በእመርታዊ የለውጥ ጉዞ ውስጥ የሚገኝ ዘርፍ

በሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ዕድገት እየተመዘገበ ስለመሆኑ መንግሥት የሚሰጣቸው መግለጫዎች፣ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ። ዕድገቱን ገበያውም፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር አረጋግጠውታል።

ይህ ዕድገት እየታየባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል የግብርናው ዘርፍ በዋናነት ይጠቀሳል። ዕድገቱ/ስኬቱ ለውጡን ተከትሎ በዘርፉ በተካሄዱ የሪፎርም ሥራዎች የተመዘገበ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ስኬቶች እመርታዊ የተሰኙም ናቸው።

ስኬቶቹ ሊመዘገቡ የቻሉት መንግሥት ሀገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም በሚገባ ተገንዝቦ በግብርናው ዘርፍ ላይ በትኩረት በመሥራቱ ነው። ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገው ርብርብ ግብርናው ምርትና ምርታማነቱ በየዓመቱ እየጨመረ እንዲመጣ አስችሏል።

ባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት አነስተኛ ማሳ ካላቸው አርሶ አደሮች እርሻ 530 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን፣ ይህ አኃዝ ዘንድሮ ወደ 610 ሚሊዮን ኩንታል ያደገበትን ሁኔታ ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። በተያዘው የመኸር ወቅት ደግሞ 690 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የሕዝብ ቁጥሯ እየጨመረ ለመጣው፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ለሆነባት፣ ግብርና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ መሣሪያ ለሆነባት ኢትዮጵያ የግብርና ምርት ጨመረ ማለት ትርጉሙ ከምግብ ዋስትና ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም። የምግብ ሉዓላዊነት ማስከበር ጉዳይም አብሮ ይነሳል።

ከአጠቃላይ የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ዕድገት የስንዴን ለብቻ ለይቶ በመመልከት ለውጡን በሚገባ ማሳየት ይቻላል። በመኸርም፣ በበልግም በበጋ መስኖም በስንዴ ልማት በተከናወኑ ተግባሮች ስንዴ የሚለማበት ማሳም፣ የሚገኘው የምርት መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ዓመት 300 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተገኝቷል። ይህ የስንዴ ልማቱ ስኬት ሀገሪቱን ስንዴ ከውጭ ከመግዛት ታድጓታል።

ይህ በስንዴ የተገኘው ምርት በቀደሙት ዓመታት የሀገሪቱ ሀገራዊ የግብርና ምርት መጠንን እንደሚያህል መረጃዎች ያመለክታሉ። በአንድ የሰብል ዓይነት ምርት ብቻ ቀድሞ ዓመታዊ የግብርናው ዘርፍ ምርት መጠንን መድረስ ትልቅ ስኬት ነው።

ይህ የስንዴ ምርታማነት ሀገሪቱ ከአፍሪካ በስንዴ አምራችነት አንደኛ ደረጃን እንድትይዝ እስከ ማድረግ ደርሷል። ስኬቱ በአኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገሮች መንግሥታት እስከ መደነቅ፣ ተሞክሮ እስከመሆን የደረሰም ነው።

በስስት ከምትመለከተው የውጭ ምንዛሪዋ እየቀነሰች ስንዴ ስትገዛ የኖረች ሀገር፣ ለስንዴ ግዥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ስታወጣ በውጭ ጠላቶቿ ከፍተኛ ጫና ሲደርስባት የቆየች ሀገር… ስንዴ በዚህ ልክ አምርታ ራሷን ስትችል መመልከት በእርግጥም መደነቅ ይኖርበታል።

ይህን ከሚነገረውም ከሚገለጸውም በላይ በክብር ቆሞ፣ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እየተናገረ ያለው የስንዴ ልማት ስኬት፣ ለስንዴ መግዣ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ ለመቅረብም ችሏል። የምግብ ሉዓላዊነትን በማስከበር በስንዴ ግዥ ወቅት በተለያዩ ወገኖች ይደርስ የነበረውን ጫና አምክኗል። በስንዴ የሀገሪቱን እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ ኃይሎችን ቅስምም ሰብሯል።

በዚህች ሀገር ከውጭ የሚመጣ ስንዴ ሲታሰብ አብሮት ሲታሰብ የኖረው ርዳታ ነበር። የርዳታ መገለጫው ስንዴ ሆኖ ኖሯል። በአንድም ይሁን በሌላ ከውጪ የሚመጣ ስንዴ የለም ማለት የርዳታ አመለካከቱም እየተሰበረ ይመጣል ማለት ነው። ይህም ሌላው ፋይዳው ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ሌላው በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ መሆን የተቻለበት ቡና ነው። በዓመት ከ700 ሚሊዮን ዶላር ዘሎ የማያውቀው ወደ ውጭ ከተላከ ቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ፣ በ2017 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። የቡና ልማቱና ግብይቱ በየዓመቱ አዳዲስ ክብረ ወሰኖችን እያስመዘገበ፤ ነው አሁን ላለበት ከፍተኛ ደረጃ ደረጃ የበቃው።

ወደ ውጭ የሚላከው ቡና መጠንም የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም ባለፈው በጀት ዓመትም ብዙ እመርታ የመጣበት ነበር፤ በዚያ በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፤ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ የቡና ኤክስፖርት ተብሎ የተመዘገበም ነበር። ዘንድሮም ይህ ክብረ ወሰን ተሰብሯል።

ሀገሪቱ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ቡና አብዛኛው ኮሜርሻል ቡና ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጠው ልዩ ቡና መላክ ላይ ትሠራለች፣ በዚህም ወደ ውጭ ከሚላከው ልዩ ቡና ከፍተኛውን መጠን ወደ መያዝ ተሸጋግሯል። ይህ በብዙ ጥረት የተገኘ ውጤት ነው። ልዩ ቡና የሚያስገኘው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደመሆኑ ለውጡ እመርታዊ ነው ሊባልም ይችላል።

አሁንም በስንዴና በቡና ላይ እየታየ ባለው ለውጥ ባለመዘናጋት ይልቁንም ለበለጠ ለውጥ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። የስንዴና የቡና ልማቱን ከማጠናከር በተጨማሪ በሌሎች የሰብል ዓይቶች ለመድገም እየተሠራ ነው። ይህን ተከትሎም እንደ ሻይ ቅጠል፣ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር ባሉት ላይም ለውጦች እየታዩ ናቸው። በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬም እንዲሁ በተለይ አቮካዶ ላይ በሰፊው እየተሠራ ምርቱም ለውጭ ገበያ እየቀረበ በሀገር ውስጥም የአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እየሆነ  ነው።

ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ያላት እምቅ አቅም በእስከአሁኑ ቁርጠኝነት እንደሚለማ ይጠበቃል፣ መንግሥት ግብርናውን በመደገፍ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ የሚሄድ እንደመሆኑ የምርትና ምርታማነት እድገቱ በቀጣይም በላቀ መልኩ እንደሚጨምር ይጠበቃል።

መንግሥት በማዳበሪያ ድጎማና አቅርቦት ማቀላጠፍ፣ በሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች አቅርቦትና በፋይናንስ ግብርና ሊደገፍ እንደሚገባው በጽኑ በማመን ሲያደርግ የቆየው ተጨባጭ ጥረት ፍሬያማ ስለመሆኑ በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ይህ ዕድገት ያስገነዝባል። ይህ የሜካናይዜሽን መስፋፋት፣ የፋይናንስ ተቋማት ለግብርና ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ የጀመሩበት ሁኔታ ወዘተ ሲታሰቡ ግብርናው ገና ብዙ ዕድገት እንደሚያስመዘገብ መገመት ይቻላል።

እንደ ስንዴ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉትን ክረምት ከበጋ በመስኖ በማምረት በአርሶ አደሩ ዘንድ ማምጣት የተቻለው የሥራ ባህል ለውጥ፣ ዓመቱን ሙሉ ማምረት፣ አንድን ማሳ ሁለትና ሦስቴ ማልማት መቻል ላይ የተደረሰበት ሁኔታ እንዲሁም የሚለማው ማሳ በየዓመቱ እየጨመረ ያለበት ሁኔታ በቀጣይም የምርትና ምርታማነቱ ዕድገት ቀጣይነት ሌሎች ማረጋገጫዎች ናቸው።

ሀገሪቱ ገና በቅጡ ያልለማና ጨርሶም ያልለማ ለእርሻ ሥራ ሊውል የሚችል ሰፊ መሬት ያላት ናት። ይህን ማልማት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ እንደመምጣቱ መጪዎቹ ዓመታት የላቀ ምርት የሚታፈስባቸው ስለመሆናቸው መተንበይ አያዳግትም።

በእርሻ ማሳ ማስፋፋት ላይ በስፋት ተሠርቶ ውጤትም ተገኝቷል፤ ባለፉት ዓመታት አነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች የሚታረስ መሬት ብዛትን ከነበረበት 17 ሚሊዮን ሄክታር ወደ 20 ሚሊዮን ማድረስ ተችሏል። የእርሻ ማሳ የማስፋፋቱ ሥራ አሁንም ቀጥሏል። ዘንድሮ በመኸር እርሻ ብቻ ከ21 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እንደሚታረስ ይጠበቃል።

አንዳንድ ክልሎች ካለባቸው የመሬት ውስንነት ጋር በተያያዘ በባሕር ዛፍ የተያዘ መሬትን ወደ እርሻ እየመለሱ ናቸው። ከዚህ አኳያ የሲዳማ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ባሕር ዛፍ በመመንጠር 12 ሺ ሄክታር መሬት ለእርሻ ሥራ ያዋለበት ሁኔታ ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል።

ለእርሻ ሥራ መዋል ሲገባቸው ያልዋሉ ቦታዎችን ለእርሻ ሥራ እንዲውሉ እንዲሁም ማሳ ጦም እንዳያድር እየተደረገ ያለው ጥረት፣ በተቋማትና በመሳሰሉት ግቢ ውስጥ የሚገኝ ያልለማ መሬት ለሰብል ልማት እንዲውል እየተከናወነ ያለው ተግባር የምርትና ምርታማነቱ ዕድገት ቀጣይነት ሌሎች ማሳያዎች ይሆናሉ።

አንድን ማሳ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ መጠቀም እየተለመደ መጥቷል። በበልግ አምራች አካባቢዎች እንዲህ ዓይነቱ እርሻ ሲሠራበት የኖረ ሲሆን፣ በተለይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከመጣ ወዲህ አንድን ማሳ ሁለት ሦስቴ በማልማት በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ማምረት እየተቻለ ነው፤ አርሶ አደሩ የዚህን ፋይዳ በሚገባ ያጣጣመ በመሆኑ ይህ ሁኔታ በቀጣይም በስፋት እንደሚቀጥል ይታመናል። አንዳንድ አካባቢዎች የበቆሎ አዝመራ ሰብስበው ሌላ ሰብል እየዘሩ ያሉበት ሁኔታ ለእዚህ ማሳያ ይሆናል።

ሀገራችን በመስኖ ሊታረስ የሚችል 10 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህን መረጃ ስንዴን ይዘን ብንመለከተው ከዚህ መሬት ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ብቻ መጠቀም እየተቻለ መሆኑን እንገነዘባለን። እርግጥ ነው የአትክልት ልማትም እየተካሄደ ነው። እንዲያም ሆኖ ሀገሪቱ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት አላት።

ወንዞችን በመጥለፍ፣ የውሃ ጉድጓዶችን በማውጣት፣ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር ብዙ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፤ ይህም ሥራ ቢሆን ሀገሪቱ ካላት የውሃ ሀብት አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይደለም። አርሶ አደሮች እና ክልሎች ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማሽን በማስቆፈር፣ በራሳቸው የጉድጓድ ውሃ በማውጣት፣ ወንዝ በመጥለፍ፣ አስቀድሞ በተገነቡ የመስኖ መሠረተ ልማቶች በመጠቀም ልማቱን እያካሄዱ ይገኛሉ።

በትላልቅ የመስኖ መሠረተ ልማቶች በኩል ግን የመጣ ብዙ ለውጥ አለ ተብሎ አይወሰድም። ትላልቅ የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የመገንባቱ ጥረት መጓተት ይታይበታል። የመስኖ መሠረተ ልማት ግንባታው ሀገር በምትፈልገው ልክ እየተጓዘ አይደለም። ያሉትን የመስኖ መሠረተ ልማቶች ፈጥኖ ለልማት ማዋል ላይም ክፍተት ስለመኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የጋምቤላውን የአልዌሮ ግድብን በመጠቀም አሁን በተያዘው መንገድ የመስኖ ልማት ለማካሄድ የረባ እንቅስቃሴ የተጀመረው በቅርቡ ይመስለኛል። በዚህ ግድብ የግሉ ዘርፍ ቀደም ሲል አንስቶ የሚያካሂደው ልማት ቢኖርም፣ ይህም ከታለመለት አንጻር ውጤታማ የሚባል አይደለም። ይህን ግድብ በመጠቀም የመስኖ ልማት ለማካሄድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥረቶች እየተደረጉ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ጥረቶቹ ፍሬያማ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ይገባል።

