የግንባታው ዘርፍ እንዴት ይደግ ?

የኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መሠረተ ልማት አውታሮች፣ ፋብሪካዎችንና መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በእጅጉ እያሳደጉ ካሉና በቀጣይም ሊያሳድጉ ከሚችሉ ዘርፎች ውስጥ በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ከፌዴራል መንግሥት ካፒታል በጀት ውስጥ ከ55 እስከ 66 ከመቶ የሚሆነው ለግንባታው ዘርፍ የሚውል መሆኑም የዘርፉን ጠቀሜታ አጉልቶ ያሳያል። ዘርፉ ከግብርና ቀጥሎ ከፍተኛ የሰው ኃይል የያዘና ለሌሎች ዘርፎችም ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ከመሆን በዘለለ ከፍተኛ ግብር ከሚያስገኙ መስኮች ውስጥ ዋነኛው በመሆኑ ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ ነው።

መንግሥት ይህን ዘርፍ ለማበረታታት የአቅም ግንባታ ፕሮግራም በመቅረፅ በሥልጠና፣ በማሽነሪ አቅርቦት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማውጣት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ እድገትና ብቃት መሻሻል ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ ቢልም ጥረቱ ግን በበቂ ሁኔታ ለዘርፉ እድገት ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ብዙዎች ይስማማሉ።

ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋፅኦ ያህል የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዳይወጣ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን መንግሥትም ሆነ ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን በጋራ ለመፍታት እያደረጉ ያሉት ጥረትም አርኪ እንዳልሆነ ይነገራል።

የእንፉቅቅ እየተጓዘ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ የግንባታ ዘርፍ ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት የግንባታ ዘርፍ ጋር ሲነፃፀር አሁንም ገና ብዙ ይቀረዋል። በተለይ ደግሞ ዘርፉ አሁንም ድረስ እውቀትን መሠረት ባደረገና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በተከተለ መልኩ እየተከናወነ ባለመሆኑ እድገቱ አዝጋሚ ስለመሆኑ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ።

የኮንስትራክሽን ዘርፉ እስካሁን ያካባተውን አቅም በማገዝ ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግና በጥቂት ዓመታት ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን ታዲያ በርካታ የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንዳሉም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።

የዘርፉ ባለሙያዎች የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግና ለማዘመን ቀዳሚው መፍትሔ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሁለንተናዊ የዕድገት ስትራቴጂ ማዘጋጀትና በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊተገበሩ የሚገቡ አካሄዶችን መወሰን ነው ይላሉ።

ይህም አንደኛ በአጭር ጊዜ እቅድ በንዑስ ሥራ ተቋራጭነት /sub-contract modality/ የግንባታ ዘርፉን ፈር ማስያዝ ያስችላል። ለዚህም የውጭም ሆኑ የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች በሚወስዱት ሥራ ላይ ለንዑስ ሥራ ተቋራጮች የሚሰጡት ሥራ ዓይነትና መጠን በመቶኛ እየተሰላ እንዲሰጡ የሚያስገድድ ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል። ይህም አካሄድ የሥራ ተቋራጩንም ሆነ በሥራ ተቋራጩ ሥር የሚሠሩ ባለሙያዎች የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ፣ ዘመናዊ የኮንትራት አስተዳደር ክህሎት እንዲያዳብሩ ከማስቻሉም በላይ የፋይናንስ ሽግግርንም ያሳልጣል።

አሠራሩ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ተበጅቶለት በጨረታ ወቅት ከሚቀርብ እጩ ንዑስ ሥራ ተቋራጭና ከሙያ ማህበራት ጋር በመሥራት በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱና ምንም እሴት ሳይጨምሩ በማገናኘት/በድለላ/ ሥራ ላይ ያሉ ተዋንያንንም ይቀንሳል። አሠራሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሥራ ተቋራጮች በሚወስዱት ሥራ ላይ ተፈፃሚም ይሆናል።

ይኸው አሠራር ከደረጃ አንድ እስከ አነስተኛና ጥቃቅን ያሉ ማህበራትን ባስተሳሰረ መልክ ለመሥራት የሚያስችል በመሆኑ በየደረጃው የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ከማድረጉም በላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግንባታው ዘርፍ አንድ ዓይነት አተያይና የእውቀት አተገባበር እንዲሰፍን ያደርጋል።

በሁለተኛ ደረጃ የመካከለኛ እቅድ የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጩ በንዑስ ተቋራጭነት የሚያገኘውን ልምድ ግምት ውስጥ በማስገባት ከውጭ ሀገር ሥራ ተቋራጮች ጋር በጥምርት/joint venture/ እንዲሠሩ፤ የተለየ ልምድና ብቃት በማይጠይቁ ሥራዎች ላይ ደግሞ የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ከሌሎች የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ጋር በጥምረት /joint ven­ture/ በመሥራት የተቋራጮችን ወይም የባለሙያዎችን አቅምና ልምድ ማሳደግ ያስችላል። ይህም የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ከውጭ ሀገር ሥራ ተቋራጮች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

በሶስተኛ ደረጃ የረጅም ጊዜ እቅድ ደግሞ በንዑስ ሥራ ተቋራጭነት ይሠራ የነበረው የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ እቅዶች ውስጥ ከተጠቀሱት ልምዶች ተነስቶ ዋና ተቋራጭ /main contractor/ ሆኖ ይሠራል፤ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ደግሞ የልዩ ሥራ ንዑስ ተቋራጮችን በአጋርነት በመያዝ /specialized sub-contractor/ በመሆን ለትላልቅ ሥራዎች ራሱን ያዘጋጃል፡፡

በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኙ ትልልቅ ሥራ ተቋራጮች በሀገራቸው የውጭ ሥራ ተቋራጮችን ሥራ ተክተው ከመሥራት ባለፈ ባገኙት ልምድና ተቀባይነት ከሀገር በመውጣት በጎረቤትም በሌሎች የተለያዩ ሀገራት ሊያሠራ የሚያስችል አቅም ያጎለብታሉ።

ሁለተኛውና በዚህ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ለግንባታው ዘርፍ ማደግ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለው ከሚጠቁሟቸው የመፍትሄ ሃሳቦች ውስጥ የጠነከረ የቁጥጥር ማሕቀፍ ማዘጋጀትና በዚሁ አግባብ መከታተል ይገኝበታል።

በዚህ እሳቤ መሠረትም የቁጥጥር ማሕቀፍ መጠናከር የገንዘብ ብክነት ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ለሕግ የበላይነት ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋል። በረጅም ጊዜ ሂደት ደግሞ የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጭ አገልግሎቱን ከሀገር ውጭ በመስጠት ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ይረዳዋል።

የቁጥጥር ማሕቀፉ መሬት ወርዶ እንዲሠራበት ከተፈለገ ታዲያ በቅድሚያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተቆጣጣሪ ቦርድ / constraction sector regulatory body/ ማቋቋም ያስፈልጋል። ይህም በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የሚኖሩ ሕግጋቶች፣ ውድድሮችና ቁጥጥሮች በአግባቡ እንዲከናወኑ ከማድረጉም ባለፈ ማንኛውንም አሠራር በጥናት ላይ በተመረኮዘ መልኩ ለማከናወን ያስችላል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወጥነት ያለው የግንባታ ፅንሰ ሃሳብን እስከ መጨረሻ ተልዕኮ መሳካት ድረስ ባሉ የግንባታ ፕሮጀክት ሂደቶች ውስጥ መተግበርና ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ በሥራ ላይ የዋሉ ሕጎች በሚገባ እንዲተገበሩ ያደርጋል። ይህንኑ ተከትሎ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ከፍተኛ እንዲሆንና በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ሁሉ ለሕግ የበላይነት ተገዢ እንዲሆኑ ያስችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ የዘርፍ ባለሙያዎች በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያለውን የግዢ ሥርዓት ለብዙሃኑ የዘርፉ ተዋንያን ተደራሽ ማድረግና ዘርፉን ከብልሹ አሠራር በፀዳ መልኩ እንዲመራ ማስቻል ለዘርፉ መጎልበት ዓይነተኛ ሚና ከሚጫወቱ ነጥቦች ውስጥ ሶስተኛው ነው ይላሉ።

