አገራችን ኢትዮጵያ በ2025 የዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራትን ተርታ ለመቀላቀል እቅድ ነድፋ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች። ለዚህ ዕቅድ ዕውን መሆን የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የመንገድ አገልግሎት መኖር ቀዳሚው ጉዳይ ነው። ከአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ጀምሮ በመላው ሀገሪቱ የገጠር ተደራሽ መንገድ ዝርጋታ ፕሮግራም እየተካሄደ ይገኛል።
የሁሉን አቀፍ የገጠር ተደራሽ መንገድ በሀገሪቱ ያሉትን የገጠር ቀበሌዎች በሙሉ እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ መንደሮችን በአቅራቢያቸው ከሚገኝ ዋና የአስፋልት መንገድ ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተቀረፀ ፕሮግራም ነው። በዚህ ፕሮግራም በአንጻራዊነት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን አበረታች ስራ የተከናወነ ቢሆንም፤ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ግን ከተያዘው 90ሺ ኪሎ ሜትር እቅድ ባለፉት አራት አመታት ማከናወን የተቻለው 9,557 ኪሎ ሜትር ወይም የእቅዱን 21 በመቶ ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ጉዳዩ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አቅም በላይ እንደሆነ በመግለጽ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለከተማ ልማት ኮንስትራክሽንና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣኑን የስድስት ወር አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለፕሮግራሙ የተያዘ በጀት እየተሰጠ አይደለም። ክልሎችም የገንዘብ እጥረት ስላለባቸው ፕሮግራሙን በተገቢው መንገድ እየደገፉት አይደለም። በመሆኑም በዚሁ ከቀጠለ ሙሉ ለሙሉ ሊቆም ይችላል። ይሄን ደግሞ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ለፕላን ኮሚሽንና ለሚመለ ከታቸው አካላት በሙሉ ብናሳውቅም እስካሁን የተገኘ ምላሽ የለም።
የዚህ ክፍተት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊሰራ የታሰበው የመንገድ ግንባታ እቅድ ይሄንን ያካተተ በመሆኑ አጠቃላይ የመንገድ ዝርጋታ አፈጻጸሙንም ዝቅተኛ ያደርገዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከከተሞች በርቀት የሚኖሩ ዜጎች ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር የትም ጌታ አስራት በበኩላቸው በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በአምስት አመት ውስጥ ሰባ ሺ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ለመስራት ታቅዶ ሃምሳ ሺ ኪሎ ሜትር መገንባት ተችሎ ነበር። ይህም በእቅዱ መሰረት ያልተጠናቀቀ ቢሆንም አሁን ካለው አንጻር ግን ጥሩ ውጤት የታየበት ነበር። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተጀመረውን በመቀጠል በአምስት አመት ውስጥ 90 ሺ ኪሎ ሜትር ለመስራት ቢታቀድም ባለፉት አራት አመታት ማከናወን የተቻለው ግን አስር ኪሎ ሜትር የማይሞላ ብቻ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት የነበረው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን በጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተከሰተው የበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ የፌዴራል መንግስትና ክልሎች መመደብ ባለመቻላቸው ነው።
ከተያዘው እቅድ አኳያ በአሁ ኑወቅት ቢያንስ ከሀምሳ ሺ ኪሎ ሜትር ያላነሰ መሰራት ነበረበት የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ይሁንና የተሰራው አስር ኪሎ ሜትር የማይሞላ እንደሆነ በማስታወስ የቀረውን ሰማኒያ ሺ ኪሎ ሜትር በእቅዱ በተቀመጠው የግዜ ገደብ ሊጠናቀቅ እንደማይችል ተናግረዋል። በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የአንድ አመት ከፍተኛው አፈጻጸም ሀያ ሺ ኪሎ ሜትር ነበር። በቀጣዩ በጀት አመት ገንዘቡ ተገኝቶ የዚህን ያህል መስራት ቢቻል እንኳ በአጠቃላይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ማጠናቀቂያ ሊሰራ የሚችለው የእስካሁኑን ጨምሮ ከሰላሳ ሺ ኪሎ ሜትር የበለጠ አይሆንም። በመሆኑም በቀጣይ ፕሮግራሙን ለማስፈጸም ምን ያስፈልጋል የሚለውን ያካተተ ዝርዝር ጥናት ተካሂዶና ለሚመለከታቸው አካላት መነሻ የሚሆን እቅድ ቀርቦ በፌደራልና በክልል ደረጃ ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል።
ኢንጅነር የትም ጌታ ችግሩን ለመቅረፍ በመሰራት ላይ ያሉ ስራዎችንም ሲያብራሩ በፌዴራል በኩል ከበጀት ጥያቄው ጎን ለጎን ገንዘብ ማፈላለግ ስራ እየተሰራ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ክልሎች ካላቸው በጀት አብቃቅተው እንዲመድቡ የፕሮጀክቱን አስፈላጊነትና እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ግንዛቤ ማስጨበጥ በማስፈለጉ ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ሰነዶች፣ ስታንዳርዶችና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ተልከውላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በየክልሉ ከወረዳ ጀምሮ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ በፌዴራል ማሰልጠኛ ተቋማት ለተከታታይ ግዜ ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
«ስራ አላቆምንም እየሰራን ያለነው ግን በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተጀመረውን ነው» የሚሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል መንገዶች ባለስልጣን የገጠር መንገዶች ተደራሽነት ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ አበራ ናቸው። አቶ ተፈሪ እንደሚያብራሩት በመጀመሪያ የታቀዱት ባለመጠናቀቃቸው አዲስ የተያዘ እቅድ የለም። በመጀመሪያው ዙር ከ2004 እስከ 2007 52 ሺ ኪሎ ሜትር ለመስራት የታቀደ ቢሆንም የዘንድሮን በጀት አመት ጨምሮ ባለፉት ሰባት አመታት መስራት የተቻለው ግን 35 ሺ ኪሎ ሜትሩን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የበጀት እጥረቱ ቀዳሚ ችግር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በኮንሰልታንቶችና በአማካሪ መሀንዲሶች በኩል በአግባቡ ያለመቆጣጠርና የተሟላ ዲዛይን አለማዘጋጀት እንዲሁም በኮንትራክተሮች በኩል በቂ የግንባታ እቃና ባለሙያ ይዞ አለመቅረብ ለአፈጻጸሙዝቅተኛነት ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ፕሮግራሙ ሲጀመር “መንገዶቹ ከተጠናቀቁ በኋላ እንዴትና በማን ይጠገናሉ በሚለው ጉዳይ ላይ የተወሰነ ነገር አልነበረም።” የሚሉት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ተሰርተው ከነበሩት መንገዶች አብዛኛዎቹ ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን በመጠቆም በህብረተሰቡ በኩል ቅሬታ እየቀረበ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ በጀት ከተገኘ የሚሰሩት ስራዎች አዲስ ግንባታ ማከናወን ብቻ ሳይሆን ጥገናንም ማካተት እንዳለባቸው መወሰኑንና ለዚህም ክልሉ ከፌዴራል በጀ ትእስኪያገኝ ከሌሎቹ በጀቶች እየቀነሰ እንዲመድብና የህዝብ መዋጮ ታክሎበት ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
«በጀት ለተያዘለት ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገብ የተቻለ ቢሆንም በእቅዱ መሰረት ሲመዘን ግን ዝቅተኛ ነው»። የሚሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው አበባየሁ ናቸው። እንደ ሃላፊው ገለጻ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መጀመሪያ ሁለት ዓመታት ከእቅዱ በጣም ያነሰ ቢሆንም የተሻለ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር። በ2008 እና በ2009 አጠቃላይ 2764 ኪሎ ሜትር ለመስራት በጀት የተለቀቀ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2686 ኪሎ ሜትሩን ማከናወን ተችሏል። በ2010 እና በ2011 ዓ.ም ግን የተያዘ በጀት ባለመኖሩ ከአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ጀምሮ ያሉትን ያልተጠናቀቁ ስራዎች ለማጠናቀቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛል። በዚህ ፕሮግራም በክልሉ በአጠቃላይ እስካሁን 11 ሺ ኪሎ ሜትር የተገነባ ሲሆን በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከ9ሺ ኪሎ ሜትር በላይ ቢታቀድም ሊሰራ የቻለውግን ሶስት ሺ ኪሎ ሜትር የማይሞላ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ለግንባታው የተቋቋሙ ማህበራትም እየተበተኑ ነው።
«መንገድ ያለድልድይ ዋጋ የለውም በአንድ መንገድ ከአራት እስከ አምስት ቦታ ድልድይ መገንባት ያለበት አለ» የሚሉት ሃላፊው እስካሁን ግንባታዎች ሲካሄዱ አቅምእስከሚፈጠር ድልድዮች ይቆዩ ተብሎ እየተዘለሉነበር። በክልሉ ከተገነባው11 ሺ ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ውስጥም ከ373 በላይ ድልድዮች መኖራቸውን በመግለጽ ከነዚህ ውስጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት አስራሶስት የተገነባ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 360 የሚደርሱ ምንም ያልተጀመሩ ድልድዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ኃላፊው ጨምረው እንደተናገሩት በክልሉ አሁንም ከዋና መንገድ ጋር ያልተገናኙ 900 ቀበሌዎች አሉ። በቀን እስከ አራት ቀበሌ ጥያቄ ይቀርባል። በአንዳንድ ቦታዎች አርሶ አደሩ በራሱ ሙሉ ወጪየሚሰራቸው ስራዎች ቢኖሩም ከሚፈለገው አንፃር እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። በመሆኑም ከክልሉም ሆነ ከመንግስት የሚለቀቀው በጀት እቅዱን ለማሳካት የግድ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