
አሁን ዓለም የምግብ ዋስትናውን ከማረጋጋት አልፎ የተመጣጠነ ምግብ ማስጠበቅ ላይ ደርሷል። ለዚህም መሠረቱ ሁለት ነገሮች እንደሆኑ ይገለጻል። የመጀመሪያው ዜጎች በቂ የሆነ ምግብ እንዲያመርቱና እንዲጠቀሙ ማስቻል ሲሆን፤ ሁለተኛው ምግብን መግዛት የሚችል ዜጋን መፍጠር ነው። እኛ ከየትኛው ላይ ነን ከተባለ መልሱ ሁለቱም ገና ልፋትን ይጠይቀናል የሚለው ይሆናል። ምክንያቱም ምርትና ምርታማነትን እንኳን በቅጡ አላረጋገጥንም። ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሰው ምክንያት ግብርናውን በዘመነ መልኩ መጠቀም አለመቻላችን ነው።
እኛ እንደሀገር በተፈጥሮ የታደልን ነን፤ ለሥራ የሚተጋ ሕዝብ አለን፤ የጎደለን ቴክኖሎጂ ነው። ያንንም ባለን አቅም ተጨባጭ ማድረግ አልቻልንም። ይህንን ሳናደርግ ዓመታትን ተጉዘናል። በዚህም ሕዝባችንን መግበን የተሻለ አምራች አድርገን ኢኮኖሚያችንን መገንባት አቅቶናል።
የተባበሩት አረብ ኢምሬት አይነት ሀገራት ምንም አይነት ለእርሻ የሚሆን ለም አፈር ሳይኖራቸው የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠው እናገኛቸዋለን። ለዚህ ያገዛቸው ደግሞ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብታቶቻቸውን በአግባቡ አይተው መጠቀም በመቻላቸው ነው። የተፈጥሮ ሀብታቸው ለዜጎቻቸው ምግብ እንደ ልብ መግዛት አስችሏቸዋል። ሀገራትም መርጠዋቸው ጥሩ ምርቶችን እንዲያቀርቡላቸው አስችሏቸዋል።
ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሀብቷን እንደዚህ ብትመለከትና ብትሠራበት የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ አልፋ ለሌሎች ትተርፍ ነበር። ከዚያም ተሻግራ ዓለም እያደረገ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ ማስጠበቅ ላይ ትኩረቷን ታደርግ ነበር። ሆኖም እንደ ሀገር ግብርናችንን ብቻ ብናነሳ የተመቻቸውን የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ ባለመጠቀሙ ብዙ ጉድለቶች አሉበት።
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ገበሬዎች የእለት ጉርስ ማግኛ፣ የገቢ ምንጫቸው፣ የኢኮኖሚ መሠረታቸው ግብርና ነው። ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የሥራ እድል መፍጠሪያም እርሱ. ነው። ከዚህ አንጻርም ይህ ዘርፍ ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን ማህበራዊውንም ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ይወጣል።
ኢትዮጵያ ያላት አራቱም ወቅቶች ለግብርናው ዘርፍ እድገት ሁነኛ ሚና ያላቸው ናቸው። በጋ ከክረምት ቢሠራባቸው ምርታማነትን በመጨመር የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የማይቻልበት ምንም ነገር የለም። አሁን እየተሠሩባቸው ያሉ ተግባራትን ማጠናከር ከምንም በላይ ያስፈልጋል።
አሁን ደግሞ ያለንበት ወር በበጋ እና በክረምት መካከል የሚገኘው የመኸር ወቅት በመሆኑ በስፋት ልንጠቀምበት የሚገባው ወቅት ነው። ይህ ወር የቀኖቹ ቆይታ የሚቀንስበት እንዲሁም የሙቀቱ መጠን ዝቅ የሚልበትና ምድሪቱ በአረንጓዴ ጸጋዋ የምታሸበርቅበት የለውጥ ጊዜ ነው፡፡
ለውጥ መጀመሪያ ያሉብንን ክፍተቶች መለየትና መድፈንን ይጠይቃል። ከዚህ አንጻርም ባለፉት ጊዜያት በዘርፉ ፈተና ናቸው የሚባሉት የግብርና ልማቱ እውቀትን ከቴክኖሎጂው ጋር በሚገባ አዳምሮ አለመጓዙ፤ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙ፣ በመስኩ ያለው ተቋማዊ የአመራር ሁኔታ ችግሮች የሚታዩበት መሆኑ፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ችግሮች፣ የመስኖ አጠቃቀም ክፍተቶች፣ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና አጠቃቀም ተግዳሮቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው ፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንደሀገር በሦስት የስትራቴጂክ ዓላማዎች መሠራት እንዳለበት ባለሙያዎች ይጠቁማሉ።
የመጀመሪያው ምርታማነትን ሊጨምሩ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን፤ የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን አውቀን መጠቀም ለዚህ ሁነኛ መፍትሄ ይሰጠናል። ተፈጥሮ ሀብት ሲባልም የአየር ንብረት መልከአምድር ብቻ አይደለም። የሰው ሀብታችንን ጭምር ነው። ቴክኖሎጂውን እያፈለቀ ያለው ማንም ሳይሆን የተማረው ኃይል እንደሆነ ግልጽ ነው።
ስለዚህም ፈጠራዎችን በማበረታታት በተለይም እንደሀገር ከፍተኛውን የውጪ ምንዛሬ የምናገኝበትን የግብርና ምርት እንዲያግዝ ማድረጉ ላይ መሥራት ይገባል። በተመሳሳይ ዝናብ ጠባቂ ከሆነው አስተሳሰብ መላቀቅና በመስኖና መሰል አማራጮችን መጠቀምና ምርትና ምርታማነትን መጨመር ያስፈልጋል።
ሁለተኛው የእርሻን ክቡርነት ከማዕዱ በፊት ባለው የእርሻ ተግባራት ጭምር ለማህበረሰቡ ማስተማር ነው። ይህም ምርታማነትን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ምግብ የመግዛት አቅም ይጨምራል። የመሥራትን ባህልም ያዳብራል። ከዘልማድ አሠራርም እንድንወጣ ያደርጋል። በተለይም ጭቃ ውስጥ ገብቶ መሥራት የአርሶአደሮች ተግባር ብቻ እንደሆነ ማሰብን ያስቀራል።
ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ግብርናው በተማረ ኃይል እንዲመራ፤ በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ያደርገዋል። ለዚህም እንደ ሀገር የተጀመሩ ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ ስለመሆናቸው መናገር ለቀባሪው አረዱት ነው።
አሁን በተፈጠረው የትምህርት ሁኔታ ዜጎች ለአርሶአደሩ ያላቸውን አመለካከት እንዲቀይሩና እነርሱም ቢሠሩበት አማራጭና ሕይወታቸውን የሚቀይር ዘርፍ እንደሆነ እንዲመለከቱም እየሆነ ነው። ለዚህም በማሳያነት የምንጠቅሰው በጓሯቸው እንዲያመርቱና ከወጪ ራሳቸውን እንዲታደጉ መደረጉ፤ ተማሪዎች በትምህርትቤት ውስጥ መደብ ተሰጥቷቸው የፈለጉትን ሰብል ተክለውና ተንከባክበው ለፈለጋቸው ዓላማ እንዲያውሉት መፈቀዱና መሰል ተግባራቱ ሁኔታውን ራስን ከመመገብ አልፎ ለሌሎች እስከ መትረፍ የሚደርስ የግብርና ሥራ መጀመሩን የሚነግረን ነው።
ሦስተኛው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት ተደርጎ መንቀሳቀስ መቻል ነው። ሥራን ሳይጀምሩ በእቅድ ጨርሶ ወደ ተግባሩ መግባት ብዙ ነገሮችን ያቀላል። ችግሮች እንዳይከሰቱ ከማድረጉም ባሻገር የሚፈጠሩ ችግሮችንም ፈጥኖ ለመፍታት ያስችላል። ስለሆነም የግብርና ዘርፉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ከምንም በላይ ያስፈልገዋል።
ማዳበሪያ ማስገባትና ማሰራጨት፤ ለሰብል ጥበቃ የሚሆኑ መድሃኒቶችን በቂ በሆነ መልኩ ማቅረብ፤ ለአርሶ አደሩ የተሻሻለ ምርጥ ዘር ማቅረብ፤ ባለሙያዎች እንዲያማክሩ እድሎችን ማመቻችት ደግሞ ወሳኝ ናቸው ከሚባሉት ተርታ ይመደባሉ። በዚህ ደግሞ አሁን ያለንበት የግብርና ወቅት መኸር በመሆኑ እንደ መንግሥት በትኩረት እየተሠራ ስለመሆኑ በግብርና ሚንስቴር በኩል ሲያሳውቅ ሰምተናል ።
አሁን ላይ መንግሥት ሀገርን የሚታደገው ግብርናው እንደሆነ አምኗል። ለዚህም በሁሉም ዘርፍ ግብዓት ይሆናሉ ያላቸውን በማከናወን ላይ ይገኛል። ይህ ደግሞ በውጤት እየተተረጎመ እንደሆነ የሚያሳዩን ተግባራት አሉ። አንዱ ግብርናው ላይ የሚሳተፈውን ዜጋ ማስፋት ነው። ለዚህም በአብነት የምንጠቅሰው ግብርናው ላይ የሚሳተፈው እንደ እስከዛሬው አርሶአደሩ ብቻ ሳይሆን ከተሜውም፤ ተማሪውም ሆኗል።
መሬት ፆሙን እንዳያድር ያለውን ሁሉ እየዘራ በግቢው ሳይቀር ምግቡን ማጨድ ጀምሯል። ዝናብ ጥበቃም ቀርቷል። ወራቱን ሁሌም የሰብል ወቅት ለማድረግ ቆሻሻ ውሃን ሳይቀር አጣርቶ ይጠቀማል። ዛሬ ሀገር እየጨመረ የመጣውን የምግብ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን እየተጋች ያለችው መፃኢ እድሎቿን ብሩህ ለማድረግም ጭምር ነው።
አብዛኞቹ ምርቶቻችን ላይ የወጪ ምርት አቅርቦት መጓደል ያጋጥማቸው ነበርና እርሱን በማሻሻል ገቢዋን ሳይቀር ከፍ ለማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ መጪው የመኸር ወቅት እንደሚያግዛት በመተማመን ተስፋ ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች ነው። ይህ ወቅት በግብርናው ዘርፍ ሰፊ ቦታ የሚሰጠውና በጉጉት የሚጠበቅ ስለሆነም አርሶ አደሮች መሬት ከማረስ ጀምሮ ብዙ ተግባራትን እያከናወኑ ነው፡፡
አርሶ አደሩ አሁን ላይ መንግሥት በዘርፉ እያሳየ ያለውን መነቃቃት ተከትሎ መሬት ጦም እንዳያድር ረግረጋማ ቦታዎች ጭምር የእርሻ መሬት እንዲሆኑ እየተሠራ ነው። ለሰብል ጥበቃ፤ማዳበሪያ፤ ሜካናይዜሽን ሥራዎች ራሱን እያዘጋጀ እንዳለ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህ ደግሞ በምግብ እህል እራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ጥልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በክብረ መንግሥት
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም