መስታወት አስተዋዋቂው ገዴ በመንገዴ

በየዓመቱ የበዓልን መምጣት ተከትሎ ከቅርብ ጎረቤቶቼ ጋር በመሆን ሙክት ልንገዛ በምሄድበት ሰሞን የተወዳጀሁት በግ ነጋዴ ወዳጅ አለኝ። በኑሮ ውድነቱ ሁሉም ቤት ያፈራውን ቀምሶ የሚውልበት ክፉ ቀን ሳይመጣ በፊት ማለቴ ነው…። ገበያ ደርሼ ይሄን ወዳጄን ሳላይ አልመለስም በሚል የራስ ሙግት ወደ በግ ተራ አቀናሁ።

በገበያ ሳልፍ.. አንድ የመስታወት ማስታወቂያ አይቼ ፈገግኩ። በተለያየ ቅርጽ የተሰሩ የተለያየ መጠን ያላቸውን መስታወት የሚሸጥ ሰው በእጁ አንድ መስታወት ይዞ ወረሩን በመስታወቱ ውስጥ እያጤነ..‹ውበት የሚጨምር የቤቶ ግርማ ሞገስ..እኔ ነኝ እንዴ ብለው በራሶ ግራ እስኪጋቡ ወዘናዎን የሚመልስ መስታወት..እኔ ዘንድ ብቻ ይገኛል›

በሰውዬው ተስቤ ባለሁበት ቆምኩ..ጥቂት ሰዎች ሳቅ ባረበበበት ገጽ ከበውታል። አንዳንድ መንገደኞች ወዳለበት ይተማሉ..። ከስንት አንድ የሚሆኑት በማስታወቂያው ተታለው (ሌላ ምን ይሆናል?) ከተቀመጠበት መስታወቱን በማንሳት የተባለውን ለማረጋገጥ ራቅ ቀረብ እያደረጉ ራሳቸውን ሲመለከቱ አየሁ። እብድ ቀን አይመሽም ትል ነበር እናቴ..እብድ ቀን የቱን ዓይነት እንደሆነ ግራ እንደገባኝ አደኩ። አሁን ሲመስለኝ እብድ ቀን ይሄ ዓይነቱ ቀን ይመስለኛል። ይሄ ቀን እብድ ካልሆነ ከዚህ የተለየ እብድ መሳይ ቀን ከወዴት ይመጣል?

እኔም ወደ ሰውዬው አፈገፈግኩ። አንድ እብድ በገዛ ሃሳቡ አብዶ ብዙ ጤነኞችን ወደ እብድነት ሲቀይር አስባለሁ። ከነዛ እብዶች መሀል አንዱን ሆኜ ወደዛ ሰው መጠጋቴ እንደከበቡት ሰዎች ገጼ ፈገግታን ጸነሰ። እውነት ቢሆንስ ስል በሥርዓት ከተደረደሩት መስታወቶች አንዱን አንስቼ መልኬን መቃኘት ያዝኩ..ከነባሩ መልኬ ምንም የተለወጠ ነገር አላስተዋልኩም። ለሰላሳ ሁለት ዓመታት የማውቀው ራሴ ነኝ። ቤታችን ግድግዳ ላይ በተሰቀለው ከጀርባው አንዲት የቻይና ሞዴልን በለጠፈው መስታወት የማውቀው መልኬ ነው። እንደተሞኘሁ ያወኩት ይሄን ጊዜ ነው።

ወደሰውዬው አሰገግኩ..ጮሌነትና አራዳነት ወጣት ይሁን ጎልማሳ እድሜውን በደበቀ ፊቱ ላይ አስተዋልኩ። ከቅንድቡ ከፍ ብሎ ግራ ግንባሩ ላይ ደም ስር ተጋድሟል..ደምስሩን አጤንኩት ቀስተኛ እንቅስቃሴ ያደርጋል። ወደሽፋሽፍቱ አየሁ..ቢቆጠሩ አስር የሚሆኑ ብቻ ናቸው።

የምገዛው መስሎት ‹አሪፍ መስታወት ነው የመረጥከው..በጥሩ ዋጋ እሸጥልሃለሁ። በአሁኑ ሰዓት በምድር ላይ ያለ ብቸኛው የስጦታ እቃ ነው…ፍቅረኛ ካለችህ..ከሌለህም ለምትመጣው ይሆንሃል..እንዳያመልጥህ› ሲል ረጅም ወግ አወጋ።

