
– በግኝት የታዩ ክፍተቶች ለማረም እንደሚሠራ ባለሥልጣኑ ገልጿል
አዲስ አበባ፡- የግብርና ባለሥልጣን በተደረገው የክውን ኦዲት ግኝት የታየበትን ሕጎችን የመተግበር ክፍተት እንዲያርም የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ቄራዎች አደረጃጀት እና የስጋ ምርት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነት በተመለከተ በተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ትናንት ውይይት አድርጓል።
የሚገነቡ ቄራዎችን የግንባታ ቦታ መረጣው መስፈርቱን ያሟላ መሆኑ ለማረጋገጥ በተደረገ ሙከራ ማንኛውም ቄራ ሲገነባ ከመኖሪያ አካባቢ ቢያንስ 500 ሜትር መራቅ፣ የተለያየ ብናኝ፣ ሽታና ጭስ ከሚያወጡ ኢንዱስትሪዎች ቢያንስ አንድ ኪሎ ሜትር መራቅ እና ቢያንስ በ5 ሄክታር መሬት ላይ መገንባት ያለበት እንደሆነ ቢገለጽም በተግባር ግን ይህን ያሟላ እንዳልሆነ በኦዲት ግኝቱ ሪፖርት ተጠቁሟል።
በኦዲቱ በናሙና ከታዩት አምስት ኤክስፖርት ቄራዎች ይህንን አሟልተው እየሠሩ ባለመሆኑ የምግብ ደህንነት የማስጠበቅ ችግር ያለባቸው መሆኑ ተገልጿል።
የሚገነቡ ቄራዎችን መዝግቦ እውቅና ከመስጠቱ በፊት የግንባታ ቦታ መረጣው መስፈርቱን ያሟላ ስለመሆኑ፣ ከሳይት ፕላን አንፃር የቆዩትን ኤክስፖርት ቄራዎች ወቅታዊ ማድረግ እና አዲስ የተገነቡትም በሳይት ፕላኑ መሠረት ከማስተናገድ አንፃር ችግር መኖሩን ግኝቱ አመላክቶ፤ ይህም የአካባቢና ማሕበረሰብ ተጽዕኖ ግምገማ ጥናት ቀርቦ በሚመለከተው አካል የጸደቀና የተረጋገጠ ስለመሆኑ መረጃ ያልቀረበ መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ታይቷል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ቤቱ የስጋ ምርት አገልግሎት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያሉትን ችግሮች በጥናት በመለየትና ችግሮቹ እንዲቀረፉ ከሚመለከተው አካል ጋር በቅንጅት አለመሠራቱም በሪፖርቱ ቀርቧል።
በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የእንስሳት ጤናና ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ ስለ እንስሳት ልየታና ክትትል ሥርዓት የሚገልጽ ድንጋጌ የተቀመጠ ቢሆንም፤ ረቂቅ አዋጁ ከተዘጋጀበት ሰኔ 2009 ዓ.ም ኦዲቱ እስከ ተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በሚመለከተው አካል እንዲፀድቅ ክትትል ባለመደረጉ ምክንያት እስከአሁን በአግባቡ ወደ ሥራ አለመገባቱ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ ሀገር የምትመራው በሕግ እና ሥርዓት መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለሥልጣን መሥሪያቱ የተገኙበትን ክፍተቶች እንዲያርም አሳስበዋል። ሕጎችን እና መስፈርቶችን የማያሟሉ ቄራዎች ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከተቋማት ጋር በመናበብ እንደሀገር የታቀዱ ግቦችን ለማሳካት እና ሀገር የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እንዲሠሩም ምክትል ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።
ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ምላሽ እና ማብራርያ የሰጡት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በግኝቶቹ የተገኙ ክፍተቶች ወደ ውጭ የሚገፉ አይደሉም። ሁሉንም ክፍተቶች ወስደን እናርማለን ብለዋል።
ከቆሻሻ አወጋገድ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክፍተቶችን እንደሚያርሙ እና በመስፈርቱ መሠረት ፈቃድ የመስጠት አካሄዶች ላይ የተነሱ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ተቋሙ ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመግባቱ በቀጣይ ለውጦች እንደሚመጡ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደምም መሥሪያ ቤቱ የአዋጅ ክፍተት የነበረበት መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ አሁን አዋጁ በመጽደቁ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ተቋሙ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለመወዳደር እና መስፈርቶችን አሟልቶ ለመገኘትም በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በግኝቱ የቀረቡ ክፍቶችንም ለማረም ከክልሎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሠራ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮን እየወሰዱ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ ፤ ከላብራቶሪ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ፈትተናል፤ በአክሪዲቴሽንም ማረጋገጫ አግኝተናል ብለዋል።
በመክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም