ትንሽ ድብርት ቢጤ ሲጎሻሽማት ወደ ደጅ ወጣ ትልና የበሶብላውንና ቃሪያዎቿን በትንሽዬ ዶማ ትኮተኩታለች። ባህሪው ወጣ ካለውና እንደ ውሻ ሰዎችን ካልተናከስኩ ብሎ ግብግብ ከሚፈጥረው ዶሮዋ ጋር ትጨቃጨቃለች። ያሰጣችውን የሽሮ እህል ካልበላን ከሚሉ ወፎች ጋር ግብግብ ትገጥማለች። ለእንስሳት ፍቅር ሰላላት ይሁን በአንዳች አጋጣሚ የሁሉም ባህሪ አስገራሚ ነው። ዶሮው ካልተናከስኩ ሲል ድመቷ ደግሞ የምግብ ምርጫዋ የተለየ ነው። ፈንዲሻውን፣ሙዙን፣ለውዙንም ሆነ ጥራጥሬውን ታነክተዋለች። አጃኢብ ነው!
ግቢዋን በቤት እንስሳትና አትክልቶች የከበበችው ቀለቧን ለመስፈር ብላ አይደለም። ይልቁኑ የእናት አባቷን የአርሷደርነት ጥንካሬ ስለሚያስታውሳት እንጂ።
ታዲያ በዚህ ኡደት እየተገረመች በረንዳዋ ላይ ቁጭ ብላ የእንጀራ ማውጫ ሰፌድ በአክርማና ሰበዝ እየሰፋች፣ በአለላ እያስጌጠች በእንስሳቱና በተፈጥሮ እኩል ትደነቃለች። በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ያሳደገቻት ፀጉራም ድመቷ ይበልጥ ቀልቧን ትስበዋለች።
ከእለታት በአንዱ ቀን በማለዳ ለልደታ ቡና አፍልታ ደርበብ ብላ በቤቷ ውስጥ ተቀምጣለች። ለቡናው ድምቀትና ለታዳሚው ቁርስ ብላ ካፈነዳችው ፈንዲሻዋ ዘገን እያደረገች ደግሞ ለድመቷ እየሰጠች ከራሷ ጋር ታወራለች። አጠገቧ እንደነበርኩ እንኳን ያስተዋለች አይመስልም። ‹‹ወይ ጉድ! አሁን ምን የሚሉት ነው? ድመትን በጥሬ መጠርጠር›› እያለች ፈገግ ትላለች።
አባባሉ ከቀደሙት ግዜያቶች በተለየ ትኩረቴን ሳበው። እውነቷን ነበር። ‹‹ለመሆኑ ማን ድመት ጥሬ ይበላል ብሎ ይጠረጥራል›› ስል ለራሴ መልሼ ጠየኩት። እሷ ድመቷን ፈንዲሻ እየመገበች ከራሷ ጋር ስታወራ እኔ ደግሞ ድንገት ለአባባሉ ትርጓሜ መልስ ፍለጋ እኳትን ጀመር። ጆሬዬን ጣል ሳደርግ ደግሞ እንዲህ እያለች ቀጥላ ኖሯል…
‹‹…አሁን ማን ይሙት ኢትዮጵያዊ ወገኑ ላይ እጁን ያነሳል፣ እንደ ሰደድ ቤት ንብረቱን በእሳት ይለኩሳል ብሎ ማን ይጠረጥራል? አጃኢብ ነው! ›› ትላለች፤ በድመቷ ጥሬ መብላት በተናካሽ ዶሮዋ መገረሟ ሳያንሳት ወገን ወገኑ ላይ መጨከኑን ስትሰማ እውነትነቱን ለመቀበል እያዳገታት። ደግሞ ቀጠል ታደርግና እንዲህ ትላለች ‹‹እውነት በአንድነቱና በአልበገር ባይነቱ ነጭን በጀግንነት ያንበረከከ ኢትዮጵያዊ ደርሶ የዘር ጉልቻ ውስጥ ይወሸቃል ብሎ ማን ይጠረጥራል›› ትላለች አንጀቷ መብገኑ ያስታውቅባታል።
የአገሩ አንድነት የሚያሳስበው በቅኝ፤ በግራ በዘረኝነት አይኑ የታወረው ወገኗ ልዩነታቸውን በዓለም አቀፍ አደባባዮች በግቢዋ ላይ እንደምታሰጣው የበርበሬ ድልዝ ሲዘርሩት ስታይ ብስጭት ይላትና ‹‹አሁን ማን ይሙት ኢትዮጵያዊ በዘር ቀረጢት ተቋጥሮ ከነጭ ፍትህ ለማግኘት ጉሮሮው እስኪሰነጠቅ ይጮሃል ብሎ ማን ያምናል! አጃኢብ ነው›› ትላለች በሚሆነው ሁሉ እየተገረመች።
ፈልቶ የሰከነውን ቡናዋን ሃጫ በረዶ በሚመስሉ ስኒዎች ውስጥ እየቀዳች ከራሷ ጋር ማውራቷን ተያይዛዋለች ‹‹አጃኢብ ነው! በግቢዬ የዘራሁት ቃሪያ ከጤናዳሜ ጋር እንደሚጣላው ልክ እንደዛ፣ በሶብላዬ ከሽንኩርት ማሳዬ ጋር ግብግብ እንደሚገባው አይነት የማይመስል ነገር…›› እያለች የምፀት ፈገግታ ትለግሳለች። ደሞ ቆየት ብላ ለግርምቷ እራሷ ምላሽ ትሰጣለች ‹‹ለነገሩ የኔ ዶሮ እንደውሻ ይናከሳል፤ ድመቴስ ብትሆን ጥሬ ትመገብ የለ…›› እያለች የቀዳችውን ቡና አቀበለችኝና ግራ እጇ ላይ የተረፈውን ፈንዲሻ ከፊት ለፊቷ ቁጢጥ ላለችው ውሮ በተን አደረገችላት…!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም
በዳግም ከበደ