ዛሬ፤ በአንድ በኩል በብዙ ተስፋ የታጀበ ስኬት እያየን ያለንበት(ለምሳሌ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የስኬት ጉዞ)፤ በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ወደ ኋላ፣ የተመለስንበትና በወርቃማው ዘመን የወርቃማዎቹ ትውልድ አባላት የተከሉልንን አበባ እየነቀልን፤ በተለይም የኛ ያልሆኑትን፤ ጭራሹንም የማይጠቅሙንን ብቻ ሳይሆን የሚያጠፋንን እየተከልን የምንገኝበት አስፈሪም ጊዜ ነው።
በዛ ያገሪቱ የኢትዮጵያ ፍልስፍና መባቻ ዘመን የነበረው ትውልድ አባላት ፕሮፌሰር ጌታቸው (2001፣ 23) እንዳሉት “የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአእምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተሰጥኦ” ያላቸው፤ የረቀቀና የመጠቀ ሀሳብ ባለቤት ነበሩ። በመሆኑም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ አሻራቸውን ጥለው አልፈዋል። ከዘመነ ማርክሲዝምና ኮሚኒዝም በኢትዮጵያ ጀምሮ እየተነቀለና በስፍራውም ሌላ ፍልስፍና እየተተከለ ቢሆንም።
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ዋና ዋና የፍልስፍና ዘርፎች (ሥነ-አመክንዮ – ”logic”፣ ሥነ-ኑባሬ – ”Ontology”፣ ሥነ-እውነት – ”metaphysics”፣ ሥነ-ዕውቀት -”epistemology”፣ ሥነ-መለኮት – ”theology”፣ ሥነ-ምግባር ”ethics”፣ ሥነ-ውበት – ”esthetics”፣ ሥነ-መንግሥት – ”politics”፣ ሥነ-ቋንቋ – ”Linguistics” ወዘተ ወዘተ) ላይ አስቀድሞ የተፈላሰፈ ቢኖር እሱ ኢትዮጵያዊ ነው እስከሚባል ድረስ የተሄደበት ርቀት መኖሩ የሚዘነጋ አይደለም።
ይሄው መነቀልና በሌላ መተካት ያሳሰባቸው የሚመስሉት ፕ/ር ጌታቸው ትውልዱም ከዚሁ መነጠሉን በሚያመለክት ሁኔታ አገሩ “ትውልዱ የነፃ ሀሳብና የምርምር ሰዎች እንደነበሯት ሲያውቅ ይኮራል።” ሲሉ የዘመናትን ርቀት በመስበር የትውልዶች ድልድይ በመሆን ያገናኛል ሊባል በሚችለው “ደቂቀ እስጢፋኖስ” ስራቸው የቀድሞዎቹን ወደዚህ ወደ አሁኑ ዘመን በማምጣት አስተዋውቁናል። ምን ያህል ተሳክቶላቸው መንቀል ቀርቶ ተጨማሪ ተከላዎች እንደሚከናወኑ ወደ ፊት የሚታይ ነው የሚሆነው።
እርግጥ ነው ያለንበት ዘመን የጉግማንጉግ ዘመንን ይመስላል። ዛሬ ¨monologue” (እኔን ስማኝ) እንጂ “dialogue” (ውይይት) የለም፤ ያለው የመከነ የሚመስል፣ ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀውን “civil society” (የነቃ ማህበረሰብ) መፍጠር ቀርቶ ለራሱም የማይሆን “political society” (የፖለቲካ ማህበረስብ) ነው ያለው። ነባሩ ፍልስፍናችን፣ አጠቃላይ ትውፊትና ማህበረ ባህላዊ እሴቶች እንዲነቀሉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ያለም የአንቂነት ሚና ይጫወታል ተብሎ የሚጠበቀው አካል በፖለቲካዊ አስተሳሰብ በድርቅ መመታትና ከፖለቲካ ፍልስፍና ጋር ጭርሹን አለመተዋወቅ ነው። ይህም ፈላስፋው ቸርበርት እንደሚሉት በዜጎች መካከል ስር የሰደደ ጥላቻና መጠፋፋት (deeper hatred and animosity) እንዲሰርፅ እየተሰራ መገኘቱ ከበቂ በላይ መረጃ ነው።
ነባሩን “ፊውዶ-ቡርዧ” ነቅለን በ”ኮሚኒዝም”፤ “ኮሚኒዝም”ን በ”ፌደራሊዝም”፤ “አንዲት ኢትዮጵያ”ን በ”ክልሎች”፣ “አንድነት”ን በ”ልዩነት”፤ “ዜግነት”ን ነቅለን “ብሄር” ተክተናል። የመብት ጥጋችን “እስከመገንጠል” ድረስ የዘለቀ ሲሆን፤ አሁን የደረስንበት ደረጃ ደግሞ ላቅ ያለና የቀድሞውን “ኢትዮጵያ ትቅደም” ነቅሎ በ”ኢትዮጵያ ትውደም” (down down Ethiopia) የተካ የፖለቲካ ቁልቁለት ነው። ድሮ በሁለት ቃላት (በህግ አምላክ) ብቻ ቀጥ ይል የነበረው ወንጀልና ህገ-ወጥነት ዛሬ ባታሊዮን ጦርን በመገዳደር አቤልና ቃኤልን እያፈራ፣ ሀብትና ንብረትን እያወደመ፣ ከተሞችን ወደ ፍርስራሽነት እየቀየረ፤ ኢንተርሀይሙዌያዊ ፖለቲካን እያነገሰ ይገኛል። ሌብነት ቁጥር አንድ ሀጢያት እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ ሙስና የባለ ፀጋነት ሀሁ ሆኖ አርፎታል። (እዚህ ላይ ያ ተነቅሎ ለምን ይሄ ተተካ አይደለም የዚህ ፅሑፍ ክርክር፤ ክርክሩ ውጤቱ ላይ ነውና በዚሁ መልኩ መረዳት ተገቢ ነው።)
የዘርዓያዕቆብ የስነምግባር ስነ ሰብእ ፍልስፍናና በስርአተ ትምህርቱ ውስጥ የመካተቱን አስፈላጊነት (“የኢትዮጵያ ፍልስፍና”፣ ገፅ 212 – 215 ይመለከተዋል) ያንን ያህል የለፋበት አቢይ ጉዳይ ይህ እንዳይሆን ነበርና አሁንም ጊዜ አለ።
ኢትዮጵያ ከማንም በፊት የራሷ ልጆች ያፈለቁት የራሷ የሆነ ፍልስፍና ያላት አገር ነበረች። በጉዳዩ ላይ ሰፋና ጠለቅ አድርገው ከሄዱበት አጥኚዎች እንደምንረዳው ኢትዮጵያ በበርካታ ጉዳዮች ቀዳሚ ነበረች፤ ነችም። ምንም እንኳን “የመጀመሪያ” የሚለው ቃል በአንድ ወቅት አጓጉል ውሎን ውሎ አሰልቺ የነበረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ በበርካታ ጉልህ ሀሳቦች ቀዳሚ መሆኗን የሚሽር የለም።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲው ብሩክ ዓለምነህ የዘርዓያዕቆብን እና ደቀመዝሙሩ ወልደ ህይወትን መ(ሟ)ሟገቻ በማድረግ በርካታ ምሁራንን በአንድ ያካተተበትና ጠቃሚ የውይይት መድረክ የከፈተበት “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መጽሐፉ እንደሚነግረን በዘርዓያዕቆብ አማካኝነት ኢትዮጵያ የመሪነትን ቦታ ይዛለች።
ብሩክ ምንጮችን ጠቅሶ በዘርዓያዕቆብን አማካኝነት “ዘመናዊ ፍልስፍና በአውሮፓና በኢትዮጵያ በእኩል ዘመን (በ17ኛው ክ/ዘመን) ላይ ነው የተጀመረው።” (ገፅ 5) ይለናል። ይሁንና እነሱ እዚህ ሲደርሱ እኛ የት ጋር ነው ያለነው የሚለው የሁሉም ጥያቄ መሆኑ እርግጥ ሲሆን፤ ችግሩ አሁንም የባሰ ወደ ኋላ ለመሄድ እየነቀልን የምንተክለው ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና አጠቃላይ ፍልስፍናችን መብዛቱ ነው። ከላይ (deeper hatred and animosity) ያልነውን ጨምሮ።