መዳፌን አየሁት..ከሰላምታ በቀር ሰው አጠናፍሮ አያውቅም፣ ይሄን ሰው በማጠናፈር የመጀመሪያው ታሪከኛ መዳፍ ላደርገው አሰብኩ። ፊቱ ላይ የአምስት ጣቴን ሰንበር ከመዳፌ ሙዳ ጭረት ጋር መተው አሰኝቶኝ ነበር። ለአንድ ጊዜ በመጣ እልኸኝነት ፊቱ ላይ ብዘምትበት..ጮሌነቱን በቡጢ በአደባባይ ባስንቅበት ፈለኩ። እንዲህ በሽቄ እመለሳለሁ እንጂ ያበሸቀኝን ሰው ላይ እልሄን ተወጥቼ አላውቅም። ፈሪ ሆኜ እንዳልሆነ አውቃለሁ..በእውነቱ ለክብሩ የሚሟገት ብርቱ ሰው ነኝ። በኋላን በአሁን ፊት አስቀምጬ ነገን እማልዳለሁ ያኔ እረጋጋለሁ..

እንዴት ወደዚህ ሰው መጣሁ? እብድ ቀን አብዶ የሚያሳብድ ይሆን? እናቴ ዳግም እቅፏ ውስጥ አስቀምጣ ብትነግረኝ..። ባልገቡን የሕይወት ፈር ስር ነን..እየጠየቅን እስከነገ እንድንሄድ በሆነ ሰው መሆን ውስጥ..

አየሁት! አፈ ግንዱን ሲያብስ አገኘሁት። ፊቱ ቅድም በሌለ ላብ አቸፍችፏል። ስሩ መቆሜ አንዳች ልፈጥርበት እንደሆነ ገብቶት ያላበ መሰለኝ። ባይመስለኝም በዛ ማላዘን ላብ አይደለም ሌላም ነገር ሲያንሰው ነው። እያሳዘነኝ መጣ..ከኋላው አንዳች ታሪክ አነበብኩ። አልሸጥ ብሎት..ሊከስር እንደሆነ ሲያውቅ አፍረቱን ከልሎ በእብድ መላ ሰው ፊት የቆመ መሰለኝ.. ፊቴን መስታወቱን እንደማልፈልግ በሚናገር ሁኔታ ወደነበረበት ብመልሰው ገበያውን የምዘጋበት መስሎ ታየኝ። ወትሮስ ሃሳቤ ምን ሆነና እንደዚህ አሰብኩ? ቢቻለኝ ግብግብ ፈጥሬ አንተ ሌባ ወራዳ ብዬ እሪ ብዬ ላሲዘው እንዳላሰብኩ ደርሶ አዛኝ መሆኔ ለራሴም ገረመኝ።

በውሸቱ ተታለው ብዙ ሰዎች እየገዙት ሄዱ። እኔና እሱ ብቻችንን መቅረታችንን ሳውቅ አንድ ሁለት ጥያቄዎችን ልጠይቀው ስሰናዳ..

‹ምነው አልተመቸህም እንዴ? ስለእቃው ጥራት እኔ ከምነግርህ በላይ ያየሃቸው ደንበኞቼ ምስክሮች ናቸው። አሁን ፊቴ ቆመው ሲገዙኝ ያየሃቸው የቆዩ የመስታወት ደንበኞች ናቸው። በሳምንት ሁለት ጊዜ ይገዙኛል› ሲል ቀላመደ። በሳምንት ሁለት ጊዜ? አልኩ በብሽቀት ለራሴ። ቆይ ምኔ ሞኝ ይመስላል? ምኔ ላይ ቂልነትን አየብኝ? የተደበቀ ሞኝነቴን ፍለጋ ራሴን ከእግር እስከራሴ ቃኘሁት..ራስን በዚያ መንገድ መፈተሸ..በድርጊቴ ሳቄ መጣ። በድጋሚ በመስታወቱ ውስጥ ራሴን በጥንቃቄ ፈተሸኩት..በትንሹ ከታጠፈ የሸሚዜ ኮሊታ በቀር ክፉ አላገኘሁም። ምናባቱ ሆኖ ነው ታዲያ እንደሞኝ ደንበኞቹ ሊያሞኝ የተነሳው ስል አፈጠጥኩ። በሸሚዝ ላይ ኮት ነውር ይሆን?

ዓይኖቼን እንከን ወደማያጣው እግሮቼ ሰደድኩ..ጫማዬ ከአንድ ጎን ተበልቶ ተረከዜን ገንድሶ፣ ሚዛኔን ወደአንድ ጎን አንሸራቶ ጅላንፎ አስመስሎኛል። ጫማ ገዝቼ በሳምንቱ ለምን እንደዛ እንደሚሆንብኝ ለብዙ ዘመን ያልተመለሰ ጥያቄ አለኝ። ዓለም የእግር ባለጅ ባለማኖሯ እንደትልቅ እንከን እቆጥርባታለሁ። እንደ ብረት ሙያተኛ እግርም ቀጥቃጭ ቢኖረው እላለሁ። በምድር ላይ ጫማህን ፍታ እንደሚል ቀልድ የማልወደው የለም። ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ካልሲዎቼ እንዳለ ቀዳዳዎች ናቸው። ተቀዶ አይቶት ይሆን..? ወይስ በተረከዜ መበላት እንደቂላቂል ቆጥሮኝ?

ኧረ እንደው ልቤ ድፈርና ዛሬ ልኩን አሳየው ይለኛል ውስጤ..ተው አይሆንም የሌለበት ወኔ ናፈቀኝ። ተያይዘን ለገላጋይ የምናስቸግርበት ትዕይንት እየመጣ ይሄድብኛል። ‹በሳምንት ሁለት ጊዜ ይገዙኛል› ያለኝ ቧልቱ አልረሳ ብሎ ለቡጢ ይተናነቀኛል። ከልጅነቴ ጀምሮ መልኬን እያየሁበት ያደኩት የእናቴ ወዛም ዘኒት ቅባትና አደስ እያሟለጨኝ ልጅነቴን የሰዋሁበት በኋላም ከእሷ ወደእኔ ተላልፎ በቅርስነት ሊመዘገብ ጥቂት የቀረው የቤታችን እድሜ ጠገብ መስታወት ስንቱን ትውልድን የኳለውና ለቁም ነገር ያበቃው ለብቻው አይደል? ዛሬ በዚህ ሰው የሀሰት ትርክት ውለታው መበላቱ አናደደኝ። እብለቱ እያበሳጨኝ መጣ።

‹ለመሆኑ ይሄን በድህነት የሚማቅቅ ሕዝብ የማደናገሪያ ጥበብ ከየት አገኘኸው? ስል ጠየኩት።

አልደበቀኝም..አይነግረኝም ብዬ ስሰጋ እንደ ግምቴ እቅጩን ነገረኝ። ‹ሕይወት ናት እንኳ ስትል የሰጠችኝ› ሲል ወደልፍለፋው ተመለሰ።

ባልገባው ፊት ‹እንዴት ማለት? በማለት በተራዬ ከልፍለፋው አስተጓጎልኩት።

‹የእኛ ሰው አስቸጋሪ ፍጡር ነው እውነት ብትነግረው አያምንህም። ውሸት ስትነግረው ግን እንዳየኸው በወረፋ ተረባርቦ ነው የሚቀበልህ። እንዳየኸው ይሄ መስታወት ውበት የሚጨምር ሆኖ አይደለም እውነቱን በውሸት ቀይሬ በመናገሬ ያመጣሁት ነው። ሰው እውነትን ካልመረመረ ውሸታሞች አንድ ሲደመር አንድ ሶስት ነው ብለው ይመጡበታል። አሊያም በበሬ ወለደ መሞት ለማይፈልጉ እነሆ የሞት መድኃኒት ስትል ሰናፍጭና ዳማከይሴን ቀላቅለህ በቀን ሶስቴ በሚል ትዕዛዝ እንደባሕል ሐኪም ከጥሩ ማስታወቂያ ጋር ውድ ዋጋ አውጥተህለት ጎዳና ላይ ትሰየማለህ..አትጠራጠር ያምንሀል› ሲለኝ እኔም አምኜው በሚቀጥለው ቀን ለዚህ ውሸት ራሴን በማሰናዳት ነበር።

ምንም ሳልለው ላነሳሁት መስታወት የሚገባውን ከፍዬ ወደበግ ነጋዴ ወዳጄ ተሰደድኩ። መንገድ ላይ ነበር ከእሱ የባስኩ እብድ እንደሆንኩ የተገለጠልኝ..ውሸት እንደሆነ እያወኩና እየነገረኝ መግዛቴን ሳውቅ።

እብድ ቀን ላይ አይደለሁ..! መልኬን ከቀየረው ብዬ መንገድ ላይ ፊቱን በመስታወቱ ውስጥ አጤንኩት..። ከኋላዬ በሁኔታዬ ተገርማ ይመስለኛል አንዲት መልከ መልካም ፎቶ እንደሚነሳ ሰው ፈገግ ብላ ቆማ አየሁ…

እያወጋን ሄድን..ከሶስት ወር ቆይታ በኋላ ሚስቴ ላደርጋት ቀለበት ያሰርኩላት መሆኔን ማን ያምናል?

ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

አዲስ ዘመን ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You