የውጭ ዜጎች የቋሚ ንብረት ባለቤት የሚያደርገው ረቂቅ አዋጅ አንድምታ

ዜና ትንታኔ

የሚንስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 44ኛ መደበኛ ስብሰባው የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም ባለይዞታ የሚሆኑበትን አግባብ ለመደንገግ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል። ይህም የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ ለውጭ ዜጎች ሕጋዊ አሠራር መዘርጋቱ የውጭ ካፒታል በሀገራችን ሥራ ላይ እንዲያውሉ ማበረታታትን ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተመላክቷል።

በተጨማሪም የቤት ልማት እና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማነቃቃት፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ የተጠቆመ ሲሆን፣ ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ታምኖበት ረቂቅ አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል። ለመሆኑ ይህ ረቂቅ አዋጅ እንደ ሀገር ምን አንድምታ ይኖረዋል በሚለው ላይ የዘርፉን ምሁራን ጠይቀናል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)፤ በነበረው ክልከላ ምክንያት በአፍሪካ ሕህብረትና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት እየሠሩ ረጅም ዓመት በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ቤት እንዳይኖራቸው አድርጎ ቆይቷል። እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ያላቸው ሀገራዊ አበርክቶ ከፍ ያለ ቢሆንም መሬትን ጨምሮ ቋሚ ንብረት የሚያፈሩበት እድል አልነበረም። በመሆኑም ረቂቅ አዋጁ ቢጸድቅ እንደሀገር አትራፊ እንሆናለን ይላሉ።

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፤ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ንብረት ማፍራት መፈቀድ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ካፒታል ይጨምራል። ይህን ተከትሎም የሚሰበሰበውን ሀገራዊ ገቢም ያሳድጋል። ይሁን እንጂ አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪ ሆነው ይወጣሉ ወይ የሚለው ላይ ስጋት እንዳላቸው ያነሳሉ።

ረቂቅ አዋጁ አንድ የኢትዮጵያ አርሶ አደርና አንድ የቻይና ባለሀብት እኩል ሀብት ማፍራት የሚችሉበትን መብት የሚሰጥ ነው የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ይህን ሁኔታ መቋቋም የሚያስችል አቅም ፈጥረናል ብለው እንደማያምኑ ይጠቅሳሉ።

ስለሆም አዋጁን ጥቂት አዘግይተነው የሀገሪቱን ሰላም ጸጥታ በማረጋገጥ ምርትና አገልግሎት በነጻነት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ላይ ብንሠራ ይሻላል ይላሉ።

ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገራት ሄደው ሲኖሩ ቤትም ሆነ የትኛውንም አይነት ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ የሚጠቅሱት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ይህን ሁኔታ ሌሎች ኢትዮጵያ መጥተው ሲኖሩ ግን ይህ እድል አልነበራቸውም። ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ወደ ተግበራ ከገባ የኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በሙሉ ልብ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል እድል መሆን ያብራራሉ።

አሁን ላይ በሪል ስቴት ዘርፉ የውጭ ዜጎች እንዲሳተፉ መፈቀዱን አስታውሰው፤ ሌሎችም የማይንቀሳቀስ ሀብት ላይ ማፍራት መቻላቸው ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ማሳያ ሊሆን የሚችል እንደሆነ ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤት ባለቤት ለመሆን አዳጋች ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ከውጭ ሀገር ዜጎች የሚገኘው ተጨማሪ ካፒታል የሚፈጥረውን አቅም በመጠቀም የቤት ችግርን መቅረፍ የሚቻልበት እድል እንደሚፈጥርም ያራብራራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጨምረው ያስረዳሉ።

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፤ ይህን አዋጅ ወደ ሥራ ከማስገባታችን በፊት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ። ሊደረጉ ከሚገባው ዝግጅቶች አንዱ እያንዳንዱ ዜጋ እጁ ላይ ያለውን ክህሎትና እውቀት ወደ ሀብት መቀየር የሚችልበትን ሁኔታ መፈለግ ይጠበቅበታል የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ባንኮችም ሃሳብን እንደማስያዣ ተጠቅመው ገንዘብ ማበደርና ዜጎች ሃሳባቸውን ወደ ምርትና አገልግሎት የሚለውጡበትን እድል መደገፍ ይኖርባቸዋል ይላሉ።

በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት መዋቅርም የዜጎች ጥረት ማገዝ እንዳለበት የሚገልጹት ተንታኙ፤ አገልግሎት ላይ ብቻ ሳይሆን አምራችነት ላይም ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። የሥራ ባህላችንን በማሳደግም በቀን ረዘም ያለ ሰዓት ሥራ ላይ ማሳለፍን መለማመድ ይጠበቅብናል። ይህም ጠንካራ ሀገራዊ አቅም በመገንባት ኢኮኖሚው በውጭ ኃይሎች እንዳይዋጥ አቅም እንደሚፈጠር ያብራራሉ።

እንደ ምሁራኑ ገለጻ፤ የውጭ ዜጎች የማይንቀሳቀስ ሀብት እንዲያፈሩ ቢፈቀድ ካፒታልን በመጨመር ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠርና ገቢን ለመጨመር ያስችላል። ይሁን እንጂ የሚንቀሳቀሰውንም የማይንቀሳቀሰውንም የሀገሪቱ ሀብት ሌሎች እንዲገቡበት ስንፈቅድ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል በቂ አቅም መፍጠራችንን ማረጋገጥ አለብን። ምርትና ምርታማነትን በማሳደግም ኢኮኖሚው ላይ ያለንን ሚና ማሳደግ ይጠበቅብናል።

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You