በኢትዮጵያ የሆቴል ሎጅ ልማት ዘርፍ ሲጀመር በዘርፉ ተሰማርተው ከተሳካላቸው ጥቂትና አንጋፋ ባለሃብቶች ውስጥ አንዱ ናቸው። ከላንጋኖ ቢሻንጋሪ ቀጥሎ በቅርቡ አሥረኛው የኢትዮጵያ ክልል በሆነው የሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ የተገነባ ሁለተኛው የግል ሆቴል ሎጅ የእርሳቸው ነው። ሎጁ በቱሪስቶች ዘንድ ተመራጭ በመሆኑም በኢኮቱሪዝም ካላንደር ውስጥ ገብቶላቸዋል።
በ2011 ዓ.ም በሲዳማ ዞን በተፈጠረው አለ መረጋጋት ብዙ ዓመታትን የተሻገረው ሎጃቸው ጉዳት ቢደርስበትም፣ ተስፋ ባለመቁረጥ ከወደቀበት ቀና ለማድረግ ዛሬም እየጣሩ ይገኛሉ- የአረጋሽ ሎጅ ባለቤትና መስራች አቶ ግሪጎሪ ሚሳይሊደስ።
አቶ ግሪጎሪ ሚሳይሊደስ የተወለዱት በ1930 ዓ.ም በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለሃገር በአሁኑ አዲሱ የሲዳማ ክልል ዳሌ ወረዳ ይርጋለም ከተማ ልዩ ስሙ አናፋ በተባለ ቦታ ነው።ይርጋለም በወቅቱ የክፍለ ሀገሩ መናገሻ ነበረች። እርሳቸው ወደዚች ዓለም ሲመጡ ይርጋለም ከተቆረቆረች ስምንት ዓመቷን አስቆጥራለች። የከተማዋና የእርሳቸው እድሜም ተቀራራቢ ነው። የተወለዱባት ይርጋለም ከተማ ቤተሰቦቻቸውም የኖሩባትና በወቅቱ ብዙም የታወቀችና የተስፋፋችም አልነበረችም።
የሜካኒክነት ሙያን በልጅነታቸው የተማሩት አቶ ግሪጎሪ እስከ አምስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቢቆዩም ማቋረጥ የግድ ይሆንባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ የአባታቸው መታመምና ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መርዳት ሆኖ መገኘቱ መሆኑን ይገልጻሉ።በእዚህ የተነሳም ገና የ13 ዓመት ታዳጊ እያሉ በመካኒክነት ሙያቸው በወር ስልሳ ብር እየተከፈላቸው ለዓመታት ሰርተዋል። የራሳቸውን የቮልስ ዋግን ጋራዥ በአዲስ አበባ ከተማ አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ በመክፈት ሲሰሩም ቆይተዋል።
በባህላዊ ቤት ገጠር ውስጥ የተወለዱት አቶ ግሪጎሪ እናታቸው ኢትዮጵያዊ አባታቸው ደግሞ በ1920 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው የመጡ ግሪካዊ ናቸው። ግሪጎሪ ከእህትና ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን እናታቸው ሲዳማ ያለውን ቦታቸውን ሽጠው ወደ ከተማ እንዲገቡ ግፊት ቢያደርጉም ፣እናት ሃሳቡን ሳይቀበሉት ይቀራሉ፤ቦታው ለቱሪስት እንደሚሆን ተረድተው ልጆቻቸው አንድ ነገር እንዲሰሩበት የጠይቁ ነበር።ወቅቱ ለቱሪስት የሚሆን ሥራ ለመስራት የማይታሰብበት የደርግ ዘመነ መንግሥት ነበርና ይህ የሚታሰብ አልሆነም ።
የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ የሆቴል ቱሪዝም በሩ በትንሹም ቢሆን ተከፈተ። ግሪጎሪም ከእህትና ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን በሆቴል ሎጅ ዘርፍ መዋእለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ከውሳኔ ላይ ደረሱ። የሲዳማን የቤት አሰራር ጥበብንና ይርጋዓለምን ለዓለም ለማስተዋወቅና የእናታቸውንም ህልም እውን ለማድረግ በእናታቸው ስም የሰየሙትን ‹‹አረጋሽ›› የተሰኘውን ሆቴል ሎጅ በ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አቋቋሙ። ሎጃቸው በወቅቱ ሥራ ሲጀምር ሰባት ባናጋሎችን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ ሙሉ ሥራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ፈጅቶባቸዋል።
በጊዜው ሆቴል ሎጁን ለመስራት የሚያስፈልጉ እቃዎች ብዙም ውድ ባለመሆናቸው የሲዳማ የቤት አሰራርን ለቱሪስቶች በማስተዋወቅ ስኬታማ ለመሆን ቻሉ። ከሁሉም የዓለም ዳርቻዎች ቱሪስቶች ሎጁን መጥተው ማየትም ጀመሩ። ከመፀዳጃ ቤት ሴራሚክ ሥራዎች ውጪ የቤት አሰራሩ ባህላዊ መንገድን የተከተለ በመሆኑ፣ ወንበሮቹና አልጋዎቹም ጭምር በቀርከሃና በባህላዊ መንገድ በመሰራታቸው ወደስፍራው የሚመጡ አብዛኛዎቹ ቱሪስቶች ፍላጎትም ይህንኑ ባህላዊ አሰራር ማየት ነበር።
በሆቴል ሎጁ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ቁሳቁስም በሀገር ውስጥ ተመርተው የቀረቡ ናቸው፤ሳህኖቹን ታቦር ሴራሚክ አቅርቧል። ሹካና ቢላዎች ደግሞ በአቃቂ ብረታብረት ፋብሪካ የተሰሩ ናቸው። ብርድ ልብስና ፎጣዎችንም ደብረ ብርሃን ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፣ የአልጋ ልብሶችን የሀዋሳ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ አቅርበዋል። ዘጠና አምስት ከመቶ ያህሉ ባህላዊ እቃዎችም በሀገር ውስጥ ተሸፍነዋል።
አቶ ግሪጎሪ የሆቴል ሎጁን ከመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይርጋለም ከተማንና አካባቢውን እንዲሁም የሲዳማ ባህላዊ የቤት አሰራርን ለዓለም ለማስተዋወቅ ብዙ ደክመዋል። በዚህም ስኬታማ ለመሆን ችለዋል። የጣልያን ክልስ ከሆኑትና የአካውንቲንግ ሙያ ከነበራቸው ባለቤታቸው ጋር ትዳር መስርተውም አምስት ልጆችንና ስምንት የልጅ ልጆችን አይተዋል። የባለቤታቸው ሁለቱም ወንድሞች መሐንዲስ በመሆናቸው በሎጁ ግንባታ ወቅት ሙያዊ አስተዋጽኦ አቸውን አብርክተዋል።
በወቅቱ እንደእርሳቸው ባህላዊ ሆቴል ሎጆች በይርጋዓለምና አካባቢው ብዙም ባይኖሩም ፉራን የመሳሰሉ ጥቂት ዘመናዊ ሆቴሎች ግን ነበሩ። የገነቡት ሆቴል ሎጅ ባህላዊና ከከተማ ወጣ ብሎ ደን ውስጥ የሚገኝና የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ ሁሉ ነገር ያለው በመሆኑ የቱሪስቶችን ቀልብ ይስባል። ቱሪስቶች ወደዚህ ሥፍራ ሲመጡ ከሎጁ በስተጀርባ ከእንሰት የተለያዩ ምግቦች እንዴት እንደሚዘጋጁ የማየቱ አጋጣሚ ይፈጠርላቸዋል። የቡና ተክሎችና ከ95 በላይ ዝርያ ያላቸው ወፎች በስፍራው ስለሚገኙ እነዚህንም ለማየት ያስችላቸዋል። ድኩላን ጨምሮ ጅቦች፣ አነርና ቀበሮዎችም ስለሚገኙ በቱሪስቶች ዘንድ ይበልጥ ተመራጭ ያደርገዋል። እነዚህም ሎጁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮቱሪዝም ተመራጭ ቦታ እስከመሆንም አድርሰውታል።
ሆቴል ሎጁ ከተማዋ አጠገብ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ወደ ኮንሶ፣ አርባምንጭና ሌሎችም አቅጣጫዎች መንቀሳቀስ ለሚፈልጉ ቱሪስቶች ሁነኛ ማረፊያም ሆኖ ያገለግላል። በዚህም ሎጁ የኤኮ ቱሪዝም ካላንደር ውስጥ ገብቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ለመሆን በቅቷል።
አምስት ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩት አቶ ግሪጎሪ የተወለዱት ሲዳምኛ፣ አማርኛ፣ ግሪክኛ እንዲ ሁም ጣሊያንኛ ይናገራሉ። እን ግሊዝኛንም ይናገራሉ።
በ2011 ዓ.ም የሲዳማ ዞን የክል ልነት ጥያቄን ተከትሎ በተ ፈጠረው አለመረጋጋት ሆቴል ሎጃቸው ጥቃት ደርሶበት እስከ ወደመበት ጊዜ ድረስ 55 የሚጠጉ ሠራተኞችን ይዞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም አሥራ ስምንት ሠራተኞችን ይዞ እየተ ንቀሳቀሰ ነው።
ሎጁ ጥቃት የደረሰበት ግንባ ታው መቶ በመቶ ሳይጠናቀቅ እንደ ነበር አቶ ግሪጎሪ ተናግረው፣ ተስፋ ሳይቆርጡ ሎጁን መልሰው ለመገንባት እየሰሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ሎጁ ከኤኮ ቱሪዝም መዝገብ እንዳይሰረዝ፣ የቱሪዝም ዘርፉንም ለማበረታታት እንዲሁም የሀገሪቷን ችግርም ለመፍታት በማ ሰብ ያላቸውን ጥሪት አሟጠው በመ ውጣት ሎጁን በድጋሚ እያደሱት እንደሚገኙ ያብራራሉ።
አቶ ግሪጎሪ መንግሥትም ለውድመቱ ካሳ እሰጣለሁ ባለው መሰረት ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንድ ነገር እንደሚያደርጉ ተስፋ አድርገዋል። በሎጁ ላይ በደረሰው ጥቃት የእንግዳ መቀበያው፣ ቢሮዎቹና አንድ አዲስ ሚኒባስ መኪና የተቃጠሉ ሲሆን፣ በውስጡ የነበሩ ልዩ ልዩ እቃዎችና የቤተሰብ ቅርስ ተዘርፈዋል። በጥቅ ሉም ከሰላሳ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት አጥተዋል።
አቶ ግሪጎሪ በአሁኑ ወቅት ሎጁን ዳግም በማደስ አምስት ቤቶችን ዝግጁ አድርገዋል። ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ወጥ ቤቱና ሬስቶራንቱም እንዲዘጋጅ አድርገዋል።አንዳንድ ነገሮችን በማሟላት ለጊዜው ሎጁ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል። ከባህላዊ ምግብ ጀምሮ ሙሉ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን አንድ የሆቴል ሎጅ የሚሰጠውን አገልግሎት ይሰጣል።እስከ ተቃጠለበት ጊዜ ድረስ 26 ባንጋሎች ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ቢሮው፣ ሬስቶራንቱና መፀዳጃ ቤቱ በተለየ መልክ ተሰርተዋል። አንዱ ባንጋሎ ሁለት ክፍሎችና አራት አልጋዎች ነበሩት።
ግሪጎሪ ሎጁ በአሁኑ ወቅት ከቆመበት እየቀጠለ ያለ ቢሆንም በቀጣይ በዚሁ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ለመስራት ግን እድሜያቸው እንደማይፈቅድ ይገልጻሉ። ያም ሆኖ ግን በልጆቻቸው አማካኝነት ተጨማሪ የማስፋፊያ ሎጆችን የመስራት እቅድ አላቸው። ሎጁ የእናታቸው አደራ ጭምር ያለበት በመሆኑ ለማስቀጠል ልጆቻቸውን አስተባብረው ለመስራት ሃሳቡ አላቸው። የአገሪቷ የሰላም ሁኔታ ከተስተካከለም ከዚህም በላይ ለመስራት ውጥን ይዘዋል።
‹‹የሆቴል ሎጅ ኢንቨስትመንት ወቅታዊ ችግር የሰላም እጦት ነው›› የሚሉት አቶ ግሪጎሪ፣ የሁሉ ነገር መሰረት ሰላም ነው፤ሰላም ካለ ሥራ አለ ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት የወጣቱ መንፈስ እየተበላሸ ድንጋይ መወርወርና ዝርፊያ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፣ገንዘብ ብቻ ማግኘቱን እንጂ ሀገሬ ምን ትለኛለች እንደማይልም ያመለክታሉ። በትምህርት ቤቶች እየተከሰተ ባለ ዘረኝነት ብሄር ተኮር ግጭቶች በስፋት እንደሚታዩም ተናግረው፣ይህም የአገሪቱን ሰላም እያደፈረሰ እንደሚገኝ ያስገነዝባሉ።
አቶ ግሪጎሪ በሀገሪቱ በተከሰተ የሰላምና የፀጥታ መደፍረስ ሎጃቸው ቢጎዳም ፣ወጣቶችን በማስተማር መጥፎውን መንፈስ መውጣት እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ሌሎች ባለሃብቶችም የወደመውን ንብረት መልሶ በመገንባት ጥንካሬያቸውን ማሳየት እንዳለባቸው ይናገራሉ። የእነርሱ መሸሽ ሀገሪቷን ገደል እንደሚከታትም አስታውቀው፣ሀገሪቷ ወደፊት እንድትራመድ መርዳት እንጂ ወደኋላ ማፈግፈግ እንደማይገባም ይገልፃሉ።
ሎጃቸው ከፈረሰ በኋላ የሀገር ሽማግሌዎች መጥተው ይቅርታ እንደጠየቋቸውና የይርጋለም ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናትም እንዳበረታቷቸው አቶ ግሪጎሪ ገልፀው፤ ገንዘባቸውን በማውጣት በአሁኑ ወቅት የፈረሰውን ሎጅ ወደነበረበት ለመመለስ እየሰሩ እንደሚገኙም ይናገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም እነዚህን ሁሉ ፈተና አልፈው ስልጣን ቢይዙ ነገሮች ሊስተካከሉ እንደሚችሉም ይገምታሉ።
