
ምህረት ለወላጆቿ የመጀመሪያ ልጅ ስትሆን ትውልድና እድገቷ በጅማ ከተማ ነው። ዝቅተኛ ከሚባሉ የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው ወላጆች የተገኘችው ምህረት በሥሯ የሚገኙ ታናናሽ ሁለት እህቶቿን እና አንድ ወንድሟን የመንከባከብ ኃላፊነት በቤት ውስጥ ይጠብቃታል። ታላቅ ሴት ልጅ እንደ መሆኗም በቤቷ ውስጥ አብዛኛውን ሥራ ከእናቷ ጎን ለጎን ትሠራለች። ምህረት ተማሪም ጭምር ናት፤ ታዲያ ቤት ውስጥ ከሚኖርባት ኃላፊነት ባሻገር በትምህርት ቤቷ ከእኩዮቿ ጋር መጫወትን ፣ ማጥናትን የምትወድ እንደ እድሜዋ መቦረቅን የምትሻ ናት።
የምህረት ወላጆች አነስተኛ ገቢ በሚያስገኝ የሥራ ዘርፍ ላይ ተሠማርተው የሚሠሩ ሲሆን፤ አባቷ በጥበቃ ሥራ እናቷ ደግሞ እንጀራ ጋግረው በመሸጥ እና በተለያዩ ሰዎች ቤት ልብስ በማጠብ ልጆቻቸውን ያስተዳድራሉ። ለልጆቻቸው የተሻለ ሕይወትን ለመስጠት በሚያደርጉት ጥረት ግን ምህረት የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኗ ለታናናሾቿ ከቤተሰቦቿ ቀጥሎ የወላጅነት ኃላፊነቱን እንድትወስድ ይጠበ ቅባታል። በእርግጥ እርሷም ይህንን ጉዳይ በሚገባ ታውቃለች እና ኃላፊነቷን ለመወጣት በእጅጉ ትጥራለች።
ሀና የምህረት የቅርብ ጓደኛ ስትሆን አብረው በሚኖሩበት ሰፈር ጭምር የሚቀራረቡ ናቸው። በመሆኑም የምህረት ወላጆች እና የሀና ቤተሰቦች እንዲሁ ይተዋወቃሉ። ታዲያ ሀና የ10ኛ ክፍልን የሀገር አቀፍ ፈተና ባለማለፏ ትምህርቷን አቋርጣ ሥራ እሠራለሁ በማለት ወደ አዲስ አበባ ትመጣለች። ምህረት ደግሞ ሀገር አቀፍ ፈተናውን አልፋ ወደ 11ኛ ክፍል በመዛወሯ ቀጣይ ትምህርቷን በሞራል በማለፏ ቀጥሎ ያለውን ትልቅ ህልም በማለም ትምህርቷን መማር ቀጥላለች። የቤት ውስጥ ኃላፊነቷም እንዳለ ነው። ምህረት ታናሽ ወንድሞቿንና እህቶቿን እንዲሁም በእድሜ እየገፉ ያሉ ወላጆቿን ማገዝ የምንግዜም ህልሟ ነው።
ለእዚህም መፍትሔው ትምህርት እና ትምህርት መሆኑን ታምናለች። ወላጆችም ልጆቻቸው አድ ገው ለቁምነገር ሲበቁ ማየት እድሜያቸው ሲገፋ በልጆቻቸው መጦር እና የለፉበትን ልጆቻቸውን ለማሳደግ የከፈሉትን ዋጋ በልጆቻቸው ስኬት ውስጥ ማየትን ይሻሉ። ለእዚህም ዘወትር ሞታቸውን ከልጆቻቸው በፊት እንዲያደርገው ልጆቻቸው በክፉ ነገር እንዳይጠመዱ እና እንዳይሰናከሉ ይጸልያሉ። እንደ ምህረት ያሉ ወላጆች ደግሞ ይህንን ኃላፊነት ባልተገባ መንገድ ልጆቻቸው ላይ በመጫን ለአላስፈላጊ ጭንቀት እና ያለእድሜያቸው እንዲያስቡ ከእድሜ እኩዮቻቸው እኩል የልጅነት የታዳጊነት ሕይወትን እንዳያጣጥሙት ሊያደርጉ ይችላሉ።
ምህረት የ12ተኛ ክፍል ትምህርቷን ጀምራለች። በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለመግባት ማለፍ የሚጠበቅባትን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለማለፍ የበኩሏን እያደረገች ነው። ታዲያ በእዚህ ወቅት አብሮ አደግ ጓደኛዋ ሀና ሥራ ለመሥራት እና የቤተሰቦቿን ሕይወት ለመለወጥ በማሰብ ወደ አዲስ አበባ ከሄደች በኋላ ለቤተሰቦቿ የምታደርጋቸውን ቁሳቂ ነገሮች የምህረት ወላጆች ይመለከታሉ። ታዲያ ምን ብትሠራ ነው ይህንን ማድረግ የቻለችው ሳይሆን የሠራችውን እና ለወላጆቿ ያደረገችውን በመመልከት ከገዛ ልጃቸው ጋር ያነጻጽሯት ነበር። በእዚህም ወቅት ምህረት እንዳሰበችው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባትን ውጤት ማምጣት ሳትችል ቀረች።
ይህን ጊዜ ምህረት እርሷም ለቤተሰቦቿ ለመድረስ የተሻለ ሕይወትን ለመስጠት የአቅሟን ለማድረግ ከአብሮ አደግ ጓደኛዋ ጋር መነጋገር ጀመረች። ሀናም ሆነች ምህረት ይህ ነው የሚባል ሊያስጠጋ የሚችል ቤተሰብ የቅርብ ዘመድ የላቸውምና ምህረት ማረፊያዋ የት እንደሚሆን እና ምን ልትሠራ እንደምትችል ከተወያየች በኋላ ቀጣይ ጉዞዋን ወደ አዲስ አበባ አደረገች። አዲስ አበባ እንደመጣች የተቀበለቻት ሀና ስትሆን ጥቂት ቀናትን ሀና በምትኖርበት ቤት ውስጥ ከቆየች በኋላ ጓደኛዋ ሀገሩን ለምዳዋለች እና በምታውቃቸው ሰዎች አማካኝነት በቤት ሠራተኝነት እንትቀጠር ደመወዝ ተስማምታ አስገባቻት።
አዲስ ሕይወት
ምህረት ተማሪ ነበረች፤ የምትወደውን ትምህርት በመጠቀም ህልሟን እና የቤተሰቦቿን የወደፊት እጣ ፈንታ ለመቀየር የምታስብ ሕጻን፤ ነገር ግን ከእድሜዋ በላይ የምታስብ ልጅም ነበረች። ነገር ግን ድህነት እና ከሕይወት ጋር ትግል መግጠም ትንሿን ምህረትን እዚህ ጋር አስቀምጧታል። ሕጻናትን መንከባከብም ሆነ የቤት ውስጥ ምግብ ማብሰል እና ቤትን ማጽዳት እንዲሁ ዕለት ዕለት የምታደርገው በመሆኑ አልከበዳትም፡፡
የገባችበት ቤት ውስጥ ሁለት ሕጻናት ልጆች ሲኖሩ፤ አንደኛው ትምህርት ቤት ለመግባት እድሜው የደረሰ ሲሆን፤ የሁለት ዓመት ከስድስት ወር የሆነ ሕጻን እንዲሁ በመንከባከብ ጊዜዋን ታሳልፋለች። ከልጆቹ ወላጅ ከሆኑትና ከቀጣሪዎቿ ከሆኑት እናት እና አባት ጋርም ቢሆን ለመግባባት ያንን ያህል ጊዜ አልወሰደባትም። ነገር ግን ከገባች ገና ወራት ቢቆጠሩም ያልጣማትና ምቾት ያልሰጣት ነገር ግን ገጥሟታል። ይህንን ለማን ማውራት እንዳለባት ማንን እንደምታማክር የጨነቃት ምህረት በተለያየ መንገድ ችግሩን ለማለፍ ጥረት ታደርጋለች። የምትሠራበት ቤት ውስጥ እናት እና አባት ሁለቱም ሥራ ያላቸው ሲሆን፤ ጠዋት ልጅን ትምህርት ቤት ለመሸኘት፤ ቁርስ መሥራት፣ ምሳ እቃ ማሰር ሲኖርባት እናት ቀድማ ከቤት ስትወጣ ባል ግን ወደ ሥራ የሚሄደው አርፍዶ ነው።
ታዲያ ምህረት ሚስትን እና ልጅን ከሸኘች በኋላ ለአባወራው ቁርስ ማቅረብ ይኖርባታል። የቤት ጽዳት ሥራዎቿም ከእዛ በኋላ የሚቀጥሉ ይሆናሉ። ታዲያ በአንዱ ሰንካላ ቀን ምህረት የፈራችው ነገር ሊገጥማት ሆነ፤ ራሷን ለመከላከል ብትጥርም ከአቅሟ በላይ በመሆኑ ሕይወቴን እለውጥበታለሁ ያለችው ሥራ ባላሰበችው መልኩ የሕይወት አቅጣጫዋን ቀየረው። በምትሠራበት ቤት ውስጥ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ደረሰባት። ጥቃት አድራሹም የቤተሰብ ኃላፊነቱን ሳይሆን አውሬነቱ አይሎበት በፈጸመው ተግባር ሳይጸጸት የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ምህረት ከቤቱ እንድትወጣ አደረገ።
ምህረት ከምትሠራበት ቤት ስትወጣ የነበራት አማራጭ ተስፋ አይታ የመጣችባት አብሮ አደግ ጓደኛዋ ሀና ጋር መሄድ ነበር። እርሷ የምትኖርበት ቤት በአንድ ግሮሰሪ ውስጥ ሲሆን፤ እዚያው እየሠራች የምትኖር በመሆኑ ምህረትም የአስተናጋጅነት ሥራን እንድትሞክረው በጓደኛዋ አሳማኝነት ሥራዋን ጀመረች። ነገር ግን ጉዳዩ ሌላ እንደሆነ የተረዳችው ቆይታ ነበር።
ሀና በእዚሁ ግሮሰሪ ውስጥ በምትሠራው የአስ ተናጋጅነት ሥራ ሽፋን ከተለያዩ ወደ ግሮሰሪው ከሚመጡ ወንዶች ጋር በማደር በየቀኑ ገንዘብ የምታገኝበት ሥራ ሆኗል። ታዲያ ይህንን ሥራ ምህረት የምትቀበለው ባይሆንም ነገር ግን በደረሰባት የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ባሳደረባት ጫና ምክንያት እንዲሁም በጓደኛዋ ግፊት እርሷም ይህንን ሥራ መሥራቷን ቀጠለች።
በእዚህ አጋጣሚ ነበር በተደጋጋሚ እሷን ብሎ የሚመጣውን ታደሰ የተዋወቀችው፤ ታደሰ ምህረትን ካያት ጀምሮ በተደጋጋሚ አብሯት የሚያድር ሲሆን፤ ይህም በመሐከላቸው ቅርበት እንዲፈጠር አድርጓል።
ፍቅርን በጉልበት
ምህረት እና ታደሰ እንደሚቀራረቡ በግሮሰሪው ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ሆኑ ባለቤቶች የሚያውቁ ሲሆን፤ ነገር ግን የምህረት ሥራ እርሱ የሚላትን ብቻ እንድታደርግ፤ አልያም እርሱን ብቻ እንድትጠብቅ አያደርጋትም። አሁን የምትሠራውን ሥራ እንድትተው የሚያደርግም ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ቅርርብ የላቸውም፤ ነገር ግን የእርሱ ተግባር እና ድርጊት የፍቅር ጓደኛው እንደሆነች አድርጎ ማሰቡ በሕይወቷ ላይ እክልን እየፈጠረ ነው።
ከእለታት በአንዱ ቀንም በመሐከላቸው የተፈጠረው ተደጋጋሚ አለመግባባት እና የእርሷ እምቢተኝነት ያልተዋጠለት ታደሰ የፍቅር ጓደኛ መሆኑ ቀርቶ የእብሪተኝነት ልብሱን ተከናንቦ በመምጣት ግሮሰሪው ውስጥ መጠጥ አዞ መጠጣት ጀመረ። የመጣበት ሰዓት ወደመምሸቱ ነበርና ምህረት ከሌላ ሰው ጋር እየጠጣች እና እያወራች ነበር። ታዲያ ከምህረት ጋር አብሯት ያለው ሰው ይዟት ለመሄድ ተስማምተው አስቀድሞ ከግሮሰሪው ሲወጣ ምህረት ተከትላው ወጣች። ነገር ግን በእዚህ መሐል ያልታሰበ ነገር ተከሰተ፤ የፍቅር ጓደኛዬ ነች ብሎ ራሱን የሰየመው ታደሰ ሳይታሰብ ደብቆ በያዘው ስለት ጉዳት አደረሰባት።
በግሮሰሪው ውስጥም ጩኸት ሆነ፤ በተደጋጋሚም ባደረሰባት ጉዳት የተለያዩ የሰውነት ክፍሏን በያዘው ስለት በመውጋት አቅም እንድታጣ እና ከፍተኛ ደም እንዲፈሳት አደረገ። ከቦታው በፍጥነት ወጥቶ ያመለጠ ሲሆን፤ የግሮሰሪው ባለቤቶችም ሆኑ ሠራተኞች ትኩረታቸው የእርሷን ሕይወት ማትረፍ ላይ ነበር።
