
ዜና ሀተታ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ በሰው መነገድና በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ተከላካይ የትብብር ጥምረት አደራጅቶ መሰል ወንጀሎችን የመከላከል ሥራ እየሠራ ይገኛል። በ2014 ዓ.ም በወጣ ደንብ መነሻነት የተመሠረተው ይህ የትብብር ጥምረት በስሩ የሚያስተባብራቸው ስድስት የሥራ ቡድኖች አሉት።
እነዚህ ቡድኖች በአዲስ አበባ ትምህርት፣ ፍትህ፣ ጤና፣ ፕላንና ልማት፣ ሥራና ከህሎት እንዲሁም በሴቶችና ማህበራዊ ቢሮዎች የሚመሩ ናቸው። ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችል የጥናትና ምርምር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የግንዛቤ፣ የችግሩ ሰለባዎች ድጋፍ የመሳሰሉ ሥራዎች እንደሚሠሩም ከአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከተመሠረተ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ የትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት በየጊዜው እየተገናኘ አፈፃፀሙን ይገመግማል። ወንጀሎቹን በመከላከል ረገድም ውይይት ያካሂዳል። ሰሞኑንም በተመሳሳይ በ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወር አፈፃፀሙና በ3ኛው የፍልሰት ዕቅዱ ላይ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በሰው መነገድና በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ድርጊት አፈፃፀም መልኩንና ቅርፁን ቀይሮ መምጣቱ በውይይቱ መነሳቱን አንስተዋል። ከዚህ በፊት ፈቃድ ባላቸው አካላት የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገናኝ ወዘተ በሚል ሕገ ወጥ ሥራ ይሠራ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ግን በነፃ የትምህርት ዕድልና፣ በጉዞ ወኪል ስም ጉዞውን ደርሶ መልስ በማስመሰል የተባለው ሀገር ሲደርሱ የማስቀረት፣ የማገናኘት ብሎም እንግልት ውስጥ የመክተት ወንጀሎች እንዳሉ በውይይቱ መጠቀሱን ገልጸዋል። ተቋማቱ ይህንን ሕገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል በሚመጥን መልኩ እንዲደራጁና መመከት እንዲችሉ ማድረጉ ላይ ጥምረቱ በትኩረት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ዜጎች በተቻለ መጠን የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድሎችን ሳይንቁና ሳያማርጡ ሊጠቀሟቸው እንደሚገባም አስረድተዋል። በውጭ ሀገራት ተንቀሳቅሶ የመሥራት ፍላጎት ካላቸውም በሥራና ክህሎት በኩል በርካታ ሕጋዊ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ዕድሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የጥምረት ፅህፈት ቤቱ በዋናነት የዜጎችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ እንደሚሠራ ገልፀው፤ ይህም ዜጋው ወደ ወንጀል ድርጊቱ እንዳይገባና የወንጀል ድርጊቱ ተጎጂ እንዳይሆን ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል። ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የድርጊቱ ሰለባዎችን የማዳን ሥራዎችን በሀገር ደረጃ ከተቋቋመው የትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት እንደሚሠራ ገልፀዋል። ይህም የህክምና፣ የሥነልቦና እንዲሁም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚያልፉት የሥራ ዕድል ድጋፍ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ የወንጀል ድርጊቱን የመሩና ያስተባበሩትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ነው ያብራሩት።
የትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤቱ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዮሀንስ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ፍልሰት በራሱ ችግር አይደለም ብለዋል። ችግሩ ፍልሰትን የምናስተዳድርበት መንገድ ነው፤ ጤናማና ሕጋዊ ፍልሰቶች የሥራ ባህልን የመቀየር፣ የቴክኖሎጂ እንዲሁም የእውቀት ሽግግርን የማስረፅ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በአንፃሩ ሕገወጥ ፍልሰት ዜጎችን ለሥነ ልቦና፣ ለኢኮኖሚ እንዲሁም ሕይወትን መስዋዕት እስከማድረግ የሚደርስ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን አስረድተዋል።
የትብብር ጥምረት ፅህፈት ቤቱ የዘጠኝ ወር አፈፃጸሙ ላይ ተመስርቶ ደካማ አፈፃፀም ያላቸውን ቡድኖች በቀጣይ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል። እንዲሁም ዜጎችን ከሕገ ወጦች ከመከላከል አኳያ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራና መሰል ወንጀሎችን የሚመለከት መረጃ መቀበያ ነፃ የስልክ ጥሪ አገልግሎቱን በሰፊው ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች በዋናነት እንደእቅድ የተያዙ ሥራዎች በተጨማሪም ከዲያስፖራው ጋር ግንኙነት ፈጥሮ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ድርሻ እንዲኖረው ማድረጉ ላይ አጥጋቢ ሥራ እንዳልተሠራ ገልፀው፤ በርካታ ሥራዎች እንደሚጠበቁባቸው ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር ዓባይ ጥምረቱ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመከላከል ባሻገር ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በውይይቱ ላይ መግለጻቸው ይታወሳል።
በነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም