የኑሮ እሽክርክሪቷ ማቆሚያ ድንበር የላትም። ከምስራቅ አንስታ ምዕራብ፤ ከሰሜን ወስዳ ደቡብ ትሰዳለች። የሰው ልጅ እትብቱ ከተቀበረት ወስዳ ባህር ማዶ ታሻግራለች።በአገር ውስጥም ቢሆን ከቆላው ደጋ፣ ከብርዳማው ሞቃታማ ስፍራ፤ እንዲሁ በተቃራኒው ከሐሩሩ ወስዳ ውርጭ የበረታበት አካባቢ ታመላልሳለች።ሕይወት አዙሪቷ ቀላል አይደለም። በስደት ታንቀዋልላለች፤ በማግኘትና በማጣት መካከል ከልዋሳ ታደርጋለች።በቀኝ ስትቃና በግራ ታዘማለች፤ ልኬቷ ከላይ ሞላ ሲባል ከሥር ሽንቁሯን ትከፍታለች። ህይወት ባለብዙ ጠርዝ፤ ባለብዙ ፈርጅ ነች።
በዛሬም እትም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› አምድ ከትውልድ መንደራቸው የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ስኬት እየናፈቁ፤ ኑሯቸውን ለማቃናት እየጓጉ ጉዟቸው ከመሃል መንገድ ስለተሰናከሉ ሰዎች እናወጋለን።
አስፋወሰን ዓለሙ ሰሜን ሸዋ ዞን ሲያደብርና ዋዩ ወረዳ ሰንከታ ከሚባለው ቆላማ አካባቢ ነበር በ1994 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ያቀናው። ከዚህ ቀደም ሲል በአንድ ጤና ጣቢያ በ450 ብር ወርሃዊ ደመወዝ እየተከፈለው ይሠራ የነበረ ሲሆን፤ የእርሻ መሬት ስለነበረው ኑሮውን በሚገባ ይደጉምና ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱንም በሥርዓት ያስተዳድር ነበር። ማህበራዊ ሕይወቱም ቢሆን የተስተካከለና መስተጋብሩም የተጠናከረ ነበር።
ይሁንና ቅልጥፍናን እና ተግባቦቱን የተመለከቱ ሰዎች አንተ እኮ ወደ አዲስ አበባ ብትሄድ ከዚህ የበለጠ ደመወዝ ታገኛለህ። ፈላጊህም ብዙ ነው።ገቢህም ይሻሻላል።አንተ ብቻ ሳትሆን ቤተሰብህም እንዲሁ ይለወጣሉ ወደ አዲስ አበባም ይዘሃቸው ትገባለህ ይሉታል። እንዲያውም መልከ መልካም ከመሆንህ የተነሳ ብዙ ዕድል አለህ ሲሉትም ይመክሩታል። እርሱም አንዳንዶች ቀደም ብለው ወደ አዲስ አበባ መጥተው ልብስ ቀይረው፤ ፀጉራቸውን አበጣጥረው፤ በጅንስ ሱሪ ተወጣጥረው ወደ አገር ቤት ሲመለሱ ይመለከት ስለነበር ይህ ነገር እውነት ነው ሲል ለራሱ ነገረ ራሱንም አሳመነ።
የተወለደበትን አካባቢው ወላፈን ትቶ የአዲስ አበባ ጠረን ናፈቀው።ገጠር አስጠልቶት ከተሜ መሆን ከጀለ። እርሻውን ትቶ፤ ጉልጓሎውን ረስቶ፣ ሞፈርና ማገሩን ከጓሮ አስቀምጦ አዲስ አበቤ መባሉን ቋመጠ። አላስቆምም፤አላስቀምጥ አለው ልቡ ሸፈተ። በአንድ ጉዜ ከአዲስ አበቤ ለመቀላቀል ወሰነ። ሃሳቡን ሲያወጣና ሲያወርድ ሰንብቶ ወደ ከተማ መግባት ይበጃል ሲል ለባለቤቱ አማከረ። እርሷ ግን ወይ ፍንክች! አለችው። ታዲያ አለመግባባቱ ሲመጣ በዚህ ጊዜ የድርሻችንን መሬትና ንብረት ውሰጂ የድርሻዬን ልውሰድ ብሎ እንቅጩን ነገራት።
ነገሩን የሰሙት ጎረቤቶቹና ወንድም እህቶቹ አይሆንም፤ ከአሁን በኋላ ከተማ አይበጅህም ሲሉት መከሩት። አስፋወሰን ግን አሻፈረኝ አለ። እንዲያውም በአጭር ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ እንደወሰነ እንቅጩን ነገራቸው። ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ። በመጨረሻም በአገሬው ደንብ መሰረት ከሚስቱ ጋር ያለውን ሀብት ተካፍሎ ትዳሩን አፈረሰ። የእርሱን ድርሻ መሬት እና ሌሎች እርሾ በሙሉ ሸጠ። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጣ።
በእርግጥ በመጀመሪያዎቹ ወራት ገንዘብ ስለነበረው አልተቸገረም። ለሚለብሰው ሆነ ለሚጎ ርሰው ችግር አልገጠመውም። ይሁንና ያሰበው አልገጠመውም፤ ቀደም ሲል ይሰራ የነበረውን የጥበቃ ሥራም ለማግኘትም ተቸገረ። የሚያስጠጋው ዘመድም አላገኘም።ገንዘቡ እያለቀ በመሄዱ የቀን ሥራ እየሠራ የተሻለ ሥራ ማፈላለግ ጀመረ ግን አልተሳካም።
አሁንም ተስፋ አልቆረጠም። ሰዎችም መልከ መልካም ስሆንክ ፈላጊህ ብዙ ነው ያሉት ቃል በአዕምሮ እየተመላለሰ ትዝታውን ይቀሰቅስበታል። ግን ሁሌም ነገር እንዳሰበው ሳሆን ቀርቶ መና ሆነ።ይባስ ብሎም በቀን ሥራ ራሱን መደጎም እየከበደው፤ ኪራይ መክፈል እየተሳነው መጣ። በዚህ ጊዜ ወደ አገር ቤት እንዳይመለስ ሁሉ ንብረቱን ሸጦ ስለመጣ ሲመለስ ምን ላይ እንደሚያርፍ ሲያስበው አልዋጥ አለው። ሁሉንም ነገር ቢያወጣው ቢያወርደው እንደማይሆን ገባው። በመጨረሻም አዲስ አበባ ውስጥ ደፋ ቀና ብሎ ህልሙን ለማሳካት ወሰነ ግን አሁንም እነዚያ የተስፋ እንጀራ ሲመግቡት የነበሩ ሰዎችና መካሪዎቹ ከአጠገቡ የሉም።
አስፋወሰን ሕይወት እየከበደው ሲመጣ በረንዳ ማደር ጀመረ። ሥራ ሲጠፋ ወዛደርነት ጀመረ። በቀን ያገኛትን ያክል ለሆዱ እያደረገ የምትተርፈውን ገንዘብ ደግሞ በየቀኑ ለመኝታ ይከፍል ጀመር። አሁንም ግን ይህ ሕይወት ከበደው። በረንዳ ማደሩ ጀመረ። በኋላ ግን በረንዳ ማደሩን ትቶ ወደ ቤተክርስቲያን ተጠጋ። ለነብሴ ያሉ ሰዎች የሚመፀውቱትን ምግብና ትርፍራፊ እየበላ ሕይወቱን ለመምራት ሞከረ።አሁንም ኑሮ እየከበደው መጣ። በመጨረሻም አዲሱ ገበያ እግዚአብሄርአብ ቤተክርስቲያን በር አካባቢ የፕላስቲክ ሸራ ወጥሮ ለመኖር ወሰነ።
ከተወለደበት ሰፈር ከወጣ 20 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ቀርተውታል። በልቡ እትብቴ የተቀበረበት መንደሬ ሰፈሬ እያለ ቢያስብም ፊቱን ወደቀየው ለመመለስ ግን የሚያስችለው አንዳች አቅም የለም። እናም ከተሜና ባለፀጋ ለመሆን ወደ አዲስ አበባ የመጣው ሰው ከቶውንም ሕይወት እርሱ ካሰበው በተቃራኒ ሆና እንቆቅልሽ ሆናበት፤ ከሞቀ ቤቱና ጎጆው ወጥቶ ፀሐይና ቁር እየተፈራረቀበት ሕይወቱን ለመምራ ተገዷል- የ56 ዓመቱ ጎልማሳ አስፋወሰን ዓለሙ።
ተስፋዬ ቱሉ ከ25 ዓመት በፊት ነበር ከደገም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ የመጣው። ከተማ ሥራ ይገኛል፤ ኑሮ ጥሩ ነው በሚል የጓደኞቹ ምክር ታክሎበት ገጠር ኑሮ ስለከበደው አዲስ አበባን የመረጠው። በወቅቱ የራሱ የሆነ የእርሻ መሬት አልነበረውም። ወዲህ ደግሞ ከቤተሰቤ በጉልማ አሊያም ደግሞ በድጎማ የተሰጠው ሀብት የለም። በዚህም የተነሳ የቤተሰብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ውሎ ማደሩን ጠላው። በመጨረሻም አዲስ አበባ
ሥራ እንደሚገኝ አስቦ ይመጣል። እንደመጣ የቀን ሥራ እየሠራ ራሱን ለማሸነፍ ይሞክራል።ጉልበት ስለነበረው በኮንስትራክሽንና ሥራዎች ባሉበትና ሌሎች አካባቢዎችም እየተንቀሳቀሰ ራሱን ለማሸነፍ ሞከረ። ወዛደርነት ሥራንም ለረጅም ዓመታት ሰርቷል።በተቻለ መጠን ራሱን ለማኖር ያልሞከረው ሥራ አልነበረም።
እንዲህ! እንዲህ! እያለ የሚችለውን ያክል ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ።የተለያዩ ሥራዎችንም እያከናወነ የራሱን ጉርስ ሸፍኖ የቀረችውን በመቆጠብ 10 ሺ ብር አጠራቀመ። በመጨረሻም ወደ አገር ቤት ገብቶም አነስተኛ ሱቅ ከፍቶ ለመስራት አሊያም ደግሞ ካፒታሉ በፈቀደ መጠን ወደ ንግድ ሥራ ለመሠማራት አቅዶ ገንዘቡንም ማጠራቀሙን ተያያዘው። በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ ገንዘቡን ከባንክ ያወጣ እና ወደ ቤተሰብ ለመሄድ ይወስናል። ግን ከኮተቤ አካባቢ ተነስቶ ወደ መርካቶ ወደ ሚገኘው መናኸሪያ አመራ።ከተሳፈረባት ታክሲ ላይ ወርዶ ትንሽ እንደቆየ ኪሱን ሲፈትሽ ባዶ ነው።
እዚያው መናኸሪያ ውስጥ እሪታውን አቀለጠ። ሰዎች ተሰበሰቡ ግን አንዳች የሚፈይዱት ነገር አልነበረም። ገሚሱ አውቆ ነው የተለመደ ማጭበርበር ነው ሲሉ ተሳለቁ፤ ገሚሱ ደግሞ አይዞህ ብለው የአቅማቸውን ለማገዝ ሞከሩ። ብቻ ሁሉም እንደመሰለው የራሱን ግምትና መላምት እየሰጠ አለፈ።ተስፋዬም ወደ አገር ቤት የመሄድ እቅዱን ሰረዘው። ሃሳቡን ለወጠ። እንደገና ሰርቶ ለመለወጥ እና ገንዘብ ለማጠራቀም ወሰነ። ይሁንና በሆነው ነገር ልቡ ተሰብሮ ነበር እና ንዴቱን ለመርሳት አረቄ እና አልኮል መሰል ነገሮች መቀማመስ ጀመረ። ችገሩን ለመርሳት ብሎ የጀመራት መጠጥ ወደ ሱስ ተሸጋገረ እና ሕይወቱን ተቆጣጠረው። ሥራው ሁሉ ተበላሸ፤ በመጨረሻም መጠጥ ማባረርና ሕይወቱን በሌላ መስመር ውስጥ ሆና አገኛት። አዲስ አበባ ውስጥ ወጥቶና ወርዶ ያጠራቀማትን ገንዘብ በአዲስ አበባ ውስጥ በከተሙ ሰርቆ አደሮች ነገሮች ሁሉ ተጨናገፉበት።
ተስፋዬ ለኑሮው ተስፋ እዘራለሁ ብሎ ለዓመታት ደፋ ቀና ብሎ የደከመበትን ገንዘብ በአንዲት ጀንበር ሲያጣ ወደ ቀድሞ ሕይወቱ መመለስ ከበደው። ኑሮ እየከበደው፤ ነገሮች እየተወሳሰቡ ሲሄድ የጎዳና ሕይወትን መላመድ፤ በረንዳ ማደርን አንድ ብሎ ጀመረ። የሚባለውና የሚጠጣውም መከራ ሆነ። በዓላትን እየቆጠረ ወደ ቤተክርስቲያን እየተጠጋ ምፅዋት መቀበል ጀመረ። በሌላ ቀን ደግሞ በተዝካር፣ ክርስትና፣ ሰርግና ሌሎች ሁነቶች ባሉበት ያገኘውን እየቀማመሰ መኖርን ተያያዘው። በአሁኑ ወቅት ቋሚ አድራሻ የለውም፤ እግሩ በወሰደው ቦታ እየተዘዋወረ ያገኘውን ይቀምሳል፤ ያገኘውን ለመሥራት ይሞክራል። ግን ማታ ላይ ዞሮ ዞሮ ወደ ቤተክርስቲያን አጥር ጥግ ተጠልሎ ይተኛል።
ግን ክረምት በመጣ ቁጥር የሚያሳልፈውን ፍዳ ከባድ እንደሆነ ነው የሚናገረው። በተለይ ደግሞ ብርድና ዝናብ ሲፈራረቅበት ከመሰሎቹ ጋር ተጠጋግቶ ከመተኛት ባለፈ የምናደርገው ነገር የለም ይላል። ብርዱ ይበርድናል፤ ቁሩ ይፈራርቅብናል፤ የፀሐይ ግለትም በተራራው ይፈትነናል ሲል የህይወትን ትግል ይናገራል። ተስፋዬ ነገሮች እንቆቅልሻቸውን ቢከብደውም አንድ ቀን ግን ሕይወቴ ይስተካከል ይሆናል የሚል ተስፋም አለው። እስከ ጊዜው ግን ከቤተክርስቲያን አጥር ስር መከለሉ ግን ግድ ሆኖበታል።
50 ዓመት ተጠግቻለሁ የሚለው ተስፋዬ፤ ያለፈው ሕይወቱ በከንቱ እንደባከነ ለራሱ በትካዜ ይነገራል። ግን ደግሞ ‹‹አናፍ ራቢ ጂራ›› አሊያም ‹‹ለእኔ ፈጣሪ አለ›› እያለ ራሱን ያፅናናል። ነገሮች ከተሣኩለት ወደ ትውልድ ቀየው ተመልሶ መኖርን ይመኛል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር