
ጌቱ መስፍን ወንድሙ የሚታወቅበት ስም ሲሆን ተፈራ ደግሞ ሌላኛ መጠርያ ስሙ ነው። ትውልድና እድገቱ በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ ሲሆን የ 12 ክፍል ትምህርቱን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ የተማረው በእዚያ ነው።
ትምህርት ወላጆች ለልጆቻቸው የሚወርሱት፣ የወደፊት ሕይወታቸውን የሚወስኑበት ነውና ልጁ በትምህርት ትልቅ ደረጃ እንዲደርስ የማይፈልግ ወላጅ አለ ማለት አይቻልም። ነገር ግን አስተዳደግ፣ ተከታታይ ክትትል ማድረግ እና የልጆችን አካሄድ ዝንባሌ መረዳት በትምህርታቸውም ሆነ በሕይወታቸው ላይ ያላቸውን ስኬት የሚወስን ነው።
ጌቱም እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ የመሰናዶ ትምህርቱን ሊቀጥል አልቻለም። የጌቱ ቀጣዩ የሕይወት እቅድ የነበረው ወደሥራው ዓለም መግባት ነበርና በዚያው በነገሌ ቦረና የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቶ የተሻለ ሥራ ለማግኘት በሚል በ2010 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ፊቱን አዞረ። እዚህ የተሻለ ሥራ፣ ክፍያ እንዲሁም አዲስ ሕይወት ጌቱ ለመመስረት በማሰብ ወደ ከተማዋ ከመጣ በኋላ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል። ለረጅም ጊዜ ይሠራ የነበረውም የቀን ሠራተኛ ሆኖ ሲሆን የተለያዩ ጅምር ህንጻዎች ላይ እንደ ጉልበት ሠራተኛ በመቀጠር የእለት ተእለት ሥራውን ያከናውናል።
ታዲያ ጌቱ በቅጽል ስሙ ተፈራ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዷዊ ስሙ ለገሀር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን በሥራ የሚገኘው የኖህ ሪልስቴት ግንባታ ሥራ አገኘ። ግንባታው የራሱ የሆኑ የተለያዩ ሠራተኞች እና የሥራ ክፍሎች፣ ያሉት ሲሆን ጌቱ የቀን ሠራተኛ በመሆን በዚያ ተቀጥሮ ሥራውን መሥራት ቀጠለ። በስፍራው አብዛኛዎቹ ሠራተኞች ወንዶች እንዲሁም በተመሳሳይ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ከሥራ ውጪ ያለውን ሰዓታቸውን እንዲሁም የምሳ ሰዓታቸውን በጋራ ያሳልፋሉ።
ሀጂብ ያሲን ከጌቱ ቀደም ብሎ የኖህ ሪልስቴት ውስጥ መሥራት የጀመረ ሲሆን፤ ጌቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ሲያገኝ እንደ ጓደኛ የተዋወቀው እና የቀረበው ሰውም ሀጂብን ነበር። በሥራ ላይ ከሁሉም ሰው ጋር ፍጹም መስማማት፤ ፍጹምም ተቃራኒ የሆነ ግንኙነት ባይኖርም በአንዳንድ አጋጣሚዎች ግን ሰዎች እርስ በእርስ ላይስማሙ ይችላሉ። የሀጂብ እና የጌቱ ግንኙነትም ብዙ አለመግባባት ጥቂት ጓደኝነት የተሞላበት ነው። በቀን ውስጥ በሃሳብ ፣በሥራ ሳይጋጩ እርስ በእርስ ሳይከራከሩ አሳልፈው አያውቁም። ታዲያ በዚህ መሀል ሁለቱም በተመሳሳይ እድሜ ላይ የሚገኙ እና ባህሪያቸውም ተመሳሳይ የሚባል በመሆኑ እርስበእርሳቸው በሚከራከሩበት ጊዜ መተላለፍ ያቅታቸዋል። ነገር ግን ስፍራው የሥራ ቦታ ነውና ይህ ነው የሚባል የከረረ ጸብ በመሀከላቸው አይኖርም።
የቀን ጥቁር
የክረምት ወቅት እና ሥራ ለብዙዎች ደስታ የሚሰጥ አይደለም። አብዛኛው ሰው ክረምትን የሚወድ ቢሆንም ነገር ግን ከቤት መውጣትን አይፈልግም፤ አልያም በቤቱ ውስጥ ሆኖ ሞቃት በሆነ ሁኔታ ከቤተሰብ እና ወዳጅ ዘመዱ ጋር እየተጫወተ ማሳለፍን ይመርጣል። ሀጂብ በዚህ ቀን ወደሥራ ሲሄድ ይህንን በማሰላሰል በጠዋት የጀመረውን ዝናብ ተቋቁሞ ወደ ተለመደው የሥራ ቦታው አቀና።