ነገር ግን የምህረትን ሕይወት ማትረፍ አልተቻለም። መረጃው የደረሰው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ወንጀሉ በተፈጸመ በሦስተኛው ቀን በቁጥጥር ስር በማዋል የማጣራት ሥራውን ጀመረ።
የወንጀል ዝርዝር
ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539/1/ሀ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሽ ሰውን ለመግደል ሆን ብሎ በማሰብ ሐምሌ ሦስት (03) 2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 11 ሰዓት ከ30 ሲሆን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው አረቄ ሰፈር ደጀኔ ግሮሰሪ ውስጥ ሴተኛ አዳሪ ሥራ የምትሠራውን እና የፍቅር ጓደኛው የሆነችው ሟች ምህረት ታደሰን ጨካኝነቱን እና አደገኝነቱን በሚያሳይ ሁኔታ ጩቤውን በሽርጥ ውስጥ ጠቅልሎ በመያዝ ወደ ግሮሰሪው ከገባ በኋላ ሟችም ግሮሰሪው ውስጥ እንዳለች ሆዷን ደረቷን እንዲሁም አንገቷን፣ ትከሻዋን፣ እጇን፣ ክንዷን እና ፊቷን በተደጋጋሚ በመውጋት 4 ሳንቲ ሜትር በአንድ ነጥብ አምስት ሳንቲ ሜትር በ10 ሳንቲ ሜትር ስፋት ያለው የስለት ውጊያ ቁስል በአንገት እና በታችኛው የሰውነቷ ክፍል ላይ ሁለት ሳንቲ ሜትር በአንድ ሳንቲ ሜትር ውጊያ የሚያሳዩ ሲሆን፤ ተከሳሽ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል።
ማስረጃዎች
ዓቃቤ ሕግ ክስ ከመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ የሟች የአስክሬን የምርመራ ውጤት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የተላከ የምርመራ ውጤት፤ ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት የሟችን አሟሟት የወንጀል ስፍራ የሚያሳይ 14 ፎቶግራፍ፣ ተከሳሽ የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸመ አምኖ ቃል ሲሰጥ የሚያሳይ አንድ ሲዲ፣ የሰነድ ማስረጃዎች ተያይዘዋል። ዐቃቤ ሕግ በማስረጃው ተከሳሽ ወንጀሉን የፈጸመበትን ጩቤ በኤግዚቢትነት የያዘ ሲሆን፤ ተከሳሽ ከሐምሌ ስድስት 2015 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ሲሆን፤ እንዲሁም ወንጀሉ በተፈጸመበት ዕለት በቦታው የነበሩ 10 የሰው ማስረጃን ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ ላይ አካቷል።
ውሳኔ
በከሳሽ ፌዴራል ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ታደሰ መላክ ታሪኩ መካከል በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር በግንቦት ዘጠኝ 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም