በየዘመናቱ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተሞከሩ የጥፋት ተልዕኮዎች፣ የተቃጡ ዘመቻዎችና ተግዳሮቶች መልካቸው ብዙ፣ ሴራዎቹም ውስብስቦችና የረቀቁ ነበሩ። በሉዓላዊነታችን ላይ ከተደረጉ የውጭ ወረራዎችና ጦርነቶች እስከ ውስጥ የአመጽ ደባዎችና ሥነ ልቦናን የማፈራረስ ሴራዎች ድረስ ሀገሪቱና ሕዝቦቿ በእጅጉ ተንጠዋል፤ ተፈትነዋልም። መከራዎቹና ተግዳሮቶቹ መልካቸውን እየለዋወጡ ቢያስጨንቁንም ፈተናዎቹን ተቋቁመንና እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትነን በመንጠር ታሪካችንን በክብር እየጻፍንና እያጻፍን እነሆ ዛሬ ላይ ደርሰናል።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በአህያ ቆዳ ተገንብቶ በጅቦች ጩኸትና ማሽካካት የሚፈራርስ የተረት ግምብ አይደለም። በሰባት ዙሮች የእሥራኤል ሰልፈኞች ጩኸትና እሪታ በፈራረሰው ኢያሪኮ የሚመሰል ቅጥር እንዳይደለም፤ በገሃድ ያስመሰከርንባቸው ታሪኮች ብዙዎች ናቸው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፀንተው የቆሙት በሺህ ዘመናት የጀግኖች የደም ግብር በተለወሰ መሠረት ላይ ሲሆን፤ የተዋቀሩበት ቋሚና ማገርም በነፃነት መቅኒ በወዛ በብርቱዎቹ የእምዬ ልጆች የአጥንት ክስካሽ ነው።
አጥንቴም ይከስከሰ፤ ደሜም ይፍሰስላት፣
ይህቺ ሀገሬን ጭራሽ፤ አይደፍራትም ጠላት።
አክትሟል አበቃ የእናንት ምዕራፋችሁ፣
የማይሆን ቅዠት ነው ከንቱ ነው ህልማችሁ።
ስትቅበዘበዙ አልፋችሁ ከልኩ፣
በአንድነት ብለናል ሀገሬን አትንኩ።
ጥንት አባቶቻችን ዛሬም ልጆቻቸው፣
ጀግንነት ወርሰናል ከደም ካጥንታቸው።
ስለዚህ አንፈራም ግዴለንም እኛ፣
ቆርጠን ተነስተናል እኔን ትተን እኛ።
እየተባለ ሲዘመር፣ ሲፈከርና ሲቀነቀን የኖረው እውነት እና ሐቅ ስለሆነ እንጂ ዜማና ግጥሙ ስለተዋበ ወይንም ይዘቱ በስሜት እንፋሎት ስለሚወዘውዝ አይደለም። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የሚንተከተከው የሀገርና የሕዝብ ፍቅር እሳተ ጎመራ እንደ አፋሩ ኤርታሌ እየፈላ የሚገነፍለው በጋለ ሕዝባዊ ፍምና የኅብረ ብሔራዊነት ውብ ቀለማት መንታ ባህርይ ተሸምኖ ጭምር ነው።
ኢትዮጵያዊነት ትናንት፣ ዛሬና ነገ ብለን ከምንገልጸው ከተፈጥሯዊው የጊዜ ዑደት ባህርያት ጋር በሚገባ ይመሳሰላል። የትናንቱ የኢትዮጵያዊነት ደማቅ መልክ ዛሬም ወዙ እየፈካ ያብብ ካልሆነ በስተቀር ደብዝዞ የሚወይብ አይደለም። ነገም ደምቆ ያብለጨልጫል እንጂ ጠይሞ አይፈዝም። በኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን፤ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኢትዮጵያን ፈልቅቆ ለማለያየት መሞከር ቀደም ሲል በጠቀስኩትና እየተንተከተከ በሚፍለቀለቀው የእሳተ ጎመራ ሐይቅ ውስጥ ገብቶ የመዋኘት ያህል ጅልነትና እብደት ነው። “ነብር ዝንጉርጉርነቱን፣ ኢትዮጵያዊም መልኩን ሊለውጥ አይችልም” በማለት ቅዱስ መጽሐፍ ከመሠከረው ውጪ ሌላ ማረጋገጫ ማጣቀሱ “ከጳጳሱ ምዕመኑ” ይሉት አባባልን ከማስታወስ የሚዘል አይሆንም።
የኢትዮጵያዊነት እውነተኛ መልክ በውስጥም ሆነ በውጭ ራሷ ኢትዮጵያ ነች። የመልኳ ስሪት የተዋበውና የቆነጀው በብሔር ብሔረሰቦቿ ውብ ኅብረ ቀለማት፣ ውህደትና ስምረት ነው። ቋንቋዎቿና ባህሎቿ ወርቀ ዘቦ ዘርፎቿ ናቸው። ኢትዮጵያዊነትን አዝለንና ታቅፈን እንድንዞር የተጫነብን ሸክም ሳይሆን በልባችን ላይ ተቀርፆ፣ ታትሞና ከመንፈሳችን ጋር ተዋህዶ የምንኖረው እኛነታችንና ማንነታችን ስለሆነ ነው። በረቂቅ ቅኔዎች የተመሳጠረውን ኢትዮጵያዊነታችንን የምናዜመው በሀገር ቤት ስንኖር ብቻ ሳይሆን ባህር ተሻግረን፣ ውቂያኖስ አቋርጠን ከአጥናፈ ዓለም ዳርቻ ብንገኝም እንኳን የዜማው ቅኝት አይጎለድፍም፤ የስሜት ግለቱም አይቀዘቅዝም።
ጠጠር ወርዋሪዎቹ ዘመናዊ ሟርተኞች፤
“ሟርተኝነት ሥጋ በመልበስ የሚገለጥ ሰይጣናዊ ነብይነት” መሆኑን መዛግብተ ቃላት ይደነግጉልናል። “ጠጠር ጣይነት” ደግሞ “እንዲህ ይሆናል፣ እንዲህ ይደረጋል፣ እንዲህ ሊፈጠር ይችላል እየተባለ የሚጠነቆልበት የአባይ ጠንቋይነት መገለጫ ነው። ” ታዳጊ ሴት ሕፃናት ቅልልቦሽ እያሉ በትነው እያፈሱ የሚጫወቱበት ጠጠር ለልጅነት የዕድሜ እኩዮች ለመዝናኛና ጊዜ ማሳለፊያነት ይጠቅም ካልሆነ በስተቀር የሟርት፣ የድግምትና የመተት ምስጢራት መገለጫ ሆኖ ሊታመንበት የሚችል አይደለም።
ሰሞኑን በአንዳንድ ታላላቅ የዓለማችን ከተሞች አውራ ጎዳናዎች ላይ በመሰባሰብ ጥቂት የእንግዴ ልጆች “Down Down Ethiopia! Down Down Habesha! Down…” እያሉ በስመ ሰላማዊ ሰልፍ በሀገር እና በተወሰነ ታላቅ ብሔር ላይ የአመጽ ጥሪ ለማስተላለፍ ሲወረውሯቸው የከረሙት የሟርት ጠጠሮች እንኳን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አቁስለው ሊያፈራርሱ ቀርቶ ሠልፈኞቹ በግዞት ከተጠለሉበት የባእድ ቀዬ ፈቅ ብለው እንደማይርቁ ልባቸው በሚገባ ያውቀዋል።
የሥልጣን ቅዠት እያናወዛቸውና በእንክርዳድ የጠመቁትን ጉሽ እየተጎነጩ ናላቸው ሲዞር አደባባይ የሚውሉት ፀረ ኢትዮጵያ ስብስቦች በርግጠኝነት ከጩኸታቸው ፋታ ወስደው ኅሊናቸውን ቢያደምጡ እውነቱን ይረዱት ነበር። እነዚህ የሟርት ጠጠር ሲወረውሩ የሚውሉት ነገረ ዓለሙ የተምታታባቸው የዲያስፖራ አባላት ሌሎች ሕዝቦች ዋጋ ከፍለው በዘረጓቸው የተመቹ አውራ ጎዳናዎች ላይ እየፈነጩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ሲያዋርዱ የሚውሉት የራሳቸውን እፍረት በራሳቸው ዋንጫ ለመጎንጨት ካልሆነ በስተቀር በሀገር ቤት ያለው ሕዝብማ አንቅሮ ከተፋቸው ውሎ አድሯል። “ወይ አለመተዋወቅ!” አለ ሌቦ ሳህሉ ይባላል። መቼም ለቤተሰብ ክብር የላቸውም እንጂ እስቲ እየፈጸሙ ስላሉት እኩይ ድርጊት የራሳቸውን ቤተሰብና ብሔር ይጠይቁና ምን መልስ እንደሚያገኙ ይሞክሩት።