ጊዜው ዝናባማ ይሁን እንጂ በጅምር ህንጻው ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች ቀጥለዋል። ሀጂብ በሥራው የጌቱ መስፍን አለቃ ሲሆን የሥራ ሂደት፣ የሥራ ዝርዝር እና ክፍያ ሁኔታ በእርሱ በኩል የሚያልፍ ነው። ታዲያ የሥራ መብዛት፣ የደሞዝ መዘግየት በሠራተኛ እና በአሰሪ መካከል ግጭቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ናቸው።
በእለቱ ሀጂብ ወደሥራ የገባው አረፋፍዶ ቢሆንም ጌቱን ግን በሥራ ገበታው ላይ አልተመለከተውም። ታዲያ በፈረቃ የሥራ ሰዓት የሚሠሩ ሠራተኞች ወጥተው በህንጻው 16ኛ ወለል ላይ ጌቱ እና አለቃው ሀጂብ ይገናኛሉ። ንግግራቸውም ሥራ ትተህት የት ሄደህ ነው በሚል ይጀመራል። ጌቱም ለጉዳዩ መልስ ባለመስጠት ዝም ካለ በኋላ ደሞዜን ለምን አዘገየህብኝ የሚል ሌላ ጥያቄን ያቀርባል።
በንግግር የተጀመረው ወደ ጭቅጭቅ እና ንትርክ ሲያመራ በሁለቱ ፈርጣማ ግንበኞች መካከል ያለው የሃይለ ቃላት ልውውጥ ወደ እጅ መሰንዘር አመራ። ከዚህ በኋላ በቦታው ጭር ማለት እና በሰዓቱ በአካባቢው ሰው አለመኖር ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን ለማከናወን የሚያመች፣ በቦታው የሆነውን እንዳይሆን የሚያገላግል አልነበረም እና ወደ አካላዊ ጥቃት ያመራው የሁለቱ የሥራ ባልደረቦች ግጭት አንዱ የሌላኛውን ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አጥፍቶ የሥራ ቦታውን ለቆ ወጣ። ጌቱ መስፍን በሥራ ባልደረባው ሀጂብ ያሲን ላይ አሰቃቂ ግድያ ከፈጸመ በኋላ አስክሬኑን በህንጻው ታችኛው ወለል የሚገኝ የውሃ ማጠራቀሚያ ውስጥ አስቀምጦት ላይመለስ ከአካባቢው ተሰወረ። ሀጂብ የት ደረሰ የሚለውን ለማወቅ ግን አንድ ቀን ብቻ በቂ አልነበረም።
የምርመራ ሒደት
ተከሳሽ ጌቱ መስፍን የሥራ ባልደረባውን ሀሰን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለው በኋላ ለሟች ቤተሰብ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ለቤተሰቦቹ ደውሎ ህንጻው ግራውንድ ስር እቃ አስቀምጬላችኋለው ሄዳችሁ ውሰዱ በማለት ሟች ራሱ መግደሉን ተናግሮ ወንጀሉን ፈጽሞ ተሰውሯል።
ተከሳሽ አሰቃቂ ወንጀል ፈጽሞ ከተሰወረ ከሁለት ዓመት በኋላ ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ሊውልም ችሏል። ይህ እንዲሆን ግን ፖሊስ መረጃው ከደረሰው ቀን ጀምሮ ወንጀለኛውን በቁጥጥር እስካዋለበት ቀን ድረስ የተለያዩ ርምጃዎችን፣ የምርመራ ሒደቶች፣ ሙከራዎችን አድርጓል።
በዚህም ፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት በአራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ተጠርጣሪው ወንጀሉን ፈጽሞ በማምለጡ በተገኘበት እንዲያዝ የመያዣ ትእዛዝ አስፈቅዶ የክትትል ሥራውን ጀምሯል።
ፖሊስ መረጃው ከደረሰው በኋ የተለያዩ ማጣራቶችን በማድረግ፣ የተለያዩ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ እና የራሱን ማጣራቶችን በማድረግ ወንጀለኛው ሕግ ፊት በማቆም እና ፍትህን ለማረጋገጥ የራሱን ተከታታይ ማጣራቶችን አድርጓል። ተጠርጣሪው ወንጀሉን ፈጽሞ ከተሰወረ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ቦረና የሚገኙ ቤተሰቦቹ ጋር በመሄድ የተወሰነ ጊዜ ቆይቷል። ፖሊስም ተጠርጣሪው በዚያ እንደሚገኝ መረጃው ሲደርሰው አባላቱን አሰባስቦ ቦታው ድረስ በመሄድ ከአሮሚያ ክልል መንግሥት ነገሌ ቦረና ዞን ትብብር በመጠየቅ የራሱን ማጣራት ቢያደርግም ነገር ግን ይህም ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህም ተጠርጣሪው ያለበትን ቦታ ለማጣራት በሚደረጉ ጥረቶች መሀልም የተለያዩ የሰነድ እና የሰው ማስረጃዎችን ወደ ውጤቱ የሚያደርሱ መረጃዎችን ሲያጠናክር ቆይቷል።
ፖሊስ ባሳለፈው የምርመራ ሒደት ተጠርጣሪው ያለበትን ቦታ ለማጣራት በተደረገው ጥረት ተጠርጣሪው በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በሥራ ላይ እንደሚገኝ መረጃው ይደርሰዋል። በዚህም በ2016 ዓ.ም ሚያዝያ ወር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ለመከላከያ የሰው ሃይል መረጃ ማስረጃ ክፍል ተጠርጣሪው በዚህ ውስጥ ተቀጥሮ የሚገኝ መሆኑን እንዲያረጋግጥ እና ተቀጣሪው ሲቀጠር ያስያዘውን ማስረጃ ኮፒ እንዲሁም ተጠርጣሪው በሥራ ላይ የሚገኝ አልያም የለቀቀ ስለመሆኑ እንዲጣራለት በደብዳቤ ጠይቋል።
ፖሊስ በሚያደርገው ማጣራት እዚህ ለመድረስ የተለያዩ ማጣራቶችን አድርጓል። በዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰው ሃይል መረጃ እና ማስረጃ ክፍልም ተጠርጣሪው በሀገር መከላከለያ ሠራዊት፣ በደቡብ ዕዝ ውስጥ አባል ሆኖ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ሚያዝያ ዘጠኝ 2016 ዓ.ም በላከው ደብዳቤ አረጋግጧል። በዚህም ፖሊስ የመያዣ ትእዛዝ በማውጣት እና የፈጸመውን ወንጀል በመጥቀስ ተጠርጣሪው ተላልፎ እንዲሰጠው ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጠይቋል።
ይዘገይ ይሆናል ፍትህ መረጋገጡ እውነትም መጋለጡ አይቀርም እና አሰቃቂ እና ከባድ የሰው መግደል ወንጀል ፈጽሞ የተሰወረ ከዚያም በአንድ አጋጣሚ ራሱን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በመደበቅ ሲሰራ የሚገኘው፤ በአንድ ጊዜ ሁለት የተለያዩ ማንነቶችን ለመያዝ ሲሞክር የነበረው ሰውም ከሁለት ዓመት የጊዜ ቆይታ በኋላ ጉዳዩን ሲከታተል በነበረው ቡድን ጥረት በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።
የወንጀል ዝርዝር
ተከሳሽ ሰውን ለመግደል አስቦ በቀን 27/12/2014 ዓ.ም ከረፋዱ አራት ሰዓት ከ 30 ደቂቃ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ለገሀር ተብሎ በሚጠራው የኖህ ሪልስቴት ከሚገኘው ጅምር ህንጻ ላይ 16ኛ ወለል ላይ በመካከላቸው በተፈጠረ ጸብ መነሻነት ሟች ሀጂብ ያሲን የተባለውን ግለሰብ በፌሮ ብረት ግንባሩን አንድ ጊዜ በመምታት እና በሽቦ ገመድ አንገቱን በማነቅ ሕይወቱ እንዲያልፍ ካደረገ በኋላ ሽቦ ለማሰር በሚጠቀምበት ጉጠት ሽቦውን አንገቱ ላይ ቋጥሮ አስክሬኑን ከህንጻው ላይ ተሸክሞ በማውረድ የህንጻው መሠረት ስር የሚገኝ ውሃ ውስጥ በመክተት ከአካባቢው ሊሰወር ችሏል። ሟችም ራስ ቅሉ ላይ ጉዳት የደረሰበት እና አንገቱን በሽቦ በመታነቁ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ ጌቱ መስፍን በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል።
ማስረጃዎች
ዐቃቤ ሕግ ወንጀሉ መፈጸሙ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ባደረጋቸው ጥረቶች ልክ የተለያዩ ማስረጃዎችን ሲያጠናክር ቆይቷል። ሟች በሚሠራበት ቦታ የነበሩ ተጠርጣሪ ናቸው ያላቸውን የተለያዩ ሰዎች ላይ ምርመራ አድርጓል። ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላም ባደረገው ማጣራት ተከሳሽን እና ሟችን የሚያውቁ 13 የሰው ምስክር ማስረጃዎችን አያይዟል።
በሰነድ ማስረጃው የፌዴራል ፎረንሲክ ምርመራ ክፍል የራሱን ምርመራ ካደረገ በኋላ የአስክሬን ምርመራ እንዲደረግ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በተገኘው መረጃ የ29 ዓመት ወጣት የሆነው ሟች ሀጂብ ያሲን መሀመድ በነሀሴ 12/ 2014 ዓ.ም ከረፋዱ ሶስት ሰዓት ወደ ሥራ ቦታው ከሄደ ግን አልተመለሰም ።
በዚህም በቀን 28 ማለትም በቀጣዩ ቀን በሚሠራበት ኖህ ሪልስቴት ተብሎ በሚጠራ ግንባታ ስፍራ ሕይወቱ አልፎ ተገኝቷል። በዚህም ወደ አስክሬን የምርመራ ውጤት በ12 – 24 ሰዓት ቆይቶ የሄደ ሲሆን፤ በውጤቱ በውጫዊ አካሉ እና ውስታዊ አካሉ ላይ የደረሰውን በምርመራ ውጤቱ ቀርቧል። በዚህም በውጫዊ አካሉ አንገቱ ላይ የተጠመጠመ የሽቦ ገመድ፣ ከመሞቱ በፊት የተፈጠረ የአንገት እንቃት ጠባሳ፣ አብዛኛው ሰውነቱ ክፍሎች ላይ የቆዳ መጋጥ፣ መበለዝ እና መሰንጠቅ በሰውነቱ ላይ መኖሩን አረጋግጧል።
በውስጣዊ አካሉ ላይ የደረሱ አደጋዎች በምርመራ ውጤቱ ላይ የተገለጹ ሲሆን የሞቱ መንስኤ በራስ ቅሉ ላይ ጉዳት ደርሶበት በሌላ ሰው በሽቦ ገመድ በመታነቁ፤ የአሟሟቱ ሁኔታ የግድያ ወንጀል ሆኖ የሚታይ እና የአስክሬን ምርመራ ውጤቱ ጭካኔያዊ አገዳደል መሆኑን የሚጠቁም መሆኑን የሆስፒታሉ የአስክሬን የምርመራ ውጤት ገልጸዋል።
ተከሳሽ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ወንጀሉን መፈጸሙን አምኖ በወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ቁጥር ወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ 27(2) መሠረት ለፖሊስ የሰጠው ቃል እንዲሁም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ቁጥር 35 ለፍርድ ቤት የሰጠው ቃል ተካቷል። ሌላኛው የገላጭ ማስረጃ ሲሆን የወንጀሉን ስፍራ፣ ሟች ላይ የደረሰውን ጉዳት እና በጊዜው የነበረው የሟች ገጽታ፣ ምስክሮች ተከሳሽ ጌቱ መስፍንን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች መካከል ሲመርጡት የሚሳያይ ፎቶግራፍ፣ እንዲሁም ተከሳሽ ወንጀሉን የተፈጸመበትን ስፍራ በመሄድ ድርጊቱን እንዴት እንደፈጸመ ሲገልጽ የሚያሳይ 69 ፎቶ ግራፍ በመግለጫ ማስረጃው ላይ ተቀምጧል።
እንዲሁም ተከሳሽ ጌቱ መስፍን የወንጀል ድርጊቱን አምኖ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ቁጥር 27(2) መሠረት ለፖሊስ የእምነት ቃሉን ሲሰጥ የሚያሳይ ቪዲዮ በማስረጃነት ቀርቧል።
ውሳኔ
ተከሳሽ ጌቱ መስፍን ወንድሙ በተከሰሰበት ሰው መግደል ወንጀል ጉዳይ በክርክር ላይ የነበረና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ በታህሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ ክስና ማስረጃ ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ተከሳሽ በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ይቀጣ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል። ከሳሽ የፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ ተከሳሽ ጌቱ መስፍን ወንድሙ በሌላ ስሙ ተፈራ መስፍን የ27 ዓመት ሲሆን ወንጀሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን ኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539(1)ሀ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ።
በሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም