የሰኔ 30 ትዝታዎች

በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር አንድ ዓመት በውስጡ አሥራ ሦስት ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፤ ከእነዚህ ከአራቱ ወቅቶች አንዱ ዘመነ ክረምት ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ክረምቱ ሰኔ 26 ቀን ጀምሮ መስከረም 25 ቀን ያበቃል።

ስለ ሰኔ ምን ተባለ?

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሬዲዮ ዜና አንባቢና ታላቁ ደራሲ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ስለ ሁሉም ወራት ባህርያትና ግብር በዘረዘሩበት “የዓመቱ ወራት” የሚል ርዕስ በሰጡት ግጥም ውስጥ፦

‹‹ሰኔ ደሞ መጣ ክረምት አስከትሎ፣ ገበሬው ተነሳ ማረሻውን ስሎ።››

‹‹አንድ ሰኔ የነቀለውን ሁለት ሰኔ አይተካውም››፣ “ሰኔ ሰላሳ የለውም ካሳ” ... የአማርኛ ምሳሌዎች ናቸው።

አቶ ግርማቸው ላቀው ‹‹የኢትዮጵያ 13 ወራትና የሳምንቱ 7 ቀናት ትርጓሜና ምስጢራቸው›› በሚለው መጽሐፋቸው፣ ሰኔ ‹‹ሰን›› ከሚለው ቃል የተወረሰ ሆኖ ‹‹የመመገቢያ ሰሀን›› የሚል ትርጓሜ አለው ይሉናል።

«ሠኔ» ከግዕዙ «ሠነየ» ከሚለው ቃል የተባዛ ሲኾን ‹‹አስጊያጭ፣ አሳማሪ›› ማለት ነው።

ሰኔ በስልጢኛ ቋንቋ “ሰኜ” የተሰኘ መጠሪያ ያለው ሲሆን “ሰኜ” ማለት ደግሞ እህል ወይም ዘር የሚል ትርጓሜ አለው። ምናልባት ወርሃ ሰኔ “የሰኜ”ን ስያሜ ያገኘው ሰኔ የዘር ወቅት መሆኑን ተከትሎ እንደሆነ ያመለክታል።

ሰኔ የቃሉ ምንጭ ትግረ፣ ትግርኛ እንደሆነ ሌሎች ጽሑፎች ያሳዩናል። በትግረ ‹‹ሰነየ›› ማለት መልካም፣ ሰናይ ሆነ፣ አማረ›› ማለት ነው።

ይህ የሰኔ ወር በአርጎብኛ ቋንቋም ጭምር ‹‹ሰነይ›› ይባላል።

አማርኛው በሂደት ቃሉን ከሰነይ ወደ ሰኔ ቀየረና የዚህ ወር መጠሪያ አድርጎታል መባሉን አንብበናል።

እናም…

ወርሃ ሰኔ ለአርሶ አደሩ፣ ለመምህሩና ለተማሪው ልዩና ለሕይወቱ ወሳኝ ትርጉም አለው። ዕድሜና ጤና ከሰጠን በዚህ ዝርዝር ጉዳይ ሌላ ጊዜ የምንመለስበት ሲሆን ዛሬ ግን ስለ ሰኔ 30 ቀን ብቻ ጥቂት ነገር ለማለት ወደድንና እነሆ ብዕርን ከወረቀት ጋር አዛምደናል።

«ሠኔ» ከግዕዙ «ሠነየ» ከሚለው ቃል የተባዛ ሲኾን አስጊያጭ፣ አሳማሪ ማለት ነው……

“ሰኔ ሰለሳ የሴቶች አበሳ” ነው ወይንስ ደግሞ “ሰኔ ሰላሳ የሰነፍ አበሳ?”

ሁላችሁም ሰኔ 30ን እንደምታስታውሱት እናምናለን። ከዓመታት በፊት ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበርንበት ጊዜ የአንዳንድ ጓደኞቻችንን የፊት ገፅታ፣ ፈገግታቸውንና ኩርፊያቸውን በፍጹም አልዘነጋውም። እነዚህ ተማሪዎች ክረምቱ አልፎ፣ መስከረም መባቻ ትምህርት ቤት ተከፍቶ ወደ ትምህርት ቤቱ ግቢ ሲዘልቁ ወይም ወደ ክፍል ሲገቡ ፊታቸው ላይ ይነበብ የነበረው ደመቅ ያለ የልጅነት፣ የዋህነት፣ የፍቅር፣ የናፍቆት ምልክት እስከ ዛሬ ሕያው ነው።

ያ ውብ መልዕክት በጭራሽ ያለመፍዘዙ ምክንያት ደግሞ ጉዳዩ በጥልቅ ትዝታ፣ በንፁህ ፍቅር፣ በቅንነት፣ በተግባቦት የተገነባ ስለነበር ያሻውን ጊዜ ያስቆጠረ ቢሆን እንኳን ትዝታውን በቀላሉ ለመጥፋት አዳጋች ነው። ይህ የምላችሁ ልዩ ምልክት በእኔም፣ በእናንተም ልብ ውስጥ በልዩ ሥፍራና በድንቅ ማህደር ተዘግቦ ያለ ነው። ታዲያ የዚህ ውብ ቀለም ማድመቂያው ተፈጥሮ አልያም ሌላ አጋጣሚ ብቻ ይመስላቹኋል? በፍፁም እንዳይመስላችሁ። የሰኔ 30 አጠቃላይ ድባብ፣ ድብድብና ቡጥጫ ለትዝታ የቀሩ የሾሉ ጥፍሮች ዐሻራ የራሳቸው ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

መቼም ሰኔ ክረምት/ዝናብ/አስከትሎ ግም ሲልም በሉት ጊዜ ወድቆ ጊዜ ሲነሳ በርካታ ነገሮች ይከሰታሉ፤ በሂደትም ይቀየራሉ። እንደሚታወቀው በአንዱ የትውልድ ኑባሬ ውስጥ አልፎ ሌላው ሲተካ የራሱን ታሪክና ትውስታን በወጉ እንደያዘ መጓዙን ይቀጥላል። እነዚህ ብለን እነዚያ የትምህርት ዓለም ገጠመኞች፣ የትምህርት ቆይታ ሂደቶች፣ የአብሮነት ውሎ ድርጊቶች፣ በጎም ይሁኑ ክፉ ታሪኮች አይረሴ ክስተቶችን፣ ጣፋጭ ትውስታዎችን መሰነቃቸው አይቀርም። ቀናቶች እንደዋዛ እየፈጠኑ፣ ወራቶች በዓመታት ሲጣፉ ያለፈው ሁሉ በትዝታ እየተዋዛ ትውስ ባለ ቁጥር እንባ አሊያም ፈገግታን ሲያጭር ይታያል።

ያ ባይሆን ኖሮ ዘንድሮ ላይ ቆመን ድሮ ባላልን ነበር፤ ዛሬ ላይ ሆነን ትናንትን ባልዘከርነው ነበር። ያለፈውን እውነታም በአሁኗ ቅጽበት ላይ ሆነን «ነበር» እያልን ባላወጋነው። ካቻምና ለዓምና፤ ዓምና ለዘንድሮ፤ ዘንድሮ ለከርሞ፤ ብሎም ትናንት ለዛሬ፤ ዛሬ ለነገ የተዘረጋ መሰላል ነውና የቀደመውን ሁሉ “ነበር” ማለታችን አይቀሬ ይሆናል፤ ለዚህም ይመስለናል የብዙ ሙያዎች ባለቤት የሆነው ደራሲ ሰለሞን ሹምዬ ምስጢር በተሰኘው የግጥም መፅሀፉ

“አሁን ቅድም ሆኖ ሲመጣ በኋላ፣

ነበር ብቻ ኗሪ ዘመን እያሰላ።” ብሎ የተቀኘው።

አይ ጊዜ! ወይ ዘመን!

ውድ አንባብያን፦ እንግዲህ ከርዕሰ ጉዳያችን ሰኔ እንዳንርቅ እንጂ የድሮን ነገር ድሮ ያነሳዋል የሚል ነገር ሰምታችሁ ይሆን? እስቲ ደግሞ ዘንድሮ ላይ ሆነን የኛውን ዱሮ በጥቂቱ እናስታውሰው።

እንደሚታወቀው የሰኔ ወር ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበትና ከነበሩበት ክፍል መውደቅና ማለፋቸውን የሚያረጋግጡበት ወሳኝ ጊዜ ነው። በዚህ ወር ልክ እንደ ብርቱ ገበሬ በትምህርት ቤቶችና በመምህራን ዘንድ ሥራ የሚበዛበትና የተለየ ትኩረት የሚሰጥበትም ነው። የሰኔን ወር የመጨረሻውን ቀን በጉጉትና በፍርሃት የሚጠብቁ ተማሪዎች ቁጥር ቀላል አይሆንም።