ይሁን እንጂ የግንባታው ዘርፍ የግዢ መስፈርትና ሥርዓት በአብዛኛው የሚከወነው በቀጥታ ከሙያው ጋር ግንኙነት በሌላቸው ባለሙያዎችና ተቋማት ነው። ይህ ደግሞ ዘርፉ ለከፍተኛ ብልሹ አሠራርና ለገንዘብ ብክነት ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል። ያለ አግባብ በተቀመጠ የግዢ መስፈርትና ብልሹ የግዢ ሥርዓት አፈፃፀም ምክንያት ብቸኛው ሥራ ተቋራጭ የሥራ እድል እንዲነፈግና ጥቂት የማይባሉ ሥራ ተቋራጮችም ድርጅታቸውን እንዲዘጉ ብሎም ሠራተኞቻቸውን እንዲበትኑ አስገድዷቸዋል።

ከዚህ በመነሳትም የገዢ መስፈርቱ አብዛኛውን ተደራሽ እንዲያደርግ የሥራ ተቋራጮችን አቅም በማጥናት መስፈርቱ እንዲሻሻል በማድረግ የግዢ ሥርዓቱ በአግባቡና ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ መሆኑን በቅድመና ድህረ ኦዲት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

የግዢ ሥርዓቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲታገዝና ከፍ ባለ ተቋም ስር በማደራጀት ቀጥታ የሙያ ችሎታ ባላቸው ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ ይገባል። ለሁሉም ሀገር በቀል ሥራ ተቋራጮች የሥራ እድል ሊፈጥር በሚያስችል ሁኔታና ፍትሃዊ፣ አሳታፊ፣ ግልፅና ወጥነት ባለው አሠራር እንዲመራ ለማስቻል ከሁሉም መንግሥታዊ ግዢ ፈፃሚ አካላትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል።

አራተኛውና ለግንባታው ዘርፍ መጎልበት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠቁሙት ሃሳብ ብቃት ያላቸው የውል አስተዳደር /contract administration/ አካላት መኖር ሲሆን ከዚህ በተቀራኒ ግን በኢትዮጵያ የተፈረሙ የሥራ ውሎችን የሚያስተዳድሩ አካላት በኮንትራት አስተዳደር ዙሪያ የሥራ ተቋራጩን አበሳ እያበዛ የመጣ ችግር ሆኗል ይላሉ።

እነዚሁ የሥራ ውሎችን የሚያስተዳደሩ አካላት ብቃት የሌላቸው፤ አሠራራቸውም ፍትሃዊነት የጎደለው ሆኖ ይታያል። አንዳንዴም አሠራራቸው አሠሪን፣ መንግሥትን፣ ሕዝብንና የሀገር ጥቅምን ያላስቀደመ ነው። በውል አስተዳደር ኃላፊነት ቦታ ላይ የተሰየሙ ግለሰቦችም ሁሉም ባይሆኑ አንዳንዶቹ ቅንነት፣ ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነት የጎደለው የውል አስተዳደር ውሳኔ ሲያሳልፉ ይታያሉ። ከዚህ አንፃር ብቃት ያላቸው የውል አስተዳዳሪ አካላት መኖር ለዘርፉ ማደግ ወሳኝ ነው።

