የቻምፒዮናውን ጅማሬ ያሳመሩ አጓጊ ፉክክሮች

13ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች እና 4ኛው ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ትናንት በድሬዳዋ ስቴድየም ተጀምሯል። በማለዳ የተጀመረው ቻምፒዮና በተለያዩ ርቀቶች በተካሄዱ የማጣሪያና የፍፃሜ ፉክክሮች የደመቀም ነበር።

አጓጊ የነበረውና ብርቱ ፉክክር ያስተናገደው ከ20 ዓመት በታች የወንዶች 3ሺህ ሜትር መሰናክል የፍፃሜ ውድድር ተመልካቹን ቁጭ ብድግ ያደረገ ነበር። በርካታ አትሌቶች ተመጣጣኝ ፉክክር ባደረጉበት ፍልሚያ ሁለት አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ በመጨረሻው መቶ ሜትር አስደናቂ ትግል አድርገዋል።

በ2024 ፔሩ ሊማ ላይ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አትሌት ሃይሉ አያሌው በትናንቱ ፍፃሜ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት ነበር። ወጣቱ አትሌት እንደተጠበቀው በውድድሩ ብዙ ዙሮችን እየመራ አስደናቂ ብቃት ማሳየት ቢችልም በመጨረሻ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ተቀድሞ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል። 8:51.82 ሁለተኛ ሆኖ የፈፀመበት ሰዓት ሆኖ ተመዝግቧል። አጨራረሱን ያሳመረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌት ዲንቃ ፍቃዱ እልህ አስጨራሹን ፉክክር በ8:51.76 ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ ጨርሷል። ጀማል ጁሀር ከኦሮሚያ ኮንስትራክሽን 8:53.23 በመግባት ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።

ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የ3ሺህ ሜትር መሰናክል ፍፃሜ በአማራ ፖሊስ አትሌት ዓለምናት ዋለ አሸናፊነት ተደምድሟል። ዓለምናት ፉክክሩን በድል ስትቋጭ ያስመዘገበችው ሰዓትም 9:47.06 ነው። በስምንት ማይክሮ ሰከንድ ዘግይታ 9:47.13 ያጠናቀቀችው ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌት ኬና ቱፋ ሁለተኛ ደረጃን ስትይዝ፣ ዘሪቱ ዳባ ከሸገር ከተማ 9:51.61 በማጠናቀቅ ሦስተኛ ሆናለች።

የቻምፒዮናው የመጀመሪያ የሜዳ ተግባራት ውድድር ፍፃሜ በወንዶች ከ20 ዓመት በታች ከፍታ ዝላይ ፉክክር ተጀምሯል። ጥሩ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት የሆነው ዳል ማች 2.06 ሜትር ከፍታ በመዝለል አሸናፊ ሆኗል። 2.03 ሜትር የዘለለው የመቻሉ አትሌት ኦስሎ ኡጁሉ ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት ፉክክር፣ ፓሊፓ ኡማን ከሲዳማ ቡና 2.00 ሜትር በመዝለል የነሐስ ሜዳሊያውን ደረጃ ይዟል።

ከድሬዳዋ ስቴድየም ውጪ በተከናወነው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ጦር ውርወራ ፍፃሜ ሩት አሬሮ ከአዳማ ከተማ 45.65 ሜትር በመወርወር አሸናፊ ሆናለች። የሸገር ከተማዋ ዱኩ ኔንቆ ደግሞ 44.92 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ አትሌት የሺወርቅ አንማው 44.116 ሜትር በመወርወር ቀጣዩን ደረጃ ይዛለች።

በትናንቱ ከሰዓት በኋላ መርሃግብሮች ሁለት የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ፍፃሜ አግኝተዋል። አንደኛው ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ዲስከስ ውርወራ ሲሆን፣ 30.63 ሜትር መወርወር በቻለችው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አትሌት ራሄል ቶሎሳ አሸናፊነት ተጠናቋል። 28.50 ሜትር የወረወረችው የኦሮሚያ ክልል አትሌት ድጋፌ ሹሌ ሹር ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ አትሌት አብርሀት ኃይሉ 21.88 ሜትር በመወርወር ከትግራይ ክልል ሦስተኛ ሆና ፈፅማለች። ሌላው ከ18 ዓመት በታች የወንዶች ከፍታ ዝላይ ፍፃሜ ሲያገኝ የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛው አትሌት ዲየን የን 1.92 ሜትር በመዝለል አሸናፊ ሆኗል። 1.89 ሜትር የዘለለው የኦሮሚያ ክልል ተወዳዳሪው አትሌት ብሩክ እያሱ ሁለተኛ ሲሆን፣ ኦግል ኡጁሉ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 1.70 ሜትር በመዝለል የነሐሱን ደረጃ ይዟል።

በድሬዳዋ ካለው ሙቀት ጋር በተያያዘ በርካቶቹ ውድድሮች ከማለዳ በተጨማሪ በምሽትም መካሄዳቸው ነፋሻማው አየር ቻምፒዮናውን ልዩ ድባብ አላብሶታል። ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደውና ወጣት አትሌቶችን የሚያፋልመው ቻምፒዮና ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውለው የተለያዩ የማጣሪያና የፍፃሜ ፉክክሮችን ያስተናግዳል። ከነዚህ መካከል ጠዋት የሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የወንዶች 10ሺ ሜትር ፍፃሜ፣ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ከፍታ ዝላይ ፍፃሜ፣ ከ18 ዓመት በታች የወንዶች ዲስከስ ውርወራ ፍፃሜ ይጠበቃል። በከሰዓቱ መርሃግብር ደግሞ ከ20 ዓመት በታች የወንዶች አሎሎ ውርወራና ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ከፍታ ዝላይ የፍፃሜ ፉክክር የሚያስተናግዱ ይሆናል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You