የምትጠባ ጥጃ አትጮህም ።ይህ የአባቶቻችን ብሂል እውነት ነው ።ማግኘት ያለባትን ለማግኘት ስራ ላይ ስለሆነች።ይህን ወደ ሰውኛ ስናመጣው የሚሰራ እና በስራውም ውጤታማ የሆነ ማንም አካል እዩኝ እዩኝ አይልም። ምክንያቱም ሰውየው ከሚናገረው በላይ ስራው ምስክር ስለሚሆን እና ከስራውም ተጠቃሚ ስለሚሆን ለወሬ ብሎም እዩኝ እዩኝ ለማለት ጊዜ አይኖረውምና ነው።ሰሞኑን የዓባይን የውሃ ሙሌት ሂደት ስንመለከት የምትጠባ ጥጃ አትጮህም አይነት ነው።ብዙ ሰው የውሃ ሙሌት ሂደቱን በቅጡ ባልሰማበት እና ብዙ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሃገር በሚያተረማምሱበት እና በሚራኮቱበት ወቅት መንግስት የተሰጠውን ኃላፊነት እና የገባውን ቃል በዚህ መልኩ የመጀመሪያ ዙር የሙሌት ሂደት ማጠናቀቁን የብስራት ዜና ስንሰማ መንግስት በተግባር በስራ ላይ ተጠምዶ መሰንበቱን ለመረዳት ብዙ ማሰብን አይሻም።
አንዳንድ ተፎካካሪ ፖለቲከኞቻችን መንግስትን በፖለቲካል መርሆ ከመፎካከር አልፈው ሃገር በማተራመስ ሂደት ላይ በተጠመዱበት ፤ የኮሮና ወረርሽኝ ሃገር እየፈተነ ባለበት ፤ የበረሃ አንበጣ ኢትዮጵያን በብዙ ስፍራዎቿ በወረረበት ሰዓት፤ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ ዓለም አቀፋዊ ጫና እያደረገች ባለችበት ሰዓት እንደዚህ አይነት የምስራች በመስማት ደስታን ገላጭ ቋንቋ ለማግኘት ያዳግታል ።
መንግስት እና ኢትዮጵያን የወከሉ ተደራዳሪዎች በድርድሩ ሂደት ያሳዩት እልህ አስጨራሽ ድርድር የሃገር ፍቅር የሚለውን ረቂቅ ምስጢር ዓባይን በተግባር በመገደብ ለህዝብ ግልፅ በሆነ መልኩ ያስረዱበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ታሪክም ሲዘክረው የሚኖር በደማቅ ቀለም የተፃፈ የታሪክ አሻራ ነው።ኢትዮጵያን የወከሉ ተደራዳሪዎችም በአንድ ሃገር የዜጎች መፃዒ እድል ላይ ለመወሰን የተሰየሙ መሆናቸውን በውል የተረዱ በአጠቃለይ በቅርፅም ሆነ በይዘት ሃገራዊ ባህሪይ የተላበሱ ተደራዳሪዎች መሆናቸውን በግልፅ ማየት የተቻለበት የታሪክ አጋጣሚ ነው።በመሆኑም መንግስት እና ኢትዮጵያን የወከሉ ተደራዳሪዎች ያልሆነ የሆነውን ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና ያልሆነ ተስፋ መስጠትን በፕሮፓጋንዳ ለተጠመዱ አካላት ወደ ጎን በመተው ሃገራቸው ያቀደችውን በተግባር ለማሳየት ሲሰሩ ስለመቆየታቸው የዓባይ የውሃ ሙሌት ጥሩ ማሳያ ነው።ለዚያም ነው የጽሁፌን ርዕስ የሰራተኛ አካላትን ባህሪ ለመግለፅ የምትጠባ ጥጃ አትጮህም ማለቴ።
በሌላ በኩል አንዳንድ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለኢትዮጵያ ህዝቦች ስርአተ ማህበር ፣ ታሪክ ወዘተ ያላቸው ግንዛቤ ማነስና ስለህብረተሰብ እድገት እና የታሪክ ህግጋት ያላቸው አመለካከት በጎጥ ውስጥ በመቀርቀር ሆነ ብለው ለፖለቲካ ቁማራቸው የህዳሴ ግድብ ስራን በማስያዝ ሲቆምሩ እያየን ነው ።እነኝህ አካላት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሆነ ያልሆነውን ፕሮፓጋንዳ በመንዛትና ህዝብን በማሸበር እና እርስ በእርስ ብሎም ከመንግስት ጋር በጥርጥሬ እንዲተያይ በማድረግ እና ለግብፅ ተላላኪ እስከ መምሰል የደረሱ በወሬ ሃገር መገንባት የሚቻል የሚመስላቸው ናቸው።
ለእነኝህ ፖለቲከኞቻችን የፖለቲካ ልዩነታቸውን በህዳሴው ግድብ ላይ በክፋት መርዝ (poisonous evil) ለመሞሸር መሞከራቸው በህግም፣ በሞራልም፣ በታሪክ ተጠያቂ ስለሚያደርግ እና አሁን የተፈጠረውን የአንድነት ስሜት ስለሚንድ ለምትሰሩት ስራ ዘጠኝ ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ የሚለውን አባባል በአፅንኦት ልትመለከቱት ይገባል እላለሁ።
አፍላ ዕድሜ ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞን ለመቀልበስ ወይም ለማሰናከል የሚራኮቱ ሃይላት የኢትዮጵያን ህዝቦች አንድነት የሚጠሉና የኢትዮጵያን በህዳሴ ግድብ የመጠቀም እና የሌሎች ፕሮጀክቶች የወደ ፊት እጣ ፋንታ በአጋም እሾክ ውስጥ የሚተክሉ፤ የህዝቡን ጥቅም የረሱ፤ የራሳቸውን ጥቅም ያስቀደሙ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ ከገደል አፋፍ እንደተቀለሰች የጎጆ ነዋሪዎች በስጋት አረንቋ ውስጥ የዘፈቁ መሆናቸው ለአፍታም የሚያጠራጥር አይደለም። አንድ እና መተኪያ የሌላት ኢትዮጵያን በችግር በመደንገር ፤በተንኮል በመተብተብ ለማፍረስ መሮጥ እና ራስን እንደ ነፃ አውጭ መቁጠር ምን አይነት ነፃ አውጭነት ነው? እዚህ ላይ እንድ ነገር መገንዘብ ያስፈልጋል። የለውጥ ጋሬጣዎች ስንል የተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማለት አይደለም። ለፖለቲካ ጥቅማቸው ሲሉ ለሃገር ምንድግና ጠንቅ የሆኑትን አንዳንድ አካላት ለመግለፅ እንጂ።
ሀገራዊ ለውጡ የመጣባቸው እንዳለ ሁሉ የመጣላቸውም እልፍ አላፍ ናቸው። ለውጡ ከመጣላቸው አንዱ የህዳሴው ግድብ ነው። በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እንደሚታወቀው እና ሁሌ እንደሚባለው በማህፀን ውስጥ ካለ ፅንስ እና በመቃብር ውስጥ ካሉ ሙታን በስተቀር ሁሉም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በመተባበር ለግድቡ መጠናቀቅ በቃላት ብቻ ሊገለጹ የማይችሉ ገድሎችን ፈፅመዋል፤ እየፈፀሙም ነው።ይሁን እንጂ የግድቡን ሂደት በበላይነት ሲመሩ በነበሩት ከለውጡ በፊት በነበሩ አመራሮች እንደ ጣና በለስ፤ ኦሞ ኩራዝ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች የህዳሴውም ግድብ በዳዋ ሊበላ ተቃርቦ እንደነበር ሊዘነጋ አይገባም።ነገር ግን የለውጡ መንግስት ለፕሮጀክቱ እንክሮ በመስጠት አሁን ለደረስንበት የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት መድረስ ችለናል።ለዚያም ነው እንደ ሃገር ለውጡ ከመጣላቸው አንዱ የህዳሴው ግድብ ነው መባሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር እንዲሉ ከለውጡ በፊት ያሉ አመራሮች ራሳቸው ስንት ፕሮጀክቶችን በመሰረት ድንጋይ ብቻ እንዳላስቀሩ፤ የህዳሴው ግድብ ከጊዜ እስከ ገንዘብ (ግድቡ በጊዜው ቢያልቅ የምናገኘው ገንዘብ) ያለምንም ርህራሄ ዶጋ አመድ እንዳላደረጉ፤ እነጣና በለስንና ኦሞ ኩራዝን ሲያጓትቱ እንዳልነበር፤ ስንት መንገድ እና ድልድይ ከጥራት ችግር በመነጨ ለምርቃት ሳይደርስ በጎርፍ እንዳልተወሰደ ሁሉ፤ አሁን የለውጡ መንግስት የህዳሴውን ግድብ ሸጠው እያሉ በእርጅና ቅዥት መንከባለል እና ሃገርን ለትርምስ ያለ የሌለ ሃይልን መጠቀም ምን የሚሉት ነው? ሃገርን ለማተራመስ ያለ የሌለ ሃይልን የተጠቀማችሁትን ያህል ለሃገር ግንባታ ብትጠቀሙት ኢትዮጵያን ባስመነደጋችሁ እና ለታሪካችሁም ለትውልድም የሚነገር አንድ ቁም ነገር በሰራችሁ።
በመጨረሻም የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ዓላማን አንግቦ ለሚጠበቅበት ታሪካዊ ግዴታ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ በማስቻል የኢትዮጵያን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዕድገት መነሻ ንድፍ ለመንደፍ ብሎም ድህነትን እስከ መጨረሻው ደፍጥጠን ለማለፍ የሚያስችል መስፈንጠሪያ የሚሆን ልዩ አጋጣሚ ነው።ስለሆነም ጠንካራ ኢትዮጵያን መፍጠር የሚቻለው ተዋዶ ፣ ተከባብሮ ፣ ተደጋግፎ በመቆም ነው። በሃገረ መንግስት ግንባታ የሚያስፈልገው ቁልፉ ነገር አንድ የሚያደርገንን ሚስጥር ማግኘት እና ያን የአንድነት ቁልፍ በጋራ ተንከባክቦ መያዝ ነው።ለዚህም ሃገርን አንድ ሊያደርግ የህዳሴው ግድብ ትልቅ ዕድል ሆኖ በፊታችን ቆሟል።ስለሆነም ግድባችን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይጠናቀቅ ዘንድ ሁላችንም እጅ ለእጅ በመያያዝ እንተባበር።ልክ እንደ አባቶቻችን አኩሪ ገድል እንፈፅም መልዕክቴ ነው።ሰላም!!!
አዲስ ዘመን ሐመሌ 20/2020
በአሸብር ሃይሉ