
ትናንት ምን ነበር? ቀን፣ ሳምንት፣ ወራት፣ ዓመታት ዓመታትን እየተኩ በታለፉ ረዥም ዘመናት ውስጥ ሁሉ አዲስ ዘመን ጊዜና ሁኔታን ተናጋሪ ዱካና ዐሻራ ነው:: አስገራሚና አንዳንዴም ለማመን የሚከብዱ እውነታዎችን ሁሉ ተሸክሟልና ከእነዚሁ ጉዳዮች፤ እናት በወለደቻት ልጅ ላይ ጨክና ሞትን ትፈርዳለች ብሎ ማን ያምናል? የሠራተኛው እንቅስቃሴና ጥያቄ የወለደው አድማ ጊዜን ያሳየናል:: አውሮፕላን ጠላፊው ኢትዮጵያዊና የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎችም ይገኙበታል::
የወለደቻትን ሕጻን ቀብራለች የተባለች ተያዘች
በቤንች ማጂ ቤንች ወረዳ ቃሽ በተባለው ቀበሌ የወለደቻትን ህጻን ከነሕይወቷ ቀብራለች ያላትን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ:: ግለሰቧ ደግሞ ያለፍላጎቷ ተደፍራ የወለደች በመሆኗ በብስጭት መቅበሯን ገለጸች::
የዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወታደር ናካ ባንዚኬስ ከትናንት በስቲያ እንደተናገሩት የሦስት ልጆች እናት የሆነችው የሠላሳ ዓመቷ ወይዘሮ ጥር 4 ቀን 1994 ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ የወለደቻትን ህጻን ከነሕይወቷ የቀበረችው በጓሮዋ ነበር::
የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ ባደረጉት ጥቆማ ግለሰቧ በሦስተኛው ቀን ተይዛ ስትጠየቅ በጓሮዋ እንደቀበረቻት በመናገሯ የሕጻኗ አስክሬን እንዲወጣ ተደርጎ ለምርመራ ወደ ሚዛን ተፈሪ ሆስፒታል መላኩን ኃላፊው አስታውቀዋል::
ግለሰቧ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸመች ተጠይቃ ሦስት ልጆቿን የወለደችለት ባለቤቷ ከሦስት ዓመታት በፊት በሞት ከተለያት ወዲህ በከፍተኛ ችግር ላይ መውደቋ ሳያንሳት አንድ ግለሰብ ገበያ ውላ ስትመለስ አስገድዶ በመድፈር እንዳስረገዛት ገልጻለች::
ግለሰቡ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ክስ ብመሠርትም ምንም ፍትሕ ለማግኘት ባለመቻሌ ህጻኗን በብስጭት ለመቅበር ተገድጃለሁ በማለት ተናግራለች::
(አዲስ ዘመን ጥር 12 ቀን 1994ዓ.ም)
የሠራተኛ እንቅስቃሴ
ቁጥራቸው ከ90 ሺህ በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር አባሎች፤ በኢትዮጵያ ሲደረግ የመጀመሪያ የሆነው የ4 ቀን ጠቅላላ የሥራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ፤ በዚህ ሳምንት በሙሉ ሥራቸውን ጀምረዋል:: የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት ማኅበር አባሎች የ4 ቀን ሥራ ማቆም አድማ ያደረጉት የኑሮ ውድነት ወደ 60 በመቶ ከፍ በማለቱ ተመጣጣኝ የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸውና አንዳንድ የመሻሻል ለውጥ እንዲደረግ ለመጠየቅ ነበር:: ሠራተኞች ሥራ ባቆሙበት አራት ቀን ውስጥ በነሱ ተወካዮችና በመንግሥት፤ እንዲሁም ከምክር ቤት በተውጣጣ ቡድን መካከል የተደረገ ንግግር ሠራተኞች በጠየቋቸው 17 ጉዳዮች፤ በየደረጃ በሥራ እንዲውሉ የሚመለከት ስምምነት ተደርጓል::
…
የሲቪል አቪዬሽን መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የአበል ጭማሪን፤ የሕይወት ዋስትናን፤ የማኅበር ማቋቋምና የቋሚ ሠራተኛነትን መብት ጥያቄ አመልክተው የሥራ ማቆም አድማ በማድረጋቸው፤ በኢትዮጵያ አየር ላይ የሚበርሩ የውጪ ሀገር ኤሮፕላኖች እንዳይገቡ አድርጓል::
(አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 1966ዓ.ም)
አውሮፕላን የጠለፈው ኢትዮጵያዊ ታወቀ
ባለፈው ረቡዕ ንብረትነቱ የምሥራቅ አፍሪካ አየር መንገድ የሆነ ፎክነር ፍሬንድሺፕ ፕ.ኤፍ.57 የተባለ አኤሮፕላን ከኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ወደ ማሊንዲ 30 መንገደኞችንና አራት የአኤሮፕላን ሠራተኞችን ይዞ በሚበርበት ወቅት በኢትዮጵያውያን ባልና ሚስት ተጠልፎ ኡጋንዳ ውስጥ ኢተንቤ አኤሮፕላን ማረፊያ ነዳጅ ለመሙላት እንዳረፈ በጉዳዩ ጄኔራል ኢዲ አሚን ጣልቃ ገብተው ኢትዮጵያዊው ጠላፊ ከነባለቤቱ እጁን መስጠቱ መገለጡ ይታወሳል::
ይህንኑ የሚመለከተውን ጉዳይ ኢስት አፍሪካን ስታንዳርድ የተባለው ጋዜጣ በዝርዝር አውጥቶታል:: በጋዜጣው እንደተመለከተው፤ አቶ ከሠተ የተባለ ኢትዮጵያዊና ባለቤቱ አኤሮፕላኑን የጠለፉት፤ ከናይሮቢ ወደ ማሊንድ በበረራ ፕሮግራሙ መሠረት ተነሣሥቶ የ15 ደቂቃ በረራ እንዳደረገ ነው:: ኢትዮጵያውያኑ ባልና ሚስት የአኤሮፕላኑን ሠራተኞች በሽጉጥ ካስፈራሩ በኋላ የአኤሮፕላን ነጂ አቅጣጫውን ለውጦ ወደ ሊቢያ እንዲበርር አለዚያ ግን እንደሚገደል ጠላፊዎቹ ነግረው የአኤሮፕላኑን ነጂ ካፒቴን ፔንፎልድ ጉዞውን ወደ ሊቢያ ከመቀጠሉ በፊት ነዳጅ ለመጨመር ኡጋንዳ ውስጥ ኢንተቤ አኤሮፕላን ማረፊያ አረፈ:: የምሥራቅ አፍሪካ አየር መንገድ ባለሥልጣኖች የኡጋንዳ ባለሥልጣኖች ርምጃ ለመውሰድ ጣልቃ እንዳይገቡ ቢጠይቁም፤ የኡጋንዳው ፕሬዚዳት አሚን በአስቸኳይ ወደ ሥፍራው ሔደው ጠላፊውን በማነጋገር ከነባለቤቱ እጃቸውን እንዲሠጡ ለማግባባት መቻላቸውን ጋዜጣው አመልክቷል::
ኢትዮጵያዊው መምህርና ባለቤቱ አኤሮፕላኑ ለጊዜው ወደ ሊቢያ እንዲበርር አስገደዱት እንጂ ለመሔድ ያሰቡት ወደ ሞስኮ እንደነበር በጋዜጣው ተጠቅሷል:: ጀኔራል አሚን ጠላፊዎቹን አግባብተው እጃቸውን እንዲሰጡ ካደረጉ በኋላ ከተሳፋሪዎቹና ከአኤሮፕላኑ ሠራተኞች ጋር ምሳ ተጋብዘዋል::
ከአዲስ አበባ መጣሁ የሚለው ከሠተ ያልተስተካከለ እንግሊዝኛ መናገር የሚችል ሲሆን ስሟ ያልተጠቀሰው ባለቤቱ ግን፤ የምትናገረው አማርኛ ብቻ መሆኑን ጋዜጣው ገልጧል:: መምህር ነኝ የሚለው ከሠተ አኤሮፕላን የጠለፈው ሀገሩ አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ስለምትገኝ ከዚሁ ለመራቅ በማሰብ መሆኑን ገልጧል::
(አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 1966ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
-ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*የአዲስ አበባ ትራፊክ ክፍል ከባድ ቁጥጥር ጀምረናል ሲሉ በራዲዮ የተናገሩትን ሰምቼ ነበር:: ቁጥጥሩን ግን ምን እንደሆነ አላየሁም:: ለመሆኑ አንተ አይተሃል?
-ኧረ እኔም አላየሁም:: ሲሉ ግን ሰምቻለሁ::
*የሩጫ ስሜት አድሮብኝ የቸገረኝ ነገር ጫማና ቱታ ነው:: የምገዛበትም የለኝምና ምን ይሻለኛል?
(መለሰ ጌታቸው)
-ያለ ጫማና ቱታ መሮጥ ይቻላል:: እንዲያው አበበ ቢቂላ ሮም ላይ ያሸነፈው ያለጫማ ሩጦ ነውና ሰበብ ሳታበዛ ትሮጥ እንደሆን ሩጥ::
*ሁለት እግሮቹ በእርዝማኔ እኩል ያልሆነ ሰው ካለ እባክህ ንገረኝ?
-ሞልቶ፤ ሜዳው ሙሉ ብቅ ጥልቅ የሚል ብቻ አይደለም እንዴ? ስንቱን ልንገርህ?
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 1966ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም