ለማስገባት እንዲሁም ሌሎች ስምምነት ላይ የተደረሱ ጉዳዮችን ለማስፈፀም 71 አባላት ያለው የቴክኒክ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የቴክኒክ ኮሚቴውም ከምሁራን 11፣ ከአባ ገዳዎች 54፣ ከኦዲፒ 3 እንዲሁም ከኦነግ 3 አባላት ያለው ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
ዘላለም ግዛው