የሚገርመው እንቆቅልሽ እነርሱ በባእድ ምድር ተሸጉጠው የማይሆንላቸውንና የማይሞከረውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማፈራረስና ለመናድ እየቃዡ የመፈክር ጠጠር ሲወረውሩ የሚውሉት ጠግበው እያገሱ፣ ተጋድመው እያንኮራፉ፣ ሸቅጠው እያተረፉና በሰዓት የሚከፈላቸው ዶላር እንዳይጎድልባቸው እየተጉ ኑሯቸውን በማደላደል ነው። የግዞተኝነት ካርድ የሰጣቸውን ሀገር ሕግና ሥርዓት፤ የሕዝቡንም ባህልና ወግ እየተንቀጠቀጡ አክብረው በመኖርም ጭምር።
የሟርት ጠጠራቸውን ከየማኅበራዊ ሚዲያው እየለቀመ መልሶ በራሱ ላይ እንዲወረውር “ጃስ!” እያሉ የሚያስደነብሩት የሀገር ልጅ ደግሞ የዕለት ዳቦ ያረረበት፣ ጣሪያው የማያፈስ መጠለያ ብርቅ የሆነበት፣ ቅያሪ ልብስ የቸገረው፣ የኑሮ ትግል ያጎሳቆለው፣ ንፁሕ ውሃ የናፈቀው፣ የኤሌክትሪክ ብርሃን ብርቅ የሆነበት ግፉዕ መሆኑ ተቃርኖውን ያወሳስበዋል። በሀገሪቱ ብልጭ ያለው የለውጥ ተስፋ እንዲደበዝዝ፣ የተጀማመሩት የልማት ውጥኖች እንዲመክኑ፣ እንደ ማለዳ ወገግታ መድመቅ የጀመረው የሀገሪቱ ተስፋ እንዲዳምን ተግተው መሥራታቸው የተምታታው ዓላማቸው ብቻ ሳይሆን ሰብእናቸውም ጭምር ራሱ ጤነኛ መሆኑ የሚያጠራጥር ነው። ቢጎመዝዛቸው ይጎምዝዛቸው፣ ቢያንገሸግሻቸውም ያንገሽግሻቸው እንጂ በምንም መስፈርትና መለኪያ የዛሬዋ ኢትዮጵያ የእነርሱ “ነፍስ አባቶች” ሲግጧትና ሲቦጠቡጧት የነበረችው የትናንቷ ኢትዮጵያ አይደለችም።
እነዚህ የባህር ማዶ ነውጠኛ ጠጠር ወርዋሪዎች በደምና በአጥንት የተጋመደው ኢትዮጵያዊነት እንዲተረተርና እንዲላላ ነጋ ጠባ “ተነስ! አፍርስ! አቃጥል! ግደል!” እያሉ የሚያሟርቱት ቢያንስ ቢያንስ ወገኔ የሚሉትን ክፍለ ሕዝብ በቅርበት አቅፈውት ጠረኑን እያሸተቱ ጉድለቱን ለመሙላት አስበው ሳይሆን ከውስጣቸው በሚፈልቀው የዘረኝነት ሃሳብ ሰክረው ለማሳከር ነው።
እርግጥ ነው ከባህር ማዶ ሟርተኞቹ እየተወረወረ የሚዘራው ክፉ ዘር በአንዳንድ የዋህ ዜጎች ልብ ውስጥ ጠልቆ ከመግባቱ የተነሳ የደረሰው የሰሞኑ የንፁሐን ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት ትቶብን ያለፈው ጠባሳ በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም። በክፉዎቹ ሴረኞች ቅስቀሳ አብደውና የህሊና ጨርቃቸውን ጥለው በርካታ ሕይወት የቀጠፉትና የዜጎችን ሀብትና ንብረት ያጋዩት የእነዚያ ልበ ስውራን ድርጊት ለሕግና ፍትሕ እየቀረበ መሆኑ የሚያበረታታ ነው። ቢቻል ሕጉ ከሚሰጣቸው ብያኔ በተጨማሪ ባቃጠሏቸው ንብረቶችና ፍርስራሾች ላይ ቆመው ሰይጣናዊ ድርጊታቸውን እንዲመለከቱና የፍርስራሹን አመድ እንዲዘግኑ ቢደረግና ኅሊናቸው እንዲቀጣቸው ዕድል ቢሰጥ በእጅጉ መልካም ይሆናል። ቪዲዮውም ተቀርጾ ለእነዚያ የባህር ማዶ ስምሪት ሰጭዎቻቸው ቢላክ አይከፋም። ከክፋትም የከፋው ክፉ ቅጣት ይህ ነው።
እጃቸውን የታጠቡበት የንፁሐን ደምና ያደረሱት ውድመት በሕጉ መሠረት ተመዝኖ ተገቢው ብይን እንደሚተላለፍባቸው ቢጠበቅም በታሪካቸውና በሰብእናቸው ላይ ያተሙት ክፉ ድርጊት ግን ወደ መቃብርም አብሯቸው እንደሚወርድ ይጠፋቸዋል ማለት አይቻልም። ጠጠር ወርዋሪዎቹ የባህር ማዶ ሟርተኞችም ቢሆኑ ጊዜና ወቅቱን ጠብቆ በምድራዊ ዳኝነትም ሆነ በሰማያዊው ፈራጅ አምላክ ፊት የእጃቸውን ማግኘታቸው የሚቀር አይሆንም።
በኅሊና ህመምና በመንፈስ ስብራት ሲያነክሱ ኖረው በጥላቻ ጨለማ እንደተዋጡ ለሚያልፉት ለእነርሱ ይብላኝላቸው እንጂ የተፈናቀሉት ንፁሐን ዜጎቻችን ተመልሰው በየቀያቸው መሰባሰባቸው፣ የወደመው ሀብታቸውም መተካቱ፣ የሞት መከራ የገጠማቸው ወገኖችም መጽናናታቸው አይቀሬ ቢሆንም፤ የተፈጸሙት እኩይ ድርጊቶች ግን በቀላሉ የሚሽሩና የሚጠግጉ አለመሆናቸው እሙን ነው። ዛሬ በባእድ ምድር ቢሸሸጉም የነገው ትውልድ አድኖ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። እነርሱም ቢሆን ኅሊናቸው የሞተ ስለሆነ ሀገር ወዟ ሲፈካ ፓስፖርታቸውን አድሰው ተሸቀዳድመው መምጣታቸው አይቀርም። ያኔ የሚሆነው ይሆን ይመስለኛል።
በውጭ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር ቤት በሚገኙት ዜጎቻችን ልብ ውስጥ የሚዘራውን የዘር ዓይነቶች በተመለከተ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሰ አንድ ግሩም ምሳሌ ጋር ማመሳሰል ይቻላል። “የዘሪው ምሳሌ” በመባል የሚታወቀው ይህ ታሪክ እንዲህ ይነበባል።
“እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ ዘር በመንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሙት። ሌላውም ዘር ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረ ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፤ አንዱም መቶ፣ አንዱም ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ አፈራ። ”
ከኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተፈልቅቀው መገኘታቸውን ክደውና ናውዘው ጎጠኝነትና ዘረኝነትን በማክረር መንፈሳቸውና ማንነታቸው የተሳከረባቸው እነዚያ የባህር ማዶዎቹ ነውጠኞች በሉዓላዊ ክብርና በብዙ የጋራ እሴቶች በተጋመደው ሕዝብ መካከል ክፉ ዘራቸውን በመዝራት ለማበጣበት የሚሞክሩት ቢያንስ ከምሳሌው ውስጥ የሦስቱን የዘር ዓይነቶች እየዘሩ ነው።
አንዳንዱ የፕሮፓጋንዳ ዘራቸው አንኳንስ ፍሬ ሊያፈራ ቀርቶ መንገድ ላይ ፈጥኖ ሲመክን ብዙ ጊዜ አስተውለናል። በተለይ ምሁራን ተብዬዎቹ “የተማሩ መሃይማን” በመርዝ የተለወሰ የመበታተን ተረት ተረት በማውራትና በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ዙሪያ የሚሳለቁትና እቅዳቸው የሚከሽፍባቸው ከዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው።
አንዳንዶች የሚዘሩትም ዘር በመርዝ የተለወሰ ቢሆንም እንኳ ከወፎች ሲሳይነት ጋር የምናመሳስለው ለከንቱ ሚዲያዎች ፍጆታ ካልሆነ በስተቀር ምንም ፋይዳ ሳይኖረው መክኖ ሲቀር ስለምንመለከት ነው። ኅሊናቸውን በእሾህ ባጠሩ በአንዳንድ ልቦች ላይ የሚወድቀው ዘርም ለጊዜው የፋፋ ቢመስልም ፈጥኖ የሚጠወልገው አንዳችም ፍሬ ሳያፈራ ነው።
በአንጻሩ ለኢትዮጵያዊ ክብርና በኢትዮጵያዊነታቸው ደምቀው ሀብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ሙሉ ኃይላቸውን በማስተባበር “ከባእድ ፊት ቆርሰው ከወገኖቻቸው ጋር የሚጎራረሱ”፣ የእጃቸውን ዘር በሕዝባቸውና በወገኖቻቸው መካከል የሚዘሩ ምርጥ ዜጎቻችን አዝመራቸው ሺህ በሺህ እንደሚቆጠርና መልካም ትሩፋታቸውም ለሀገራችን ዕድገት ከፍ ያለ ድርሻ እንዳለው በተግባር እያስተዋልን ነው።
ለቁርጥ ቀን ብቻ ሳይሆን በወትሮው ፍቅራቸውም ጭምር አካላቸው ቢርቅም መንፈሳቸውና ነፍሳቸው ከሀገራቸውና ከሕዝባቸው ጋር የተቆራኘው ብዙው ዜጎቻችን ለዕድገታችን ፍኖት አሻራቸውን እያኖሩ ሀገር ሲገነቡ፤ ጥቂት ወበከንቱዎች ደግሞ የሚያሳክር የእንክርዳድ ዘር እያመረቱ ወገን ከወገን ሲያናክሱ መዋላቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው። እነዚህ በሀገርና በሕዝብ ላይ ክህደት የፈጸሙ ጥቂት ግለሰቦች የክፉ ሃሳባቸው መዳረሻ ቅርብ መስሎ ይታያቸው እንጂ እየተራመዱ ያለው የከሰል ፍም እየረገጡ የመጓዝ ያህል አደገኛ እንደሚሆን ውለው አድረው ውጤቱን ሲያስተውሉ ይገባቸዋል።
በባእድ ምድር ተሸሽገው በጎዳና ላይ ትርዒት የሟርት ጠጠራቸውን የሚወረውሩትን ጥቂት ህሊና ቢሶች በሺህ እጥፍ የሚያስከነዱ ምላሽ ሰጭ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ስናስተውል ልባችን በሐሴት መለምለሙ፣ መንፈሳችን በደስታ መረስረሱ አልቀረም። እነዚያ ዓላማ ቢሶች በተጓዙባቸው “ኮረኮንች መንገዶች” ላይ ሳይሆን በግላጭ አደባባዮችና ጎዳናዎች ላይ በኅብረ ብሔራዊነት ደምቀው፣ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸው ጥላ ሥር ተሰባስበው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አጉልተው ለሚዘምሩ ብዙኃን የሀገር ኩራቶች ሞገስ ይሁን። የሟርተኞች ሟርት ረክሶ የአሸናፊዎች እልልታ ከፍ ብሎ መደመጡ ሁሌም እውነት ነው። “ኢትዮጵያ!” እያሉ በባእዳን ሰማይ ላይ ሀገራቸውን ከፍ በማድረግ ታሪክ ለሚሠሩ ጀግኖች አክብሮታችንና አድናቆታችን ይድረሳቸው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑር። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ)