ቅድመ- ታሪክ
ልጅነቱን በቡረቃ አሳልፎ ፊደል በቆጠረባት ደብረማርቆስ እስከ አስረኛ ክፍል ተምሯል። አስረኛ ክፍል ሲደርስ ወደቃጣዩ ደረጃ መሻገር አልቻለም፤ የነበረበት ዕድሜ አፍላ ነበርና ገንዘብ ማግኘትና ራስን መቻል አማረው። ያለማሰለስ ሥራ ማፈላለግ ያዘ። እሱን የሚመጥን መተዳደሪያ አላጣም። በከተማዋ ለብዙዎች እንጀራ ማግኛ ከሆነው የመብራት ሃይል መሥሪያቤት ተቀጥሮ ደሞዝተኛ ሆነ።
ቢተው አማረ በወቅቱ የሚከፈለው ገንዘብ ለፍላጎቱ በቂ ነበር። እኩዮች በትምህርት በልጠው ትተውት ቢያልፉም እምብዛም አልተቆጨም። በየወሩ የሚቆጥረውና በትርፍ ሰዓት የሚያገኘው ክፍያ ተዳምሮ አበረታው። ያሻውን ማድረጉና በገንዘብ ማዘዙ ውስጡን አረካው።
ወጣቱ ውሎ ሲያድር የጓደኞቹን መለወጥ ተረዳ። በርካቶች በጀመሩት በርትተው ገፍተዋል። ከነዚህ መሀል ጥቂት የማይባሉት ዩኒቨሲርቲ ገብተዋል። ከምረቃቸው በኋላ ከእሱ በተሻለ ደሞዝ የሚከፈላቸው እንዳሉም ሰምቷል። የእነሱን ለውጥና የፈጠነ እርምጃ መጠነ። ዛሬ ባልንጀሮቹ ከእሱ ማንነት በእጅጉ ርቀዋል።
አሁን ከእኩዮቹ ጋር በእኩል ዓይን የሚያየው የለም። ይህ ሲገባው ቆም ብሎ ራሱን ፈተሸ። እሱን መሰል ጓደኛ ፈልጎ ማግኘት አልቻለም። እየቆየ በቁጭት መንደድ ጀመረ። ሀሳብና ትካዜ አብሮት ውሎ አደረ። ይህኔ ሌት ተቀን ቢሮጥ እነሱ ካሉበት እንደማይደርስ ገምቶ ተስፋ ቆረጠ።
ወዶ ዘማች
ቢተውና ትምህርት ከተለያዩ ቆይተዋል። አንዳንዴ ድንገት ደርሶ ያቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል ይፈልጋል። ይህ ሀሳቡ ግን እምብዛም ሳይጓዝ እንደጉም ይበተናል። በዚህ መወላወል መሀል እንዳለ አንድ አጋጣሚ ተከሰተ። የኢትዮ -ኤርትራ ጦርነት።
ይህ ጊዜ አገራዊ ስሜት የተቀጣጠለበት፣ ትንሽ ትልቁ በአንድ ቋንቋ የተግባባበት ጊዜ ነበር። ሀገር ተደፈረች፣ ድንበር ተጣሰ ይሉት ዜና በርካቶችን አስቆጥቶ ለዘመቻ አነሳስቷል። በተለይ እንደ ቢተው ላሉ ወጣቶች ይህ አይነቱ ድፍረት ማንነታቸውን የሚፈትን ሆኖ ለቁጣ አነሳስቷል።
ቢተው በመላው ሀገሪቱ የተቀጣጠለውን ሀገር የማስከበር ጥሪ በሰማ ጊዜ ወኔው ተነሳሳ። የወጣትነቱን አቅም ለማሳየት ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ እንደሌለ ገባው። እንደሌሎች የአገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ወሰነ። ጊዜ ሳይፈጅ በውትድርና ተመልምሎ ወደ ብርሽለቆ ማሰልጠኛ አመራ።
ቢተው የስልጠና ቆይታውን አጠናቆ በአገራዊ ግዳጅ ተሰማርቶ ቆየ። እንዳሰበው ሆኖም ወጣትነቱን ለቁምነገር መክፈሉ ከልብ አስደሰተው። በተሰማራበት የውትድርና አውድ ክፉና በጎውን አሳልፏል። ከብዘዎች ተዳምሮም ሕግና ሥርዓትን ተምሯል።
ከጦር ሜዳ መልስ
ጦርነቱ እንዳበቃ ቢተው በሙሉ አካልና በድል ብስራት ከተመለሱት ወታደሮች መሀል አንዱ ሆነ። ያሳለፋቸውም ጊዜያት ፈታኝ ነበሩ ። ቢተው የህይወትን ውጣውድ ለመሸከም የበረታ ትከሻው፣ ሰፊ እንደሆን በገባው ጊዜ ነገን በጥንካሬ ለመቀበል ራሱን አዘጋጀ።
ቢተውና መሰል ዘማቾች በተቀናሽነት ተመዝግበው ከሠራዊቱ በክብር ተሰናበቱ። አብዛኞቹም በወቅቱ የተሰጣቸውን ክፍያ ይዘው ወደመጡበት ተመለሱ። ቢተው የያዘውን ይዞ ወደ ሀገሩ አልገባም። የተከፈለውን ጥቂት ገንዘብ እንደቋጠረ አዲስ አበባ ገብቶ ከተመ።
አዲስ አበባ፣ ቢተውና የቋጠረው ገንዘብ ለጥቂት ጊዜ እንደተዋደዱ ቀጠሉ። ጎጃም በረንዳ አካባቢ በዕለት ክፍያ በተከራየው አልጋ አርፎ ገንዘቡን መነዘረ። እየተዝናና፣ እየተጠጣ ዓለምን የረሳ ቢመስለው ትናንትናውን ዘነጋ። ውሎ ሲያድር ከእጁ ያለው ሲሳይ እያለቀ መሆኑኑ ገባው። ይህኔ ነገን ለመኖር አማራጩን መፈለግ ጀመረ። ቢተው ከነበረበት ሆቴል ርቆ ገርጂ አካባቢ ሲገኝ የመጀመሪያ እርምጃው ማረፊያውን መሻት ነበር።
እንዳሰበው ሆኖ ከሌሎች ጋር የቀየሰው የላስቲክ ቤት ጎኑን ለማሳረፍ ተስፋ ሆነው። የቀረውን ጥቂት ገንዘብ ይዞ ከመሰሎቹ ሲቀላቀል በሆነው ሁሉ አልተማረረም።
አሁን የትናንትናው ዘማች ወታደር ከላስቲክ ቤቱ ኑሮን ጀምሯል። በአቅራቢያው ያሉ ጎረቤቶቹ በራሳቸው መተዳደሪያ ሲባትሉ ይውላሉ፤ ቢተው የአብዛኞቹን ሥራ ጠንቅቆ ያውቃል፤ ጥቂቶቹ በጉልበት ሠርተው አዳሪ ናቸው። አንዳንዳች የሰው እጅን ናፍቀው ይለምናሉ፣ ሌሎች ደግሞ አመቺ ጊዜና ቦታን መርጠው ማንጅራት ይመታሉ።
ቢተው የላስቲክ ቤት ኑሮው ብዙ አስተምሮታል። ለእሱ የሚመጥን ሥራ ባገኘ ጊዜ ወጣ እያለ የአቅሙን ይሞክራል። ድግስና የጉልበት ሥራ በተገኘ ጊዜ ቀድሞ ለመታደም የሚፈጥኑት መሰሎቹ እሱንም ያሳትፉታል። ቢተው አብሮት የኖረው እልህ ባህሪው ሆኖ ከሰዎች ጋር አይስማማም። በንግግር ከመፍታት ይልቅ ሃይልን ይጠቀማል። ብዙ ጊዜም ይህ ልማዱ ከችግር ይጥለዋል።
ቢተው በድብደባ ወንጀል ተከሶ ታስሮ ያውቃል፤ ሃይለኝነቱን የሚያውቁ ብዘዎች እሱን እንደባህሪው ለመያዝ ይሞክራሉ፤ ግልፍተኝነቱ፣ ለድብድብ እየጋበዘው ከበርካቶች መጣላቱን የላስቲክ ቤት ጎረቤቶቹ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
አዲስ ጓደኛ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብሮት መኖር የጀመረው በቀለ ከቢተው ጋር ክፉና ደጉን አሳልፏል። ለአንድ ዓመት ጎጆን በተጋሩበት አጋጣሚ በግድግዳው ቀዳዳ የደጇን ጨረቃ እያዩ የውስጣቸውን አውግተዋል። ክረምት ከበጋን ተሳስበው፣ ቁራሽ በእኩል ተካፍለዋል። ከአንድ ወለል ተኝተው እራፊ ሸማ ተጋፈዋል።
ቢተውና በቀለ አልፈውት የመጡት መንገድ ተመሳሳይ ነው፤ ዛሬን ኖረው ስለነገ የሚያስቡት ተስፋ በእኩል ሲያራምዳቸው ቆይቷል። በቀለ የጓደኛውን እልኸኛነት አሳምሮ ያውቃል። አንዳንዴ እሱንም ሳያስቀይመው አይውልም። ብስጭቱን ባየ ጊዜ ግን እንደታናሽነቱ ታግሶ ያሳልፋል። ሲበርድለትም ተመልሶ ከእሱ ይቆርሳል።
ህይወት በላስቲክ ጎጆቤት ውስጥ ቀጥሏል። ገርጂ ከመሰረተክርስቶስ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ የቆመችው ደሳሳ በቆሻሻ ገንዳዎች እንደተከበበች ውላ ታድራለች። በአካባቢው ተደጋግፈው የቆሙት ሌሎች ቤቶች ተመሳሳይ ህይወት ያላቸውን ሰዎች አቅፈዋል፤ በነዚህ ጎጆዎች ስር እምብዛም የኑሮ ልዩነት የለም።
በቀለ አንዳንዴ የደባሉ ባህርይና ልማድ ያስከፋዋል፤ ሁሌም ጉልበትን የሚጠቀመው ቢተው ነገሮችን ለማለፍ ትዕግስት የለውም። መጠጥ በቀማመሰ ቁጥር በእርሱ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፤ ኩርፊያው፣ ቁጣውና መነጫነጩ ሁሉ ከአቅሙ በላይ ይሆናል።
ሁሌም ቢሆን የባልንጀሮቹ ጠብና ጭቅጭቅ በብዙዎች ዘንድ ተለምዷል። በተለይ ሁለቱም ሰክረው በገቡ ጊዜ ጩኸታቸውን በርካቶች ይሰሙታል ። ምሽቱን በነገር አሳልፈው ሲነጋ ግን ወዳጅነታቸው ይቀጥላል። ይህ ከዓመት በላይ አብሯቸው የቆየ ልማድ ነው። ሥራ ባገኙ ጊዜ በአንድ ተ ስ ማ ም ተ ው ይሠራሉ። ካገኙትም ተካፍለው ይበላሉ። ይ ጠ ጣ ሉ ፣ ይሰክራሉ።
መስከረም 17 ቀን 2005 ዓም
ዛሬ ዕለቱ የመስቀል በዓል የ ሚ ከ በ ር በ ት ነው፤ በዚህ ቀን በዓሉን በድምቀት የሚያሳልፉ በርካቶች በ አ ካ ባ ቢ ያ ቸ ው ደመራ ይተክላሉ። የአንዳንድ መንደር ነዋሪዎች ይህን ቀን ለማክበር ገንዘብ አዋጥተው፣ ከብት ያርዳሉ ፣ መጠጥ ገዝተው ይዝናናሉ፤ በዚህ ቀን በአካባቢው የተገኘ ሁሉ ከግብዣቸው በእንግድነት ይታደማል።
የመስከረም ወር በሚጋመስበት በዚህ ወቅት በአሉን ለማክበር ከተሰባሰቡት መሀል ቢተውና ጓደኞቹ ተገኝተዋል። እነሱ በስፍራው መታየታቸው እንደሌሎቹ ነዋሪዎች ስለሆኑ አይደለም። በርካቶች ካዋጡት ገንዘብ መሀል የእነሱ አንድ ሳንቲም የለበትም። በስፍራው የመገኘታቸው ምክንያት ነዋሪዎቹ ከመጠጥና ከምግቡ የሚሰጧቸውን ለመቀበል ነው።
አሁን እነ ቢተው እንዳሰቡት ሆኖ ከግብዣው ተገኝው ከምግብና ከመጠጡ መጋበዝ ቀጥለዋል፤ ያሻቸውን በልተው እንደጨረሱ ወደመጠጡ መዞራቸውን ያዩ ጋባዦች ያለስስት እየቀዱ ከሞቅታ አደረሷቸው። ይህኔ ቢተው አብሮት ያለውን በቀለን በተለመደው የነገር ጉንተላ ይተነኩሰው ያዘ።
ቀኑን ጨርሰው ምሽቱን ሲጀምሩ ባልንጀሮቹ ወደ ጎጇቸው ለመሄድ መንገዳቸውን ያዙ። ሁለቱም ይንገዳገዳሉ። ሲጠጡት የቆዩት አልኮል ክፉና ደግ ያናግራቸው ይዟል። በቀለ ድምጹን ከፍ አድርጎ እያወራ ነው፤ ቢተው የጓደኛው ድምጽ እንደረበሸው ያስታውቃል። እየደጋገመ ቀስ ብሎ እንዲያወራ ያስጠነቅቀዋል።
በቀለ የቢተው የንዴት ንግግር እያበሰጨው ነው። ዛሬም በእልህ ሊወርፈው መሆኑን እያሰበ መንጭርጨር ይዟል። ቢተው የበቀለን መለዋወጥ ባየ ጊዜ ድርጊቱን ከንቀት ቆጠረው። በድጋሚ ቀስ ብሎ እንዲያወራ እየነገረ ጮኸበት። በቀለ ሊሰማው አልፈለገም። አለቃው እንዳልሆነና ሊያዘው እንደማይችል እሱም እየጮኸ መለሰለት።
የሁለቱም ንግግር በእልህ እንደተሞላ መንገዱን አጋመሱ። ለደቂቃ ተግ ያለው ጭቅጭቅ ከአፍታ በኋላ ሲጀምር በድበድብ የታጀበ ሆነ። አንገት ለአንገት ተናንቀው ታገሉ፤ ገላጋይ በሌለበት ውድቅት አንዳቸው ሌላውን ለመጣል ተያያዙ።
ጥቂት ቆይቶ በቀለ ከእጁ በገባ ድንጋይ የቢተውን ጭንቅላት እየመታ ታገለው፤ ቢተው እንደምንም ከእጁ አምልጦ ለመሮጥ ሞከረ፤ እየተሳደበና እየተራገመም በጨለማው ሮጦ አመለጠው። በቀለ በድል አድራጊነት እየተንገዳገደ ጓደኛውን ተከተለው፤ አልደረሰበትም።
በላስቲክ ጎጆው
ቆይታቸው በጠብ እንደተቋቸጨ በቀለ ወደላስቲክ ቤታቸው አመራ። እንደወጉ የተሸፈነውን በር ቢጤ ገልጦም በቁመናው ካገኘው መኝታ ላይ ተዘረረ። በፊት ከሚያደርገው በተለየ ፊቱን አዙሮ ጎኑን አሳረፈ። አፍታ ሰይቆይ ጭልጥ ያለ ዕንቅልፍ ወሰደው።
ጥቂት ደቂቃዎች እንዳለፉ ከላስቲክ ጎጆው በራፍ የሌላ ሰው ኮቴ ተሰማ። ቢተው ነው። ንዴትና ስካሩ አልበረደለትም። እየተበሳጨ፣ እየተነጫነጨ የደሳሳ ቤቱን
መግቢያ አልፎ ወደመሀል ደረሰ። ወዲያው ከአንድ ጥግ የሚንኮሻኮሽ ድምጽ ሰማ። ቀረብ ብሎ አጣራ ጓደኛው ከእሱ ሸሽቶ ፈንጠር ብሎ ተኝቷል። ንዴቱ አገረሸ። ዓይኖቹ በጨለማው መሀል ተቅበዘበዙ። በእጁ የገባውን ባለሚስማር ዱላ እንደያዘ ተጠጋው።
ባለሚስማሩ ዱላ ደጋግሞ በበቀለ ጭንቅላት እንደአረፈ አስደንጋጭ ጩኸት ሰፈሩን ሞላው። በየላስቲክ ቤቶቹ ያሉ ነዋሪዎች በዚህ ውድቅት የተሰማውን ደማቅ ድምጽ መለየት አልቻሉም። ቢተው አሁንም ያለማቋረጥ ጓደኛውን እያጠቃ ነው። ዱላውን ከጭንቅላቱ ወደ እግሮቹ እያፈራረቀ በጭካኔ መቀጥቀጡን ቀጥሏል።
የጓደኛው ድምጽ በድንገት ጸጥ ማለቱን እንዳወቀ በእጁ የያዘውን ዱላ አሸቀንጥሮ ደም ወደለበሰው በቀለ ተጠጋ። የተለየ ድምጽ የለም፤ በጨለማው ውስጥ አካሉን ዳሰሰው። ባልንጀራው ሊከላከለው አልሞከረም። በድንጋጤ እየተደናበረ የጣለውን ባለሚስማር ዱላ ይዞ ወደሜዳው ሮጠ፤ ጥቂት አለፍ እንዳለ ከጎረቤቶቹ አንዱን ከመንገድ ላይ አገኘው።
ቢተው ለጎረቤቱ እየተንቀጠቀጠ የሆነውን ሁሉ ነገረው። በቀለን ክፉኛ እንደጎዳውና ሁኔታው ስላሰጋው ወደውስጥ ገብተው እንዲያዩት ተማጸነው፤ ጎረቤቱ በሁኔታው ደንግጦ ተከተለው።
በቀለ በደም ተነክሮ ጥቂት ይተነፍሳል። ይህን ያየው ሰው ወደውጭ ወጥቶ በአካባቢው ያሉ ጥበቃዎችን እርዳታ ጠየቀ፤ ሊያግዙት አልፈቀዱም፤ ሌሎች ጎረቤቶችን እየዞረ ለመናቸው፤ እነሱም በፍራቻ ሊከተሉት አልወደዱም።
ይህ ሁሉ ሲሆን ራቅ ብሎ የሚያየው ቢተው በጨለማው ውስጥ እየተንቀጠቀጠ አዲስ ነገር ጠበቀ። ያለምንም እርዳታ ሊሊቱን ያሳለፈው በቀለ ከወደቀበት ሳይንቀሳቀስ ወድቋል። ለሊቱን ስለሱ የሰሙ ጎረቤቶች ንጋት ላይ ተሰባስበው ወደጎጆው አመሩ። ያዩትን ማመን አልቻሉም፤ በቀለ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ክፉኛ ተደብድቦ ወድቋል፤ ቀረብ ብለው አዳመጡት። ህይወት አልነበረውም።
የፖሊስ ምርመራ
በማለዳው ከላስቲክ መንደሮቹ መሀል የተገኘው የፖሊስ ቡድን የሟችን አስከሬን ከማንሳቱ በፊት አስፈላጊውን የቴክኒክ ምርመራ አጠናቀቀ። መረጃዎችን ለማግኘትም ነዋሪዎችን አንድ በአንድ ጠየቀ፤ ጎረቤቶቹ የሚያውቁትን እውነት ነገሩት፤
ፖሊስ አብሮት የሚኖረው ባልንጀራው ከስፍራው መሰወሩን እንዳወቀ የምርመራ ቡድን አዋቅሮ ክትትሉን ጀመረ። በረዳት ሳጂን አማረ ቢራራ የሚመራው ቡድን በየዕለቱ ያገኛቸውን መረጃዎች እየመዘገበ ተፈላጊውን ማሰሱን ቀጠለ።
ቢተው ከምሽቱ ድርጊት በኋላ የጓደኛውን ዕጣ ፈንታ አላወቀም። ምን አልባት ዕድል ቀንቶት በቶሎ ከዳነ በእግሩ ስር ተንበርክኮ ይቅርታ የሚጠይቅበትን ቀን እያሰበ ይጨነቃል፤ ስለደህንነቱ ለማወቅ በየቀኑ የሚደውለው ስልክ በምላሹ የበቀለን ደህንነት እያሰማው ነው። ይህን ያወቀው ቢተው አሁን መረጋጋት ጀምሯል።
ከቀናት በኋላ የፖሊስ ምርመራ ቡድን ተፈላጊውን ካለበት ስፍራ ተገኝቶ በቁጥጥር ስር አዋለው። ቢተው በየቀኑ የሚደውለው ስልክ ያለበትን ስፍራ የሚጠቁም ነበር። ከፖሊስ እጅ ገብቶ ቃሉን ሲሰጥ ድርጊቱን በድንገት እንደፈጸመው ተናገረ። ፖሊስ የዕምነት ክህደቱን ቃል መዝግቦ ሌሎች ማስረጃዎችን በማደራጀት ለዓቃቤ ሕግ ክስ አሳለፈው።
ውሳኔ
ሰኔ 10 ቀን 2007 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሽ ቢተው አማረ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ተደራጅቶ በደረሰው የክስ መዝገብም ድርጊቱ ከባድ የሰው መግደል ወንጅል መሆኑን አረጋግጦ ጥፋተኛ መሆኑን አሳውቋል። በዕለቱ ባሰለፈው ውሳኔም ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ የአስራዘጠኝ ዓመት እስራት ‹‹ይቀጣ›› ሲል ብይን ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2012
መልካምስራ አፈወርቅ