‹‹ማርሽ ቀያሪው›› በሚለው ቅፅል ስሙ ይታወቃል። በሩጫ ውድድሮች የማብቂያ ዙሮች ላይ ፍጥነቱንና የአሯሯጥ ዘዴውን በድንገት በመቀየር ተፎካካሪዎቹን አስከትሎ የሚገባ ታላቅ አትሌት ነው። በጠንካራ ስራና በጥልቅ የሐገር ፍቅር ስሜት የታጀቡ የበርካታ አንጸባራቂ ድሎች … ለፈተናዎች ሳይበገር በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ድርብ ድል ያስመዘገበ የጽናት ተምሳሌት … ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር!
ምሩፅ ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማኖትና ከእናቱ ወይዘሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ ጥቅምት 5 ቀን 1937 ዓ.ም. ዓዲግራት ውስጥ ተወለደ። በወጣትነቱ በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ በመሰማራት ቤተሰቦቹን ይረዳ ነበር። በ17 ዓመቱ ወደ አስመራ በመሄድ ኑሮውን በዚያው አደረገ። ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ አንፀባራቂ ድሎች ማስመዝገቡን በተደጋጋሚ የሰማው ምሩፅ፤ ስለሩጫ ማሰብ ጀመረ። በአበበ ድሎች የተደነቀው ምሩፅ እርሱም እንደ አበበ መሆንን ተመኘ።
ምሩፅ ስመጥር አትሌት መሆንን ተመኝቶም አልቀረ … ሩጫን መለማመድና በውድድርም ለመሳተፍ ጥረቱን ጀመረ። ምሩፅ ወደ ሩጫ የተቀላቀለው በአበበ ቢቂላ ምክንያት ነው። ይህንንም ‹‹ … ሩጫ የጀመርኩት ስለ አበበ ቢቂላ ከሰማሁ በኋላ ነው። እንደ እርሱ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። ሁልጊዜም ስለእርሱ አስብ ነበር። በዚህ ምክንያት ነው ወደ ሩጫ ውድድር የገባሁት›› በማለት በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ ተናግሮ ነበር።
በመስከረም 1961 ዓ.ም. አበበ ቢቂላንና ማሞ ወልዴን የያዘውና በሜክሲኮ ኦሊምፒክ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአትሌቲክስ ቡድን የመጨረሻ ጉዞውን ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ከማድረጉ በፊት ለልምምድ ያረፈው አስመራ ከተማ ነበር። እነ አበበ በአስመራ ንግሥተ ሳባ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርጉ የተመለከተው ምሩፅ ይፍጠር፤ ለወደፊት ሕይወቱ በር ከፋች አጋጣሚ ተፈጠረለት። በልምምድ ሩጫው ላይ ከነ ማሞ ወልዴ ጋር አብሮ ሮጠ። ምሩፅ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ ቢያጠናቅቅም አሯሯጡንና አቅሙን ያስተዋሉት አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ በአየር ኃይል ስፖርት መምሪያ እንዲካተትና ልምምድ እንዲያደርግ አደረጉ። ቅጥሩንም ፈጸመ። ለ20 ዓመታት ያህል በአየር ኃይል የስፖርት ቡድን ውስጥ ሲያገለግል እስከ ‹‹ሻምበል›› ማዕረግ ደርሷል።
‹‹ንብ›› የሚባለውን የአየር ኃይል ስፖርት ክለብን እየወከለ በብሔራዊ ሻምፒዮናና በጦር ኃይሎች ውድድሮች ላይ እየተካፈለ ውጤታማ ሆነ። በ1962 ዓ.ም በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአንድ ሺ 500 ሜትር ውድድር ከኦሊምፒክ ባለወርቁ ኬፕቾግ ኬይኖ ጋር ተፎካክሮ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አገኘ። በ1963 ዓ.ም. በአሜሪካ በተካሄደው የአፍሮ-አሜሪካን ውድድር ላይ ተሳትፎ በ10 ሺ ሜትር የወርቅ፤ በአምስት ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ድልን አጣጣመ።
በ1964 ዓ.ም በተካሄደው የሙኒክ ኦሊምፒክ ምሩፅ ኢትዮጵያን በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ወክሎ ቀረበ። የ10ሺ ሜትር ውድድሩን ሦስተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ የነሐስ ሜዳሊያ አገኘ። የአምስት ሺ ሜትር ውድድሩን ግን በአሰልጣኞቹ ስህተት ምክንያት ሳይወዳደር ቀረ። በዚህም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ‹‹ … በውድድሩ ያልተሳተፈው ላለመወዳደር ፈልጎ ነው …›› ተብሎ ለስምንት ወራት ያህል ታሰረ። በኋላም ጥፋቱ የአሰልጣኞቹ እንጂ የምሩፅ እንዳልሆነ በመታወቁ ከእስር ተፈትቶ ልምምዱን ቀጠለ።
በ1965 ዓ.ም በሌጎስ – ናይጀሪያ በተካሄደው ሁለተኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ10ሺ ሜትር የወርቅ እና በአምስት ሺ ሜትር ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን አሸነፈ። በዚያው ዓመት ከሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ከተውጣጡት ስፖርተኞች መካከል ‹‹የኢትዮጵያ ስፖርት ኮከብ አትሌት›› ተብሎም ተመርጧል።
የ1968 ዓ.ም የኦሊምፒክ ውድድር የተደገሰው በሞንትሪያል-ካናዳ ነበር። በወቅቱ በአፓርታይድ አገዛዝ ስር የነበረችው ደቡብ አፍሪካ በየትኛውም የስፖርት ውድድር ከተሳተፈች አፍሪካውያን ራሳቸውን ከውድድር እንደሚያገሉ አሳውቀው ነበር። ኒውዚላንድ የራግቢ ብሔራዊ ቡድኗን ለጨዋታ ወደ ደቡብ አፍሪካ
ልካ ስለነበር ‹‹ኒውዚላንድ ከውድድሩ መታገድ አለባት›› በሚል ጥያቄ በኦሊምፒክ መድረኩ ተሳታፊ ከነበሩት 28 የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ 26 አገራት ራሳቸውን ከውድድሩ አገለሉ። በዚህም ምክንያት ጥሩ ዝግጅት ያደረገውና የአሸናፊነትን ግምት አግኝቶ የነበረው ምሩፅ ከሞንትሪያል ኦሊምፒክ ውጭ ሆነ።
በ1969 ዓ.ም በዱዘርዶልፍ-ጀርመን በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ ምሩፅ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ድርብ ድል አስመዘገበ። ምሩፅ በዚህ ውድድር ላይ አፍሪካን የወከለው ተቀናቃኙን ኬንያዊውን የሦስት ሺ ሜትር መሰናክልና የአምስት ሺ ሜትር ሩጫዎች የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ሔንሪ ሮኖን በመርታት ነበር።
በ1971 ዓ.ም በተካሄደው የሞንትሪያል የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫም ምሩፅ በድጋሚ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፍ ሌላ ወርቃማ ድርብ ድል አስመዘገበ። በዚህ ሁለተኛ ድርብ ድል ባስመዘገበበት የሞንትሪያል የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ የተሳተፈው ደግሞ የመጀመሪያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዳካር፣ ሴኔጋል ሲካሄድ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማሸነፉ ነበር። እነዚህ የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ ውድደሮች በወቅቱ አትሌቶች አገራቸውን ሳይሆን አህጉራቸውን ወክለው የሚሳተፉባቸው መድረኮች ስለነበሩ የምሩፅ ድሎች ከኢትዮጵያ አልፈው የአፍሪካውያንም ጭምር ነበሩ።
አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ባገኘባቸው የዱዘርዶልፍና የሞንትሪያል የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ ውድድሮች ያሳየው ብቃትም እጅግ የሚደነቅ እንደነበር ብዙዎች ዛሬም ድረስ በአግራሞት ያስታውሳሉ። ምሩፅ በእነዚህ ውድድሮች ላይ የአምስት ሺ ሜትር ሩጫው 500 ሜትር ሲቀረው የ10ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ 600 ሜትር ሲቀረው ነበር ማርሽ ቀይሮ በማፈትለክ ያሸነፈው። በተለይ በሞንትሪያሉ ውድድር ላይ የምሩፅ ዋነኛ ተፎካካሪ የነበረው አሜሪካዊው ክሬግ ስቴቨን ቨርጂን ከውድድሩ አስቀድሞ ‹‹ … በመጨረሻው ዙር ላይ ከሁሉም በላይ የሚያስፈራኝ ምሩፅ ነው። ሌሎች ጠንካራ አትሌቶች ቢኖሩም ከእኔ የበለጠ አይፈጥኑም … ጠንካራና ፈጣን መሆን ይኖርብኛል፤ ምክንያቱም እርሱ ከእኔ በላይ ፈጣን ነው። ይህን ውድድር ለማሸነፍ ያለኝ ብቸኛ አማራጭ በዚህ መልኩ መፎካከር ነው …›› በማለት ለጋዜጠኞች ተናግሮ ነበር።
ምንም እንኳን ምሩፅ የሩጫ ውድድር የጀመረው በ800 ሜትር እና በአንድ ሺ 500 ሜትር እንዲሁም አንፀባራቂ ድሎችን ያስመዘገበው በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ቢሆንም በጎዳና ላይ ሩጫዎችም ተደጋጋሚ ድሎችን አግኝቷል። በተለይ በተከታታይ ዓመታት ድል የተጎናፀፈበት የፖርቶሪኮ ግማሽ ማራቶን (የ21 ኪሎ ሜትር) ውድድር ለዓለም ክብረ ወሰን ባለቤትነት ያበቃው ነበር። ጥር 29 ቀን 1969 ዓ.ም. በኮዓሞ፣ ፖርቶሪኮ የግማሽ ማራቶን ውድድር ምሩፅ እና መሐመድ ከድር ተከታትለው ሲያሸንፉ፣ ምሩፅ የገባበት አንድ ሰዓት 02 ደቂቃ 57 ሴኮንድ የዓለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል።
ቀጣዩና ሶቭየት ኅብረት ያስተናገደችው የ1972 ዓ.ም የሞስኮ ኦሊምፒክ መላው ዓለም የምሩፅን ኃያልነት የተመለከተበት ውድድር ነበር። የእርሱ ባልሆነ ስህተት ምክንያት በሙኒክና በሞንትሪያል ኦሊምፒኮች ድልን የማጣጣም ህልሙ የተጨናገፈበት ምሩፅ፤ እንደተለመደው ኢትዮጵያን በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ወክሎ ቀረበ።
በሙኒክና በሞንትሪያል ኦሊምፒኮች ባለድል የነበረውና ሦስተኛ የኦሊምፒክ ድሉን ለማጣጣም የተዘጋጀው ፊንላንዳዊው አትሌት ላሲ ቪረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሸንፍ በመተማመን ተናገረ። የፖርቶሪኮ ግማሽ ማራቶንን በድጋሚ ያሸነፈው (1972 ዓ.ም) ምሩፅ በበኩሉ ‹‹ … ሐሩርም ይሁን በረዶ እኔ ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም … የማተኩረው በሞስኮ ኦሊምፒክ ላይ ስለሆነ በፖርቶሪኮው ድሌ አልኮራም …›› በማለት በልበ ሙሉነት ተናገረ።
የውድድሩ ቀን ደረሰና ፍልሚያው ተጀመረ። በአምስት ሺ ሜትር ውድድሩ ሊጠናቀቅ 200 ሜትር ሲቀረው በ10 ሺ ሜትር ደግሞ 300 ሜትር ሲቀረው ምሩፅ ማርሽ ቀይሮ ተፈተለከ። ምሩፅ ሙኒክ ላይ ያሸነፈውን፣ ሞንትሪያል ላይ እርሱ በሌለበት ባለድል የሆነውንና ‹‹የሞስኮ አየር ጥሩ ከሆነ አሸንፋለሁ›› ብሎ ተናግሮ የነበረውን ፊንላንዳዊውን ላሲ ቪረንን በመርታት በሞስኮ ኦሊምፒክ በአምስት ሺ እና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳሊዎችን አሸንፎ ድርብ የኦሊምፒክ ድል አስመዘገበ።
በወቅቱ የአምስት ሺ ሜትር ውድድር ሁለት፤ የ10ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ አንድ ማጣሪያዎች ነበሯቸው። ምሩፅ በሁለት የፍፃሜ ውድድሮች አሸንፎ ድርብ ድል ያስመዘገበው ሁሉንም የማጣሪያ ውድድሮች በድል በመወጣት ነበር። በዚህም ምሩፅ በአጠቃላይ የሮጠው 35ሺ ሜትር ነበር። ይህ ክስተትም የምሩፅን የኦሊምፒክ ድል ልዩና አስደናቂ አድርጎታል።