የጊዳቦ ግድብ ከተመረቀ በኋላ በተለይ በሲዳማ ክልል በኩል ያለውን ወደ ሥራ ለማስገባት ዓመታት ወስደዋል። አሁን ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ባላውቅም ወጣት የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃንን በማደራጀት በዘመናዊ የግብርና ሥራ ለማሰማራት ከዓመት በፊት የተጀመረ ሥራ እንደነበረ አስታውሳለሁ።

ለመስኖ ልማት የሚውሉ ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ ግድቦች በተለይ በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በኩል እየተገነቡ እንደሚገኙ ይታወቃል። እነዚህ ግድቦች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደዚህ ሥራ ሲገቡ ግን ብዙም አይታይም። እዚህ ላይ በትኩረት ከተሠራ የመስኖ ልማቱ ትርጉም ባለው መልኩ ሊያድግ ይችላል። ግድቦቹ ለትልቅ ዓላማ የሚሠሩ ናቸውና።

በሀገሪቱ ሰፊ የእርሻ መሬት በአፈር አሲዳማነት እየተጠቃ ነው። ይህን አፈር በማከም ወደ ምርታማነት መመለስ እንደሚቻል ታምኖበት እየተሠራ ነው። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተከናወነ ተግባርም ምርታማነትን መመለስ የተቻለበት ሁኔታ መፈጠሩ እየተገለጸ ይገኛል።

በአንድ ወቅት ለእዚህ ሥራ የሚያስፈልግ ኖራ እጥረት ነበር። ይህም ችግር በሲሚንቶ ፋብሪካዎች በኩል እየተፈታ ነው። ግብርና ሚኒስቴር ይህን አሲዳማነት ለማከም በስፋት እየሠራ ሲሆን፣ ይህም ለምርትና ምርታማነት ማደግ የበኩሉን አስተዋፅዖ ያበረክታል።

ሜካናይዜሽን ሌላው ለመጪው ምርታማነት ማደግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይጠበቃል፤ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባሮች በትራክተር የማረስ ምጣኔን ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በተሠሩ ሥራዎች 25 በመቶ ማድረስ ተችሏል። በትራክተር የማረስ ምጣኔን እዚህ ደረጃ ማድረስ የተቻለው ከነበረበት 5 ነጥብ ሰባት በመቶ በመነሳት ነው።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያለው የትራክተር ማረስ ምጣኔ ለእርሻ ሥራ ከዋለው ከ20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ አምስት በመቶው በሜካናይዜሽን እንዲለማ የተደረገ መሆኑን ያመለክታል።

በ10 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ እየተሠራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል። በእቅዱ መሠረት የትራክተር ብዛትን አሁን ካለበት 20 ሺህ አካባቢ ወደ 65 ሺህ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ለሜካናይዜሽን እርሻ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የታመነበት ኩታ ገጠም እርሻም በየዓመቱ እየጨመረ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ይህ ሁሉ ሲሆን ምርታማነቱ የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት አይከብድም።

አረንጓዴ ዐሻራና የሌማት ትሩፋት ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ዕድገት የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ የፍራፍሬ ተክሎች እየለሙ ናቸው፤ የቡና ልማቱ ተጠናክሯል፤ የተተከሉ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች፣ የተጎነደሉ የቡና ዛፎች በቀጣይ የምርትና ምርታማነት ዕድገቱ የት ሊደርስ እንደሚችል ሌሎች አመላካቾች ናቸው።

ማዳበሪያ በምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል። መንግሥት ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ማዳበሪያ በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ መሥራቱን አጠናክሯል። በማዳበሪያ ላይ በየጊዜው የሚታየው የዋጋ ጭማሪ በአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳርፍ ለማድረግ መንግሥት ማዳበሪያ መደጎሙን ቀጥሏል፤ እንደሚቀጥልም ይጠበቃል።

ልማቱ የሚፈልገውን ማዳበሪያ በዚህ መልኩ ከውጭ እያስገቡ መቀጠል እንደማይቻል በመገንዘብም የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት በመንግሥት በኩል ጥናት ተካሂዷል፤ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ለመገንባትም ከናይጀሪያው ባለሀብት ጋር እንደሚሠራ ተጠቁሟል። ፋብሪካውን በ40 ወራት ገንብቶ ለማጠናቀቅም ታቅዷል።

ይህ ሁሉ መጪው ጊዜ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለውን ለውጥ እመርታዊ ማድረግ በሚያስችሉ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች እንደተሞላ ይጠቁማል። ይህን እመርታዊ ለውጥ ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታዎች ብቻ በቂ አይደሉም። እስከ አሁን ሲደረግ የቆው የዘርፉ ኃይሎች ርብርብም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You