ተማሪው ውጤቱን በሰርቲፍኬት በተደገፈ ማረጋገጫ የሚቀበልበትና የቀጣዩን ክፍል ዕጣ ፈንታ የሚያውቅበት በመሆኑ ጎበዞቹ ሰኔ 30ን በጉጉት ይጠብቁታል። በትምህርታቸው ደከም የሚሉና የትምህርት መቀበያ ጊዜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ ያሳለፉት ደግሞ በታላቅ ፍርሃትና ስጋት ተወጥረው በቀኑ መድረስ ይታወካሉ።

ከዚህ ባሻገር ግን ሰኔ 30ን ለተለየ ውሎ የሚጠቀሙበት ተማሪዎች ጥቂቶች አልነበሩም። በየክፍሉ ውጤት ተሰጥቶ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደተለመደው ለነገ ቂም ከማያሳድሩበት የትግል ሜዳ ወርደው ለይዋጣልን ፍልሚያ ራሳቸውን የሚያዘጋጁ በርካቶች ነበሩ። የድብድቡን አጀብ ዙሪያውን ከበውና በቡድን ተሰባስበው ተደባዳቢዎቹን የሚያበረታቱና የጀግንነት ወኔን የሚቀሰቅሱ የነገር አድማቂዎች ጥቂት አይደሉምና እንደ ነጻ ትግል ከዳር ሆነው እየጮሁና እያዋከቡ ለተፋላሚዎቹ የጠብ አታሞ ይጎስማሉ። አብዛኞቹም ትርዒቱን ከማየት የዘለለ ለመገላገል ሲፈጥኑ አይስተዋልም።

የየቡድኑ ተደባዳቢ ካለበት ወሳኝ ፍልሚያ ቀድሞ የያዘውን ቀጠሮ ሊሰርዘው አይፈልግም። ይህንን አድርጎት ቢገኝ ለከርሞ የሚለጠፍበትን «ፈሪ ቦቅቧቃ፣አፈ ቦሃቃ” የሚለውን ዘለፋ መቋቋም አይቻለውም።

ዘመነ_ክረምት፦በዘመነ_ውሃ ይሰለጥንና ውሃ አፈርን አጥቦ፣ እሳትን አጥፍቶ በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ፤ ወርሃ ሐምሌ፣ ነሐሴና ጳጉሜ አልፎ መስከረም ሲጠባ ትምህርት ቤት ይከፈታልና ተማሪው ዳግም ሲገናኝ ፈሪ መባልን የማይሹ ተፋላሚዎች በድብድቡ ቢሸነፉም በቀጠሮ ሊገናኙ ግድ ነው። በትግል ሜዳው ድል ቀንቷቸው ግዳይ ባይጥሉ እንኳን ጉልበታቸውን አሳይተው አቅማቸውን ፈትሸዋልና ማንነታቸውን ለማስከበር ያግዛቸዋል።

በእኛ የተማሪነት ዘመን ጎበዝ የሚባሉ ተማሪዎች ሰነፍ የክፍል ጓደኞቻቸውን ለማስኮረጅ ባልፈቀዱ ጊዜ ዓመቱን ሁሉ የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ «ቆይ ሰኔ ሰላሳ እንገናኝ» የሚል ነበር። አንድ ወዳጃችን እንዳለው ልክ እንደ ዓመት ዝክር ወራቱን ሁሉ ሲቆጥሩ የሚቆዩ አንዳንዶችም ራሳቸውን እንደ ስፖርተኛ አበርትተውና ለድብድቡ በእጅጉ ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ። የእነሱ የመደባደብ አዋጅ የሚሰማው ለአብዛኛው ተማሪዎች በመሆኑም ደጋፊዎቻቸውና አጃቢዎቻቸው ይበረክታሉ።

እነዚህ «ጉልቤ» የሚባሉ ትዕቢተኛ ተማሪዎች በበርካቶች ዘንድ የሚፈሩና የሚከበሩ በመሆኑ እነሱን በውዴታም ይሁን በግዴታ ለመደገፍ የሚሰባሰበው የተማሪ ቁጥር የዋዛ አይሆንም። ምናልባት የድብድቡ ዜና አስቀድሞ ቤተሰብ ዘንድ ከደረሰ በዕለቱ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩና ለቀጣዩ ዓመትም ትምህርት ቤት እስከመቀየር የሚደርሱ ወላጆች እንደነበሩ አይዘነጋም።

አይ ሰኔ ሰለሳ! … ዛሬ ላይ ሆነን ወደ ኋላ በሃሳብ ነጉደን ስንመለስ በጣም የሚገርመን ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ቆነጃጅት ሴት ተማሪዎችን የኔ ናት፣ የኔ ናት በሚል ውርርድ የሚደረገው የድብድብ መሰናዶ ነው። በእርግጥ ድብድቡና ፉክክሩ በወንድ ተማሪዎች ላይ ብቻ የተገደበ አልነበረም። የተወሰኑ ሴት ልጆችም በተለየ ዝግጅት ጥፍሮቻቸውን አሹለው የማሳደግ ልምምድ ነበራቸው።

ከዚህ በዘለለ አንድ መጥፎ ትውስታም አለን። ሴቶች የሚፋለሟቸውን ተማሪዎች እይታ ለማደናቀፍና ድሉን ለመቀዳጀት ሲሉ ሚጥሚጣ አልያም በርበሬ ይዘው የሚመጡ ተማሪዎች እንደነበሩ አጋጥመውናል። ደቃቅ አሸዋና አፈር ዓይን ውስጥ ለመክተት የሚሽቀዳደሙትንም አስተውለናል፤ በተለይ ድብድቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ የያዙትን ብናኝ ዓይን ውስጥ የመጨመሩ ዕድል ከገጠማቸው ያለምንም ጥርጥር ተቀባይነት የሌለውን ግጥሚያ በድል ያጠናቅቃሉ። በኋላ ሲታሰብ ግን ስልቱ የጭካኔ ስለሆነ አስነዋሪነቱ ይጎላል።

ታዲያ እንዲህ አይነቶቹ ልጆች ባሾሏቸው ጥፍሮች መቧጠጥ የሚፈልጉት የተፋላሚያቸውን የፊት ለፊት ፊት ብቻ ይሆናል። ይህንን ቡጨራ ማድረጋቸው ገጽታን ለማበላሸትና ልዩ የፊርማ ምልክት ለማኖር ይመስላል! ‹‹ድሉም የእኔ ነው» ብሎ ተሻጋሪ ጉራ ለመጎረር ያግዛቸው ይሆናል።

እግረ መንገዳቸውንም በፊት ላይ ያኖሩት በጥፍር የመቧጨር ዐሻራ ማንነታቸውን የሚያስመሰክር ነውና ማንም እንዳይዳፈራቸው ነጥብ ለማስቆጠር ጭምር ይጠቀሙበታል። እንግዲህ እንዲህ አይነቶቹ ተማሪዎች በዕለተ ሰኔ 30 የሚተውት ዐሻራ ወይም ማህተም ነው መስከረም ድረስ ሳይደበዝዝ የሚቆየው። ሰኔ 30ሳ አስፈሪነቱ በዋናነት ለሴት ተማሪዎች ነው። ምናልባት ‹‹እወድሻለሁ፣ አፈቅርሻለሁ›› ብሏት በነገር የመለሰችው፣ በምላስ የለኮሰችው፣ ወይም በጎ ምላሽ የነፈገችው አኩራፊ”ቆይ ጠብቂኝ ሰኔ ሰላሳ” እያለ መዛቱ የተለመደ ነው፤ «ሰኔ ሰላሳ የሴቶች አበሳ» የሚለውን መርህ አብዛኛው ተማሪ የሚረሳው አይመስለንም።

በእዚያ ቀን የድብድብ ቀጠሮ ካላቸው ተማሪዎች ባሻገር ምንም ሳይነጋገሩ ድንገት በተፈጠረ አጋጣሚ ለጠብ የሚገባበዙ ተማሪዎች ሊያጋጥሙም ይችላሉ። ለምን? ከተባለ ደግሞ ቀኑ ሰኔ 30 ስለሆነ ነዋ! እንዲህ ያለው ቅጽበታዊ ፀብ ሲያጋጥም በተለይ ፈጽሞ ለመደባደብ ላላሰቡት አንዳንድ ተማሪዎች ፈተና የሚሆንበት ጊዜ ይበረክታል። ገላጋይም፣ ተመልካችም ይፈነከታል። ጠቡን ያሰበው ተማሪ የቀደመ ቂሙን የማይረሳና እሱ ብቻ የሚዘጋጅ ስለሚሆንም አንዱ ወገን ያልታሰበ ጉዳትን ማስተናገዱ አይቀሬ ይሆናል።