ነልሰን ማንዴላ በ”LONG WALK TO FREEDOM: The Autobiography of NELSON MANDELA” ላይ በአጭርና ጠንካራ አገላለፅ የገለፁት ታሪክና የአይን ምስክርነታቸውን መሰረት ያደረገ ሀሳብ ቢኖር “ኢትዮጵያ የአፍሪካ መፈጠሪያ ስፍራ ነች።” የሚለው ሲሆን፤ ይህንንም ሀሳብ ብሩክ ጉዳዩን ቀደም ሲል ከጠቀስንለት፤ ከአውሮፓ ወደ አፍሪካ ያመጣውና “የዘርዓያዕቆብ ሀተታ በአፍሪካ ውስጥ በሥነ ጽሑፍ የተዘጋጀ የመጀመሪያው የፍልስፍና መጽሐፍ ነው።” (4) ሲል ያረጋግጥልናል። ከዚሁ ከሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ሳንወጣ የምናገኘው ሌላ መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር የአፍሪካ ሥነጽሑፍ ጉዳይን ጉዳዬ ብለው የያዙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የዶ/ር መላክነህ መንግሥቱን ሀሳብ ሲሆን እሱም “የአፈወርቅ ገብረየሱስ ‘ጦቢያ’ በአፍሪካ ቋንቋ የተፃፈ የመጀመሪያው አፍሪካ የሥነ ጽሑፍ ስራ ነው።” የደራሲት Drusilla Dunjee Houstoን ስራዎች መመልከቱ ኢትዮጵያ ምን ያህል የአለም ስልጣኔ እናት እንደነበረች መረጃና ማስረጃዎችን ቆጥሮ ይቀበላልና እንጠቁማለን። እንደ ኦፕን ዩኒቨርሲቲዋ ዶክተር ካሚላ ጆርዳን ጥናት ለአሁኑ ዘመን ኮምፒዩውተር መፈጠር መነሻዋ በጥንታዊያኑ ሲራራ ነጋዴዎቿ አማካኝነት ኢትዮጵያ ነች። (ከቢቢሲ አርካይቭ “Amazing Methods of Ethiopian Culculation” በሚል የተዘጋጀውን ዘጋቢ ፊልም ይመልከቱ።)
ከዚሁ ጋር አያይዘን ለ750 ዓመታት በህገ መንግስት ሰነድነት አገሪቱ ስትመራበት የነበረውን ፍትሀ ነገሥት”፤አለም ከመዝረፉም በላይ ሊነጥቀን (እስካሁን ካልነጠቀን) ያሰፈሰፈውን “መጽሐፈ ሄኖክ”ን እና የመሳሰሉትን ስናካትት ቀዳሚው ፍልስፍናችን ምን ያህል ተጠንቶ እንደተተከለ፤ በአሁኑ ዘመንም ምን ያህል “አበባው እየረገፈ” እንደ ሆነ እንረዳለንና ቢያሳዝንም ሆነ ቢያስቆዝም አይገርምም።
ወደ ፕ/ር ጌታቸው ሀይሌ ስንመጣም የምናገኘው ሀሳብ የበለጠ የሚያስቆጭ እንጂ አስደሳች ስሜትን የሚፈጥር አይደለም። ፕሮፌሰሩ ቀደም ሲል በጠቀስነው የመረጃ ቋት መጽሐፋቸው የ15ኛውን ክፍለ ዘመን ከፍታ ከፍ አድርገው ያሳዩንን ያህል አሁን እየሰራን ባለነው የንቅለ ተከላ ስራ ደግሞ ዝቅ እንድንል የሚያደርግ ነው። እንዲህ ነው የሚሉን፤
“ደቂቀ እስጢፋኖስ የተነሱት በአፄ ይስሀቅ (1406 – 1421) ዘመን ሲሆን ማርቲን ሉተር በጀርመን ላይ ተመሳሳይ ሀሳብ ይዞ ከመነሳቱ ከሰላሳ ዓመት ግድም በፊት ነው።” (24) ይሁን እንጂ እነዚህ ቀዳሚ የኢትዮጵያ ፈላስፋዎችና ፍልስፍናዎች እንዲነቀሉ ተፈረደባቸውና ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት “አበባቸው እረገፈ።” (24)
ወደ ብሩክ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ስንመለስ የኢትዮጵያን ፍልስፍና በአለም አቀፍ የፍልስፍና መስፈርትና መድረክ ላይ ተመዝኖ እናገኘዋለን። እንደ ብሩክ ጥናትና ድምዳሜ የዘርዓያዕቆብ ፍልስፍና የቆመበት መሰረት “ሜታፊዚክስና ኤቲክስ” ነው። በመሆኑም ይህን “በጣም አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ የ19ኛው ክፍለ ዘመን የጀርመን ፈላስፎች የሆኑት ሼሊንግና ሄግልም የዘርዓያዕቆብን አይነት የሜታፊዚክስ ፕሮጀክት [የ]ነበራቸው” (ገፅ 8)መሆኑ ነው።
በሀይማኖትና ወታደራዊው ዘርፍም ኢትዮጵያ ቀዳሚ ቦታ አላት። የአፍሪካ ጃዝ ሙዚቃ አባት ሙላቱ አስታጥቄ እንዳለን ከሆነ በወታደራዊ ሰልፍ ወቅት የማርሽ ባንዱ የሚመራበት ዘንግ (በማሽከርከር) መነሻው ወይም የተወሰደው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን መቋሚያ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ የህንድ አምባሳደር የነበሩት ሰው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩትም ሆነ፤ የቀድሞው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሞሃን ሲንግ እዚህ አዲስ አበባ፤ ፓርላማ ተገኝተው እንደተናገሩትም በአራተኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ወታደሮች አገራቸው ተገኝተው አስፈላጊውን እገዛና ሰላም ማስከበር ስራ ሁሉ ባይሰሩ ኖሮ ህንድን እንደ አገር የመመስረቱም ሆነ እዚህ የማድረሱን ሂደት አስቸጋሪ ያደርገው ነበርና የኢትዮጵያ ስልጣኔ፣ የፍልስፍና አድማሷና ተፅእኖዋ እጀ ረጅም መሆኑን ያሳየናል። የ“Ethiopianism”ን ፍልስፍናንም ከዚህ ጋር አያይዞ ማሰብ ይቻላል።
በጥበቡ ዘርፍ፤ ማለትም በአጠቃላይ (ጥበብ) “craft/””art-craft” (ሥነ-ጥበብ፣ እደ-ጥበብ፣ ኪነ-ጥበብ እና አውደ-ጥበብ) ዘርፉም ኢትዮጵያ ከማንም በፊት ነበረች፤ አገር በቀል እውቀቱም እንደዛው።
ፍልስፍናውን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ከሚያሰኙት እሴቶች አንዱ እደ ጥበብ እንደመሆኑ መጠን ከእነዚህም መካከል አንዱ የሸክላ ስራ ነው። ምን ያደርጋል ያ እየተነቀለ፤ በምትኩ የሴራሚክስ እንስራ፣ የሴራሚክስ ጀበና … በቦታው እየተተከለ (የሚመለከታቸው ወገኖች ቢያንስ ለዜጎች የስራ እድልና ኢኮኖሚያዊው አስተዋፅኦው ሲሉ ለምን ከመነቀል እንደማይታደጉት ባይታወቅም) ይገኛል። በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ተግባራትንና የየዘመኑን ፍልስፍናዎች ለመረዳት፤ በተለይ እያልንለት ያለው “ዘመነ ንቅለ ተከላ” ምን ያህል ወደ ኋላ እንዳስቀረን ዋና ትኩረቱ ማህበራዊ ሂስ ላይ ያደረገውን፤ የየዘመናቱን ሃይማኖታዊ፣ ማህበረ-ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ግራ መጋባት፤ አድሏዊና ኢፍትሀዊ አሰራርን የሚያጋልጠውን፤ ማህበረሰቡ ከዚህ እንዲላቀቅ ምን መደረግ እንዳለበት፤ እስከዛሬ ከዚህ አይነቱ የጥንቱን አገራዊ ፍልስፍና ያለማሳደግና አለማዘመን አሰራር ባለመላቀቃችን ያስከፈለንን ዋጋ በአፅንኦት የሚመክረውን የፍሥሐ ይሁን “መጽሐፈ ቡዳ”ን ደግሞ ደጋግሞ መፈተሽ ይገባናል።
