
አዲስ አበባ ፡- ለውጡ በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የታሪክ ምዕራፍን ቀይሯል ሲል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ሂክማ ኸይረዲን ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች የኢትዮጵያ ሴቶች የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ላይ መሠረታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።
በዚህ ለውጥ ስኬት የሴት አደረጃጀቶች ሚና የጎላ እንደሆነ አስታውሰው፤ ለውጡም በሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የታሪክ ምዕራፍን ቀይሯል ብለዋል።
መንግሥት በወሳኝ ተቋማት ላይ በተለይም በፌዴራል ደረጃ የሴት አመራሮች ቁጥር እንዲጨምር የተደረገበት አግባብ ለኢትዮጵያ ሴቶች ዘመን የማይሽረው ታሪክ የተሰነደበት ዓመት ሆኖ የሚዘከር እንደሆነ ወይዘሮ ሂክማ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ ሥርዓተ መንግሥታትን ያሳለፈች ብትሆንም በተለይም የሴቶችን ውሳኔ ሰጭነት በተግባር ከመተርጎም አንጻር መሠረታዊ የሆነ የአመለካከት ማነቆ እንደነበረባት ሚንስትር ዴኤታዋ አስታውሰዋል።
የሀገራችንን ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና የሀብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ሂደት ውስጥም ግንባር ቀደም ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን፣ የሕግ ማዕቀፎችንና ፓኬጆችን በመንደፍ ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረጉን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት ፌዴሬሽኑ የሴቶችን መብት በመጠበቅ፣ እድሎችን በመፍጠር እና እምቅ ችሎታቸውን የሚገድቡትን እንቅፋቶች በመታገል ወሳኝ ሚና መጫወቱንም ጠቁመዋል።
የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም መብትና ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ጉዞው ገና ያልተጠናቀቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሥርዓተ ጾታ እኩልነት እስኪረጋገጥ፣ ስልቶች እና የጋራ ትግሎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ፌዴሬሽኑ የተለያዩ የሴት አደረጃጀት ስብስብ ጥምረት እንደመሆኑ መጠን በእስካሁኑ ጥረት የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋፋት ፤ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት እና ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችሉ ስልቶችን ለመንደፍ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአደረጃጀት ዘርፍ ባሉት ተቋማት መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር ይገባል ያሉት ሚንስትር ዴኤታዋ፤ ፌዴሬሽኑም ተሞክሮዋቸውን እንዲለዋወጡ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽንን ማደስና ማጠናከር እያንዳንዱ አባል ለውጥ እንዲያመጣና አቅም እንዲኖረው ማስታጠቅ መሆኑን በመጠቆም፤ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣም ጠንካራ አመራር እና አደረጃጀት መፍጠርና መገንባት ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል።
የፌዴሬሽኑ አሠራር በግልጸኝነትና ተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎችን በመቀመር ከመተዳደሪያ ደንቡ ጋር የተጣጣሙ የአሠራር ሥርዓቶች መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የእውቀትና የልምድ ሽግግር ማድረግ፣ የትብብርና የአጋርነት መንፈስ ማዳበር፣ የጋራ መድረኮችን በቋሚነት መፍጠር፣ በሕግ መሠረት መንቀሳቀስና መፈፀም፣ የመላውን ሴቶች ተሣትፎ ማረጋገጥና ንቅናቄ መፍጠር ላይ ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሠጥቶ የሚንቀሳቀስ መሆኑን አመልክተዋል።
በእንቅስቃሴው እያንዳንዱ አባል ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ጥንካሬ የሚለካው በአባላቱ ተሳትፎ ቁርጠኝነት እና በማንኛውም ስፍራ የኢትዮጵያን ሴቶች ድምጽ በማጉላት እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። አባላቱ ቁርጠኛ እንዲሆኑ፣ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እና የሚፈለገውን ለውጥ በባለቤትነት እንዲይዙ አሳስበዋል።
የፌዴሬሽኑ ዋነኛ ተልእኮ ለሴቶች መብት መሟገት ብቻ ሳይሆን የማብቃት፣ የመደገፍ እና ጥቅሞቻቸውን የማስከበር እንደሆነ ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ሴቶች ብልፅግናን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸው ከወዲሁ አውቀው ለጠመዝማዛው ጉዞ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው ሚንስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሂክማ ጥሪ አቅርበዋል።
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም