
ሰሜን ኮሪያ፤ የሀገሪቱን መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ባስቆጣው የአዲስ የጦር መርከብ ክሽፈት ምክንያት አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን አሰረች። በሀገሪቱ መንግሥት የሚተዳደረው ኬሲኤንኤ የዜና ወኪል፤ የሠራተኞች ፓርቲ የጦር መሣሪያ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ሪ ሃዮንግ ሰን፤ ባለፈው ሳምንት ለተከሰተው “ከፍተኛ አደጋ በአብዛኛው ተጠያቂ ናቸው” ሲል ዘግቧል።
አምስት ሺህ ቶን የሚሸከመው የጦር መርከብ በመገልበጡ የተነሳ ውሃ ላይ የሚያርፈው ዋነኛው የመርከቡ ክፍል ተጎድቷል። ኪም ጆንግ ኡን ይህንን ክስተት የሀገሪቱን ” ክብር እና ኩራት በእጅጉ የጎዳ”፤ “የወንጀል ድርጊት” ሲሉ ገልጸውታል። መርከቡ በባለሙያዎች ቡድን ጥገና እየተደረገለት እንደሆነ የዜና ወኪሉ ዘግቧል። የፓርቲው ማዕከላዊ ወታደራዊ ኮሚሽን አባል የሆኑት ሪ ሃዮንግ ሰን፤ በዚህ ክስተት ምክንያት እስካሁን ከታሰሩ ሰዎች መካከል ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ናቸው ተብሏል።
ኮሚሽኑ የሰሜን ኮርያ ሕዝብ ሠራዊትን የሚያዝ እንዲሁም የሀገሪቱን ወታደራዊ ፖሊሲዎች የማዘጋጀት እና የመተግበር ኃላፊነት ያለው ነው። ፒዮንግያንግ፤ የጦር መርከቡ በተሠራበት እና በከሸፈበት ሰሜናዊ ቾንግጂን የመርከብ ግንባታ የሚገኙ ሶስት ባለሥልጣናትን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስራለች። ባለሥልጣናቱ ዋና ኢንጂነር፣ የንግባታ ኃላፊ እና የአስተዳደሩ ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው ተገልጿል።
ኪም፤ ክስተቱን “በፍጹም ግድየለሽነት፣ ኃላፊነት በጎደለው እና ሳይንሳዊ ባልሆነ ልምምድ” የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። የታሰሩት ባለሥልጣናት ምን ቅጣት ሊጣልባቸውና ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አልታወቀም። ነገር ግን የሀገሪቱ መንግሥት ጥፋተኛ ሆነው ያገኛቸውን ባለሥልጣናት በግዳጅ የጉልበት ሥራ እና በሞት ጭምር እንደሚቀጣ ይታወቃል።
በሰሜን ኮሪያ በሀገር ውስጥ የተፈጠረ አደጋን ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ነገር ያልተለመደ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የተወሰኑ የከሸፉ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራዎች ተገልጸው ያውቃሉ። አንዳንድ ተንታኞች፤ የኪም ጆንግ ኡን ፈጣን እና ጠንካራ ምላሽ ፒዮንግያንግ ወታደራዊ አቅሟን ማጠናከሯን እንደምትቀጥል የሚያመለክት እንደሆነ ያምናሉ።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሰሜን ኮርያ ባለሙያ የሆኑት ኤድዋርድ ሆውል፤ “ይህ ሰሜን ኮሪያ የባሕር ኃይል ቴክኖሎጂዋን ለመጠገን እና ለማጠናከር የምታደርገውን ሙከራ እንደማታቆም ለደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል” ሲሉ ለኤቢሲ ተናግረዋል።
ደቡብ ኮሪያ በሚታተመው እና በሰሜን ኮሪያ ላይ በሚያተኩረው ዴይሊ ኤንኬ የዜና አውታር ላይ የወጣ አንድ አስተያየት፤ የኪም ጆንግ ኡን “የግዴታ ግልጽነት” የባሕር ኃይልን ማዘመንን ወሳኝ እና ቅድሚያ የሚሰጠው ርምጃ አድርጎ እንደሚመለከት ያሳያል ብሏል። “ይፋዊ ክሽፈቶች ሰፊውን የወታደራዊ እድገት ትርክት አያደናቅፉም” ሲልም አመልክቷል።
የባለፈው ሳምንቱ አደጋ የተፈጠረው ሰሜን ኮርያ በሌላ የሀገሪቱ ክፍል ተመሳሳይ የጦር መርከብ ይፋ ካደረገች ከሳምንታት በኋላ ነው። ኪም የጦር መርከቡ፤ የሰሜን ኮሪያን የባሕር ኃይል ለማዘመን “ፈርቀዳጅ” ሲሉ የጠሩት ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታውቀዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም