መዲናዋን ከትምባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ

ትምባሆ ዘርፈ ብዙ ጉዳቶች ያደርሳል:: ጉዳቶቹ ደግሞ በዜጎች ጤና፣ ሥነ ልቦና፣ አካላዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ከማድረሳቸው በተጨማሪ አካባቢያዊ ምኅዳር ላይም ተጽዕኖ ማድረሳቸው የበለጠ አስከፊ ያደርጋቸዋል:: ይህ ሁኔታ በታዳጊ ሀገሮች ሲታይ ደግሞ ያለው ሁኔታ በጣም የከፋ ሆኖ ይስተዋላል::

በትምባሆ ምርት ውስጥ እስከ 7000 የሚደርሱ ንጥረ ነገሮች ይገኛሉ:: 250 የሚሆኑት ንጥረ ነገሮች ለተለያዩ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያጋልጡ ሲሆን 70 የሚሆኑት ደግሞ በቀጥታ ለካንሰር በሽታ የሚያጋልጡ ናቸው:: ትምባሆ የሚያስከትለው ጉዳት ለመቀነስና ለመከላከል መንግሥታት የተለያዩ ርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ::

ከእነዚህ ርምጃዎች ውስጥ አንዱ ፍላጎትና አቅርቦት ለመቀነስ የሕግ ማሕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ የሕግ ማሕቀፎች ስንመለከት የዓለም ጤና ድርጅት፣ የትምባሆ ቁጥጥር ማሕቀፍ ኮንቬንሽን (Framework Convention on Tobacco Control/FCTC) ኢትዮጵያ በ2006 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 822/2006 አጽድቃለች::

ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 182 ሀገሮች የዚህ ስምምነት ተዋናይ ሀገራት ናቸው። ኢትዮጵያ ከዚህ አዋጅ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 አውጥታ የዜጎች ጤንነት እንዲጠበቅ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነች ትገኛለች::

በተለይ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ የትንባሆን አስከፊ ጉዳት ከመቀነስ አንጻር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ስንመለከት በአዲስ አበባ ከተማ መድኃኒት እና ምግብ ባለሥልጣን አስተባባሪነት ‹‹ አዲስ አበባ ከተማን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ማድረግ›› የሚል እንቅስቃሴ ሚያዚያ 2013 ዓ.ም. በመመስረት በቦሌ እና በአራዳ ክፍለ ከተሞች በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል:: በቀጣይ ባሉት ዓመታትም በከተማ ደረጃ ከፌዴራል ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራት ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራት ባለስልጣኑ አከናውኗል::

ከባለስልጣኑ በተገኘው መረጃ መሰረት አዲስ አበባ ከተማን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ የተቋቋመው ንቅናቄ ዋና ዓላማ ትንባሆ የሚያስከትለው ጉዳት ለመቀነስና በምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ 1112/2011 የተደነገጉ ክልከላዎችን መሬት ላይ በማውረድ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ነው:: እንዲሁም ወቅትን በመጠበቅ በዘመቻ መልክ የሚሠራ ተግባራትን በማስቀረት ከባላድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወጥ በሆነ ሁኔታ በዕቅድ ሥራዎች ለመምራት እንዲያስችል ነው::

ይህ ተግባር ቀደም ሲል በአንድ ወቅት ሞቅ በሌላ ወቅት ቀዝቀዝ እየተባለ የሚሠራ ተግባርን በማስቀረት ዓመቱን በሙሉ ተመሳሳይ በሆነ አካሄድ የትንባሆን ጎጂ ሁኔታና የማይጨስባቸውን ቦታዎች ግንዛቤ ከማስረጽ በተጨማሪ የቁጥጥር ሥራውም በዚያው ልክ በማካሄድ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በመሆኑ ይበል የሚያስብል ተግባር ነው::

ባለስልጣኑ የንቅናቄው ዋና አካል ይሁን እንጂ ዓመቱን በሙሉ ንቅናቄው በዕቅድ ስለሚሠራ ባለድርሻ አካላቱ ተባባሪ ሳይሆኑ ባለቤት ሆነው እንዲሠሩ ስለሚያደርጋቸው የሚገኘው ውጤትም አመርቂ ይሆናል::

ንቅናቄው አዲስ አበባ ከተማን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ በሚል ሲነሳ አንድም ሰው የማያጨስበት ከተማ ትሆናለች የሚል እሳቤ ያለው ሳይሆን አዋጅ 1112/2011 ትንባሆ እንዳይጨስባቸው ክልከላ የጣለባቸው ቦታዎች ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ በሚል ነው::

እነዚህ ከትንባሆ ጭስ ነጻ እንዲሆኑ የተደነገገባቸው ቦታዎች ምግብና መጠጥ ተቋማት (ሆቴሎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች፣ ግሮሰሪዎች፣ ወዘተ.) በግቢያቸውና ከግቢያቸው ውጭ አስር ሜትር ራዲየስ (ዙሪያ) አይጨስባቸውም:: እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት፣ በወጣት ማዕከላት ወዘተ. በግቢያቸውና ከግቢያቸው ውጭ መቶ ሜትር ራድየስ (ዙሪያ) ትንባሆ እንዳይጨስባቸው እና የትምባሆ ምርት ሽያጭ እንዳይከናወንባቸው ይከለክላል::

በመሆኑም አዲስ አበባ ከተማን ከትምባሆ ጭስ ነፃ ለማድረግ በተጀመረው ንቅናቄ ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል:: የመጀመሪያው ስለ ትንባሆ ጭስ አስከፊ ጉዳት እንዲሁም በአዋጅ 1112/2011 በተቀመጡ ክልከላዎች ዙርያ በት/ቤት እንዲሁም ለንግድ ተቋማት ባለቤቶች እና ለተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ተግባራት መከናወናቸውና እየተከናወኑ መሆናቸው ነው::

ሁለተኛው የቁጥጥር ሥራ ነው፤ በዚህም የትንባሆ ምርት ሽያጭ እና አጠቃቀም በተመለከተ ክትትል በማድረግ በግኝቱ መሰረትም ርምጃ የመውሰድ ተግባር ተሠርቷል፤ እየተሠራም ይገኛል::

በእነዚህ ተግባራትም በመለስተኛ ዳሰሳ ጥናትና በሪፖርቶች የተገኙ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ንቅናቄው ሲጀመር በቀኑ ክፍለ ጊዜ በሁለቱ ክፍለ ከተሞች ከትንባሆ ጭስ ነጻ የነበሩት በወጣት ማዕከልና የጋራ መኖሪያ ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ወደ 30 በመቶ እንዲሁም የምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከ42 በመቶ ያልበለጠ የነበረበት ሁኔታ ይስተዋል ነበር:: አሁን ላይ ግን በከተማ ደረጃ በሁሉም አካባቢ ያለው ሲታይ ከ75 በመቶ በላይ ከትንባሆ ጭስ ነጻ መሆኑን ያሳያል::

ከዚህ በተጨማሪ በተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት ሕብረተሰቡ እንዲሁም የንግዱ ማኅበረሰብ ሕጉን አውቀው ለሕግ ተገዥነት ያላቸው ተነሳሽነት ጨምሯል:: በዚህም ከትንባሆ ጭስ ነጻ የሆኑ ተቋማትና አካባቢዎች ቁጥራቸው በእጅጉ ከፍ ብሏል::

ለተገኙ ውጤቶች የሕብረተሰቡና የንግድ ተቋማት እገዛ ከፍተኛ ሲሆን በቁጥጥር ተግባሩ ደግሞ ከከንቲባ ጽ/ቤት ጀምሮ በአስተባባሪው ግብረ ኃይል በቅንጅት የተሠራው ሥራ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱ እንደሆነ ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል::

ለእነዚህ ውጤቶች መገኘት የነበሩ መልካም አጋጣሚዎች አንዱና ትልቁ ጠንካራ ሕግ መኖሩ ሲሆን ሌላው አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ሲጋራና ሺሻ ማጨስን የሚጠየፍ መሆኑ ነው:: የአስተባባሪው ግብረ ኃይልም የቅንጅት ሥራ እንዲሁም በተለይ በትንባሆ ጎጂነት ዙሪያ የሚሠሩ ሲቪክ ማሕበራት የሚያርጉት እገዛም ተጠቃሽ ናቸው::

ንቅናቄው ሲከናወን ከነበሩ ተግዳሮቶች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የትንባሆ ምርት አምራች ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ነው:: በተለይ ሱስ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች በተለያዩ ሁኔታዎች እንዲያጨሱ መገፋፋትና የተለያዩ አሳሳች ስልቶች በመጠቀም ወጣቶች ለመማረክና ለመሳብ ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል::

የትምባሆ ኢንዱስትሪው የትምባሆ ምርቶችን አጓጊ ለማድረግ ሽታቸውን፣ ጣዕማቸውን ወይም መልካቸውን የሚቀይሩ ቅመሞችን እና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በመጨመር ያለማቋረጥ የመማረክ ሙከራዎች በማድረግ የትምባሆ ምርቶች ጉዳትን ለመደበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።

የትምባሆ ኢንዱስትሪው ከሚጠቀምባቸው ድብቅና አሳሳች ስልቶች መካከል ማራኪ ግብይት/ Glamor­ized marketing/ የሚለው አንደኛ ተጠቃሽ ነው:: የዚህ መገለጫ ደግሞ ቄንጠኛ ዲዛይኖች፣ ማራኪ ቀለሞች እና ማራኪ ጣዕሞች በዲጂታል ሚዲያ ቻናሎችን ጨምሮ ወጣቱን የሕብረተሰብ ክፍል ለመሳብ ስልታዊ በሆነ መንገድ ገበያ ላይ ማዋል ነው:: ሌላው ተጠቃሽ የሚሆነው የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች አደገኛና ሱስ የሚያስይዙ ምርቶች ጉዳታቸው እንዲቀንስ ተደርጓል በሚል ሰበብና ሽፋን ሕፃናት እና ወጣቶችን ለድብቅ ዓላማ ማማለላቸው ነው::

ይህም በመሆኑ የትምባሆ ኢንዱስትሪው የሚጠቀምባቸውን አሳሳች እና አማላይ ስልቶችን በመረዳት በተለይ ትውልድን ከጎጂ ምርቶች ለመጠበቅ እና ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ጤናማ የወደፊት ሕይወትን ለማስጠበቅ በተለይ የሚመለከታቸው ተቋማት በጋራ መሥራት አለባቸው::

ከትምባሆ ኢንዱስትሪው በመቀጠል ሌላው ተግዳሮት በከተማዋ ደረጃም ሆነ እንደ ሀገር በርካታ ሕገ ወጥ የሲጋራ ምርቶች በስፋትና በርካሽ ዋጋ መገኘታቸው ነው:: ከዚህ ጋር አብሮ የሚጠቀሰው ተግዳሮት በአብዛኛው ቁጥጥር የሚደረገው በቀኑ ክፍለ ጊዜ በመሆኑ በምሽቱ ክፍለ ጊዜ የሚስተዋለው የትንባሆ አጠቃቀም ነው:: በቀኑ ክፍለ ጊዜ የተሻለ ቁጥጥር ማድረግ የተቻለ ሲሆን በምሽት በኩል ያለው ቁጥጥር ግን በአብዛኛው በዘመቻ መልክ የሚተገበር ነው::

