ፍትህን ያልተማመነው በቀለኛ

እንደ ሀገር ባለን ጉርብትና እና አብሮ የመኖር እሳቤ ውስጥ እርስ በእርስ የምንደጋገፍ በችግር ፈጥነን የምንደርስ፣ ጓዳን የምንሸፍን ህዝብ ነን:: ‹‹ሩቅ ካለው ዘመድ ይልቅ ቅርብ ያለ ጎረቤት ይበልጣል›› እንደሚባለው የእርስ በእርስ ኑሯችን እጅጉን የተሳሰረ ነው::

አንድን ህጻን ልጅ ሁሉም የአካባቢው ማህበረሰብ እንደራሱ ልጅ እየቀጣ እና እየገሰጸ ያሳድገዋል:: ወላጅም ልጄን ማን ነካው ሳይሆን ካጠፋ ይቀጣ በሚለው ይስማማል:: ይህ ጉርብትና ደስታም ሆነ ሀዘን ባጋጣመ ግዜ እንደራስ አድርጎ የመመልከት አኩሪ ባህል አለን::

ይህ ባህላችን አሁን ላይ እየጠፋ መሆኑ በቅሬታ የሚነገርበት ሲሆን ከተሜነት ስልጣኔ ለዚህ ባህል መጥፋት አንደኛው ተጠያቂ ነው:: ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው ሊጠፋ የሚገባው እና በሰለጠነ ማኅበረሰብ ውስጥ ሊኖር የማይገባው አንድ ባህል አለ::

በቀለኛነት፤ በቀል መጥፎ ባህል ብቻም ሳይሆን በቀልን በሚፈጽመው ግለሰብ ላይም ሆነ በማኅበረሰቡ ላይ አሉታዊ የሆነ ተጽዕኖን የሚያሳድር ነው:: አንድ ሰው ወደ በቀል እንዳይሄድ የሚያደርጉ ችግሮችን በእርቅ የምንፈታበት መንገድ እንዳለን ሁሉ የወንድሙን ደም የማይመልስ ልጅ አይወለድ የሚባል አባባል እንዲሁ አለን::

ይህም በሰዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት የጠፋ እንደሆነ በተጎጂው ቤተሰብ ውስጥ የሚወለደው ልጅ ይህንን ደም የመመለስ ኃላፊነት እንዳለበት ከልጅነቱ ጀምሮ ይነገረዋል:: ያ ልጅም ሲያድግ ወዳጅነቱ ሳይሆን ጠላትነቱን እያሰበ የተሰጠውን ኃላፊነት እያብሰለሰለ በቀሉን ሲመልስም ጀግና የሚል ካባን ይጎናጸፋል:: ከባህል በተጨማሪ ሰዎች በቀል ለመመለስ ጊዜያዊ ንዴታቸውን የሚመልሱበት፣ ጊዜያዊ የሆነ ፍትህን የሚያረጋግጡበት አድርገው ይወስዱታል:: አሁን ባለንበት በዚህ ዘመን ይህ ሥርዓት አለ ያልን እንደሆነ ምላሹ አዎ ነው:: ይህ የሆነው የፍትህ ሥርዓቱን ባለመተማመን ነው ወይንስ የበቀል ጥማት የሚለው ጥያቄው ሲሆን የዛሬው ዶሴ ገጻችን በዚህ አስተሳሰብ ከቤተሰብ አልፎ ከተማን የተሻገረ በቀለኛነት ነው::

የ23 አመቱ አዳነ ሰውነት ትውልድና እድገቱ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ሲሆን አዳነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ቀጥታ ወደ ሥራ ነበር የገባው:: በዚያው በአማራ ክልል በጉልበት ሥራ የተወሰኑ ዓመታትን ከሥራ በኋላ በሚሠራበት የተቋራጭ ሥራ አማካኝነት ለስድስት ወር በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ቦረና እንዲሁም በግንባታ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል::

አዳነ ለወላጆቹ ሁለተኛ ልጅ ሲሆን ከቤተሰቦቹ ቤት ሲወጣ ያን ያህል ተቀባይነት አልነበረውም:: ምክንያቱም አዳነ የሚሄድበት ቦታ የሚያውቁት ዘመድ፣ ቤተሰብ የሌላቸው በመሆኑ እንዴት ሆነህ ትኖራለህ የሚል ምክንያትን ቤተሰቦቹ ለእርሱ ከመጨነቅ ያነሱ ነበር:: አዳነ ግን በባህሪው ደፋር ነውና ከሚሰራበት ነገሌ ቦረና የነበረውን የኮንትራት ሥራ ከጨረሰ በኋላ ወደ ቤተሰቦቹ ተመልሶ በዚያ ሌሎች ሥራዎችን እየሠራ ከቆየ በኋላ በድጋሚ ሌላ ሥራ አገኘ:: በሚሠራቸው ሥራዎች ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር የሚጥረው አዳነ በዚህ አማካኝነት በሶማሌ ክልል ሌላ ሥራ በማግኘቱ ቀጣይ ጉዞውን በዚያ አደረገ::

አዳነ ሁለት ወንድሞች ያሉት ሲሆን፤ በምሥራቅ ጎጃም ጎንቻ ወረዳ 011 ቀበሌ የሚኖሩት ወላጆቹ የልጆቻቸው ባህሪ ፍጹም የተለያየ ነው:: አዳነ ከቤተሰቡ ውስጥ ቁጡ የሆነ፤ በቶሎ የሚናደድ ሲሆን፤ ታናሽ ወንድሙ ሞገስ ደግሞ ዝምተኛ የሚባል ባህሪ ያለው ነው:: ታላቅ ወንድሙ እናውጋው የቤተሰቡ ታላቅ ብቻ ሳይሆን ለታናናሾቹ እንደ አባትም እንደ አማካሪ ጭምር የሚታይ ነው::

ወጣቱ እናውጋው የቤተሰቡ ተተኪ ነው:: በሚኖርበት ምሥራቅ ጎጃም ዞን በሚሠራበት ሥራ ላይ ባሉት ተፎካካሪዎች ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ማለትም አንዳንድ ጊዜ ጸብ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰላም ሆኖ ይውላል:: ነገር ግን ነገርን እንዳመጣጡ መመለስ የለመደው ተግባር ነበር::

ወቅቱ የክረምት ወቅት ሲሆን የሐምሌ ጨፍጋጋ አየር በአንዱ ቀን እናውጋው ለሥራ በወጣበት ለወትሮው በተመሳሳይ ሰዓት ይመጣ የነበረው ሰው ወደቤቱ ሳይመለስ ይቀራል:: ወጣቱ እናውጋው ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ከወላጆቹ ጋር የሚኖሩት በአንድ አካባቢ ነው:: ታዲያ የባለቤቷ መዘግየት ቅር ያሰኛት ሚስት ለወንድሙ ሞገስ ወደ እርሱ መጥቶ ስለመሆኑ ትጠይቀዋለች::

ነገር ግን በዚያን ቀን ሞገስ ከወንድሙ ጋር በአካልም ሆነ በስልክ አልተገናኙም:: ታዲያ ምናልባት ሥራ በዝቶበት ይሆናል በሚል ሲጠበቅ የነበረው አባት በሥራ ስፍራው በተፈጠረ ጸብ በጥይት ተተኩሶበት ሕይወቱ ማለፉን ቤተሰቦቹ ተረዱ:: ይህ በቤተሰቡ ዘንድ እጅግ ያልተገመተ እና ያልታሰበ ነበር:: የአንድ ልጅ አባት የሆነው እና ለወንድሞቹ እንደ አባት የሆነው እናውጋው ሰውነት በተፈጠረ ጸብ ሕይወቱ ማለፉ ሲሰማ ከቤቱ ርቆ ለሚገኘው አዳነ መናገር ደግሞ ሌላኛው የቤተሰቡ ጭንቀት ነበር::

ይህ ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ ወንጀሉን የፈጸመው አቶ እሱባለሁ የተባለው ግለሰብ ሲሆን ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ በሕግ ቁጥጥር ሥር በመዋል አስፈላጊው ውሳኔ ተሰጥቶበት በማረሚያ ቤት ይገኛል::

ያልታመነበት ፍትህ

ሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ወንድሜ እናውጋው ሰውነት በምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎንቻ ወረዳ 011 ቀበሌ የሀብታሙ እሱባለሁ አባት በእስር ላይ የሚገኝ ወንድሙን በጥይት ገድሎታል:: ይህንንም ወንድሙ ሞገስ እና የወንድሙ ሚስት ባለበት ቦታ ሆነው የወንድሙን ማረፍ ነግረውታል:: አዳነ የወንድሙን ኀዘን በቅርብ ሆኖ አለመገኘቱ እንዲሁም ወንድሙን ያጣው በሰው እጅ መሆኑ በውስጡ የሚቆጭበት እና የሚብሰለሰልበት ጉዳይ ሆኗል:: በሀገሩ ባህል መሰረት የወንድሙን ደም ለመመለስ ወደ ሱማሌ ክልል ለሥራ ሄዶ በሚገኝበት ምን ማድረግ እንደሚችል ሲያስብ ከርሟል::

