የግብርናው ዘርፍ ለኢንዱስትሪው ልማት ሽግግር እንዲያበረክት የሚጠበቅበትን ጉልህ ሚና ለማሳካት የቴክኖሎጂ ልማትና የአጠቃቀም አቅምን በፍጥነትና ቀጣይነት ባለው አኳኋን መገንባት እጅግ ወሳኝ ይሆናል፡፡ በ2007 ዓ.ም የወጣው የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ እንዳሰፈረው ባደጉና በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ባዮቴክኖሎጂን የግብርናው ልማት ወሳኝ አጋዥ አድርገው በመገንባታቸው በእጅጉ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
ይህም የሀገራችን የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ልማት ዋናው ትኩረቱ መሆን ያለበት በአገር ደረጃ ያለውን የግብርና ምርምርና ልማት እንቅስቃሴ በባዮቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ውጤታማነቱን በማሳደግና ለሚፈለገው ሽግግርና የኢንዱስትሪው ልማት አጋዥ በማድረግ መሆን እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ልማት እድገት የማያቋርጥ የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና እድገትን ይጠይቃል፡፡
የሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየውም ለግብርናው ዘርፍ ፈጣን እድገት ምክንያት የምርምር አጀንዳዎችን ለይተው ባዮቴክኖሎጂ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ፣ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ፈጥነው በመገንባትና ውጤታማ ቴክኖሎጂዎችን በተሻለ አቅም፣ ፍጥነትና ጥራት አውጥተው በመጠቀም ወደምርት እየለወጡ በፍጥነት ለመራመድ መቻላቸው ነው፡፡ የጥንካሬያቸው መገለጫ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ በዘርፉ ያለውን የቴክኖሎጂና የሳይንስ እውቀት አቅም አጠናክረው በመግፋታቸው ለቀጣይ ዘመን ብቁና አስተማማኝ መሠረት ላይ ሊገኙ መብቃታቸው ነው፡፡
ባዮቴክኖሎጂ ምንድን ነው
ባዮቴክኖሎጂ ሲባል ሕይወት ያላቸው አካላት ወይም ሥነ ሕይወታዊ ሥርዓቶቻቸው ያሉበትን፣ ለውጦቻቸውን ዑደታውን፣ እጅግ ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ መሠረታዊ መረጃ በማውጣና በመተንተን ራቸው ብዝሃ ህይወትን ወይም ውጤቶቻቸውን ወደሚፈለገው ምርታማነት ወይም የጥራት ደረጃ በማጣት ለላቀ ጥቅም እንዲውሉ የሚያስችል የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡
የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ጥልቀት ያለው የሥነ ሕይወት ሳይንስ መሠረታዊ ትንታኔ ላይ የተመረኮዘ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የመረጃ መገኛና መተንተኛ መሳሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም የሰብልና የእንስሳት እንዲሁም ማይክሮብስ የዝርያ፣ የውርስ ሂደት ወይም መስተጋብር በዘረመልና የፕሮቲን ደረጃ ባሉ መረጃዎች በመተንተን ምርምርን ወደ ውጤት ለማድረስና ልማትን ለማፋጠን የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
ባዮቴክኖሎጂ ጥቅሙ
የሥነ ሕይወት ዑደትና ተያያዥ ባዮሎጂካል ክስተቶች ግንዛቤን በማላቅ ለመቆጣጠርና ለታለመለት ዓላማ አመቻችቶ ለመጠቀም ይረዳል፡፡ ይህ የተቻለው የባዮቴክኖሎጂ አሰራሮች የሰብሎችን፣ እንስሳትንና የማይክሮብስን ጥልቅ የተፈጥሮ ይዘት ገላጭ የሆነውንና ዝርዝር የዘር ውርስ ሂደት ውስጥ ወሳኝና ቀዳሚ ሚና የሚጫወተውን የዘረመልና የፕሮቲን ኮድ በመተንተን እንዲሁም ተያያዥ ውስብስብ ዑደቶቻቸውንና ውጤቶቻቸውን በመለየትና በመተንተን ተፈጥሮን በላቀ ሁኔታ ለመገንዘብና ለሰው ልጅ ጥቅም ለማዋል በማስቻሉ ነው፡፡
ስለዚህ ባዮቴክኖሎጂ የልማዳዊ አሰራር ውጤት ለማግኘት አስቸጋሪ ወይም አድካሚ የሆኑና ረጅም ጊዜ የሚጠይቁትን የምርምር ሂደቶች ለምሳሌ ዝርያ የማሻሻል፣ አዳዲስ ምርት የማዘጋጀት፣ የዝርያ ዓይነቶችን የመለየት፣ ጥራቱን የጠበቀ ዘር የማባዛትና ሌሎችንም ሂደቶች ለማከናወንና የሚወስዱትን ጊዜ ለማሳጠር የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሳይንሳዊና መሠረታዊ መረጃ ያዘጋጃል፤ ምርታማነትና የጥራት ደረጃን ለማሳደግ ከፍ ያለ አቅም ይፈጥራል፡፡
ይህም አቅም ያለማቋረጥ እያደገ የተፅዕኖ አድማሱ እየሰፋና እየጠለቀ ያለ በመሆኑ አሁንም ሆነ ወደፊት በግብርናው ዘርፍ ለሚፈለገው ፈጣን ዕድገት የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ የባዮቴክሎጂ በርካታ ቴክኒኮች አሁንም ከፍተኛ የልህቀት ደረጃ ላይ ያሉና ወደፊትም ውስብስብነታቸው እየጨመረ የሚሄድ ሳይንሱ የሚጠበብባቸው፣ አላቂ በሆነ የፎሲል ተፈጥሮ ላይ የሚኖር ጥገኝነትን በማስወገድ የብዝሃ ሕይወት ሀብትን የማይነጥፍ የሀብት ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ወሳኝ የሆኑ የቀጣዩ ዘመን ቴክኖሎጂዎችን የያዘ ነው ተብሎ እንደሚታመንም በግብርና ባዮቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ ረቂቅ ሰነድ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በሀገሪቱ በዋነኛነትና በቀዳሚነት የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምርን እያካሄደ የሚገኝ ሲሆን ባለፈው ሳምንት እትማችን የኢንስቲትዩቱ የግብርና ባዮቴክሎጂ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ ዳባ በምርምር ማዕከሉ እየተካሄዱ የሚገኙ ምርምሮች ውጤታማት አስመልክተው እንዳብራሩት የግብርና ምርምር ሥራ ውጤት ተገኘ የሚባለው አርሶ አደሩ ወይም ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ያስረዳሉ፡፡ በተቋሙ የሚሰሩ የምርምር ሥራዎች ግብ ቤተ ሙከራ ውስጥ ብቻ ተወስነው እንዲቀሩ ሳይሆን ተጠቃሚው ጋር እንዲደርሱና ለሌሎችም ተመራማሪዎች ግብዓት እንዲሆኑ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ዶክተር ታደሰ እንዳሉት በተቋሙ በርካታ በመንግሥት የሚታገዙና ከውጭ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሚሰሩ ትላልቅ የምርምር ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን ውጤታማ የሆኑ የእጽዋት ዝርያን የማሻሻል ሥራዎች በብዛት ተሠርተዋል፤ የተጀመሩ በጎ ሥራዎችም አሉ ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ታደሰ ገለጻ ባዮቴክኖሎጂ እንደ ሌላው የግብርና ምርምር ሥራ በመጠነኛ አቅም የሚሰራ ሳይሆን፣ በጣም ከፍተኛና እምቅ የካፒታል አቅም የሚጠይቅ ነው፡፡ በጣም ውድ የሆነ የላብራቶሪ መሠረተ ልማት፣ የማይቋረጥ የመብራት ኃይልና የሰው ኃይልን ይፈልጋል፡፡ እስካሁን ድረስ በአብዛኛው እነዚህን መሠረቶች የመገንባት ሥራ ነው የተከናወነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከ62 በላይ የሚሆኑ የእጽዋት ዝርያዎች “በቲሹ ካልቸር” ማባዛት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ተሠርተዋል፤ ከእነዚህ ውስጥም የተወሰኑት ተጠቃሚ ዘንድ መድረስ ችለዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚገኘው የትግራይ ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል ትልቁ የቲሹ ካልቸር ላብራቶሪ የሚገኝበት ሲሆን፣ ማዕከሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከኢንስቲትዩቱ ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል የወጡ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን እያባዛ ለተጠቃሚ እንደሚያደርስም ዶክተር ታደሰ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የኢንስቲትዩቱ ባዮቴክኖሎጂ ማዕከል፣ ለአርሶ አደሩ በርካታ የቡና፣ ዝንጅብል፣ አናናስ፣ አፕል፣ ድንች ስኳርና ድንች የመሳሰሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዝርያዎችን በብዛት አባዝቶ እያደረሰ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ዝንጅብል በበሽታ የሚጠቃ ግን በጣም ተፈላጊ የሆነ ሰብል ሲሆን፣ ከበሽታ የጸዳ ዝርያ በብዛት ተባዝቶ ለብዙ አርሶ አደሮች እንዲደርስ ሆኗል፡፡ በሌሎችም በርካታ ሰብሎች በሚፈለገው ደረጃም ባይሆን ያሉትን አስቻይ ሁኔታዎች በመጠቀም ውጤታማ ሥራዎችም እንደተከናወኑ ዶክተር ታደሰ ገልጸዋል፡፡
ባዮቴክኖሎጂ አጠቃቀም
የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ እውቀትን ብቻ ሳይሆን ፍላጎትና ክህሎትን፣ የተሟላ ላብራቶሪና የኬሚካል አቅርቦትን እንዲሁም የማይቆራረጥ የመብራት ሃይልን በእጅጉ የሚፈልግ የሙያ ዘርፍ እንደሆነ ዶክተር ታደሰ ይናገራሉ፤ አያይዘውም ዘርፉ ጥንቃቄን የሚፈልግ ጥቃቅን ስህተቶችን ማስተናገድ የማይችልና የሚፈጠሩ ስህተቶች ውጤታማነትን በእጅጉ እንደሚጎዳ በመጠቆም በተለይም የመብራት መቆራረጥና በአፋጣኝ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችን ለማግኘት የሚፈጀው ረጅም ጊዜ ዘርፉን ወደኋላ እየጎተተው እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
ተቋሙ የሚገዛቸው ጀነሬተሮች ረጅም ሰዓት በሥራ ላይ የሚቆዩ ከመሆናቸው የተነሳ ቶሎ ቶሎ እንደሚበላሹ የጠቆሙት ዶክተር ታደሰ የምርምር ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ካስፈለገ በተለይም ከመብራትና ከኬሚካል አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት አጽንዖት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ችግሮቹን መፍታት ከተቻለም ተቋሙ ግብርናውን የሚያዘምኑ በርካታ ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሀገራችን በሰብል፣ እንስሳትና የተፈጥሮ ሀብት ዙሪያ ምርታማነትና ጥራት እንዲሁም አጠቃላይ አጠቃቀማችን መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከእነዚህ በመልማት ላይ ካሉ ሀገራት አጠቃቀም ጋር ሲነጻጸር ገና ብዙ መሥራት የሚጠበቅብን ደረጃ ላይ ነን፡፡ ከግብርና የሚገኙ ውጤቶችን በሚፈለገው ብዛትና የጥሬ ዕቃ ጥራት ለኢንዱስትሪዎች ሊቀርቡ አለመቻልና ጥሬ እቃዎች ከውጭ ማስገባት፣ የጥራት ደረጃውን የጠበቀና ተከታታይነት ያለው በቂ ምርት ውጪ ላለው የተመቻቸ ገበያ የማቅረብ ችግር በሰፊው የሚታይ ሲሆን ለዚህ የቴክኖሎጂ አቅርቦትና በልማት ዙሪያ ያለውን አጠቃቀም በእጅጉ ማሻሻልና ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚከሰት የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በርካታ የልማት ማነቆዎች መፍትሄ ለመስጠት በቀጣይነት የምግብ ዋስትናን ያረጋገጠ፣ በዓለም ገበያ ተመራጭ የሆነ የግብርናና የአግሮ ኢንዱስትሪ ምርት ማቅረብ ፈታኝ ቢሆንም እንደባዮቴክኖሎጂ የተሻሻሉና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምርምርና የልማትን አሰራር በተጠናከረና በአስተማማኝ ደረጃ በማጠናከር ተወዳዳሪ አቅም ገንብቶ ከውጭ ጥገኝነት መላቀቅ ይቻላል፡፡
ባዮቴክኖሎጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በምግብ አቅርቦት በፋብሪካ ምርት፣ ለገበያ በሚሆን ምርትና በሌሎችም እጅግ ከፍተኛና ፈጣን ውጤት እየተመዘገገበበት ያለ መስክ ነው፡፡ ስለሆነም ዘርፉ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን እጅግ መሠረታዊና ወሳኝ የልማት ምሰሶ ሆኖ ሊቀመጥ የሚገባው ነው፡፡ ያደጉ ሀገራትም ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመጪዎቹን ዘመናት የቴክኖሎጂ አቅርቦት ከአሁኑ በመድረስ ነገንም ከመቆጣጠር ባለፈ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ያለን እምቅ የሥነ ሕይወታዊ ሀብትና ሥነ ምህዳራዊ ጸጋን በአግባቡ በማወቅ በላቀና በተፋጠነ ሁኔታ ለግብርናው ልማት ለመጠቀም ባዮቴክኖሎጂን ዋና የሂደቱ ቁልፍ አካል ማድረግ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው፡፡
የሌሎችን ሀገሮች ባዮቴክኖሎጂ አጠቃቀም በዋናነት ዓላማ ያደረገው ይህንኑ ሲሆን፣ እንደ ብራዚል፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና ያሉት ወደዚህ መደምደሚያ ደርሰው ባዮቴክኖሎጂን አማራጭ የሌለው የአሁኑና የበለጠም የመጪው ዘመን መፍትሔ እንደሆነ ወስነው እርምጃ ወስደዋል፡፡ ሀገራችን በመስኩ ወደ ኋላ መቅረቷ ቁጭት የሚፈጥር ቢሆንም ለተያያዝነው ፈጣን የግብርና ልማት እመርታ ሊያመጡ የሚችሉና ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ውጤቶችን፤ ቴክኖሎጂዎችን ወይም የአሰራር ስልቶች ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ወደ ትግበራ ውስጥ ፈጥኖ በመግባት ከቴክኖሎጂው በመጠቀም ከዘርፉ ከፍተኛ ተጠቃሚ ልንሆን የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ ጥራቱን የጠበቀ በቂ ምርት ከተመቻቸ ሰፊ የውጭ ገበያ መኖር መልካም ዕድል ጋር በአንድ ላይ ሲታይ የባዮቴክኖሎጂ አቅምን ቶሎ ማጠናከር ለታቀደው የኢኮኖሚ ሽግግር አቅም ብቻ ሳይሆን ምናልባትም አማራጭ የሌለው ሊሆን ይገባል፡፡
ዘላቂ አገራዊ ግብርና የባዮቴክኖሎጂ አቅም ለማፍራት አንድ ጊዜ ቴክኖሎጂውን ገዝቶ ለምርት በማዋል ብቻ የሚሳካ ሳይሆን ቴክኖሎጂውን ገዝቶ ከመጠቀም ቀጥሎ በቅድሚያ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ በማድረግና በማላማድ ብሎም በማሻሻል በቀጣይነት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማፍራት የሚችል ዘላቂ የውስጥ አቅም በመፍጠር የሚደረስበት ነው፡፡ አሁን የዘርፉ የባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ እያስመዘገበ ያለው ፈጣን ለውጥና ቴክኖሎጂው እየፈጠራቸው ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ልማት ለማዘመንና ለማፋጠን ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ልማት ውስጥ ብትገባ እንደ ትልቅ አቅም ሆኖ ሊያስቀጥላት የሚችልና በዘርፉ ተፎካካሪ ሊያደርጋት የሚችል ነው፡፡ ያለን የሀገር ውስጥ ገበያ መጠንና የውጭ ንግድ አቅም እየጨመረ ነው፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር በፍጥነት እየተራመደ ያለ ኢኮኖሚ እየተገነባ መጥቷል፡፡ በወሳኝ ሰብሎችና የግብርና ውጤቶች ያለውን የምርታማነት ዝቅተኝነት በማሳደግ ብቻ እንኳን ሊፈጠር የሚችለው ለውጥ የሚያስከትለው ተጨማሪ የእድገት ግፊት በሴክተሩ ብቻ የተገደበ እንደማይሆን ከዚህ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከግብርና ባዮቴክኖሎጂ በሚገኘው ጥቅም በርካታ የሀገራችንን ሕብረተሰብ የማሳተፍ እድል አለው፡፡ ስለዚህ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ፈጣን እድገት ለኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ሊያግዝ የሚችል ነው፡፡
አዲስ ዘመን ሐመሌ 20/2020
አብርሃም ተወልደ