የተሟላ ዲዛይን በወቅቱ ማስረከብም ለግንባታው ዘርፍ ማደግ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚስማሙበት አምስተኛው ነጥባቸው ሲሆን በግንባታው ዘርፍ በተደጋጋሚ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው በአማካሪ መሀንዲስ በኩል የተሟላ ዲዛይን በወቅቱ ያለ ማስረከብ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ። ዲዛይን በሥራ ተቋራጮች በሚከናወኑባቸው ፕሮጀክቶችም ጭምር የዲዛይን ሥራ በተቋራጮቹ በኩል ቢቀርብም እንኳን በአማካሪው በኩል የሚከናወነው የማፀደቅ ሂደት በጥቃቅን ምክንያቶች የሚጓተትበት ሂደት እንዳለም ይጠቁማሉ።

በዚህም የተነሳ ፕሮጀክቶች ለከፍተኛ መዘግየት ከመዳረጋቸውም በዘለለ ሥራ ተቋራጮች ለከፍተኛ ወጪ ይዳረጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ችግር ምክንያት በሥራ ተቋራጮች በኩል የሚቀርቡ የጊዜም ሆነ የዋጋ ማካካሻ ጥያቄዎች አማካሪው የራሱን ድክመት ለመሸፈን በሚያደርገው ጥረት የተነሳ ተገቢውን ምላሽ ሳያገኙ ይቀራሉ።

ከዚህ አኳያ አማካሪዎችም ሆኑ አሰሪዎች ለሚሠሩት ሥራ ተጠያቂዎች የሚሆኑበት ተቋማዊ የውለታ አስተዳደርና አማራጭ የግጭት አፈታት አሠራሮችን በጥናት ላይ ተመሥርተው ተግባራዊ ቢያደረጉና የግንባታውን ዘርፍ በባለቤትነት የሚመራ፣ የቅርብ ክትትል የሚያደርግ፣ በቅርበት የሚደግፍና የአቅም ግንባታ የሚያከናውን ተቋማዊ አደረጃጀት ቢፈጠር ዘርፉን በፍጥነት ማሳደግ ይቻላል። ከዚሁ ጎን ለጎን በሰው ኃይል ግንባታ ላይም የተጠናከሩ ሠራዎችን መሥራት በተለይ ደግሞ ተከታታይ ትምህርትና ሥልጠና በሁሉም ደረጃ እንዲሰጥ ማድረግ ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ለግንባታው ዘርፍ ማደግ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለው በመጨረሻ የሚያነሱት ነጥብ በሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብዓት ልማት ላይ በስፋት መሥራትን ነው። በዚህ እሳቤ መሠረትም በጥናትና ምርመር ላይ በተመረኮዘ መልኩ የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብዓት ልማትን በማጠናከር ከውጭ ሀገር የሚመጡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡

የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮችን ልማት ያካተተና በመካከለኛና አነስተኛ ደረጃ የሚገኙ ሥራ ተቋራጮችን ትኩረት ያደረገ ኮርፖሬሽን ልማት ሊኖር እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ጠቅሰው፤ በቴክኖሎጂ ልማትም ትክክለኛና ተስማሚ፣ ጉልበት ላይ መሠረት ያደረገ ቴክኖሎጂና የቴክኖሎጂ ሽግግር ብሎም የኢንፎርሜሽንና ግንኙነት ቴክኖሎጂ በኮንስትራክሽን ልማት አውድ ውስጥ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ መሥራት እንደሚያስፈልግም ያመለክታሉ።

የግንባታውን ዘርፍ ለማሳደግና ለማዘመን የዘርፉ ባለሙያዎች ከላይ የዘረዘሯቸው ሃሳቦች እንዳሉ ሆነው መንግሥት በግንባታው ዘርፍ የሚጠበቅበትን የመሪነት ሚና ዘርፉ ከሚፈልገው አንፃር መወጣት ከቻለ የዘርፉ ተዋንያንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትክክለኛው የአሠራር ሥርዓት ውስጥ ገብተው የድርሻቸውን የሚወጡበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ብዙዎቹን ያስማማል።

ሚልኬሳ ተሾመ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You