በሀገሪቱ የሲጋራ ምርቶች በስፋትና በርካሽ ዋጋ በመገኘታቸው አጫሾች ማጨስ በፈለጉ ቁጥር እንዲያጨሱ የሚያበረታታቸው አንዱ ጉዳይ ነው:: ሀገሪቱ የትምባሆ ምርት በእሽግ እንዲሸጥ የሚያስገድድ ሕግ ቢኖራትም በነጠላ (በቁጥር) ሲሸጥ ይስተዋላል:: በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሥራ መሥራት ይገባል:: እንዲሁም በቀኑ ክፍለ ጊዜ የሚደረገው የግንዛቤ ማስረጽ እና የቁጥጥር ተግባር በምሽቱ ክፍለ ጊዜ ስለማይስተዋል ምሽቱን በተመለከተ በዘመቻ መልክ ብቻ ሳይሆን በመደበኛነት በምን መልኩ ቁጥጥርና ርምጃ ይወሰድ ብሎ ትኩረት ሰጥቶ በማለም ወደ ተግባር መግባት ይገባል::

በተለይ የተለያዩ መዝናኛ ቦታዎች በምሽት የሚከናወነው የትንባሆ ተጠቃሚነት ሁኔታ ከአጫሾቹ በተጨማሪ ለትንባሆ ጭስ ተጋላጭ የሆኑትን የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጎዳ ስለሆነ የተቋማቱ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ከፍተኛ ተቆርቋሪነት ተሰምቷቸው ሕጉ በሚያዘው መሰረት ማስቆም ይጠበቅባቸዋል::

እዚህ ላይ ሌላው የምጠቅሰው ጉዳይ ቀደም ሲል በመዝናኛ ሥፍራዎች ትምባሆ ማጨስ ክልክል መሆኑን የሚያመላክት ምስልና ጽሑፍ በየቦታው ከበቂ በላይ አስተውል ነበር:: አሁን ግን ሲጋራ ማጨስ ክልክል ነው የሚል ጽሑፍ በበቂ ሁኔታ እያስተዋልኩ አይደለምና ክልክል መሆኑ መጠቀሱ ጉዳት ስለሌለው መዝናኛ ሥፍራዎች ላይ መለጠፍ አስገዳጅ ቢሆን እላለሁ::

ማሳያ እያደረግን የቆየነው አዲስ አበባ ከተማን በመሆኑ በከተማዋ በ2017 በጀት ዓመት ከተማዋን ከትምባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፣ የዓለም ትንባሆ የማይጨስበት ቀን ምክንያት በማድረግ ደግሞ ቀኑ ከሚከበርበት ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ሁለት ወር በፊት ግብረ ኃይሉ በተለየ ሁኔታ ግንዛቤ የመስጠትም ሆነ የቁጥጥር ተግባራት ከማከናወን አኳያ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል::

የዓለም ጤና ድርጅት ዘንድሮ ቀኑን ለማክበር የያዘው መሪ ቃል “Unmasking the Appeal: Exposing In­dustry Tactics on Tobacco and Nicotine Prod­ucts” (በትምባሆ እና በኒኮቲን ምርቶች ላይ የትንባሆ ኢንዱስትሪ አሳሳችና ድብቅ ስልቶች ማጋለጥ) የሚል ነው::

ይህም በመሆኑ በከተማ ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን በአስራ አንዱ ቅርንጫፎች እና ክላስተሮች ለቀኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ በከተማ ደረጃ በሁሉም የመንግሥት እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ስለ ትንባሆ ጭስ አስከፊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ይከናወናል:: በዚህ መርሃ ግብር ላይ ተማሪዎች ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በትምህርት ቤታቸው ክበባት በኩል ቀደም ብሎ ዝግጅት ቢደረግ መልካም ነው::

ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ደግሞ ደማቅ በሆነ ሁኔታ ከፌደራል፣ ከከተማዋ እና ከባለስልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚገኙበት እንዲሁም ከከተማዋ ነዋሪዎች የተወከሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት የመጨረሻ ደማቅ መርሃ ግብር ይኖራል::

የንቅናቄውን ዋና ዓላማ ለማሳካት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እና የሚመለከታቸው አካላት በባለቤትነት መሳተፍ ይገባቸዋል እያልኩኝ ሌሎች ከተሞችም ከተማቸውን ከትንባሆ ጭስ ነጻ ለማድረግ ከመዲናዋ ተሞክሮ ይውሰዱ እላለሁ::

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ስሜነህ ደስታ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You