ከባህላዊ መድሃኒትና ህክምና ጋር በተያያዘ፤ ፕሮፌሰር ፓንክረስት፣ በደሴ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አሰፋ ባልቻ እኔ ሌሎችም እንደሚነግሩን ከሆነ ከጣሊያን ማንነታችንን የማጥፋት ሴራ ጀምሮ እየተነቀለ በመምጣት ላይ ሲሆን አሁን ጭራሹን ተመንግሎ ሊጣል የቀረው አንድ ሐሙስ ብቻ ነው።
ይህ ሁሉ፤ በርካታ እዚህ የጠቀስናቸውም ሆኑ ሌሎች፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍናም ሆነ አጠቃላይ ማንነት እየተሸረሸረ፣ “እምቦጭ፣ እንዘጭ” … እንዲል ምክንያቱ ምንድነው? ስንል ምላሽ የምናገኘው ከዚህ ቀደም እንደጠቀስነው ከወደ አርሲ ነው።
የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርት መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ሮብሰን መርጎ “A Critical Review and Analysis Ethiopian Modern Secular Education from Multiculturalism Perspectives: The Quest for Balancing Indigenous Knowledge and Western Knowledge” በሚለው ጥናታቸው እንዲህ ይላሉ፤
እንደ ዶ/ር ሮብሰን መርጎ ጥናትና ማብራሪያ አገራችን በአገር በቀል እውቀት የበለፀገች፣ የበርካታና ለአለም የተረፉ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ሆና እያለ ይህ በአገራችን ትምህርት ውስጥ ተካትቶ ሲሰጥና ትውልድን ሲቀርፅ እስከ ዛሬ አልታየም። ይህ ደግሞ የአንድ መንግስት ወይም ስርአት ችግር ብቻ ሳይሆን በአራቱም ስርአተ መንግስታት (ከአፄ ሚኒሊክ እስከ ኢህአዴግ) የተስተዋለና ተከታታይ ትውልድን ለባእዳን ፍልስፍና አምላኪነት አሳልፎ የሰጠ፤ በማንነት ጉዳይ ላይ የከፋ ውዥንብርን የፈጠረና የትውልድን ከገዛ ባህል መነጠልን ያስከተለ ሂደት ሆኖ ያለፈ፤ አሁንም እየሆነ ያለ የመማር-ማስተማር ሂደት ነው።
“አገራችን፣ ገዳ፣ ደመራ፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት “ንባብ ቤት”፣ “ቅኔ ቤት” እያለ የሚሄደውና ለማጠናቀቅ 16 ዓመታትን የሚወስደው (ይህ ከምእራባዊያን የዲግሪ ፕሮግራም ጋር እኩል ነው)፤ በእስልምናውም “መድረሳ”ን የመሳሰሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶች፤ እድሜ ጠገብ ትውፊቶች፣ ባህላዊ ህክምናዎች፣ እደጥበባት፣ የፅሑፍና የቃል ቅርሶች፤ የኮንሶ እርከን ስራ፣ ግጭት አፈታት ስርአታችን፣ ጨምበላላ …… ወዘተ የመሳሰሉ ሀብቶችና ማህበረ-ባህላዊ እሴቶች እያሏት እነዚህ በስርአተ ትምህርቱ ውስጥ ተካትተው ትውልድ እንዲያውቃቸውና ትውልድን እንዲቀርፁ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲገነቡ፣ የተለያየ ባህል ያላቸው ኢትዮጵያዊያን እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ ትውልድ ከባህሉ እንዳይነጠል ማድረግ ሲገባ አልተደረገም።” የሚሉት አጥኚው ይህ አገራዊ ችግር ከአሁን በኋላ ሊቀረፍና የአገራችን ስርአተ ትምህርት ቀረፃ ከውጪው እውቀትና ፍልስፍና ጋር ሚዛን ጠብቆ ሊካተት ይገባል ሲሉም በአፅንኦት ይመክራሉ።
ከዚሁ ከዶ/ር ሮብሰን ሀሳብ ጋር የሚሄድ አንድ ወቅታዊ ጉዳይ ቢኖር ሰሞኑን የኢሳት ቴቪ ያስኬደው ፕሮግራምና አሁን እኮ ጭራሹን ኢትዮጵያ ሲባል መስማት የማይፈልግ ትውልድ ተፈጥሯል። የሚለው ነው። ያስፈራል፤ ከማስፈራትም አልፎ ብርድ ብርድ ይላል።
ከዚህ ከትውልድ ጋር በተያያዘ፤ የተለያዩ የፍልስፍና ክፍሎች (መግቢያችን አካባቢ የጠቀስናቸው)በዘርዓየዕቆብ እና ወልደ ህይወት ሀተታዎች ማስተንተኛነት የቀረቡበት “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ሆነ የዶክተር እጓለ ዩሀንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” መፃህፍት፤ በቀጥታ የሚናገሩትን የፕሮፌሰር መስፍን “እንዘጭ እምቦፅጭ”፣ “ክሽፈት እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” እና ሌሎችንም በመፈተሽ የት እንደነበርን፣ ምን ላይ እንደምንገኝ፣ ወደ ፊት ምን ላይ እንደምንደርስ መገንዘብ ይቻላልና መልካም ንባብ እንላለን።
በመጨረሻም፤ ሌላው “ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን” የሚለው፤ “ዛሬ/አሁን”ን አጥብቆ የፈራው የሬዲዮ አድማቂው አባባል ነው። እርግጥ ነው ትናንት እና ነገ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ዛሬ ደግሞ እጅግ አንገብጋቢ ነው። በመሆኑም ከመሀል የተነቀለው “አሁን”ም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በዚህም በ”ዛሬ/አሁን” ላይ በሚገባ ልንወያይ፤ ነባር ማንነትንና ፍልስፍና ከመንቀል መቆጠብ አለብን፡፡ ወንድሙ አቤልን ከገደለው ቃኤል ተምረን ከተዘፈቅንበት ማጥ እንድንወጣ ልንነጋገር ይገባል እንጂ፤ “ነበርን” እና “እንሆናለን” እያልን “መሀል”ን ልንዘለው አይገባምና ሊታሰብበት የግድ ይሆናል። “ነበርን” ታሪክ ነው፤ “እንሆናለን”ም ተስፋ ነው። ቁልፉና የተግባር ወቅት የሆነው ደግሞ “ዛሬ” ነው። የከፋ ችግር ውስጥ ያለነው ዛሬ፤ ከ¨monologue” (እኔን ስማኝ) ልንወጣ ወደ “dialogue” (ውይይት) ተሸጋግረን ወደ መሀል መምጣትና በነባሩ ግን ደግሞ በተነቀለው ፍልስፍናችን፣ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነታችን ላይ ልንነጋገርና ልንግባባ የሚገባን ዛሬ/አሁን ነውና አባባሉ ከመሀል የነቀለውን ሊያስብበት የግድ ይለዋል።
የመጨረሻው ማጠቃለያችን፤ አንንቀል፣ ከነቀልንም እንለይ። መትከሉ ላይ ግን እንበርታ። ከመነቀል ሁሉ የከፋው ከማንነት መነቀል ነውና ማሰብ ያስፈልጋል። ማንነታችን አብሮነት፣ ወንድማማችነት ነው እንጂ ሌላ አይደለምና ወደ ነበረበት ሊመለስ ይገባል። የቆየው የአኗኗር ዘይቤያችንም ሆነ ፍልስፍናችን መሰረቱና አላማው ይሄው ነውና ሳይነቀል ሊዳብርና ሊቃናም ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ግርማ መንግሥቴ