ምሩፅ ስለ ሞስኮ ድሉ በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ ‹‹ … አምስት ዙር እንደቀረው የተቀናቃኞቼን እንቅስቃሴና ትርታ ማዳመጥ ጀመርሁ፤ ውጥረት የሚሰፍነው ደወሉ ሲደወል በመሆኑና አቅማቸውን አሰባስበው ከመነሳታቸው በፊት 300 ሜትር ሲቀር ማምለጥ እንዳለብኝ ወሰንሁ፤ ድሉንም ጨበጥኩ›› ብሏል።
ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በረጅም ርቀት ሯጭነቱ ባለፈባቸው የሩጫ ዓመታት ከ410 በላይ በሚሆኑ ውድድሮች ላይ ተሳትፎ 271 ውድድሮችን በከፍተኛ ብቃት በማሸነፍ አስደናቂነቱን በታሪክ አስመዝግቧል። ለስኬቶቹም ልዩ ልዩ ሽልማቶችን አግኝቷል። በ1971 ዓ.ም. በቼኮዝሎቫኪያ በተካሄደው የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከተመረጡት ዘጠኝ አትሌቶች መካከል አንዱ ምሩፅ ሲሆን፣ ‹‹የኮከቦች ኮከብ›› ተብሎ መመረጡና በተዘጋጀው የተሸላሚዎች መድረክ ላይም ከመሐል በከፍታ መቀመጡ ይታወሳል። የወርቅ ጫማ ተሸላሚም ነበር።
በ1972 ዓ.ም ሻምበል ምሩፅ በቅድመ ሞስኮ ኦሊምፒክ ባገኛቸው አህጉራዊና ኢንተርናሽናል ድሎች ኢትዮጵያን ለታላቅ ግርማ ሞገስ በማብቃት ለፈጸመው አኩሪ ተግባር ‹‹የጥቁር ዓባይ ኒሻን››ን ከርዕሰ ብሔሩ ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ ተቀብሏል። ከኦሊምፒክ ድሉ በኋላ ጥንታዊ ኦሊምፒክ በተመሠረተባት ግሪክ ለኦሊምፒክ ሽልማት ከተመረጡ አምስት አትሌቶች መካከል ቀዳሚ ሆኖ የኦሊምፒክ ሎሬት አክሊልን በክብር የተቀበለውም ምሩፅ ይፍጠር ነበር።
ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በ1973 ዓ.ም. በምዕራብ ጀርመን-ባደን ጉባኤውን ሲያካሂድ የዓለም አትሌቶችን ከወከሉ ሁለት አትሌቶች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊው ምሩፅ ነበር። ሌላኛው ተወካይ ደግሞ የሞስኮ ኦሊምፒክ የአንድ ሺ 500 ሜትር ባለድልና የአሁኑ የማኅበሩ ፕሬዚደንት እንግሊዛዊው ሰባስቲያን ኮ ነበር።
ምሩፅ በተለያዩ ውድድሮች ድል ባገኘበት ወቅት ጋዜጠኛ ኃይሉ ልመንህ
‹‹አብዮቱ ፈካ አበባው አማረ፣
ያለም ሻምፒዮና በምሩፅ ሠመረ።
ሞስኮ ላይ ቀደመ ዳካር ላይ ድል መታ፣
ሞንትሪያል ደገመ እንዳመሉ ረታ።
ዓለም ይሁን አለ ድሉን ተቀበለ፣
እየደጋገመ ምሩፅ ምሩፅ አለ። ›› በማለት ገጥሞለት ነበር።
ሻምበል ምሩፅ ውድድር ሲያቆም ከአትሌቲክስ አልራቀም። ‹‹ጀግና ጀግናን ያፈራል›› እንዲሉ ሻምበል ምሩፅ እነ ቀነኒሳ በቀለን፤ እነ ሚሊዮን ወልዴንና ገዛኸኝ አበራን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ጀግኖችን በማሰልጠን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በ2000 ዓ.ም ቤጂንግ-ቻይና አስተናግዳው በነበረውና ምሩፅ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ በታዳሚው ፊት ይዞ ባለፈበት 29ኛው ኦሊምፒክ ላይ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺና በአምስት ሺ ሜትር ውድድሮች የድርብ ወርቅ ሜዳልያዎች አሸናፊ በመሆን የእርሱን ክብረወሰን በተጋሩባቸው ድሎች ኮርቷል።
ምሩፅ ሞስኮ ላይ ድርብ ድል ሲያስመዘግብ በወቅቱ የሰባት ዓመት እድሜ የነበረው ኃይሌ ገብረሥላሴ የምሩን የጀግንነት ተግባር በሬዲዮ ያዳምጥ ነበር። ምሩፅ የአበበን ድሎች ሰምቶ ወደ ሩጫ እንደገባው ሁሉ ኃይሌም እንደምሩፅ አኩሪ ታሪክ ለመስራት ጉጉት አደረበት። ፍላጎቱን ወደ ተግባር ቀይሮም የሩጫው ዓለም ንጉሥ ለመሆን በቃ። ኃይሌ በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ ምልልስ ‹‹… ገጠር ነበርኩኝ፤ የዕለት ተዕለት ስራዬም ከብቶች ማገድ ነበር። በቤታችን ሬዲዮ ስለምሩፅ እየተሰማ ነው። ዛሬም ደግሞ ድል አደረገ ይላል ጋዜጠኛው። የገረሙኝ ዜናውና ሌሎች ዘገባዎች አልነበሩም፤ ጎን ለጎን ለጀግንነቱ ማወደሻ የሚቀርቡት ሙዚቃዎች እና ግጥሞች ነበሩ። ገና ሰባት ዓመቴ ቢሆንም በአድናቆት ፈዝዤ ስሰማ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ስሜታዊ ነበርኩ። ምሩፅ አሸነፈ፤ ምናምን እያሉ ሲያወሩ ሰው ሁሉ አልመሰለኝም ነበር። ምንድነው ያሸነፈው አላስጨነቀኝም። ግን ለእርሱ እንደተዘፈነውና ለእርሱ እንደተገጠመው ‹ለእኔስ› ብዬ ተመኘሁ። ከዚያማ በቃ በየቀኑ ‹ምሩፅ ነኝ› ማለት ጀመርኩ። ከጓደኖቻችን ጋር ወደ ትምህርት ቤት ለመድረስ እየተሯሯጥን ስንፎካከር ‹ምሩፅ እኔ ነኝ› … ማንም ሊነጥቀኝ አይችልም ነበር። ከስሜ ይልቅ ‹ምሩፅ› እያሉ ይጠሩኝም ነበር … ከምሩፅ ትልቅ የተማርኩት ጠንካራው ልምምዱ፤ ማርሽ ቅየራው ሌላው ሌላው የአሯሯጥ ታክቲክ አልነበረም። ለማንኛውም ውጤት እነዚህ ሁኔታዎች 50 በመቶ ድርሻ ቢኖራቸው ነው፤ ሌላው 50 በመቶ ጀግንነቱና ወኔው ነው። ከምሩፅ የተማርኩትም ይህንኑ አልሸነፍ ባይነትና ወኔውን ነው …›› በማለት ተናግሯል።
አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም በበኩሉ ‹‹ … ምሩፅ ለእኔ የሩጫ ፈር ቀዳጅ፤ ለወርቅ የሚያበቃ የማሸነፍ ታክቲክ ያስተዋወቀ፤ በአፍሪካ፤ በዓለም ሻምፒዮናና በኦሊምፒክ የተሳካለት ምርጥ ተምሳሌት ነው፤ በተለይ አንድ ጀግና ከፊት ለፊት ሲመጣ ከአካባቢህ ሲገኝ ያነሳሳል። እኛም የዛ ውጤት ነን … ምሩፅን ሁልጊዜም በሚሰጠኝ ምክር እንደ አባት ነበር የምቀርበው። መሸነፍ የሚለው ነገር አዕምሮዬ ውስጥ እንዳይገባ ይነግረኛል። ለማሸነፍ ብቻ ወደ ውድድር እንድገባ ነው የሚያነሳሳኝ። ምሩፅ በሩጫ ዘመኑ የሰራቸውን ታላላቅ ስራዎችና ታሪኮች እየዘከርን፤ ጀግንነቱን ዛሬም ልንከተለው ይገባል … ›› በማለት ስለማርሽ ቀያሪው ጀግና ምስክርነቱን ሰጥቷል።
ለ20 ዓመታት ያህል አብዛኛውን መኖሪያውን በካናዳ አድርጎ የቆየው ጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር፤ ባደረበት ጽኑ የሳምባ ሕመም ምክንያት ሕክምናውን እየተከታተለ ቆይቶ ሐሙስ ታኅሣስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ‹‹ … አገሬ ወስዳችሁ እንድትቀብሩኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታዬ ነው›› ብሎ በተናዘዘው መሰረት አስክሬኑ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ከአገር ቤትና ከካናዳ የመጡ ቤተሰቦቹ፣ ዘመዶቹና ወዳጆቹ፣ በወቅቱ በስልጣን ላይ ያሉና የቀድሞ መንግሥታት ሚኒስትሮችና የጦር መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ልዑላን ቤተሰቦችና አድናቂዎቹ በተገኙበት ስርዓተ ቀብሩ ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
ሻምበል ምሩፅ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ከካናዳ ሆኖ በባዕድ መንግሥት እየታገዘ በነበረበት ሰዓት እንኳ፣ እጅግ ውድና በገንዘብ የማይተመኑት ሽልማቶቹ በጨረታ ተሸጠው ለሕክምና እንዲውሉ ሲጠየቅ ‹‹ሽልማቶቼ የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፤ ለሽያጭ አይታሰቡም›› ብሎ የተናገረ አገሩንና ሕዝቡን የሚወድ ቃሉን አክባሪ ጀግና ነበር።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
አንተነህ ቸሬ