የቀድሞ የኦነግ አመራሮች የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ለማረጋገጥ ለረጅም ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። የደርግ መንግሥት ሲወድቅ የሽግግር መንግሥቱ አካል በመሆን በሰላማዊ ፖለቲካ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ መሠረት ሕገ-መንግሥቱን በማርቀቁ ሂደት ተሳታፊ ነበሩ። ከዚያ ቀጥሎ በ1987ቱ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቅድመ-ዝግጅት አድርገዋል። አልተሳካም እንጂ!
በስተመጨረሻ ከገዢው ፓርቲ ጋር ስምምነት በማጣታቸው አመራሮቹ ሀገር ጥለው ወጡ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሠራዊቱ አባላትም ሜዳ ላይ ተበተኑ፡፡ ይህንን ተከትሎ ለሁለት አስርት ዓመታት አስመራ የነበሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኢህአዴግ ከድተው ወታደር በመያዝ ወደ ኤርትራ የገቡትን የጀነራል ከማል ገልቹን ሠራዊት በመቀላቀል አብረው መስራት ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ ጀነራል ከማል ድርጅቱ ተሃድሶ እንዲያደርግ ከሌሎች አመራሮች ጋር ጠይቀው ባለመሳካቱ ትግሉ በዚህ መልክ ከቀጠለ የትም አይደርስም በሚል የኤርትራን ድንበር ሰብረው ለመውጣት ሙከራ የተደረገበትና ዋጋ የተከፈለበትም ጊዜ ስለመኖሩ ይነገራል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ለተቀጣጠለው አመፅና ለተገኘው ለውጥ ኦነግ የአንበሳው ድርሻ የእኔ ነው የሚል የታሪክ ሽሚያ ውስጥ መግባቱም የአመፁ ሂደት በኦሮሚያ ክልል መካሄዱን መሠረት በማድረግ እንጂ የአመፁ ዋና አቀጣጣዮችማ ከአመፀኞቹ ጋር አብረው እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ኤርትራ ተቀምጠው ምንም ሊፈይዱ የማይችሉትን ኦነግንና ሌሎች ተቃዋሚዎችን ሰላማዊ ጥሪ አቅርበው ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ሲያደርጉ አቶ ዳውድ ኢብሳም በዚሁ ዕድል ተጠቅመው በትግራይ በኩል ሠራዊታቸውን ልከው እርሳቸው አዲስ አበባ ገቡ፡፡
ቀደም ሲል ለጦርነትም ለሰላምም ሳይበቁ ኮሽ ባለበት ሁሉ ከላይ በጦር ጄት፣ ከታች መግቢያና መውጫ በሚያሳጣ ብርቱ ሠራዊት ሲታደኑ የኖሩት አማፅያን በሰላም ጥሪ ሰበብ ያገኙትን ከሰማይ የወረደ መና መሸከም ተስኖአቸው እንኳን ድርጊታቸው ንግግራቸውም ተቀየረ፡፡
«ዝሆን ጀርባ ላይ የተቀመጠች አይጥ መሬቱን አንቀጠቀጥነው!» እንዳለችው በእሳቱ የተለበለቡት እውነተኞቹ ታጋዮች እያሉ መሳደዱ ቀርቶለት ካለ ጦርነት ግባ የተባለው በአቶ ዳውድ የሚመራው ኦነግ «ድሉ የኔነው፣ ከምርጫ በፊት ሥልጣን ሊሰጠኝ ይገባል፣ የምን ትጥቅ መፍታት ነው፣ ትጥቅ አስፈቺውስ ፈቺውስ ማነው? ሠራዊታችን ራሱን እንዲከላከል አዝዘናል» እያሉ ራሳቸውን ተራራ ለማሳከልና ለነፃነትና ለዴሞክራሲ ያጎነበሰውን ኃያል መንግሥት አንኳስሰው ሲመለከቱ፤ «እነዚህ ሰዎች አርባ ዓመታት ያስቆጠረ ውጤት አልባ የትግል ዕድሜ ቢኖራቸውም የአርባ ቀን ሕፃን ናቸውን?» የሚያሰኝ ግምት ውስጥ የሚከትት ተግባራት ፈፅመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ «ማንም የማይደፍረውን የዛላምበሳን ምሽግ አሳልፈን ነው ያስገባናቸው» ሲሉ እንደገለጹት፣ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከነ ጀነራል ከማል ገልቹ የነጠቁትን ጨምሮ በዛላምበሳ የገባው አንድ ሺህ ሁለት መቶ የሚሆን ሠራዊታቸው ትጥቁን ፈትቶ ካምፕ ሲገባ እነ ከማል ገልቹ ተረከቡት። ይህ ከከማል ገልቹ ጋር ኤርትራ የገባው ሠራዊት ከዳውድ ኢብሳ ጋር በነበረው ቆይታው ደስተኛ ያልነበረ፣ የጉልበት ሥራ ላይ የተሰማራ፣ በምግብ ለሥራ የደቀቀ ሲሆን፤ የዶክተር አብይ የሠላም ጥሪ ታላቅ ገፀ-በረከት ሆኖለት ሠራዊቱ ለአገሩ ምድር መብቃቱን እንደ ተዓምር የሚቆጥር የመሆኑ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነበር።
የአቶ ዳውድ ኦነግ የኦሮሞ ሕዝብ ነፃ አውጪ አድርጎ የሚመለከተው ድርጅት በበርካታ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞዎችና ደጋፊዎቹ አቀባበል ቢደረግለትም፤ ለጦርነት አምፆ በሰው አገር ሲንከራተት መፈፀም ያልቻለውን ተግባር በደጋፊዎቹ የራሱ ሕዝብ ላይ የግድያ፣ የማፈናቀል፣ አስገድዶ ንብረት የመቀማት፣ በባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ የመዝረፍ ተግባር ሲፈፅም ማየቱ፤ ይህ ድርጅት የመንግሥትነት ባህርይ ቢኖረውና ሥልጣን ቢቆጣጠር በማናለብኝነት ምን ሊፈፅም እንደሚችል መገመት ለአርቆ አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠፋው አይደለም፡፡
አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ይህንን በንፁሃን ላይ የሚፈፀም በደልና እንግልት ለማስቀረት የኃይል እርምጃ ሳይጠቀም ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለ16 ጊዜ ሰላማዊ ድርድር ቢያካሂድም ኦነግ በእንቢተኛነቱ በመቀጠሉ መከላከያ ሠራዊቱ ሕዝብን የመጠበቅና የአገሪቱን ሠላም የማስከበር ኃላፊነት አለበትና በወሰደው እርምጃ በምዕራብ ወለጋ የፈረሰው የአስተዳደር መዋቅር እንዲመለስ፣ የሕዝቡ እንግልት፣ ዝርፊያ፣ ግርፋትና ግድያ እንዲቆም አድርጓል፡፡
ከብዙ የእንቢተኛነት ወራት በኋላ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በበኩሉ ባወጣው መግለጫና የእንደራደር ልመና ስምምነታችንና በሕዝቡ ውድ መስዋዕትነት የተገኘው የለውጥ ሂደት በአስተማማኝ መልኩ ስር በመስደድ ስኬታማ እንዲሆን የጋራ ኮሚቴ መስርተን የእንንቀሳቀስን ጥያቄን አስከትሏል፡፡
«ሂደቱ የሰው ሕይወት መስዋዕትነትን በማይጠይቅ መልኩ፣ በሀገርና በሕዝብ ንብረት ላይም ጉዳትን በማያስከትል ሁኔታ፣ እንዲሁም ያለምንም ጥድፊያና ወከባ ጊዜ ወስደን በመመካከርና በቀና መንፈስ አብረን በመስራት ማሳካት እንደሚቻል የድርጅታችን የኦነግ ጽኑ እምነታችንና አቋማችንም ነው » የሚል መግለጫም ማውጣቱ መከላከያ ሠራዊቱ ኦነግ በአጭር ቀናት ውጤታማ ሥራ እንደሰራ በግልፅ ያመላክታል፡፡
ለመሆኑ የአቶ ዳውድ ኦነግ በሰላም ለመታገል አገር ቤት ከገባ በኋላ ሠራዊት ከየት አመጣ የሚለው ጉዳይ የብዙዎች መነጋገሪያ ቢሆንም ጉዳዩ ከጀርባው በርካታ እጅ እንዳለበት ይገለፃል። እነዚህ ከጀርባ ያሉ ኃይሎች ይፋ ከሆኑ መላው የኦሮሚያ ሕዝብ ድርጅቱን በከሃዲነት ስለሚፈርጀው ኃይላችን ከዚህ መጣ ነው ሳይሉ የአካባቢውን ወጣቶችና ሕፃናትን በመመልመል በሌሎች አገሮች እንዳሉት አሸባሪዎች በነፍሰ ገዳይነት በማሰልጠን ላይ ሲሆን፤ በየቀኑ የሚገድሉት፣ የሚያፈናቅሉትና የሚዘርፉትን ሕዝብ ተገን በማድረግ በአገር ቤት ያለን ኃይል ነው የሚል ማደናገሪያ ያቀርባሉ፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት አደገኛውን የክልሉን አስተዳደር በተመለከተ ነገሮችን በጥበብ ለመያዝ ባለው አቋም መለሳለስን ቢመርጥም ከጀርባ ያለውን የፖለቲካ ቁማር ሳይገነዘበው የሚቀር አይደለም። አቶ ዳውድ ኢብሳ አሁን ሠራዊት አለን የሚል ቃላት ይሰንዝሩ እንጂ በርግጥ የእርሳቸውን የመሪውን ትዕዛዝ የሚቀበል ሠራዊት አላቸውን? የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡
በመንግሥት የሚታወቀው ሠራዊት ያለው ካምፕ ነው። ይህ ሠራዊት ደግሞ አሁን የኦሮሚያ የፀጥታ ኃላፊ ሆነው በተመደቡት ጄኔራል ከማል ገልቹ እጅ የሚገኝ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ አቶ ዳውድን አላስደሰተም። እርሳቸውን ደስ አላቸውም-አላላቸውም ሠራዊቱ ተሃድሶውን ከወሰደ በኋላ ተመልሶ የዳውድ ኢብሳ አካል የመሆኑ ጉዳይ ያከተመ ስለመሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ታዲያ የትኛውን ሠራዊታቸውን ነው እንዲከላከል አዝዘናል የሚሉት ሲባል ብጥብጥን ለማቀጣጠል በተጠባባቂነት ያስቀመጡት ወይም በስምምነት ከሌላ የተበደሩት ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡
ያም ሆነ ይህ ኦነግ ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲል ይታገሉ የነበረው በአገሪቱ የመናገር መብታችን ታፈነ፣ ዴሞክራሲ አጣን፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበብን፣ መሰብሰብ፣ ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ መደራጀት አልቻልንም፡፡ ግድያ፣ እሥራት፣ አፈና፣ መፈናቀል፣ መሰደድና ጫና ተደረገብን በሚል እንደነበር ይታወቃል፡፡
ታዲያ በዚህ ወቅት የለውጡ አራማጆች ዶክተር አቢይና ሌሎቹ ጓዶቻቸው የታሰሩትን ፈትተው፣ መደራጀትን፣ መናገርንና ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግን ፈቅደው፣ መገናኛ ብዙኃንን ነፃ አድርገው፣ አገር ጥለው የተሰደዱትንና ያኮረፉትን ፖለቲከኞች ይቅርታ ጠይቀውና ወደ አገራቸው እንዲገቡ ለምነው፣ በትጥቅ ትግል ላይ ነን ብለው የተናገሩትንም «ማንን ትዋጋላችሁ፣ የውጊያ ዘመን ፋሽን ያለፈበት ነው፤ ኑ በሰላም አገራችሁ ገብታችሁ በጋራ እንገንባ » የሚል ጥሪ አቅርበው ሳለ በተጠለለበት አገር እንኳ ሆኖ ውጊያ ማካሄድ ያልተሳካለት ድርጅት ለሠላም የተሰጠውን ጥሪ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ በአገር ውስጥ ጦርነት መጀመሩ አስተሳሰቡን አሳፋሪ ያደርገዋል፡፡
በአገር ውስጥ ሆነው ትግል ሲያደርጉ የነበሩት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይታገሉለት የነበረውና መስዋዕትነት ከፍለንለታል ሲሉ የነበሩት ዘርፈ ብዙ ችግር በፅኑ ታጋዮች ድፍረትና ብስለት እጃቸው ሲገባላቸው ተንከባክበው መያዝ ሲገባቸው «በእጅ የያዙት ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል» የሚሉት ከሆነባቸውና መንከባከብ ካቃታቸው፣ በመላ አገሪቱ መረጋጋት እንዳይኖር ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር በመተባበር በሕዝብ ላይ እልቂትና መፈናቀልን የሚጋብዙ ከሆኑ ዕድሉን ቢያገኙ አገር መምራት መቻላቸው ያጠራጥራል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተገኘው መልካም ዕድልና አጋጣሚ ማናቸውም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠብቀውት አገሪቱን ከሚያስተዳድረው መንግሥት የተሻለ ለሕዝባችን እንሰራለን፣ ለውጥ እናመጣለን፤ የሚል የላቀ የአስተሳሰብና የዕቅድ ባለቤትነታቸውን በማስረዳት ተመራጭ ለመሆን ዕውቀታቸውንና ብልሃታቸውን የሚያሳዩበት እንጂ፤ ሕዝብን የሚያሳምኑበት ዕቅድና ዕውቀት ሲያጡ ለብጥብጥና ለጦርነት መነሳሳት «ወትሮውንም ከብጥብጥ ሌላ ምንም ፋይዳ የላቸውም» ተብለው በሕዝብ እንዲወገዙ የሚያደርግ ተግባርን መፈፀም አይገባቸውም፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ከአባገዳዎችና ከሌሎች ለዕርቅ ማምጣት ከተቋቋሙ አባላት ጋር ሲወያይ የኦነጉ መሪ ሠራዊቱን ለአባገዳዎች መስጠታቸውን ተናግረው ነበር፡፡ ይህ አሻሚ ውሳኔያቸው በአንዳንዶች በኩል ተንኮልም ሚስጥርም ያለው ነው የሚል ሃሳብን ያስነሳ ቢሆንም፤ ለጉዳዩ አፋጣኝ ዕልባት ለመስጠት ሲባል በትናንትናው ዕለት ሐሙስ ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ኮሚቴው ወደ አምቦ ተጉዞ ሦስት አካላትን ማለትም የአምቦ ዩኒቨርሲቲን፣ አባ ገዳዎችንና የአካባቢው ማህበረሰብን እንዲሁም የጀስቲስ ፎር ኦል መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅትን በማካተት ስለ እርቀሰላም ጥቅምና ውጤት በመመካከር ሰላም የማውረድ ሥራ ሰርቷል።
የኮሚቴው ጸሃፊ አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ የሰላምን ጠቀሜታ በማውሳት ኮሚቴው በሚገባ ተወያይቶ የደረሰበትን ስምምነት ሲገልፅ «በ20 ቀናት ውስጥ በጫካ ያለው የኦነግ ሰራዊት በሰላማዊ መንገድ ወደ ህዝብ እንዲቀላቀል ኮሚቴው ትዕዛዝ አስተላልፏል። በዚህም መጪው አስር ቀናት የዝግጅት ጊዜ ይሆናሉ። ከአስር ቀናት በኋላ ደግሞ በየደረጃው ኮሚቴ ተቋቁሞ ለሠራዊቱ አቀባበል ይደረግላቸዋል። ከዚያም ወደ ካምፕ ይገባሉ» ብሏል፡፡ ይህ ነው ለቀረበው የሰላም ጥሪ በጎ ምላሽ መስጠት ማለት፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17 /2011
ኪሩቤል ንጉሴ