ወቅቱ እ.ኤ.አ 2014 ነበር። በአህጉረ አፍሪካ በሀገረ ጊኒ 49 ሰዎች በበሽታ ተለከፉ። የ29 ሰዎች ሕይወትም ተቀጠፈ። ተመራማሪዎች በሽታውን ለመለየት ርብርብ አደረጉ። ኢቦላ መሆኑን ደረሱበት።
በቀጣይ ሶስት ዓመታትም በበሽታው ሳቢያ በዓለም ከ11 ሺህ 325 በላይ ሰዎች ህይወት ጠፋ። የወቅቱ የዓለም ጭንቅ በሽታው ብቻ አልነበረም። የጤና ስርዓቱ ተቃውሷል። ሠራተኞች ሞተዋል። ብዙ ሆስፒታሎች ተዘግተዋል። ክፍት ከተገኙም ከአቅማቸው በላይ በሕሙማን ተሞልተው ያስተናግዳሉ።
በበሽታው ክፉኛ በተጠቁት ሴራሊዮን፣ላይቤሪያ እና ጊኒ ውስጥ ሰዎች ወደ ሕክምና መስጫ መሄድ አቁመው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። በሽታው አስፈርቷቸው ነበር። በሽታውን ብቻ ሳይሆን የጤና ባሙያዎችንም ፈርተዋቸው ነበር። ባለሙያዎቹን ማንም ሊጠጋቸው አልደፈረም። እ.ኤ.አ በ2017 የተሰራው ጥናት እንደሚያሳየው በወረርሽኙ ምክንያት ለሕክምና ሙያ የሚሰጠው ዋጋ ቀንሷል።
ሐኪም ቤት መውለድ የሚፈልጉ ነፍሰጡሮች ቁጥር 80 በመቶ ቀንሶ ነበር። ወባ የያዛቸውን ልጆች ወደ ሆስፒታል የሚወስዱ ቤተሰቦች ደግሞ 40 በመቶ አሽቆልቁሏል። ለክትባት ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱ ሰዎችም ቀንሰዋል። በአለም አቀፍ ርብርብ ወረርሽኙ ቢገታም፤ከበሽታው በላይ ጉዳት ያስከተሉት ከበሽታው ጋር ተያይዘው የመጡት ችግሮች ነበሩ።
ከዘንድሮው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞም መሰል ስጋት መኖሩን ቢቢሲ በጥናት እያጣቀሰ አስነብቧል። መቼም ሟርተኛ አይባልም ሁኔታውን አገራትም ሆኑ ግለሰቦች በጥንቃቄ ደርሰው በመታዘብ ለመሻገር መጣር እንጂ።
አገራት ኮቪዲ-19ኝን መዋጋት ቅድሚያ እንደሚሰጠው ተናግረዋል። ለሕሙማን አልጋ፣ቬንትሌተር ተዘጋጅቷል። በፍልሚያ ውስጥም ይገኛሉ።በተለያየ ዘርፍ ያሉ ጤና ባለሙያዎች ወረርሽኙን ወደመከላከል ተዘዋውረዋል።
ትኩረታቸውን በኮቪዲ-19 ወረርሽኝ የተነጠቁት የዓለም አገራት ሕዝቦቻቸው በሌሎች ገዳይ በሽታዎች ሕይወታቸው እየተቀጠፈ እንደሆነ ጥናቶችን በማጣቀስ ቢቢሲን ጨምሮ የዓለም በርካታ ሚዲያዎች አትተዋል።
የሥነ ተዋልዶ ጤና፣የአዕምሮ ጤና ፣ካንሰር እንዲሁም መደበኛ የሕክምና ክትትሎችም በአለም ላይ ችላ እንደተባሉ ጥናቱ አመላክቷል። በኢትዮጵያም የክትትላቸው ጊዜ እንዲራዘም፣ መድኃኒት የሚፈልጉት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ እንዲወስዱ እና በስልክ መረጃዎች እንዲለዋወጡ የሚደረግ ሲሆን ግዴታ መምጣት የሚገባቸው ደግሞ በአካል በመገኘት እንደሚታከሙ ሆስፒታሎች ይገልጻሉ።
በመላው አለም ያሉ የካንሰር ሕሙማን ፣የኩላሊት እጥበት፣ አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና የሚሹ ሰዎችም ሰሚ አጥተናል ይላሉ። በኢትዮጵያም የልብ ሕሙማን ማከሚያ ሆስፒታልን ጨምሮ የሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታ ተጠቂዎች ማህበራት የዚህ ዓይነት ችግሮች ተጋላጭ እንደሆኑ ይነገራል።
በጥናቱ መሰረት በድሃ አገራት ከወረርሽኙ እኩል ኤች አይ ቪ ፣ቲቪና ወባ ያሰጋሉ።ሌላው ችግር በተገቢው ጊዜ ክትባት አለማግኘት እንደሆነም ተጠቅሷል።
የአለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፤ ወረርሽኙ ቢያንስ የ68 አገሮችን የጤና ዘርፍ ስለሚያቃውስ፤ 80 ሚሊዮን ጨቅላዎች ክትባት ባለማግኘታቸው ለኩፍኝ፤ ለፖሊዮ እና ሌሎችም በሽታዎች ይጋለጣሉ። በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ከአለም የጠፋው ፖሊዮም ዳግመኛ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም አብራርቷል።
ኢትዮጵያ ችግሩን ነቅታ በመፋለም ላይ ትገኛለች። በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በመላው አገሪቱ ከ15 ሚሊዮን በላይ ሕጻናት የኩፍኝ ክትባት በንቅናቄ ተሰጥቷል። ተግባሩን በስኬት መወጣት መቻላቸውም ከስኬት የሚቆጠር ነው።
የአለም አቀፉ የምግብ ተቋም ዋና ኃላፊ ዴቪዲ ቢሲሊ እንደሚሉት ፤ዓለም ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው አይነት ቸነፈር ይጠብቃታል። 130 ሚሊዮን ሰዎች ለዚህ ተጋላጭ ናቸው።አሁን ላይ 135 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አገራት እንቅስቃሴዎችን መገደባቸውም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። የሚፈጠረው የምጣኔ ሀብት ቀውስ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ አልያም ጠጪ እንዲሆኑም ሊገፋፋ
ይችላል ይላል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲው የበሽታዎች ጥናት ባለሙያ ኢፒዲሞሎጂስት ቲሞቲ ሮበርተን ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር የኮሮና ወረርሽኝ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ መወያየታቸውን ይገልጻሉ። በምዕራብ አፍሪካ ኢቦላ ሲቀሰቀስ ምን እንደተፈጠረ ስላየን አሁንም ምን እንደሚከሰት አይጠፋንም ይላሉ።
እነቲሞቲን በጥናታቸው እንደሚሉት በኮቪዲ 19 ወረርሽኝ ከሰሃራ በታች በሚገኙ ደሃ አገሮች በተለይም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ ሁለት ጉዳቶች ያደርሳል ይላሉ።
የመጀመሪያው በጤና ስርዓቱ ላይ የሚፈጥረው ቀውስ ነው። ሰዎች እርዳታ ለመጠየቅ ሊፈሩ ይችላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ የጤና ባለሙያዎች ሊታመሙ፣ ሙሉ ትኩረታቸውን በወረርሽኙ ላይ ሊያደርጉ፣ የመድሃኒት እጥረት ሊገጥማቸው ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ። ሁለተኛው ችግር ደግሞ በቂ ምግብ ባለማግኘት ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ይጋለጣሉ የሚል ነው።
በተመራማሪዎች ትንበያ መሰረት የጤና አገልግሎት የማግኘት እድል 50 በመቶ ሲቀንስ ምግብ ማጣት ደግሞ በዚያው መጠን ይጨምራል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ልጆች ፣56 ሺህ 700 እናቶች ሊሞቱ ይችላሉ።
የልጆችን ሞት ከሚያስከትሉ በሽታዎች መካከል ኒሞኒያ(የሳንባ ምች) እና በተቅማጥ ሳቢያ የሚከሰት የፈሳሽ እጥረት ይጠቀሳሉ። ሴቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ሕይወታቸው ሊያልፍ ችላል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በየቀኑ ለ100 ሚሊዮን ሰዎች ምግብ እያደለ ሲሆን ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸው የተመረኮዘው በዚህ እርዳታ ላይ እንደሆነ ይነገራል።
በተቋሙ አሃዝ መሰረት እርዳታው ከተቋረጠ በቀጣይ ወራት በየቀኑ 300 ሺህ ሰዎች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ።
የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄን ሀዋርድ እንደምትለው በመላው አለም የተራቡ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ተችሎ ነበር።ባለፉት አምስት አመታት በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ይህ ለውጥ ተቀልብሷል።
‹‹ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ክፉኛ ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ አስደንግጦን ነበር‹‹ ስትል ትገልጻለች። ወረርሽኙ 130 ሚሊዮን ሰዎች ብቻ አይደለም
ምግብ የሚያሳጣው። ድርጅቱ ርዳታ እንዳይሰበስብም እንቅፋት ይሆናል። የከተማ ነዋሪዎች ደግሞ በወረርሽኙ የበለጠ እንደሚጠቀም መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ሁኔታም ከዚህ ጥናት ነባራዊ ሐቅ ብዙ የተለየ አይደለም። ወረርሽኙ በአገሪቱ በተከሰተበት ወቅት የሚሰጡ አገልግሎቶችን እና ዋና ትኩረትን ሙሉ በሙሉ ወደ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የማድረግ አዝማሚያዎች ታይተው ነበር። የጤና ተቋማት አገልግሎትም ከተወሰኑ አገልግሎቶች እንደ እናቶችና ሕጻናት ጤና እና ከድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት በስተቀር እንደዚያው መልኩ ተቀይሮ ነበር። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በየትኛውም የጤና ተቋም ማንኛውንም አገልግሎት መስጠት እየተቻለ እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።
የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም በአገሪቱ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት በሰፊው ተከስቷል። እስከ ሕዳር ድረስ ሊቀጥል እንደሚችልም ባለሙያዎች እየገለጹ ሲሆን ክረምቱን ተከትሎ ሌሎች ከብክለት ጋር የተያያዙ እንደ አተት ያሉ የጤና እክሎች ሊከሰቱ ይችላሉ በሚል የሕክምና ተቋማት ዝግጅት አድርገዋል።
በሌላ በኩል የኩላሊት ሕሙማን ማህበራት፣የልብ ማከሚያ ሆስፒታሎች፣ የሕጻናት ማሳደጊያዎች፣የአረጋውያን መንከባከቢያዎች ጋር በተያያዘ የሚሰሙት የድረሱልን ጩኸቶች እየበረከቱ መጥተዋል። ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በለጋሽ ድርጅቶች እጅ መሰብሰብ እና ከወረርሽኙ ለመከላከል ሲባል በአካል እየተገኘ የሚጎበኝ እና አቅሙ የፈቀደውን የሚለግስ ባለመኖሩ ለፈተናዎች መዳረጋቸው እየተሰማ ነው። በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች የተነሳ ከሚከሰቱ መቆራረጦች በስተቀር የጤና ጣቢያዎች ያለምን ችግር ተገልጋዮቻቸውን አሰልፈው ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲሰለፉ በማድረግ መደበኛ አገልግሎቶቻቸውን ሲሰጡም በአካል ተገኝተን ተመልክተናል።
ሕብረተሰቡ በሚያሳየው ችልተኝነት የተነሳ የኮሮና ስርጭቱ እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም በጤና ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ጤና ሚኒስቴር የገለጸ ሲሆን ሕብረተሰቡ መከላከሉ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ራሱን፣ ቤተሰቡን እና አገሩን ከወረርሽኙ እንዲታደግ፣ ከመዘናጋት እንዲቆጠብ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ሙሐመድ ሁሴን