በሰላም እጦትና በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት እየተቀዛቀዘ የመጣውን የሆቴል ሎጅ ኢንቨስትመንት ለማነቃቃትና ወደነበረበት ለመመለስም በተለይ መንግሥት ህግን ማስከበር እንደሚገባው አቶ ግሪጎሪ ያሳስባሉ።ለፀጥታው መደፍረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ እየሆነ ያለው ወጣቱ መሆኑንም በመጥቀስ፣ቤተሰቦች ልጆቻቸውን መምከርና መገሰፅ እንደሚገባቸውም ያስገነዝባሉ። የዚች ሀገር እጣ ፈንታ በዚህ ትውልድ ላይ የተመሰረተ ነው፤ ትውልዱ ሀገሪቷን ከውድቀት የመታደግ ኃላፊነት አለበት ያሉት አቶ ግሪጎሪ፣ለዚህም እንዲነሳ ጥሪያቸውን ያስተላልፋሉ።
በኮሮና ምክንያት የቱሪዝም ዘርፉ ቀድሞውኑ ተቀዛቅዟል እንጂ ከሰሞኑ በሻሸመኔና ዝዋይ የተፈጸመው ጥቃትና ዝርፊያ ብሎም የፀጥታ መደፍረስ በቀጣይ ዘርፉን ይበልጥ እንዳያዳፍነውና የሀገሪቷን የቱሪስት ፍሰት እንዳይገለው ያሰጋል ያሉት አቶ ግሪጎሪ፣በሰላም ጉዳይ ጠንካራ ሥራዎች ሊሰሩ እንደሚገቡም ያሳስባሉ።
‹‹ገንዘቤን በሆቴል ሎጅ ኢንቨስትመንት ላይ በማፍሰስና ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት በመስጠት ተሳክቶልኛል›› የሚሉት አቶ ግሪጎሪ፣ የስኬታቸው ዋነኛ ምስጢር ባህላዊና ተፈጥሯዊ ሎጅ መገንባታቸውና እርሳቸውና ባለቤታቸው ከዛው ሳይረቁ ከምግብ ጀምሮ እስከመኝታ ድረስ ያለውን ሁኔታ የቅርብ ክትትል ሲያደርጉ በመቆየታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
በሎጁ ውስጥ የሚያርፉ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶችንም በደምብ እንደሚንከባከቧቸውና የሚፈልጉትን ሁሉ እንደሚያቀርቡላቸውና የአገሪቷ ስም እንዳይጠፋም ጥረት እንደሚያደርጉ ይህም ሎጁ በስኬት ለረጅም ዓመታት እንዲቆይ ማስቻሉንም ያብራራሉ። ለዚህም ምስክሩ ቱሪስቶች በሎጁ ትስስር ገፅ ላይ በየጊዜው የሚሰጡት ገንቢ አስተያየት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ግሪጎሪ ገለጻ፤በተመሳሳይ የሆቴልና ሎጅ ኢንቨስትመንት ፍላጎቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሌሎች የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሃብቶችም በአገሪቱ በሆቴልና ሎጅ ኢንቨስትመንት በመሳተፍና መዋእለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ስኬታማ ለመሆን ይችላሉ።ኢንቨስትመንቱ በዋናነት የሚፈልገው ሰላምና ደህንነት በመሆኑ መንግሥት ይህን ሊያረጋግጥና ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል። ወጣቶችም አንድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት የድርጊቱን ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን ይገባቸዋል፤በጥፋት ኃይሎች ተገፋፍተው ያልሆነ እርምጃ መውሰድ የለባቸውም።
እኛም አቶ ግሪጎሪ በሆቴል ሎጅ ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሳተፍ ሲዳማንና አካባቢውን ለማስተዋወቅ ሲያደርጉ የቆዩት ጥረት መልሶ እንዲያንሰራራ በፀጥታ መደፍረስ የወደመውን ሎጃቸውን ዳግም ለመገንባት በሚያደርጉት ሂደት ሁሉ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ አይለያቸው እንላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012
አስናቀ ፀጋዬ