እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ኢትዮጵያችን ከለከፋት ሾተላይ መቼ እንደምትፈወስ ግራ ያጋባል። ማህፀነ-ለምለም ናትና ውብ ልጆችን ከማፍራት አልቦዘነችም።
ግና ምን ዋጋ አለው በዘመናት የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በተለይም በደርግ የጠብመንጃ ዘመን ትውልዶችን ገብራለች። በዘመነ ኢሕአዴግ የ27 ዓመታት ቆይታም የኢትዮጵያ ሾተላይ ሚሊዮኖችን ቀጥፏል።
“በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት የተነሳ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት” ተብሎ እንደተጻፈው መከባበርና መደማመጥ ከመካከላችን እየራቀ መጠፋፋትና የደቦ ፍርድ መገለጫችን ሆኗል። “የዳቦ ቅርጫት” ተብላ እንዳልተጠራች የዳቦ ስንዴ ለማኝ ሆናለች-ኢትዮጵያችን።
ከ2010ሩ ለውጥ በኋላ ደግሞ አይታው በማታውቀው የዕልቂትና የጥፋት ማዕበል እየተናጠች ትገኛለች። በርካቶች በብሔራቸው ተለይተው ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ንብረታቸው ወድሟል፤ ተዘርፏልም። አብያተ-ክርስቲያናትና መስኪዶች ተቃጥለዋል። የአገልጋዮችና የምዕመናን ደም ፈሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሹመኞች የጥፋት ኃይሎች ከደገሱባቸው የሞት ወጥመድ አምልጠዋል። ዶክተር አምባቸውንና ጀነራል ሰዓረን የመሳሰሉ በትውልድ መካከል እንደሰናፍጭ ለመድሃኒት ያክል የሚበቅሉ እንቁ የአገር ልጆች ደግሞ የሾተላዩ ሰለባ ሆነዋል።
ሾተላዩ ስለቱን ሞርዶ አሁንም የኢትዮጵያን የማሕጸን ፍሬዎች መቅጨቱን ቀጥሏል። የሾተላዩ ሰይፍ በደም ሰክሯል፤ የበርካቶችን ደም የጦሱ ግብር አድርጓል። በርካቶችንም የሐዘን ሸማ አከናንቦ ቅስማቸውን ሰባብሯል።
በድንቃድንቅ ዘፈኖቹ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የትግል ወኔን ያቀጣጠለው ሃጫሉ ሁንዴሳ ተረኛው የሾተላዩ ሰለባ ሆኗል። በሱ ሞት ምክንያትም በርካቶች ተቀጥፈዋል። በዚህም ምክንያት የማሕጸናቸውን ፍሬ የተነጠቁት እናቶች፤ የአብራካቸውን ክፋይ ያጡት አባቶች የዕንባ ጎርፍ ንፍር ሆኖ ምድሪቱን እየተፋረዳት ይገኛል።
የሾተላዩ ግብር አቀባዮች የዕልቂት ጥሪየዘመናችን ሾተላይ ኢትዮጵያ በደም እንድትታለል፤ በእንባ ጎርፍ እንድትጥለቀለቅ እያደረገ ያለው በነጋሪት ጎሳሚዎቹ የዕልቂት ጥሪ ነው።
ከወራትና ከዓመታት በፊት የታየውን እልቂት ለጊዜው እንተወውና በሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት ሀገር በሾተላይ ጦር ተሰቅዛ የሰነበተችበትን ሁኔታ ለአፍታ እንመልከተው።
የሃጫሉን መገደል አብዛኛው ሕዝብ የሰማው ማክሰኞ ማለዳ ነው። በአገር አማን ሰው ሁሉ ወደየተግባሩ ሊሰማራ ሲሰናዳ ነበር የአርቲስቱን በሾተላዩ መበላት የተሰማው። መላ ኢትዮጵያም በታጋዩ ዘፋኝ ሞት በሐኀዘን ተውጦ አረፈደ።
ብዙም ሳይቆይ ጃዋር መሃመድ በባለቤትነትና በኃላፊነት የሚመራው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በቀጥታ የቴሌቭዥን ፕሮግራም የአርቲስቱን አስከሬን ለምርመራ ካደረበት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ወጥቶ ለቀብር ሥነ-ሥርዓት እትብቱ ወደተቀበረባትና የታጋይነት ችቦውን ወደለኮሰባት የአምቦ ከተማ በማምራት ላይ የነበረበትን የአሸኛኘት ሥርዓት ማስተላለፉን ይቀጥላል።
የአርቲስት ሃጫሉ ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አድናቂዎች የተገኙበትን ይህንን በአጀብ የተሞላ የአሸኛኘት ሥነ-ሥርዓት በቀጥታ በማስተላለፉ በብዙዎች ዘንድ ተመስግኖ ነበር።
ይሁንና እንዲያ ባለ አስደንጋጭና አሳዛኝ ሁኔታ የአርቲስቱ ሕይወት ማለፍ የሚያስቆጣ ቢሆንም በአገራችን ወደ አስከፊ ደረጃ እየተሸጋገረ ያለውን የኮሮና ወረርሽኝ የሥነ-ሥርዓቱ ታዳሚ ሕዝብ እንዳይዘነጋና ኀዘንና ቁጣውን ኃላፊነትና ጥንቃቄ በተሞላበትና መልኩ እንዲገልጽ የሰከነና የበሰለ የሚዲያ ኃላፊነቱን መወጣት ሲገባው ይባስ ብሎ በቀጥታ ሥርጭት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭና ዕልቂት የሚጠራ የሾተላዩን ነጋሪት መጎሰሙን ተያያዘው።
የሃጫሉን ግድያ ሰበብ በማድረግ ከአገሪቱ ሕዝቦች ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቁጥር የያዙትን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦችን እርስ በእርስ የሚያጫርሱ የዕልቂት ጥሪዎችንና መልዕክቶችን በቀጥታ ማሰራጨት ጀመረ።
የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ከሌሎች ወንድምና እህቶቻቸው ጋር ትናንት በጋራ ቆመው ይህችን አገር በደግም በክፉ መሀል አሻግረዋል። ምድሯን በጠላት ሳያስደፍሩ፤ ከአድዋ እስከ ካራማራ፣ ከመተማ እስከ ዶጋሊ የጋራ መስዋዕትነት ከፍለው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብረዋል። ተጋብተው ተዋልደው ተጋምደው የቆዩ ወንድማማች ሕዝቦች ናቸው።
ይሁንና ይህንን አሽቀንጥሮ በመጣል ትውልዱ ተምሮባቸው እንዳይደግማቸው ሳይዘነጉ ለታሪክ ብቻ የሚተዉ አሉታዊ ግንኙነቶችንና የ27ቱ ዓመታት የወያኔ ከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት የዘራቸውን የተንሻፈፉና የተዛቡ የመቃቃር ትርክቶችን ብቻ ነቅሶ በማውጣት የኦሮሞ ወጣቶች በቁጣና በስሜት ተነሳስተው በወንድሞቻቸው ላይ ጥፋት እንዲያደርሱ ነበር ሲቀሰቅስ ያረፈደው።
ይህ የጥፋት ቅስቀሳውም የሩዋንዳውን የዘር ፍጅትና የያኔውን የሚዲያዎች የዕልቂት ጥሪ ነበር የሚያስታውሰው። ዓላማውም የሩዋንዳው ዘግናኝ ግጭት በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍና ታሪካዊ ሕዝቦች በሆኑት በአማራና በኦሮሞ ወንድማማቾች መካከል እንዲደገም ማድረግ ይመስል ነበር።
ይባስ ብሎም እጅግ በሚያሳፍር መልኩ ከኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ከአገራችን ሕዝቦች የጋራ ባህል ፍጹም በሚጻረር መልኩ የእናት፣ የአባት እንዲሁም የወዳጅ ዘመድ ስሜትንና ክብርን በሚነካ መልኩ አስከሬኑ ወደ አምቦ መሸኘት እንደሌለበትና አዲስ አበባ ውስጥ እንዲቀበር መወትወቱን ቀጠለ።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በቀጥታ በሚያሰራጫቸው በእነዚሁ ፕሮግራምና መልዕክቶቹ የአርቲስት ሃጫሉን ገዳይ “እከሌ ነው” ብሎ በግልጽ በመፈረጅ በመላ አገሪቱ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ይበልጡንም በአዲስ አበባ ሁከት እንዲቀሰቀስ ነበር ሲሰብክ ያረፈደው።
ይህንን የቴሌቭዥን ጣቢያውን የዕልቂት ጥሪ ተከትሎ የአስከሬን ሽኝት ሥነ-ሥርዓቱ በሁከት ተበጠበጠ። መላው የኦሮሚያ ክልልም በሾተላዩ ሰይፍ ተመታ። ሥርዓት አልበኝነትና መገዳደል ነገሰ።
የሰከረው የሾተላዩ ሰይፍ የበርካቶችን ሕይወት ቀጠፈ፤ የመንግስትና የግለሰቦች የልፋት ጥሪት የእሳት ራት ሆነ። የሾተላዩ ውላጆችም እንዳሰቡት ባይሆንም እፍኝ ትርፍ አገኙ።
የጥፋት ሚዲያዎቹ ግንባር የመፍጠራቸው ምስጢርየኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ይህንን የጥፋት ጥሪ ሲያሰራጭ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ትህነግ/ሕወሃት) ልሳኖች የሆኑት ድምጸ ወያነ እና የትግራይ ቴሌቭዥን በየፊናቸው የጥፋት ጥሪውን በመቀባበል ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ነው የሰነበቱት። አስራት ሚዲያም በተመሳሳይ የራሱ መልክ ያለው ጠርዝ የረገጠ የጎጠኝነት ቅስቀሳ ሲያደርግ ቆይቷል።
የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ የተፈጸመው የእርስ በእርስ መጠፋፋትና ውድመት ከለውጡ በፊት በነበሩት የዝርፊያና የግርፊያ ዓመታት በወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ ሲፈጸም የነበረው መንግስታዊ የአሸባሪነትና የጎሰኝነት አገዛዝ ውጤት ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።
አገሪቱ በትህነግ ገዥ ቡድን አፈና ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክም ሆነ ባለቤትና መስራቹ ጃዋር ሙሃመድ በአሸባሪነት ተፈርጀው ተሳዳጆች ነበሩ። ድምጸ ወያነና የትግራይ ቴሌቭዥንም ከሌሎቹ የኢሕአዴግ ሚዲያዎች ጋር በመሆን የአሳዳጆቹ መሳሪያና አውጋዦች ነበሩ።
ከሃጫሉ ሞት በኋላም ሆነ ከዚያ አስቀድሞ ለውጡ እንደደራሽ ጎርፍ ጠራርጎ መቀሌ የቀረቀረው የሕወሃት ቡድን በኦሮምኛ ቋንቋ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የሚተላለፉ የጥፋት ጥሪዎችን ወደትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋዎች በመመለስ በሁለቱም ሚዲያዎቹ ሰፊ የዕልቂት ቅስቀሳ አድርገዋል።
ያም ሆነ ይህ የትግራይ ቴሌቪዥንና ድምጸ ወያነ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ፍጹም በተናበበ መልኩ የጥፋት ነጋሪት ሲጎስሙ የሰነበቱት ተመሳሳይ የሆነ አገር የማፈራረስ እኩይ ዓላማ ስላላቸው ነው።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአብሮነት ሀረግ የሚመዘዘው ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ዘመን ወዲህ ብቻ በማስመሰልና ረዥሙን የአማራና የኦሮሞ ጭቁን ሕዝቦች የአብሮነትና የትግል ጎዳና “ጨቋጭ ተጨቋኝ” በሚለው የሕወሀት ውስጠ-መርዝ ትርክት ተጠቅሞ ሕዝቦቹን ለማጣላት የመሰሪነት ተልዕኮውን ሲወጣ ሰንብቷል።
ድምጸ ወያነና የትግራይ ቴሌቭዥን በበኩላቸው የሁለቱን ግዙፍ ሕዝቦች ግንኙነት “እሳትና ጭድ” በሚል በሚገልጹት እኩይ የሕወሀት ቁንጮዎች እየተመሩ የአርቲስቱን ግድያ ተከትሎ የተፈጠረውን ትኩሳት የመንግስት መፍረስና የአገሪቱ መበታተን ዋዜማ አድርገው በማቅረብ የሾተላይ ነጋሪታቸውን ሲጎስሙ ሰንብተዋል፤ አሁንም በተለያዩ መንገዶቻቸው በመጎሰም ላይ ይገኛሉ።
በዘመነ-ሕወሀት ሜጀር ጄነራል ኃየሎም አርዓያ፣ የያኔው የደህንነቱ ቁንጮ ክንፈ ገብረመድህንንና ሌሎችም በርካታ ሰዎች የሾተላዩ ሰለባ ሆነዋል። በምርጫ 97 እና በሌሎችም ታሪካዊ ክንዋኔዎች ሰበብ በርካቶች ተገድለዋል። ነገር ግን ያ ሁሉ ዝርፊያና የሰብዓዊ ጥፋት የአገር መፍረስ ዋዜማ አልነበረም፤ የጨቋኝ ሥርዓት መወገድ ዋዜማ እንጂ።
ድምጸ-ወያነ እና የትግራይ ቴሌቭዥን ግን ኢትዮጵያን ሁል ጊዜ ከዩጎዝላቪያ ጋር በማነጻጸር በመፈራረስ ቋፍ ላይ ያለች አድርገው በማቅረብ ሕዝቡን በሀሰት አምሰዋል።
በዓለም ታሪክ ተመዝግቦ እንደምናነበው ዩጎዝላቪያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቭየት ሕብረትን መፈራረስ ተከትሎ ክሮሽያ፣ ሰርቢያ፣ ቦሲኒያን የመሰሉ ስድስት አገሮች የፈጠሯት አገር ነበረች። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ ዩጎዝላቪያ ፈራርሳ በዓለም መድረክ እምብዛም ተጽዕኖ የሌላቸው ትናንሽና ደካማ ስድስት አገሮች ወደመሆን ተቀይራለች።
ኢትዮጵያችን ግን በአምስት ሺህ ዓመታት የመንግስትነት ታሪክ ውስጥ በክፉም በደግም በጋራ ሆነው አገር አቅንተው፤ ጠላት መክተው በነጻነት የኖሩ የተዋለዱና በማይበጠስ የጋራ የባህልና የታሪክ ተዛምዶ የተጋመዱ ከ80 የሚልቁ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ናት።
በክርስትናም ሆነ በእስልምና ቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደ ግብጽ በበደል፤ እንደሰዶምና ገሞራ በጥፋት ሳይሆን በጥበበኝነት፣ በደግነት፣ ለፈጣሪ ቅርብ በመሆንና በመሳሰሉት መልኮች ነው የተገለጹት።
የኢትዮጵያውያን የመንግስት ታሪክና የሕግ አክባሪነት እንዲሁም የጨዋነትና የግብረ ገብነት ተምሳሌትነት በጥንታውያኑ የግሪክ የታሪክ የቀለም ቀንዶች ሳይቀር የተመሰከረ ነው። የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንት የሥልጣኔ ቁንጮ እንዲሁም የድንቃድንቅ ቅርሶች ባለቤትም ናቸው ኢትዮጵያውያን።
ሁለቱም የወያኔ ቴሌቭዥኖች ታዲያ ይህንን ዓይነት ነባራዊ ሐቅ ወደጎን ትተው ኢትዮጵያ በሕወሃትና አሁን ባለው ሕገመንግስት የተፈጠረች ትናንት የሌላት ሥር-አልባ የ27 ዓመት አገር አስመስለው በማቅረብ የውሸት ትርክታቸውን መደርደር ይቀናቸዋል።
በባህልና በታሪክ የተሰናሰለ ሕብር ያለውን ሕዝብ ንቀው የሺ ዘመናት የአብሮነት ቋጠሮውን እየፈቱ ኮሽ ባለና የመንግስት ሕግ የማስከበር ግዴታ በላላ ቁጥር አገር ልትፈርስ ነው እያሉ በሟርታቸው ሕዝቡን ያደነቁራሉ፤ ያደናግራሉ።
ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር የጥፋት ግብር ግንባር ፈጥረው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎቻቸው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት ቀን ከሌት በመስራት ላይ ይገኛሉ። የመጨረሻ ግባቸውም በትርምስ ውስጥ በንጹሃን ደም መነገድ ልማዱ የሆነውን ጨቋኝ ሥርዓት መመለስ ነው። አይሳካላቸውም እንጂ።
በተለይም ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ ውሃ ሙሌት በመጀመር ወደወሳኝ ምዕራፍ ልትሸጋገር በተሰናዳችበት ወቅት ሕዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ተከታታይ ዘገባ ማቅረባቸው ደግሞ እነዚህ ሚዲያዎች የውስጥ ጥንካሬዋን ለማይፈልጉ የውጭ ጠላቶች ቅጥረኛ በመሆን እየሰሩ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።
እርግጥ ነው የእነዚህ ሚዲያዎች የሾተላይ ነጋሪት ጉሰማ በአገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ላይ የራሱን ጥቁር ነጥብ ማሳረፉ አልቀረም። ከኢትዮጵያ ሕዝብ 60 በመቶው የሚሆነው ወጣት በመሆኑ መልካም ዕድል ቢሆንም ቅሉ፤ ትውልድ ለማጨንገፍ ታስቦ በተተገበረው የህወሀት የትምህርት ሥርዓት መነሻ ግብረ-ገብነት፣ ምክንያታዊነትና ብስለት በቅጡ ስላልሰረጸ ሥራ-አጥነት ታክሎበት የብጥብጥና የሁከት ጎርፍ ከባድ ጥፋትን እያስከተለ አልፏል።
ይሁንና አብዛኛው ሕዝብ ከተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የሚያገኘውን መረጃ በመመዘንና በራሱም ያስተዋለውን ነባራዊ ሐቅ ከግምት በማስገባት አስተዋይነት በተሞላበት መልኩ በመንቀሳቀሱ የጥፋት ደጋሾቹ በደገሱት ልክ ሴራቸው ሳይሳካ ጨንግፎ ሊቀር ችሏል።
መንግስት በነካ እጁ አደብ ያስገዛቸው እርግጥ ነው ሃሳብን በነጻነት መግለጽ መሰረታዊ ከሚባሉት መብቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይሁንና የሕዝብንና የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ እስከሚጥል ድረስ ተለጥጦ የሚተገበር ሳይሆን ልጓም ይበጅለታል።
እናም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከገደብ አልፎ ለአገርና ለሕዝብ ደህንነት ሥጋት እንዳይሆን ሚዛኑን የሚያስጠብቅ ሕግ ያስፈልጋል።
ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ሽፋን የሚከሰቱ ጥላቻን፣ ማግለልን፣ ግጭትን፣ ጥቃትንና መሰል በግለሰቦችና በማህበረሰቡ መካከል ያለውን መልካም ግንኙነትን የሚያሳሱና የሚጎዱ ንግግሮችንና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን በህግ መከላከል እና ርምጃ መውሰድም ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ የፈረመችውና እኤአ በ1965 ዓ.ም. የወጣው ሁሉንም ዓይነት የዘር ልዩነቶችን ለማስወገድ የተደረገው ዓለምአቀፍ ሥምምነትም አገሮች ብሔራዊ የበላይነትን የሚሰብኩ ወይም የዘር ጥላቻንና ልዩነትን የሚያራምዱ ተቋማትንና ንግግሮችን ለማስወገድ ሕግ ማውጣት እንዳለባቸው ያስገነዝባል።
በኢትዮጵያም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሕዝብና ከአገር ሕልውና ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ የሚያስችሉ የተለያዩ ሕጎች በሥራ ላይ ይገኛሉ። የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ፣ የጥላቻ ንግግርን እና የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ እንዲሁም የወንጀል ሕጉ ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው።
በእነዚህ ሕጎች ውስጥ ታዲያ መገናኛ ብዙሃን ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ ሽፋን አገር አፍራሽ ሕዝብ አጫራሽ ተግባር እንዳይፈጽሙ የሚከለክሉ ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል። እንዲህ ዓይነት ዘገባዎችን ሲያቀርቡም ሊወሰዱ የሚገባቸው አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃዎች ተመልክተዋል።
በመሆኑም መንግስት ከለውጡ በኋላ የተረጋገጠውን እውነተኛ የሚዲያ ነጻነት ለእኩይ ዓላማ በመጠቀም ሕዝቡን ለጥፋት በዳረጉት ሚዲያዎች ላይ ያሳረፈውን አርጩሜ ደገምገም ሊያደርግባቸው ይገባል።
እንደዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ዕምነት ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው የለውጡ መንግስት ሕግን በማስከበር ረገድ ሁለት ወርቃማ ዕድሎች አምልጠውታል።
የመጀመሪያው የሚዲያ ነጻነትና ሃሳብን የመግለጽ መብቶች ያለገደብ መፈቀዳቸውን ሰበብ በማድረግ ሆነ ብለው ሕዝብን በማጋጨት አገር የሚያፈርሱ አጀንዳዎች በሚዲያዎች፣ በራሱ በመሪው ድርጅት ቁንጮ ባለስልጣናትና በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አማካኝነት በገበያ ሲውሉና በተለይም ወጣቱ ሲሸምታቸው ይሄ ነው የሚባል ርምጃ አልተወሰደም።
በዚህ ሳያበቃ የአርቲስቱን ሞት ሰበብ በማድረግ እንደዚያ ዓይነት ዕልቂት ሲፈጠር የፖለቲካ አመራሩና የጸጥታ ኃይሉ ተገቢና ተመጣጣኝ ርምጃ ባለመውሰዱ ውጤቱ አስከፊ ሆኖ አልፏል። (የጸጥታ ኃይል ርምጃ በወሰደባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የደረሱት ጥፋቶች በአንጻራዊነት አስከፊ አልነበሩም)
አሁን መንግስት በእውነት ለአገርና ለሕዝብ ማድረግ ያለበት ሶስተኛውንና የመጨረሻውን የዕድል ካርዱን መምዘዝ አለበት – ይኸውም ወንጀል ፈጻሚዎቹን በሙሉ ለቃቅሞ ያለምህረት ለሕግ እንዲንበረከኩ ማድረግ ነው።
ይህ ብቻም ሳይሆን በሃሳብ ነጻነት ሰበብ ሕዝብን የሚያጋጩ አጀንዳዎችን የሚያሰራጩ ሚዲያዎችን በየጊዜው እየተከታተለ የማያዳግም ርምጃ መውሰድ ይገባዋል። የኢንተርኔት መረጃዎ ሥርጭቶችንም በአግባቡ መቆጣጠር አለበት።
የማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀመው የሕብረተሰብ ክፍልም ቢሆን ከሰሞኑ የኢንተርኔት አገልግሎት መለቀቁን ተከትሎ የሚሰራጩና ዳግም ወደግጭት የሚከቱትን እኩይ መልዕክቶች መቀበልና ማሰራጨት የለበትም። ይልቁንም የሕዝቦችን አብሮነትና የአገርን አንድነት የሚያጠናክሩ በጎ ሃሳቦችን በማንሸራሸር ታሪካዊ ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
በገብረክርስቶስ