በእኛ ዘመን የነበረው የሰኔ ሰለሳ ድብድብ የበላይነትን/አይደፈሬነትን ለማስጠበቅ፣ ጀብደኝነትን/ዝናን ለማስመዝገብና የፍቅር ጉዳይንም የሚያካትት ነበር። የፍቅር ጉዳይ ሲነሳ በቀለማት ያሸበረቀ፣ በጦርና በልብ ቅርጽ የደመቀ የፍቅር ደብዳቤ መላላክ እንደ ሕግ የተደነገገ ይመስል ነበር። በነጭ ወረቀት ላይ ምርጥ የልብ ቅርጽ ተስሎ ልቧን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ የሚያልፍ ጦር ይሻጥባትና ከታች የቀይ ቀለም ነጠብጣብ ጣል፣ ጣል ይደረግበታል፤”ልቤ በፍቅርሽ ዘገር ተወግቶ ደሜ እየተንጠባጠበልሽ ነው፤ ይኼንን ተረድተሽ፣ መጠየቄን አድምጠሽ እሺ በይኝና ልቤን አክሚው” እንደማለት ሲሆን ብዙ ጊዜ ወንዶች በዓይን ብቻ አይተው የወደዷትን ተማሪ ስለማፍቀራቸው የሚገልጹበት መንገድ ነውና በርከት ያሉ ደብዳቤዎችን የምታስተናግድ ልጃገረድ የታደለችና የፍቅር ባለ ፀጋ ናት ተብሎ ይታሰባል።

አንዳንዴ ግን ደብዳቤን ተቀብሎ ማስቀመጡ፣ በዝምታ መዋጡ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል። «በፍቅርሽ አበድኩ፣ ተንገበገብኩ፣ እያደርኩ አነስኩ፣ መሞቴ ነው» እያለ ዓመቱን ሙሉ በጦር የተወጋ ልብ እያቀለመ ሲስል የከረመ አፍቃሪ ይሁንታ ማግኘትን ይሻል። ብዙ ጊዜም ደብዳቤው በተማሪዋ መግደርደር አልያም መኩራራት ሳቢያ ምላሽ ሳያገኝ የትምህርት መዝጊያው ሊደርስ ይችላልና።

ለፍቅር ልቡን ክፍት አድርጎ፣ የልቡ ሥዕል በአፎቄ ጦር ተወግቶ ደሙን ያንጠባጠበው ተማሪ/አፍቃሪ/መልስ ሲጠብቅ ቆይቶ እንዳለፉት ወራት ሁሉ እምቢ ወይም እሺ የሚለውን ምላሽ ሳያገኝ ከሰኔ ሰ30 በኋላ ያለውን የመለያያ ክረምት ታግሶ መግፋትን አይፈልግም። እናም…አፍቃሪው ልክ ሰኔ ሰ30ን ጠብቆ «እህሳ!» ማለቱ አይቀርም። ታዲያ የተፈቃሪዋ ምላሽ «እሺ የምትል ከሆነ እሰዬው!እልልል!›› ነው። አሊያም «አይሆንም›› ወይም ላስብበት» ምናምን…የምትል ከሆነ ግን ከዛቻና ማስፈራሪያ ያለፈ የመጀመሪያው ርምጃ ቀለል ያለ በስስት የታጀበ ጥፊ ወይም ምጥን የራሮት ቡጢን ማቅመስ አሊያም በመለስተኛ ካልቾ ማንከባለል ሊሆን ይችላል። «አይ ሰኔ 30!የተማሪ አበሳ» ቢባል ያንሰው ይሆን? ወይስ ሰኔ 30፣ የሰነፍ አበሳ›› ይባልለት?

የሚቀጥለውን በሚቀጥለው ብንቀጥልስ?

ሰናይ ጊዜ! ቸር እንሰንብት!

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በኃይረዲን ከድር / ከአሰላ

አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You