ይህንንም ለመመለስ ከወንድሙ ሞገስ ሰውነት ጋር በመነጋገር የወንድሙን ሕይወት ነጥቆ በማረሚያ ቤት የሚገኘው ሰው ልጅ በአዲስ አበባ አጎቶቹ ጋር እንደሚኖር መረጃው ደረሰው:: አዳነ የወንድሙን ፍትህ የሚያገኘው በዚህ እንደሆነ በማመን ቀን ቆጥሮ ወንድሙ ከሞተ ከጊዚዬያት በኋላ ዓመት ሊሞላው ሲል የወንድሙን ደም መመለስ እንዳለበት ወሰነ::

ለዚህም ከወንድሙ ሞገስ ጋር በመማከር ከሚሠራበት ሱማሌ ክልል ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከወንድሙ ጋር ጀሞ ተገናኝተው ግድያውን ለመፈጸም ሲያቅዱ ከቆዩ በኋላ መጀመርያ ቦታውን ሄደው በማየት ከዚያም ሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ላይ ያሰቡትን ለማድረግ ወሰኑ::

የአቶ እሱባለሁ ልጅ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በዚህ ቀን ከትምህርት ቤት በመመለስ ላይ እያለ በግምት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሟችን ለመግደል በማሰብ የገዙትን ስለት በመያዝ የቦታው ሰዋራነት እና የዝናብ ወቅት መሆኑን በማሰብ የያዙትን ስለት በተደጋጋሚ በሰውነቱ ላይ በማሳረፍ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ሕይወትን ለማጣፋት በሚተናነቁበት ሰዓት በአካባቢው ሲያልፉ የነበሩ ሰዎች ባሰሙት ጩኸት የያዙትን ስለት ከሰውነቱ ላይ ሳይነቅሉት ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ አደጋውን አድርሰው ለማምለጥ ሲሞክሩ በአካባቢው ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ችለዋል:: በወቅቱ በአካባቢው ከነበሩ ሰዎች በመንገዱ ሲያልፍ የነበረ የጸጥታ አባል እንዲሁ በቦታው በመኖሩ ብዙም ሳይርቁ በቁጥጥር ሊውሉ ችለዋል::

የወንጀሉ ዝርዝር

በሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ልዩ ቦታው ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን ገደል ግቡ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ሟች ሀብታሙ እሱባለው አባቱ እሱባለሁ ይርሳው የተባለው ሰው ወንድሙን እናውጋው ሰውነትን በጥይት ተኩሶ ገድሎታል (በ2014 ዓ.ም) የተፈጸመው ወንጀል ላይ ተከሳሽ ቂም በመያዝ እና የገዳይን ልጅ ለመግደል 1ኛ ተከሳሽ አዳነ ሰውነት 2ተኛ ተከሳሽ ሞገስ ሰውነት በመሆን በማቀድ ሟች ከሚማርበት ትምህርትቤት ሲወጣ ጠብቆ በመከተል ለግድያው ስለት በመያዝ (ገዝተው) ሟች ወደ መኖርያ ቤቱ በመሄድ ሳለ ወንጀሉን ፈጽመዋል:: በዚህም ፖሊስ ወንጀለኞቹን በቁጥጥር ሥር ካዋለበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ማጣራቶችን በማድረግ ማስረጃዎችን ሲያጠናክር ቆይቷል::

ማስረጃዎች

የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ዘርፍ ለባጦ ኬሚካል ምርመራ ዲቪዚዮን ክፍል በአካባቢው የነበረውን ደም በማጣራት የፎረንሲክ ምርመራውን ያደረገ ሲሆን፤ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የአስክሬን የምርመራ ውጤት፣ በቦታው ወንጀሉ ሲፈጸም የተመለከቱ እና ወንጀለኞቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያደረጉ ግለሰቦችን እንደ የሰው ምስክር ማስረጃ አድርጎ በማያያዝ ማስረጃዎቹን አጠናክሯል::

ውሳኔ

ተከሳሽ አዳነ ሰውነት እና ሞገስ ሰውነት በተከሰሱበት የሰው መግደል ወንጀል ጉዳይ በክርክር ላይ የነበሩ እና በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድቤት የልደታ ምድብ ችሎት ታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፍርድቤቱ ክስና ማስረጃን ከሕግ ጋር አገናዝቦ በሰጠው ውሳኔ ተከሳሾች እያንዳነዳቸው በ13 ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡ በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You