
ባለፉት ሰባት ቀናት የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት የተመለከቱ ሦስት ዐበይት ሁነቶች ተካሂደዋል። ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ መልስ ፍለጋ የሚደረገው ሂደት አንዱ ሊያጠነጥንበት የሚገባው ጉዳይ ርዕሰ ጉዳዩን ቋሚ ሀገራዊ አጀንዳ ማድረግ ነው። ከእዚህ አንጻር አበረታች እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ቢሆንም በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
የመጀመሪያው መድረክ የተሰናዳው በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ነው። የአውሮፓና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አማካሪ እና የአውሮፓና ዓለም አቀፍ ሕጎች ፕሮፌሰር የሆኑት አምባሳደር ግሬጎር ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ “The Right of Landlocked States in Relation to Access to the Sea under International Law” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረግህ መርህ በሚካሄድ ድርድር የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት የተለያዩ አስረጂዎችን በመጥቀስ ዝርዝር ሃሳቦችን አቅርበዋል።
ፕሮፌሰሩ ያቀረቡትን ጽሑፍ ተከትሎ በመድረኩ የታደሙ ምሁራን፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ሌሎች ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን ሰንዝረው ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። ዩኒቨርሲቲዎቻችን መሰል መድረኮችን በማሰናዳት የሃሳብ መሪነታቸውን በመጨበጥ ማረጋገጥ አለባቸው። እጀግ ቅር የሚያሰኘው ነገር ይህን የመሰለ ትልቅ ትርጉም ያለው መድረክ ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት የነበረና ቀደም ብሎ በማስታወቂያ የተነገረ ቢሆንም፤ አብዛኞቹን የመንግሥት ዋና ዋና ሚዲያዎች ጨምሮ የግሉ ዘርፍ የሚዲያ ተዋንያኖች በመድረኩ አልተገኙም።
በሌላ መድረክ ደግሞ በእዚሁ የባሕር በር ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ሁለት ዝግጅት አሰናድቶ ነበር። የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ያዘጋጃቸው ሁለት መድረኮች የሕልውና ጉዳይ የሆነው የባሕር በር ጥያቄን ማስመለስ እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን አጽንኦት የተሰጠባቸው ናቸው። በመድረኩ እንደተገለጸው፤ የቀጣናውን ትስስር በጠበቀ መልኩ ማደግ፣ መልካም ገፅታን መገንባት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባሕር በር አማራጭ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል። የኃያላን ሀገራትን ትኩረት እየሳበ የሚገኘው የቀይ ባሕር ቀጣናው አካባቢውን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ አድርጎታል።
ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ጥያቄ ከፊት ሆነው መምራት ከሚጠበቅባቸው ተቋማት እንዱና ዋነኛው ነው። እንዲህ እንደ አሁኑ የባሕር በር ጉዳይን አጀንዳው በማድረግ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት መድረኮችን መፍጠሩ ይበል የሚያሰኝ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር ነው።
በመድረኮቹ በተካሄዱት ውይይቶች የባሕረ ሰላጤው እና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የኢኮኖሚ እና የፀጥታ ትብብርን በመዳሰስ ያሉ እድሎችን፣ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች ተዳስሰዋል። በእዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን ለማረጋገጥ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኗ ተነግሯል። የተቋማት መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች በባሕረ ሰላጤው ሀገራት እና በአፍሪካ ቀንድ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ እና የጸጥታ ግንኙነት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚመክሩም ተገልጿል።
የሀገር ሙሉ የሆነ ግዛት የሚረጋገጠው በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ጭምር በመሆኑ ራሳችንን በመቻል ከጥገኝነት መላቀቅ አስፈላጊ ነው። ኢኮኖሚን ከፍ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ሎጀስቲክስ ማመቻቸት እና የንግድ ሂደት ማሳለጥ ነው። አንድ ሀገር በኢኮኖሚ ጠንካራ ሆና ወታደራዊ ኃይሏ ካልፈረጠመ ጉዳቱ ያመዝናል። የወጪ እና ገቢ ንግዷ በቀይ ባሕር በኩል የሆነው ኢትዮጵያ በቀጣናው ደህንነቷን የሚያስጠብቅ እና የሚከላከል ኃይል አለመኖሩ መልካም አይደለም። የራሳችን ወታደር በቀጣናው እንዲኖር፣ የባሕር በር አማራጭ እንድናገኝ ብሎም ሉዓላዊነታችን እንዲጠበቅ ጥያቄያችንን ማስመለስ ይገባናል።
ኢትዮጵያ ታሪክን፣ መልክዓ ምድርን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይን መሠረት በማድረግ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ጥያቄ የማንሳት መብት አላት። የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት ያደረገ በመሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ፍትሐዊነት ያለው ነው። የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን እያነሳች የምትገኘው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝ ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መንገድ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የሀገራትን ድጋፍ ለማግኘት መንቀሳቀስና የተለያዩ ኮንፍረንሶችን በማዘጋጀት ሙግቶችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹ የዘርፉ ሰዎች ብዙ ናቸው።
የተባበሩት መንግሥታት የባሕር በር ሕግ አንቀጽ 69 የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢው ያለውን የባሕር በር የመጠቀም እና የመሸጋገር ዓለም አቀፍ መብት እንዳላቸው በግልጽ አስቀምጧል። ይህ መብት በአካባቢው ሀገራት መካከል በሚካሄድ ድርድርና ስምምነት ሊፈጸም እንደሚገባ በአንቀጹ ተጠቅሷል።
የተባበሩት መንግሥታት የባሕር በር ሕግ አንቀጽ 27 ደግሞ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት በስምምነት ካልተደረገ በስተቀር ለተገለገሉበት የባሕር በር ምንም ዓይነት የትራፊክ ታክስ ወይንም ሌላ ክፍያ እንደማይጠየቁ ይደነግጋል። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ሕጎችን በመጠቀም በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውን ቀይ ባሕር የመጠቀም መብቷን ማስከበር ትችላለች።
ዓለም አቀፍ ሕጎች በሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚዳኝ እና የሚያስተዳደሩ ሕጎች ናቸው። በሁለት ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚዳኙና ችግሮችም ሲያጋጥሙ ውሳኔ የሚሰጡ ናቸው። ዓለም አቀፍ ሕጎች የሚመነጩት ሀገራት ካደረጓቸው ውሎች ነው። የዓለም አቀፍ ውሎችን ስንመለከት ኢትዮጵያን የባሕር በር የሚያሣጣት ወይም እንዳታገኝ የሚያግዳት አንዳችም ነገር የለም።
በዓለም ላይ ከሚገኙት የባሕር በር የሌላቸው 44 ሀገራትም ሆን በአፍሪካም ከሚገኙት 16 የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት የኢትዮጵያን ያህል ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለው ሀገር የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 130 ሚሊዮን ተሻግሯል። ይሄንን የሚያህል ሕዝብ ያላት ሀገር የባሕር በር አልባ ሆና እንድትቀጥል የምትገደድበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።
መግነጢስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም